አጠቃላይ ጉባኤ
በክርስቶስ ደስታ መዋጥ
የሚያዝያ 2024 (እ.አ.አ) አጠቃላይ ጉባኤ


በክርስቶስ ደስታ መዋጥ

የሰማይ አባታችን እንባ የተሞላ ልመናችንን እንደሚሰማ እና ሁልጊዜ በፍጹም ጥበቡ መልስ እንደሚሰጥ እመሰክራለሁ።

እንወድሃለን፣ ሽማግሌ ኪረን። የአነጋገር ዘዬህን ለ10 ደቂቃ ልዋሰው?

የሚናፈቁ ተአምራት

በአዲስ ኪዳን ውስጥ ዓይነ ስውሩ በርጤሜዎስ ተአምራትን በመፈለግ ወደ ክርስቶስ እንዳለቀሰ እንማራለን። “ኢየሱስም፣ ሂድ፤ እምነትህ አድኖሃል አለው። ወዲያውም አየ።”1

በሌላ ጊዜ ደግሞ ቤተሳይዳ ውስጥ የሚገኝ አንድ ሰው ፈውስ ለማግኘት ይናፍቅ ነበር። በአንጻሩ ይህ ተዓምር በቅጽበት አልመጣም። ይልቁንም፣ ”አጥርቶ ከማየቱ” በፊት ኢየሱስ ሁለት ጊዜ ባርኮታል።2

በሶስተኛ ምሳሌ፣ ሐዋርያው ጳውሎስ በመከራው ጊዜ “ሦስት ጊዜ ጌታን [ለምኖት] ነበር3”፣ ነገር ግን እስከምናውቀው ድረስ፣ ልባዊ ልመናው አልተመለሠለትም

ሶስት የተለያዩ ሰዎች። ሶስት ልዩ አጋጣሚዎች።

ስለዚህ፣ ጥያቄው፦ ለምንድን ነው አንዳንዶች የናፈቁትን ተዓምራት ቶሎ ሲቀበሉ ሌሎች ጌታን እየጠበቁ በትዕግስት የሚጸኑት?4 ለምን እንደሆነ ላናውቅ እንችላለን፣ ሆኖም በአመስጋኝነት፣ “[እኛን የሚወደንን]”5 እና “ለዘለዓለማዊ ደህንነታችን እና ደስታችን ሁሉንም ነገር [የሚያደርገውን] እርሱን እናውቀዋለን።”6

መለኮታዊ ዓላማዎች

መጨረሻውን ከመጀመሪያው የሚያየው እግዚአብሔር፣7“ጭንቀትህ እና ስቃይህ ለጥቂት ጊዜ ቢሆን ነው”8 ይህም “ለጥቅምህ”9ይቀደሳል በማለት ያረጋጋናል።

በፈተናዎቻችን ተጨማሪ መልሶች ለማግኘት ለመርዳት፣ ሽማግሌ ኦርሰን ኤፍ. ዊትኒ፦ “የትኛውም አይነት የምንሠቃይበት ህመም፣ የትኛውም የሚያጋጥመን ፈተና በከንቱ አይቀርም። እንማርበት ዘንድ ያገለግለናል።… [በትዕግስት] የምንፀናበት ሁሉ …፣ ባህሪያችንን ይገነባል፤ ልባችንን ያጠራል፣ ነፍሳችንን ያሰፋልናል፣ እንዲሁም ይበልጥ ርኅሩኅ እና ለጋሥ እንድንሆን ያደርገናል። … እዚህ ልንማር የመጣነውን ትምህርት የምናገኘው በሐዘንና በስቃይ፣ በድካምና በመከራ ነው፣ ይህም [የሰማይ ወላጆቻችንን] እንድንመስል ያደርገናል” በማለት አስተምረውናል።10

ሐዋርያው ጳውሎስ በመከራው ወቅት “የክርስቶስ ኃይል [በእርሱ] ላይ እንደሚያርፍ” በመረዳት በትሕትና፣ “ስደክም ያን ጊዜ ኃይለኛ ነኝና”11በማለት ተናግሯል።

የህይወት ፈተና ያነጥረናል።12 አዳኙ እራሱ “በመከራ [እንዲፈጸም]”፣ “መታዘዝን ተማረ”13

አንድ ቀንም በርህራሄ፣ “እነሆ፥ አንጥሬሃለሁ ነገር ግን እንደ ብር አይደለም፤ በመከራም እቶን ፈትኜሃለሁ።”14ይለናል።

በእግዚአብሔር መለኮታዊ ዓላማዎች መታመን ለደከሙ ነፍሳት ተስፋን ይተነፍሳል፣ በጭንቀት እና በልብ ህመም ጊዜም ቁርጠኝነትን ያነሳሳል።15

