አጠቃላይ ጉባኤ
ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ልበሱት
የሚያዝያ 2024 (እ.አ.አ) አጠቃላይ ጉባኤ


ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ልበሱት

ቃል ኪዳኖቻችንን በማክበር፣ እግዚአብሔር ከእነዚህ ቃል ኪዳኖች ጋር የተያያዙ ብዙ ቃል የተገቡ በረከቶችን እንዲያፈስ እናደርጋለን።

የመጨረሻዎቹ ሁለቱ ትንንሽ ልጆቼ እያደጉ ሲሄዱ፣ የሚያዝናኑ እና ትኩረትን የሚስቡ ሆነው በታሪኮቻቸው ውስጥ ምልክትን የሚጠቀሙ መጽሃፎች እንዳሉ ደረስኩበት። ማታ ማታ አብረን ስናነብ፣ ፀሃፊው ጥልቅ መርሆዎችን፣ በተለይም የወንጌል መርሆዎችን ለማስተማር የተጠቀመበትን ምልክት ልጆቼ እንገነዘቡ መርዳት እወድ ነበር።

አንድ ቀን ትንሹ ልጄ ገና በአሥራዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ ላይ እያለ ይህንን እየተረዳው እንደሆነ አወቅኩ። በታሪኩ ዘና ለማለት ብቻ በመፈለግ አዲስ መጽሐፍ ማንበብ ጀምሮ ነበር ነገር ግን አዕምሮው በሚያነበው ነገር ሁሉ ጥልቅ ትርጉም ለማግኘት ይሞክር ነበር። እሱ ሲበሳጭ እኔ በውስጤ ፈገግ እያልኩ ነበር።

ኢየሱስ በታሪኮች እና በምልክቶች አስተምሯል1—የእምነትን ኃይል ለማስተማር የሰናፍጭ ዘር፣2 የነፍስን ዋጋ ለማስተማር የጠፋ በግ፣3 የእግዚአብሔርን ባሕርይ ለማስተማር ደግሞ አባካኙ ልጅ።4 ምሳሌዎቹ “የሚሰማ ጆሮ” ላላቸው ሰዎች ጥልቅ ትምህርት የሚያስተምርባቸው ምልክቶች ነበሩ።5 ልክ ለልጆቼ እንደማነባቸው ዓይነት ተመሳሳይ መጽሃፎችን የሚያነቡ ብዙ ሰዎች ጥልቅ ትርጉሞች እንዳሏቸው እና ከእነዚህ ታሪኮች ውስጥ ሊገኙ የሚችሉ ተጨማሪ ነገሮች እንዳሉ ፈጽሞ እንደማያውቁ ሁሉ ጥልቅ ትርጉሙን የማይፈልጉ አይረዱትም6

እግዚአብሔር አብ አንድያ ልጁን ለእኛ መሥዋዕት አድርጎ ባቀረበ ጊዜ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ በሰማይ ያለው አባታችን ለእያንዳንዳችን ያለውን የማይጠፋ ፍቅር ትልቅ ምልክት ሆነ።7 ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር በግ ሆነ።8

ከእግዚአብሔር ጋር ወደ ቃል ኪዳን ግንኙነት እንገባ ዘንድ የመጋበዝ እድል እና በረከት አለን፣ በዚህም የኛ ህይወት ራሱ የዚያ ቃል ኪዳን ምልክት ሊሆን ይችላል። ቃል ኪዳኖች እግዚአብሔር በጊዜ ሂደት እንዲቀርጸን እና እንዲለውጠን እንዲሁም አዳኙን እንድንመስል የሚያነሳን አይነት ግንኙነት ይፈጥራሉ፣ ወደ እርሱ እና ወደ አባታችን9 ይበልጥ እንድንቀርብ፣ በመጨረሻም ወደ እነርሱ መገኛ እንድንገባ ያዘጋጁናል።

በምድር ላይ ያለ እያንዳንዱም [ግለሠብ] የተወደዱ የእግዚአብሔር ሴት እና ወንድ ልጆች ናቸው።10 የቃል ኪዳን አካል ለመሆን በምንመርጥበት ጊዜ፣ ከእርሱ ጋር ያለንን ግንኙነት ያሳድጋል እንዲሁም ጥልቅ እንዲሆን ያደርጋል። ፕሬዚዳንት ረስል ኤም. ኔልሰን ከእግዚአብሔር ጋር ቃል ኪዳን ለመግባት ስንመርጥ ግንኙነታችን ከቃል ኪዳኑ በፊት ከነበረው ይልቅ የቀረበ እንደሚሆን እንዲሁም በዕብራይስጥ ቋንቋ ሄሴድ ተብሎ በሚጠራው የቃል ኪዳን ፍቅር፣ በተጨማሪ ምህረት እና ፍቅር እንዲባርከን ያስችለዋል በማለት አስተምረዋል።11 የቃል ኪዳኑ መንገድ ከእግዚአብሔር ጋር ስላለን ግንኙነት—ከእርሱ ጋር ስላለን የ ሄሴድ ግንኙነት ነው።12

አባታችን ከሁሉም ወንዶች እና ሴቶች ልጆቹ ጋር ጥልቅ ግንኙነት እንዲኖረው ይፈልጋል፣13 ነገር ግን እርሱ እኛን አያስገድደንም። በቃል ኪዳን ግንኙነት ወደ እርሱ ለመቅረብ በምንመርጥበት ጊዜ፣ እርሱ ወደ እኛ እንዲቀርብ ያስችለዋል14 እንዲሁም በኃይሉ እና ከፍ ባለ ችሎታው ይባርከናል።

እግዚአብሔር የቃል ኪዳኑን ቅድመ ሁኔታዎች እና ሃላፊነቶችን ያስቀምጣል።15 ወደዚያ ግንኙነት ለመግባት በምንመርጥበት ጊዜ፣ እርሱ ባስቀመጣቸው ቅድመ ሁኔታዎች ለመታዘዝ ፈቃደኛ መሆናችንን በቃል ኪዳኑ ምሳሌያዊ ተግባራት እንመሰክራለን።16 ቃል ኪዳኖቻችንን በማክበር፣ ለመለወጥ እና ይበልጥ እንደ አዳኙ ለመሆን እየጨመረ የሚሄድ ኃይልን ጨምሮ ከቃል ኪዳኖች ጋር የተያያዙ ብዙ ቃል የተገቡ በረከቶችን እግዚአብሔር እንዲያፈስ እናስችለዋለን።17 ኢየሱስ ክርስቶስ ለምንገባቸው ቃል ኪዳኖች ሁሉ ማዕከል ሲሆን፣ የቃል ኪዳኑን በረከቶች ያስቻለው የኃጢያት ክፍያው ነው።18

ውሃ ውስጥ በመጥለቅ መጠመቅ ከእግዚአብሔር ጋር የቃል ኪዳን ግንኙነት ውስጥ የምንገባበት ምሳሌያዊ በር ነው። በውሃ ውስጥ መጥለቅ እና እንደገና መውጣት የአዳኙን ሞት እና ለአዲስ ህይወት ትንሳኤ ምልክት ነው።19 እኛ ስንጠመቅ፣ በምሳሌያዊ ሁኔታ ሞተን ወደ ክርስቶስ ቤተሰብ ዳግመኛ እንወለዳለን እንዲሁም ስሙን በላያችን ላይ ለመውሰድ ፈቃደኛ መሆናችንን እናሳያለን።20 እኛ እራሳችን ያንን የቃል ኪዳን ምልክት እንይዛለን። በአዲስ ኪዳን “ከክርስቶስ ጋር አንድ ትሆኑ ዘንድ የተጠመቃችሁ ሁሉ ክርስቶስን ለብሳችኋልና”21 የሚለውን እናነባለን። በምሳሌያዊ ሁኔታ በጥምቀታችን ክርስቶስን እንለብሳለን።

የቅዱስ ቁርባን ሥርዓትም ወደ አዳኙ ይጠቁማል። ዳቦው እና ውኃው ለእኛ የፈሰሰው የክርስቶስ ሥጋና ደም ምልክት ነው።22 አዳኙን እራሱን የሚወክል የክህነት ተሸካሚ፣ ዳቦውን እና ውሃውን እንደ የኃጢያት ክፍያው ስጦታ ምሳሌነት በየሳምንቱ ይሰጠናል። የሥጋውንና የደሙን ምሳሌ የመብላትንና የመጠጣትን ተግባር ስናከናውን፣ ክርስቶስ በምሳሌያዊ ሁኔታ የእኛ አካል ይሆናል።23 በየሳምንቱ አዲስ ቃል ኪዳን ስንገባ እንደገና ክርስቶስን እንለብሳለን።24

በጌታ ቤት ከእግዚአብሔር ጋር ቃል ኪዳን ስንገባ፣ ከእርሱ ጋር ያለንን ግንኙነት የበለጠ ጥልቅ እናደርጋለን።25 አዳኙ እና የኃጢያት ክፍያው ማዕከላዊ በሆነበት በቤተመቅደስ ውስጥ የምናደርገው ነገር ሁሉ አባታችን ለእኛ ወዳለው እቅድ ይጠቁማል።26 ልባችንን ስንከፍት እና ጥልቅ ትርጉሞችን በጸሎት መንፈሥ ለመረዳት ስንፈልግ፣ ጌታ27 በሥርዓቶች እና በቃል ኪዳኖች ምልክቶች አማካኝነት በሥርዓት ላይ ሥርዓት ያስተምረናል።

እንደ ቤተመቅደስ ቡራኬ አካል፣ ወንዶችም ሆኑ ሴቶች የቅዱስ ክህነትን ልብስ እንዲለብሱ ፈቃድ ይሰጣቸዋል። ይህ የተቀደሰ ግዴታ እና መብት ነው።

በብዙ ሃይማኖታዊ ባህሎች ውስጥ፣ ልዩ ውጫዊ ልብሶች የሚለበሱት፣ እንደ አንድ ግለሠብ የእምነት እና ለእግዚአብሔር ያለ ቁርጠኝነት ምልክት ሲሆን፣28 የአምልኮ ሥርዓቶችን የሚመሩ ሰዎች ብዙውን ጊዜ የክብረ በዓል ልብስ ይለብሳሉ። እነዚያ የተቀደሱ ልብሶች ለለባሾቹ ጥልቅ ትርጉም አላቸው። በጥንት ዘመን የክብረ በዓል ልብሶችም ከቤተመቅደስ ሥርዓት ጋር ተያይዘው ይለብሱ እንደነበር በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ እናነባለን።29

የኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን አባላት እንደመሆናችን፣ በጌታ ቤት ከእግዚአብሔር ጋር ቃል ኪዳን ለመግባት የመረጥን ሰዎች፣ በቤተመቅደስ አምልኮ ወቅት የተቀደሰ የሥርዓት ውጫዊ ልብስ እንለብሳለን፣ እነዚህም በጥንታዊ የቤተመቅደስ የአምልኮ ሥርዓቶች የሚለበሱ አልባሣትን የሚያመላክቱ ናቸው። የቅዱስ ክህነት ልብስን ደግሞ በቤተመቅደስ አምልኮ እና በቀን ተቀን ህይወታችን እንለብሣለን።30

የቅዱስ ክህነት ልብስም ጥልቅ ምሳሌ አለው እንዲሁም ወደ አዳኙ ይጠቁማል። አዳምና ሔዋን የዛፍ ፍሬውን በልተው ከኤደን ገነት ሲወጡ፣ መሸፈኛ ይሆናