አጠቃላይ ጉባኤ
እስከመጨረሻ በእምነት መፅናት
የሚያዝያ 2024 (እ.አ.አ) አጠቃላይ ጉባኤ


እስከመጨረሻ በእምነት መፅናት

በእርሱ እጅ፣ በህይወታችሁ የሚከሰት ማንኛውንም ጎልያድ መጣል ትችላላችሁ።

ውድ ወጣት ጓደኞች፣ ዛሬ ለእናንተ—ለቤተክርስቲያኗ ወጣቶች ቀጥታ መናገር እፈልጋለሁ።

የወጣት ሴቶች አጠቃላይ አመራራችን የአገልግሎት ጥሪ ከተቀበለ አንድ አመት ሆኖታል። በዚህ ባለፈው አመት ብዙ ነገሮች ተከስተዋል!

ከብዙዎቻችሁ ጋር ተገናኝተናል እንዲሁም የክርስቶስን ትምህርቶች አብረን አጥንተናል። መዝሙሮችን ዘምረናል፣ አዲስ ጓደኝነት መስርተናል፣ እንዲሁም በማህበረሰባችን ውስጥ ከእናንተ ጋር አገልግለናል። በወጣቶች ጉባኤዎች እና በአለማቀፋዊ ዝግጅቶች የእናንተን ምስክርነቶች በመስማት ጥንካሬ አግኝተናል። በጌታ ቤት ውስጥም አብረን አምልከናል።

በእያንዳንዱ ጊዜም የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስን መልዕክት አካፍለናል። ይሄ ምሽት ከዚያ የተለየ አይሆንም፤ ለእናንተ ለኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን ወጣቶች መልዕክት አለኝ።

ትልቅ ጥያቄዎች

በዚህ የሀጥያት አለም ውስጥ ስትኖሩ እንዴት ለእግዚአብሔር መታመን እንደምትችሉ አስባችሁ ታውቃላችሁ? ወደፊት ለመጓዝ እና መልካም በማድረግ ለመቀጠል ጥንካሬን ከየት ነው የምታገኙት? የእውነተኛ ደስታ ተሞክሮ የምታገኙት እንዴት ነው ?

የዳዊት እና ጎልያድ1 ተሞክሮ የሚያግዘን ይመስለኛል።

ዳዊት እና ጎልያድ

በብሉይ ኪዳን ውስጥ፣ የፍልስጥኤም ሰራዊት ከእስራኤላዊያን ጋር እየተዋጋ ነበር፣ እናም በእያንዳንዱ ጥዋት እና ማታ፣ ጎልያድ የተባለ ግዙፍ ፍልስጥኤማዊ ማንኛውም እስራኤላዊ ሰው እንዲፋለመው ጥሪ ያቀርብ ነበር።

ምስል
ዳዊት እና ጎልያድ

ከእስራኤላዊያን ሰዎች መካከል፣ ከጎልያድ እጅግ ያነሰ ነገር ግን በኢየሱስ ክርስቶስ ታላቅ እምነት ያለው ዳዊት የሚባል ወጣት እረኛ ነበር። ዳዊት ለመዋጋት ፍቃደኛ ሆነ። ንጉሱ እራሱ እንዳያደርገው ሊያሳምነው ሞከረ፣ ነገር ግን ዳዊት እምነቱን በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ማድረግን መረጠ።

ከዚያ በፊት፣ ዳዊት ከአንበሳ እና ከድብ ጋርም ተዋግቶ ነበር። ከግል ተሞክሮዎቹ፣ እግዚአብሔር እንደጠበቀው እና አሸናፊ እንዳደረገው ያውቅ ነበር። ለዳዊት፣ የእግዚአብሔር ነገር በጣም አስፈላጊው ጉዳይ ነበር። ስለዚህ፣ በማይተወው በእግዚአብሔር ላይ ሙሉ እምነቱን አድርጎ፣ አምስት ድብልብል ድንጋዮችን ሰበሰበ፣ ወንጭፉን አነሳ፣ እናም ጎልያድን ሊገጥም ሄደ።

ምስል
የዳዊት አምስት ድንጋዮች

ዳዊት የወነጨፈው የመጀመሪያ ድንገይ የጎልያድን ግንባር እንደመታው፣ ህይወቱንም በዚያ እንዳጣ ቅዱሣት መፃሕፍት ይነግሩናል።2

መልሱን መፈለግ

ዳዊት ጎልያድን አንድ ድንጋይ ተጠቅሞ ቢገድለውም፣ አምስት ነበር ያዘጋጀው። አምስት! ይሄ አለምን ለመጋፈጥ እንዴት ራሴን ማዘጋጀት እንዳለብኝ እንዳስብ ያደርገኛል።

የዳዊት እያንዳንዱ ድንጋይ በህይወታችን ድል እንድናደርግ የሚያስፈልገንን ጥንካሬ የሚወክል ቢሆንስ? አምስቱ ድንጋዮች ምን ሊሆኑ ይችላሉ? ቀጣዮቹን ሁኔታዎች አሰብኩ፤

  1. ለእግዚአብሔር ያለኝ ፍቅር ድንጋይ።

  2. አዳኛችን፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያለኝ እምነት ድንጋይ።

  3. የእውነተኛ ማንነቴ እውቀት ድንጋይ።

  4. እለታዊ ንስሃዬ ድንጋይ።

  5. ለእግዚአብሔር ኃይል ያለኝ ቅርበት ድንጋይ።

በእነዚህ ጥንካሬዎች እንዴት እንደተባረክን እንነጋገር።

መጀመሪያ፣ ለእግዚአብሔር ያለኝ ፍቅር ድንጋይ። እግዚአብሔርን መውደድ የመጀመሪያው ታላቅ ትዕዛዝ ነው።3ለወጣቶች ጥንካሬ መመሪያ እንደሚያስተምረው፦ “እግዚአብሔር ይወዳችኋል። እርሱ አባታችሁ ነው። የእርሱ ፍፁም ፍቅር እርሱን እንድትወዱት ሊያበረታችሁ ይችላል። ለሰማይ አባታችሁ ያላችሁ ፍቅር በህይወታችሁ በጣም አስፈላጊው ተጽዕኖ ሲሆን፣ ብዙ ውሳኔዎች ቀላል ይሆናሉ።”4

ለእግዚአብሔር ያለን ፍቅር እና ከእርሱ ጋር ያለን ቅርብ ግንኙነት ልባችንን ለመለወጥ እና በቀላሉ ፈተናዎችን ለማለፍ የሚያስፈልገንን ጥንካሬ ይሰጠናል።

ሁለተኛ፣ በአዳኛችን፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያለኝ እምነት ድንጋይ። ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ምድር ሲመጣ፣ ለሀጥያታችን ተሰቃይቷል5 እንዲሁም መከራዎቻችንን፣ ድክመቶቻችንን፣ እና አካላዊ እና አእምሯዊ ህመማችንን በእራሱ ላይ ወስዷል። ለዚያም ነው እኛን እንዴት እንደሚረዳን የሚያውቀው። በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ እምነትን ማድረግ ማለት ሙሉ በሙሉ በእርሱ ጥበብ፣ በእርሱ ጊዜ፣ በፍቅሩ፣ እና የሃጢያት ክፍያ መሥዋዕትን ለእኛ ለመክፈል ባለው ሃይል ላይ መታመን ማለት ነው። በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያለ የእምነት ድንጋይ በህይወታችን ወስጥ የሚኖርን ማነኛውንም “ግዙፍ” ያሸንፋል።6 እርሱ አስቀድሞ ስላሸነፈ እኛ ይህን የወደቀ አለም ማሸነፍ እንችላለን።7

