አጠቃላይ ጉባኤ
የኢየሱስ ምስክርነት
የሚያዝያ 2024 (እ.አ.አ) አጠቃላይ ጉባኤ


የኢየሱስ ክርስቶስ ምስክርነት

የማቀርብላችሁ በኢየሱስ ምስክርነት ደፋር እንደሆነ ሰው ቦታችሁን ለማስጠበቅ አሁን እርምጃ እንድትወስዱ ነው።

በ1832 (እ.አ.አ) ጆሴፍ ስሚዝ እና ሲድኒ ሪግደን የእግዚአብሔር ልጆችን ዘለዓለማዊ እጣ ፈንታ የተመለከተ አስደናቂ ራዕይ ተቀበሉ። ይህ ራዕይ ስለ ሦስት ሰማያዊ መንግሥታት ይናገራል። ባለፈው ጥቅምት ፕሬዚዳንት ዳለን ኤች ኦክስ ስለእነዚህ “የክብር መንግስታት” እንዲህ ብለዋል፣1 “በበጉ ክብር እና ድል አድራጊነት”2 ከጥቂቶች በስተቀር ሁሉም ግለሰቦች “በምርጫቸው በሚገለጠው ፍላጎታቸው መሰረት”3 በስተመጨረሻ ከእነዚህ መንግስታት ወደ አንዱ ይዋጃሉ። የእግዚአብሔር የማዳን እቅድ ለሁሉም ልጆቹ በምድር ላይ በሚኖሩበት በየትኛውም ጊዜ እና በየትኛውም ቦታ ሁሉን አቀፍ እድልን ይዟል።

ከሦስቱ መንግሥታት የሚያንሰው የቲለስቲያል ክብር እንኳን “አእምሮን ሁሉ የሚያል[ፍ]”4 ሲሆን፣ አባታችን ተስፋ የሚያደርገው—በልጁ ጸጋ አማካኝነት—ከእነዚህ መንግሥታት ከፍ ያለ ደረጃ ያለውን እና ታላቅ የሆነውን “ከክርስቶስ ጋር አብረን ወራሾች”5 የምንሆንበትን የሰለስቲያል መንግሥት በመምረጥ የዘላለም ሕይወት እንድናገኝ ነው። ፕሬዚዳንት ራስል ኤም. ኔልሰን “የሰለስቲያል መንግስትን ዘላለማዊ ግባችን በማድረግ፣ ከዚያም፣ በዚህች ምድር ላይ ሣለን የምናደርጋቸው እያንዳንዳቸው ውሳኔዎች በሚቀጥለው አለም የት እንደሚያስቀም[ጡን] በጥንቃቄ በማስላት “ስለሰለስቲያል እንድናስብ” አሣስበውናል።6

በሰለስቲያል መንግሥት ውስጥ ያሉት “የኢየሱስን ምስክርነት የተቀበሉ፣… የአዲስ ኪዳን አማላጅ በሆነው … በኢየሱስ ፍጹም የተደረጉ ጻድቃን ሰዎች ናቸው።”7 የሁለተኛው ወይም የተረስትሪያል መንግሥት ነዋሪዎች “በምድር የተከበሩ፣ በሰዎች ተንኮል ምክንያት የታወሩ” ሰዎች እንደሆኑ ተገልጸዋል። ዋናው የሚገድባቸው ባህሪ “በኢየሱስ ምስክርነት ደፋር [አለመሆናቸው]8 ነው። በአንጻሩ፣ በዝቅተኛው የቲለስቲያል መንግሥት ውስጥ የሚኖሩት “ወንጌሉን እንዲሁም የኢየሱስን … ምስክርነት … ያልተቀበሉ ናቸው።”9

በእያንዳንዱ መንግሥት ውስጥ የሚኖሩ ሰዎችን የሚለያቸው ባሕርይ ከ“ኢየሱስ ምስክርነት” ጋር ያላቸው የግንኙነት ዓይነት ሲሆን፣ እነርሱም (1) በሙሉ ልብ መከተል (2) ደፋር አለመሆን (3) በግልጽ መቃወም እንደሆኑ ልብ በሉ። እያንዳንዱ ሰው የሚሰጠው ምላሽ ዘለዓለማዊ እጣ ፈንታውን ይወስናል።

1.

የኢየሱስ ምስክርነት ምንድን ነው?