መለኮታዊ ዕይታ

ከአመታት በፊት፣ ፕሬዚዳንት ራስል ኤም ኔልሰን፣ ይህን ጠቃሚ ሃሳብ አካፍለው ነበር፥ “ሁሉንም ነገሮች በዘለአለማዊ ዕይታ ስንመለከት፣ ሸክማችንን በእጅጉ ያቀልልናል።”16

ምስል
ሆሊ እና ትሬይ ፖርተር።

እኔና ባለቤቴ ጂል በቅርቡ የ12 ዓመት ልጃቸው ትሬ በአሳዛኝ የእሳት አደጋ ህይወቱ በተቀጠፈ ጊዜ፣ ሆሊ እና ሪክ ፖርተር በተባሉ ታማኝ ሠዎች ህይወት ውስጥ ይህን እውነት አይተን ነበር። ሆሊ ውድ ልጇን ለማዳን ባደረገችው የጀግንነት ሙከራ እጅ እና እግሯ ክፉኛ በእሳት ከተቃጠለ በኋላ፣ በአጥቢያ ቅዱስ ቁርባን ስብሰባ ላይ፣ ቤተሰቧ ጭንቀት ውስጥ ሳለ ጌታ ስላፈሰሰው ታላቅ ሰላም እና ደስታ እንደ ተአምራዊአስደናቂ እና አስገራሚ የመሳሰሉ ቃላትን በመጠቀም ተናግራለች።

ምስል
የተጣመሩ የማዳን እጆች

የዚህች ውድ እናት ሊሸከሙት የማይቻል ሀዘን በላቀ ሰላም ተተክቷል፦ “እጆቼ የሚያድኑ እጆች አይደሉም። እነዚያ እጆች የአዳኙ ናቸው! ጠባሳዬን ሣይ ማድረግ ያልቻልኩትን ነገር እንደሚያስታውሰኝ ነገር ከመመልከት ይልቅ፣ በአዳኜ ላይ ያሉትን ጠባሳዎች አስታውሳለሁ።”

የሆሊ ምሥክርነት፣ ነቢያችን “ስለ ሰለስቲያል ስታስቡ፣ ፈተናዎችን እና ተቃውሞዎችን በአዲስ መልኩ ታያላችሁ” ሲሉ የሠጡትን የተሥፋ ቃል ይፈጽማል።17

ሽማግሌ ዲ. ቶድ ክሪስቶፈርሰን እንዳሉት፣ “እግዚአብሔር በቅድመ ምድራዊ ህይወት የመዳን እቅዱን ባቀረበልን ጊዜ፣ መከራን የማሸነፍ እና የማደግ ጉጉት እንደነበረን አምናለሁ።” የሰማይ አባታችን እንደሚደግፈን በማወቅ፣ አሁን ይህንን ፈተና መወጣት አለብን። ነገር ግን ወደ እርሱ መመለሣችን ወሳኝ ነው። እግዚአብሄር በሌለበት፣ የስቃይ እና የመከራ የጨለማ ተሞክሮዎች ፣ወደ መከፋት፣ ተስፋ መቁረጥ እና ምሬት ይወስዱናል።”18

መለኮታዊ መርሆዎች

ያለመርካትን ጨለማ ለማስወገድ እና፣ በምትኩም ታላቅ ሰላምን፣ ተስፋን እንዲሁም በህይወት አስቸጋሪ ፈተናዎች ውስጥም እንኳን ደስታን ለማግኘት የሚያስችሉ ሶስት መለኮታዊ መመሪያዎችን አካፈላለሁ።

አንደኛ—ጠንካራ እምነት የሚመጣው ኢየሱስ ክርስቶስን በማስቀደም ነው።19 “ባሰባችሁት ነገር ሁሉ ወደ እኔ ተመልከቱ፣ አትጠራጠሩ፣ አትፍሩ”20ሲል ተናግሯል። ፕሬዚዳንት ኔልሰን እንዲህ ሲሉ አስተምረዋል፦

“የዘለዓለም ህይወታች[ን] [በክርስቶስ] ላይ ባ[ለን] እምነት እና በኃጢያት ክፍያው ላይ የተመሰረተ ነው።”21

“በቅርብ በደረሰብኝ ጉዳት ምክንያት በሚሰማኝ ከባድ ህመም ስሠቃይ፣ ለኢየሱስ ክርስቶስ እና ከመረዳት በላይ ስለሆነው የኃጢያት ክፍያ መሥዋዕቱ ጥልቅ አድናቆት ተሰምቶኛል። አስቡት! አዳኙ ‘በመከራና በሁሉም አይነት ህመምና ፈተናዎች’ ተሰቃይቷል፣ ይህም በችግር ጊዜ እኛን ማፅናናት፣ መፈወስ እና ማዳን ይችል ዘንድ ነው።”22

ቀጥለው፦ “ጉዳቴ ደጋግሜ ስለ ‘እስራኤል ቅዱስ ታላቅነት’ እንዳስብ አድርጎኛል። እያገገምኩ በነበረበት ጊዜ፣ ጌታ መለኮታዊ ኃይሉን በሰላማዊ እና በማያጠራጥሩ መንገዶች አሳይቷል።”23

“በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ፥ ነገር ግን አይዞአችሁ፤ አለምን አሸንፌዋለሁ”24በማለት አዳኛችን ያበረታታል።

ሁለተኛ—ብሩህ የሆነ ተስፋ የሚመጣው የዘለዓለም እጣ ፈንታችንን በአዕምሯችን በማየት ነው።25 እህት ሊንዳ ሪቭስ “የአባታችንን አስደናቂ የተስፋ በረከቶች ራዕይ… በየቀኑ በዓይኖቻችን ፊት ማቆየት” ያለውን ኃይል ስትናገር፣ “ብዙ ፈተናዎች ያሉብን ለምን እንደሆነ አላውቅም፣ ነገር ግን ሽልማቱ በጣም ትልቅ እንደሆነ በግሌ ይሰማኛል … በጣም አስደሳች እና ከማስተዋል በላይ ከመሆኑ የተነሳ በዚያ የሽልማት ቀን፣ መሐሪ፣ አፍቃሪ አባታችንን፣ ‘የሚፈለገው ያ ብቻ ነበር?’ ልንለው እንችላለን።… በስተመጨረሻ እነዚያ ፈተናዎች በእግዚአብሔር መንግስት ውስጥ ለዘለዓለም ህይወት ብቁ የሚያደርጉን ከሆነ እዚህ መከራ ቢደርስብን ምን አለበት?”26በማለት አስተምረዋል።

ፕሬዚዳንት ኔልሰን ይህን አስተያየት ሰጥተዋል፦ “ጆሴፍ ስሚዝ በሊበርቲ እስር ቤት ውስጥ እፎይታ ለማግኘት ሲለምን ጌታ የሰጠውን ምላሽ አስቡ። እየተፈጸመበት የነበረው ኢ-ሰብአዊ ድርጊት ልምድ እንደሚሰጠው እና ለጥቅሙ እንደሚሆን ጌታ ለነብዩ አስተምሮታል። ‘በደንብ ብትፀና፣ እግዚአብሔርም ወደ ላይ ዘለአለማዊ ክብር ይሰጥሀል’ በማለት ጌታ ቃል ገብቶለታል። ጆሴፍ በጊዜው በነበረው ከባድ ችግር ላይ ከማተኮር ይልቅ ስለ ሰለስቲያል እንዲያስብ እና ዘለዓለማዊ ሽልማትን እንዲያስብ ጌታ እያስተማረው ነበር።”27

ይህ የዕይታ ለውጥ፣ ጆሴፍ እንዲህ በማለት ለጓደኛው በጻፈው ደብዳቤ ላይ እንደሚታየው ጥልቅ ቅድስናን አምጥቶለታል፦ “ለአምስት ወራት በእስር ቤት ግድግዳዎች ውስጥ ከታሰርኩ በኋላ ልቤ ከዚህ በፊት ከነበረው ከምንጊዜውም የበለጠ ርኅሩኅ እንደሚሆን ይታየኛል። … የደረሰብኝን በደል ባይደርስብኝ ኖሮ አሁን እንደዚህ ዓይነት ስሜት አይሰማኝም ነበር።”28

ሶስተኛ—ታላቅ ሀይል የሚመጣው በደስታ ላይ በማተኮር ነው።29 በዘለዓለም ውስጥ እጅግ ወሳኝ፣ አስጨናቂ በነበሩት ሰዓታት፣ አዳኛችን ሳያፈገፍግ መራራውን ጽዋ ጠጥቷል።30 ይህን ያደረገው እንዴት ነው? “በፊቱ ስላለው ደስታ [ክርስቶስ] በመስቀል ታግሷል፣”31 ፈቃዱም “በአብ ፈቃድ [ተዋጠ]”32የሚለውን እንማራለን።

ምስል
ክርስቶስ በጌተሰማኒ

ይህ “ተዋጠ” የሚለው አባባል በጥልቅ ያነሳሳኛል። በስፓኒሽ “ተዋጠ” “ተበላ” ተብሎ እንደሚተረጎም ሳውቅ ፍላጎቴ ጨመረ። በጀርመንኛ፣ “ተበላ”፤ በቻይንኛ ደግሞ “ተጠመጠመ” ተብሎ ተተርጉሟል። ስለዚህ፣ በህይወት ውጣ ውረዶች ውስጥ ከመጠን በላይ ጭንቀት ሲሰማኝ፣ “በክርስቶስ ደስታ ከመዋጥ [ከመበላት፣ ከመጠምጠም] በቀር ምንም አይነት መከራ እንዳንቀበል”33ጌታ የገባውን ቃል አስታውሳለሁ።

ምንም እንኳን መራራ ጽዋዎቻችሁ ገና ያልተወገዱ ቢሆኑም “ … ከምድራዊ መረዳት በላይ፣”34የሆነውን ይህን ደስታ በብዙዎቻችሁ ላይ አያለሁ። ቃል ኪዳኖቻችሁን ስለጠበቃችሁ እና ለእግዚአብሔር ምስክሮች በመሆን ስለቆማችሁ እናመሰግናለን።35 “[ዓይን የማያየው ሐዘን ጸጥ ባለው ልባችሁ ውስጥ ተደብቆ ሳለ]”36ሁላችንን ለመባረክ ስላደረጋችሁት ጥረት እናመሰግናለን። የአዳኙን እፎይታ ለሌሎች ስታመጡ፣ ፕሬዘደንት ካሚል ጆንሰን እንዳስተማሩት ለራሳችሁ ታገኛላችሁ።37

መለኮታዊ ቃል ኪዳኖች

አሁን፣ የሆሊ ፖርተር ቤተሰብ በጌታ ሲታገዝ የነበረውን ተዓምር ወደምንመለከትበት የቅዱስ ቁርባን ስብሰባ ከእኔ ጋር ተመለሱ።38 ይህን ታማኝ ቤተሰብ እና ውድ ጓደኞቻቸውን ለማጽናናት ምን ልናገር እችላለሁ ብዬ ሳሰላስል፣ “የአዳኙን ቃላት ተጠቀም” የሚል ሃሳብ መጣ።39 ስለዚህ፣ በዚያ ሰንበት ዕለት እንዳደረግሁት ዛሬም፣ “የቆሰለውን ነፍስ [በሚፈውሱት]” በእርሱ ቃላት እዘጋለሁ40

“እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፤ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም አሳርፋችኋለሁ።”41

“እናም ደግሞ በባርነት በነበራችሁ ጊዜም ቢሆን፣ በጀርባችሁም እንኳን ሊሰማችሁ እንዳይቻላችሁ፣ በትከሻችሁ ላይ ያለውን ሸክም አቃልላችኋለሁ፤ እናም ይህንን የማደርገው ከዚህ በኋላ ለእኔ በምስክርነት እንድትቆሙ ነው፤ እናም እኔ ጌታ እግዚአብሔር በእውነት በመከራቸው ጊዜ ህዝቤን እንደምጎበኝ ታውቁ ዘንድ ነው”42

“ወላጆች እንደሌላቸው ልጆች አልተዋችሁም፥ ወደ እናንተ እመጣለሁ።”43

የእኔ ምስክርነት

በደስታና ጥልቅ አክብሮት፣ አዳኛችን እንዳለ እና “ቃል ኪዳኖቹ የተረጋገጡ እንደሆኑ”44 እመሰክራለሁ። በተለይ ለተቸገራችሁ ወይም ደግሞ “በማንኛውም ሁኔታ ለተሰቃያችሁ”45 የሰማይ አባታችን በእንባ የተሞላ ልመናችሁን46 እንደሚሰማ እና ሁል ጊዜም በፍጹም ጥበብ ምላሽ እንደሚሰጥ እመሰክራለሁ።47 በከባድ ችግር ውስጥ በነበርንበት ወቅት ለእኛ ቤተሰብ እንዳደረገው፣ 48 “በክርስቶስ ደስታ ውስጥ ከመዋጥ በስተቀር ምንም ስቃይ እንዳያገኛ[ችሁ]”49 “[ሸክማችሁ እንዲቀልላችሁ]” “እግዚአብሄር ይፍቀድላችሁ”። በኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ስም፣ አሜን።