ሶስተኛ፣ የእውነተኛ ማንነቴ እውቀት ድንጋይ። ውድ ነቢያችን፣ ፕሬዚዳንት ራስል ኤም ኔልሰን፣ የእኛ ዋነኛ ማንነቶቻችን የእግዚአብሔር ልጆች፣ የቃልኪዳኑ ልጆች፣ እና የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀመዛሙርት መሆናችን እንደሆነ አስተምረውናል።8

እኔ ማን እንደሆንኩ በትክክል ሳውቅ ሁሉም ነገሮች ይቀየራሉ።9 አቅሜን ስጠራጠር፣ ብዙ ጊዜ በእምሮዬ ወይም ጮክ ብዬ “እኔ የእግዚአብሔር ሴት ልጅ ነኝ፣ እኔ የእግዚአብሔር ሴት ልጅ ነኝ፣” በማለት እንደገና ለመቀጠል በራስ መተማመን እስኪሰማኝ ድረስ ይህን እደጋግማለሁ።

አራተኛ፣ የእለታዊ ንሰሃዬ ድንጋይ። በለወጣቶች ጥንካሬ መመሪያ ውስጥ፣ እንዲህ እናነባለን፦ “ንሰሃ የሃጥያት ቅጣት አይደለም፤ አዳኙ እኛን ከሃጥያት ነጻ የሚያወጣበት መንገድ ነው። ንሰሃ መግባት ማለት መለወጥ ማለት ነው—ከሃጥያት መራቅ እና ወደ እግዚአብሔር መዞር ነው። መሻሻል እና ይቅርታን ማግኘት ማለት ነው። የዚህ አይነት ለውጥ የአንድ ጊዜ ክስተት አይደለም፤ ቀጣይ ሂደት ነው።”10

የእግዚአብሔርን ይቅርታ እንደማግኘት ያለ ስሜት እና ንጹህ መሆናችንን እና ዳግም ከእርሱ ጋር መጣመራችንን ከማወቅ የበለጠ ነጻነት የለም። ይቅር መባል ለሁሉም የሚቻል ነው።

አምስተኛው ድንጋይ የእግዚአብሔር ኃይልን የማግኘት ድንገይ ነው። በጥምቀት ስርአት ላይ የምናደርጋቸው አይነት ከእግዚአብሔር ጋር የምንገባቸው ቃልኪዳኖች፣ አምላካዊ ሃይሉን እንድናገኝ ያደርጉናል።11 የእግዚአብሔር ሃይል ፈተናዎችን እንድንጋፈጥ፣ መልካም ውሳኔዎችን እንድንወስን፣ እና ከባድ ሁኔታዎች በጽናት ለማለፍ አቅማችንን ለመጨመር የሚረዳ እውነተኛ ኃይል ነው። በሚያስፈልገን የተለየ አቅም ማደግ እንድንችል የሚያደርገን ሃይል ነው።12

ለወጣቶች ጥንካሬ መመሪያ ሲያብራራ፦ “ቃል ኪዳኖች ከሰማይ አባት እና ከአዳኙ ጋር ያጣምሯችኋል። በህይወታችሁ የእግዚአብሔርን ሃይል ይጨምራሉ።”13

ስለዚያ ጥምረት እንነጋገር። ክርስቶስ በዓለት ላይ በተሠራው ቤት እና በአሽዋ ላይ በተሰራው ቤት መካከል ስላለው ልዩነት ያስተማረበትን ጊዜ ታስታውሳላችሁ?14 ሽማግሌ ዲተር ኤፍ ኡክዶርፍ፤ “አንድ ቤት ጠንካራ ስለሆነ ከአውሎ ንፋስ አይተርፍም። ዓለቱ ጠንካራ ስለሆነ ብቻም አይተርፍም። ቤቱ ከአውሎ ነፋሱ የሚተርፈው ከጠንካራው ዓለት ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ስለሆነ ነው። ከዓለቱ ጋር ያለው ጥምረት ጥንካሬ ነው አስፈላጊው ነገር”15 በማለት አብራርተዋል።

ምስል
በዓለት ላይ የተገነባ ቤት።

ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ያለን የግል ጥምረት እምነታችንን በማያከብሩ ወይም እኛን በሚነቅፉ ሰዎች መካከል ስንሆን ወደፊት እንድንጓዝ ብርታትን እና በራስ መተማመንን ይሰጠናል። ክርስቶስ ሁሌም ስለእርሱ እንድናስብ ይጋብዘናል፤ ፣ “ባሰባችሁት ነገር ሁሉ ወደ እኔ ተመልከቱ”16 ይለናል። ስለ አዳኙ ማሰብ ውሳኔ ለመወሰን፣ ያለ ፍርሃት ለመከወን፣ እና ከእግዚአብሔር ትምህርት ጋር ለሚጻረሩ አይሆንም ለማለት የአእምሮ ግልጽነትን ይሰጠናል።17 ቀኔ ከባድ ሲሆን እና ከዚያ በላይ መቋቋም እንደማልችል ሲሰማኝ፣ ስለ ክርስቶስ ማሰብ ሰላምን ያመጣልኛል እንዲሁም ተስፋን ይሰጠኛል።

እንዴት ወደዚህ የኢየሱስ ክርስቶስ ሃይል መቅረብ እንችላለን? ቃል ኪዳኖቻችንን መጠበቅ እና በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያለንን እምነት ማሣደግ ቁልፍ ነገሮች ናቸው።

ዳዊት አንድ ተጨማሪ ድንጋይ ቢኖረው ኖሮ ብዬ እመኛለሁ፤ ይህም የ ምስክርነቴ ድንጋይ ይሆን ነበር። ምስክርነታችን በህይወታችን መለኮታዊ ተጽዕኖን በምናስተውልባቸው የግል መንፈሳዊ ተሞክሮዎች የተገነባ ነው።18 ያንን እውቀት ማንም ከእኛ ሊወስድብን አይችልም። የግል መንፈሳዊ ተሞክሯችንን ከመኖር የመጣ እውቀት ዋጋው ታላቅ ነው። ለዚያ እውቀት እውነተኛ መሆን ነጻነትን ይሰጠናል። ደስታን ይሰጠናል! እውነትን የምንወድ ከሆነ፣ እንሻዋለን፣ እናም አንዴ ካገገኘው፣ እንጠብቀዋለን።19

ግብዣ

እኔ ስድስተኛ ድንጋይ እንደመረጥኩት፣ ከክፍላችሁ፣ ከጉባኤያችሁ፣ ወይም ከቤተሰባችሁ ጋር ተገናኙ እና ለእግዚአብሔር ታማኝ ሆኖ ለመቆየት እንዲሁም በዚያም አለምን ለማሸነፍ የሚያስፈልጋችሁን ጥንካሬዎች አስቡ።

ቃል ኪዳን

ውድ ጓደኞች፣ በህይወታችን ጉዞ ላይ ክርስቶስ ከእኛ ጋር ለመሆን ይጓጓል። የብረት ዘንጉን ስትይዙ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር እጅ ለእጅ ተያይዛችሁ እንደምትጓዙ ቃል እገባላችኋለሁ፣ ።20 እርሱይመራችኋል፣ እንዲሁም እርሱያስተምራችኋል21እርሱ እጅ፣ በህይወታችሁ የሚከሰት ማንኛውንም ጎልያድ መጣል ትችላላችሁ።

ምስክርነት

በየቀኑ በመጸለይ፣ በየቀኑ መጽሐፈ ሞርሞንን በማንበብ፣ በየእሁዱ ቅዱስ ቁርባንን በመካፈልና በጣም በጥዋት ቢሆን እንኳን ወደ ሴሚናሪ በመሄድ ደስታ እንዳለ እመሰክራለሁ። መልካም በማድረግ ውስጥ ደስታ አለ።

ለአጽናፈ ዓለሙ አምላክ፣ ለዓለም አዳኝ፣ ለነገስታት ንጉስ ታማኝ በመሆን ውስጥ ደስታ አለ። የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዝሙር በመሆን ውስጥ ደስታ አለ።

እግዚአብሔር አባታችን ነው። የልባችሁን መሻት እና ሁኔታዎቻችሁን ያውቃል፣ እንዲሁም እርሱ ይታመንባችኋል።

ውድ ወጣቶች፣ እስከመጨረሻው በእምነት እንድትጸኑ ኢየሱስ ክርስቶስ ያግዛችኋል። ስለእነዚህ እውነቶች፣ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እመሰክራለሁ፣ አሜን።

ማስታወሻዎች

  1. 1 ሳሙኤል 17 ይመልከቱ።

  2. 1 ሳሙኤል 17፥40፣ 45–49ይመልከቱ።

  3. ማቴዎስ 22፥36–38 ይመልከቱ።

  4. ለወጣቶች ጥንካሬ፦ ምርጫዎችን ለማድረግ መመሪያ [2022 (እ.አ.አ )]፣ 11።

  5. አልማ 7፥11–14 ይመልከቱ።

  6. 1 ኔፊ 7፥12 ይመልከቱ።

  7. የራስል ኤም.ኔልሰንን፣ “አለምን ማሸነፍ እና እረፍትን ማግኘት፣” ሊያሆና፣ ህዳር 2022 (እ.አ.አ)፣ 95–98 ይመልከቱ።

  8. ራስል ኤም.ኔልሰን፣ “Choices for Eternity [ለዘለአለም የሚሆኑ ምርጫዎች]” (worldwide devotional for young adults፣ ግንቦት 15፣ 2022 (እ.አ.አ)፣ የወንጌል ቤተመጻህፍትይመልከቱ።

  9. የወጣት ሴቶች ጭብጥ” እና “የአሮናዊ ክህነት ቡድን ጭብጥ፣” ከወንጌል መዝገብ ይመልከቱ።

  10. ለወጣቶች ጥንካሬ፣ 7።

  11. ራስል ኤም. ኔልሰን፣ “የመንፈሳዊ ፍጥነት ሃይል፣” ሊያሆና፣ ግንቦት 2022 (እ.አ.አ) 97–100፣ በተጨማሪም ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 84፥19–21 ይመልከቱ።

  12. አጠቃላይ መመሪያ መጽሃፍ፦ በኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን ውስጥ ማገልገል3.5፣ የወንጌል ቤተመጻህፍትይመልከቱ።

  13. ለወጣቶች ጥንካሬ፣ 34፤ አትኩሮት ተጨምሮበት።

  14. 3 ኔፊ 14፥24–27 ይመልከቱ።

  15. ዲይተር ኤፍ. ኡክዶርፍ፣ “ለወጣቶች ጥንካሬ፤ አዳኙ ለእናንተ ያለው መልእክት፣” ለወጣቶች ጥንካሬ፣ መጋቢት 2024 (እ.አ.አ)፣ 38።

  16. ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 6፥36፤ አትኩሮት ተጨምሮበታል።

  17. ትምህት እና ቃል ኪዳኖች 6፥33–34 ይመልከቱ።

  18. ዳለን ኤች. ኦክስ፣ “ምስክርነት፣” ሊያሆና፣ ሚያዝያ 2008 (እ.አ.አ)፣ 26፤ በተጨማሪም አልማ 5፥46 ይመልከቱ።

  19. ለወጣቶች ጥንካሬ፣ 32፦ “በትምህርት ቤት፣ በስራ ቦታ፣ በሚድያ፣ በሁሉም ቦታ መቼም እስከማትሰርቁ፣ እስከማትዋሹ፣ እስከማታጭበረብሩ ወይም እስከማታታሉ ድረስ እውነትን ያን ያህል ውደዱ። በግልጽ እንዲሁም በግል ተመሳሳይ የሆናችሁ የኢየሱስ ክርስቶስ ታማኝ ተከታዮች ሁኑ።”

  20. ኔፊ 8፥19፣ 3015፥24–25ሔለማን 3፥29–30ን ይመልከቱ።

  21. 3 ኔፊ 22፥13 ይመልከቱ።