የመንፈስ ቅዱስ የሚሠጠው ምስክርነት እርሱ መለኮታዊ የእግዚአብሔር ልጅ፣ መሲህ እና አዳኝ እንደሆነ ነው። ኢየሱስ በመጀመሪያ ከእግዚአብሔር ጋር እንደነበረ እና የሰማይና የምድር ፈጣሪ እንደሆነ እንዲሁም “በእርሱ ወንጌል እንደነበረ፣ ወንጌልም ሕይወት እንደነበረ፣ ሕይወትም የሰው ብርሃን እንደነበረች”10 ዮሐንስ መስክሯል። “ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሞተ፣ እንደተቀበረ እና በሶስተኛውም ቀን እንደተነሳ፣ እንዲሁም ወደ ሰማይ እንዳረገ የሃዋርያት እና ነብያት ምስክርነት” ነው።11 ይህ “ደህንነት ሊመጣበት የሚችል ሌላ ስም የለም”12 የሚለው እውቀት ነው። በነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ፣ “መጨረሻ ስለእርሱ የተሠጠው ምስክርነት”፣ “እርሱ ህያው [ነው!] … እርሱ የአብ አንድያ ልጅ [ነው]—አለማትም በእርሱ እናም ከርሱም ዘንድ ናቸው እናም ተፈጥረዋል፣ እናም ነዋሪዎችዋም የእግዚአብሔር ወንድና ሴት ልጆች ናቸው”13 የሚለው ነው።

2.

ከዚህ ምስክርነት ባሻገር፣ በዚህ ጉዳይ ላይ ምን እናድርግ? የሚል ጥያቄ አለ።

የሰለስቲያል መንግስት ወራሾች በመጠመቅ፣ መንፈስ ቅዱስን በመቀበል እና በእምነት በማሸነፍ የኢየሱስን ምስክርነት በሙላት “ይቀበላሉ”።14 የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል መርሆዎች እና እውነቶች፣ ቅድሚያ የሚሰጧቸውን ነገሮች እና ምርጫዎቻቸውን ይወስናሉ። ምን እንደሆኑ እና ምን እየሆኑ እንደሆነ በኢየሱስ ምስክርነት ይታያል። ዓላማቸው ልግስና፣ “የክርስቶስ ንፁህ ፍቅር ነው።”15 ትኩረታቸው “የክርስቶስ ሙላ[ት] ልክ”ን16 በመከታተል ላይ ነው።

በቲረስትርያል መንግሥት ውስጥ ከሚገኙት መካከል ቢያንስ አንዳንዶቹ የኢየሱስን ምስክርነት ይቀበላሉ ነገር ግን በዚህ ጉዳይ ላይ በማያደርጉት ነገር ይለያሉ። በአዳኙ ምስክርነት ደፋር —“ለብ”17 ያለመሆን—ስሜት አልባነትን ወይም የግዴለሽነትን ደረጃ ይጠቁማል፣ በተቃራኒው ለምሳሌ በመፅሐፈ ሞርሞን ውስጥ የአሞን ህዝቦች ፣ “ለእግዚአብሔር … ባላቸው ቅንዓት የተለዩ”18 ነበሩ።

የቲለስስቲያል መንግሥት ነዋሪዎች የኢየሱስን ምስክርነት ወንጌሉን፣ ቃል ኪዳኖቹን እና ነቢያቱን የማይቀበሉ ናቸው። “በስጋዊ ፍቃዳቸውና ፍላጎታቸው መሰረት በመሄዳቸው፣ እናም የምህረት ክንዶች ወደ እነርሱ ተዘርግተው ሳለ፣ ጌታን በጭራሽ ባለመጥራታቸው የምሕረት ክንዶች ወደ እነርሱ ተዘርግተዋልና እነሱም አልተቀበሉትም”19 በማለት አቢናዲ ገልጿቸዋል።

3.

በኢየሱስ ምስክርነት ደፋር መሆን ምን ማለት ነው?

ለዚህ ጥያቄ መልስ ሊሰጡ የሚችሉ ብዙ አማራጮች አሉ። ጥቂቶቹን እጠቅሳለሁ። ስለኢየሱስ በመመሥከር ረገድ ደፋር መሆን፣ በእርግጠኝነት ያንን ምስክርነት ማሳደግን እና ማጠናከርን ይጨምራል። እውነተኛ ደቀ መዛሙርት፣ እንደ ጸሎት፣ ቅዱሳት መጻህፍትን እንደ ማጥናት፣ ሰንበትን እንደ ማክበር፣ ቅዱስ ቁርባንን እንደመካፈል፣ እንደ ንስሃ፣ እንደ ማገልገል፣ እና በጌታ ቤት እንደ ማምለክ የመሰሉ የኢየሱስ ምስክርነታቸውን የሚደግፉ እና የሚያጠነክሩ ትናንሽ የሚመስሉ ነገሮችን ችላ አይሉም። ፕሬዚዳንት ኔልሰን፣ “በየቀኑ ‘ከእግዚአብሔር መልካም ቃል’ [ሞሮኒ 6፥4] ያልተመገበ ምስክርነት በሚያስፈራ ፍጥነት ሊፈርስ ይችላል። ስለዚህ፣ … ጌታን የማምለክ እና ወንጌሉን የማጥናት የዕለት ተዕለት ልምዶች ያስፈልጉናል።” ከዚያም እንዲህ ሲሉ አክለዋል፣ “እግዚአብሔር በህይወታችሁ እንዲያሸንፍ እንድትፈቅዱ እማጸናችኋለሁ። ካላችሁ ጊዜ ውስጥ ተገቢ ድርሻ ስጡት። ይህንን ስታደርጉ አዎንታዊ መንፈሳዊ ፍጥነታችሁ ላይ ምን እንደሚከሰት ልብ በሉ።”20

ደፋር መሆን፣ ያለንን ምስክርነት ግልጽ እና ይፋ ማድረግንም ይጠቁማል። በጥምቀት ወቅት “በሁሉም ጊዜ በሁሉም ነገር የእግዚአብሔር ምስክር በመሆን…እስከ ሞትም ድረስ ለመቆም …”21 ፈቃደኛ መሆናችንን እናረጋግጣለን። በተለይ በዚህ የትንሳኤ ወቅት፣ በደስታ፣ በአደባባይ እና በግልፅ ከሞት ስለተነሣው፣ ህያው ስለሆነው ክርስቶስ ያለንን ምስክርነት እንናገራለን።

የኢየሱስን መልዕክተኞች መቀበል፣ በእርሱ ምስክርነት ደፋር የመሆን አንዱ ገጽታ ነው። እግዚአብሔር ወደ ተሻለው መንገድ ማለትም ወደ ቃል ኪዳኑ መንገድ እንድንገባ አያስገድደንም፣ ነገር ግን ምርጫችን የሚያስከትለውን መዘዝ እንዲያሳውቁን ነቢያቱን ያዛል። እናም ይህ ለቤተክርስቲያኗ አባላት ብቻ አይደለም። ነጻ የሚያወጣቸውን እውነት እንዲሰሙ፣22 ከአላስፈላጊ መከራ እንዲታደጋቸው እና ዘላቂ ደስታን እንዲያመጣላቸው በነቢያቱ እና በሐዋርያቱ አማካኝነት በፍቅር ዓለምን ሁሉ ይማጸናል።

በኢየሱስ ምስክርነት ደፋር መሆን ማለት ሌሎች፣ በተለይም ቤተሰቦባችን በቃልና በምሳሌ በተመሳሳይ መልኩ ደፋር እንዲሆኑ ማበረታታት ማለት ነው፣። በአንድ ወቅት ሽማግሌ ኒል ኤ ማክስዌል “በመሠረቱ ‘የተከበሩ’ [የቤተክርስቲያኗ] አባላት፣ ደቀ መዝሙርነታቸውን ጥልቅ ከማድረግ ይልቅ ላይ ላዩን ለሚመላለሱ እንዲሁም ‘በጉጉት [ከ]ማከናወን’ ይልቅ ግድየለሽ ለሆኑት መልዕክት አስተላልፈዋል (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 76፡7558፡27)።23 ሁሉም ሰው የመምረጥ ነፃነት እንዳለው አስታውሰው ሽማግሌ ኒል ኤ ማክስዌል እንዲህ ሲሉ ሃዘናቸውን ገልፀዋል፣ “እንደ አለመታደል ሆኖ ግን አንዳንዶች ችላ ማለትን ሲመርጡ ለራሳቸው ብቻ ሳይሆን ለቀጣዩ ትውልድ ከዚያም ለሚቀጥለው ይመርጣሉ። በወላጆች ላይ ያሉ ትናንሽ ጥርጣሬዎች በልጆቻቸው ላይ ትልቅ ማፈንገጥ ሊያስከትሉ ይችላሉ! በቤተሰብ ውስጥ ያሉ ቀደምት ትውልዶች ቅናዓት አሳይተው ሊሆን ቢችልም አሁን ላይ ባለው ትውልድ ውስጥ አንዳንዶቹ ጥርጣሬን ያሳያሉ። በሚያሳዝን ሁኔታ፣ በሚቀጥለው፣ መሸርሸሩ በዝቶ አንዳንዶች አለመስማማትን ሊመርጡ ይችላሉ።”24

ከዓመታት በፊት፣ ሽማግሌ ጆን ኤች. ግሮበርግ በ1900ዎቹ መጀመሪያ ላይ በሁዋዪ በአንዲት ትንሽ ቅርንጫፍ ውስጥ ይኖር የነበረን ወጣት ቤተሰብ ታሪክ አጋርተዋል። አንዷ ሴት ልጃቸው ባልታወቀ በሽታ ታማ ሆስፒታል በተኛች ጊዜ፣ ለሁለት አመታት ያህል የቤተክርስቲያኗ አባላት በነበሩ። በማግስቱ እሁድ በቤተክርስቲያን ውስጥ፣ አባትየው እና ልጁ ለብዙ ሳምንታት ሲያደርጉት እንደነበረው ቅዱስ ቁርባንን አዘጋጁ፣ ነገር ግን ወጣቱ አባት ዳቦውን ለመባረክ ተንበርክኮ ሳለ የቅርንጫፉ ፕሬዘዳንት በድንገት በቅዱስ ቁርባን ጠረጴዛ ላይ ማን እንዳለ ድንገት ስላወቀ ብድግ ብሎ፣ “አቁም። ቅዱስ ቁርባኑን መንካት አትችልም። ሴት ልጅህ የማይታወቅ በሽታ አለባት። ሌላ ሰው አዲስ የቅዱስ ቁርባን ዳቦ ሲያዘጋጅ ወዲያውኑ ውጣ። ከእኛ ጋር እንድትሆን አንፈልግም። ሂድ” በማለት ጮኸ። በሁኔታው የተደናገጠው አባት የቅርንጫፉን ፕሬዚዳንት ቀጥሎም ጉባኤውን በሚመረምር እይታ ተመለከተ፣ ከዚያም፣ የጭንቀት እና የኀፍረት ስሜት የተሞላውን የሁሉንም ስሜት በመረዳት ለቤተሰቡ ምልክት በመሥጠት ከፀሎት ቤቱ በጸጥታ ወጡ።

ቤተሰቡ አንዲት ቃል ሳይናገር በሐዘን ወደ ትንሹ ቤታቸው ተጓዘ። እዚያም ክብ ሰርተው ቁጭ አሉ፣ አባትየውም “እባካችሁ ለመናገር ዝግጁ እስክሆን ድረስ ዝም በሉ” አላቸው። ወጣት ልጁ ለደረሰባቸው ኀፍረት ለመበቀል ምን ማድረግ እንዳለባቸው አሰበ፡ የቅርንጫፉን ፕሬዘዳንት አሳሞች ይገድላሉ ወይንስ ቤቱን ያቃጥላሉ ወይንስ ሌላ ቤተክርስቲያንን ይቀላቀላሉ? አምስት፣ አስር፣ አስራ አምስት፣ ሃያ አምስት ደቂቃ በዝምታ አለፈ።

የአባትየው የተጨበጡ እጆች ለቀቅ ማለት ጀመሩ፣ አይኖቹም እንባ አቀረሩ። እናትየው ማልቀስ ጀመረች፣ እናም ብዙ ሳይቆይ ልጆቻቸው እያንዳንዳቸው በጸጥታ አለቀሱ። አባትየው፣ ወደ ሚስቱ ዞሮ “እወድሻለሁ” አላት፣ ከዚያም ያንኑ ቃል ለልጆቻቸው አንድ በአንድ ደገመላቸው። “ሁላችሁንም እወዳችኋለሁ እናም እንደ ቤተሰብ አብረን ለዘላለም እንድንሆን እፈልጋለሁ። ይህ ሊሆን የሚችልበት ብቸኛው መንገድ ሁላችንም የኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን መልካም አባላት ስንሆን እና በቤተመቅደስ ውስጥ በቅዱስ ክህነት ስንታተም ነው። ይህች ቤተክርስቲያን የቅርንጫፍ ፕሬዘዳንቱ ቤተክርስቲያን አይደለችም። የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን ናት። ማንም ሰው ወይም ማንኛውም ጉዳት ወይም የሚያሳፍር ሁኔታ ወይም ኩራት ለዘለዓለም አንድ ላይ እንዳንሆን እንዲያደርገን አንፈቅድም። በሚቀጥለው እሁድ ወደ ቤተ ክርስቲያን ተመልሰን እንሄዳለን። የልጃችን ህመም እስኪታወቅ ድረስ ብቻችንን እንቆያለን ነገር ግን ተመልሰን እንሄዳለን።”

ወደ ቤተ ክርስቲያን ተመለሱ፣ ልጃቸውም አገገመች እንዲሁም የላዬ ሁዋዪ ቤተመቅደስ ሲጠናቀቅ ቤተሰቡ በዚያ ታተመ። ዛሬ ከ100 የሚበልጡ ግለሠቦች፣ አባታቸው፣ አያታቸው እና ቅድመ አያታቸው ትኩረቱን ዘለዓለማዊ ጠቀሜታ ባላቸው ነገሮች ላይ ስላደረገ ያመሠግኑታል።25

አንድ መጥቀስ የምፈልገው፣ በኢየሱስ ምስክርነት ደፋር የመሆን የመጨረሻው ገጽታ ለግላዊ ቅድስና የምናደርገውን ጥረት ነው። ኢየሱስ የሚያስፈልገን ቤዛ ነው፣26 እናም “በምድር ዳርቻ ያላችሁ ሁሉ ንሰሃ ግቡ፣ እናም መንፈስ ቅዱስን በመቀበል ትቀደሱ ዘንድ፤ በመጨረሻው ቀን በፊቴ ያለእንከን ትቆሙ ዘንድ ወደ እኔ ኑ፣ እናም በስሜ ተጠመቁ”27 በማለት ይማጸናል።

ነቢዩ ሞርሞን በዚህ መልኩ “[በ]ታላቅ ስደት እናም መከራ” ”28 የጸኑትን የቅዱሳን ቡድን እንዲህ ይገልጻቸዋል።

“ይሁን እንጂ ዘወትር ፆሙ፣ እንዲሁም ፀለዩ፣ እናም ነፍሳቸውን በደስታና በመፅናናት እስከሚሞሉ ድረስም፣ አዎን፣ ልቦቻቸውን ለእግዚአብሔር በፍቃድ በመስጠት በሚመጣው ቅድስና ልቦቻቸው እንዲጸዱና እንዲቀደሱ እስከሚያደርጉ ድረስ በትህትና እየጠነከሩ፣ እናም በክርስቶስ እምነታቸውን እየጸኑ ሄዱ።”29 ልባችንን ለእግዚአብሔር የምንሠጥበትን እና በአዳኙ ጸጋ በመንፈስ ዳግም የምንወለድበትን ይህን ዓይነቱን ታላቅ የልብ መለወጥ ነው የምንፈልገው።30

ግብዣዬ በኢየሱስ ምስክርነት ደፋር እንደሆነ ሰው ቦታችሁን ለማስጠበቅ አሁን እርምጃ እንድትወስዱ ነው። ንስሐ ሊያስፈልግ ስለሚችል፣ “የንስሐ ቀናችሁን አታዘግዩ፣”31 “ሞት እንዳይመጣባችሁ ድምጼን አድምጡ፤ ባሰባችሁትም ሰዓት በጋ ያልፋል፣ እና መኸሩ ይፈጸማል፣ እና መንፈሳችሁም አይድኑም።”32 ከእግዚአብሔር ጋር የገባችሁትን ቃል ኪዳኖች ለመጠበቅ ትልቅ ፍላጎት ይኑራችሁ። “በቃሉ ጥብቅነት መናደድ”33 የለባችሁም። “በእግዚአብሔር ግራ እንዳትገኙ፣ ነገር ግን የምትጠሩበትን ድምፅ፣ እናም ደግሞ በእርሱ የምትጠሩበትን ስም እንድታዳምጡና እንድታውቁ፣ በልባችሁ የተፃፈውን [የክርስቶስን] ስም ሁልጊዜ እንድትጠብቁ እፈልጋለሁ እላችኋለሁ።”34 እንዲሁም በመጨረሻ፣ “[ኢየሱስ] የሚያስተምራችሁንና የሚያዛችሁን ታደርጉ ዘንድ ይህን በልባችሁ አኑሩ፣።” 35

አባታችን ልጆቹ ሁሉ በሰለስቲያል መንግሥቱ ከእርሱ ጋር የዘላለም ሕይወት እንዲያገኙ ይፈልጋል። ይህን ለማስቻል ኢየሱስ መከራ ተቀብሏል፣ ሞቷል እንዲሁም ከሞት ተነስቷል። እርሱ “ወደ ሰማይ [አርጓል] እናም አብን በሰዎች ልጆች ላይ ያለውን ምህረት ለመጠየቅ በእግዚአብሔር ቀኝ እጅ በኩል [ተቀምጧል]።”36 ሁላችንም በሚነድ የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ምስክርነት እንድንባረክ፣ እንድንደሰት እና በምስክርነቱ ደፋሮች እንድንሆን፣ እንዲሁም በህይወታችን ያለማቋረጥ የጸጋውን ፍሬዎች እንድናገኝ እጸልያለሁ። በኢየሱስ ክርስቶስ ስም፣ አሜን።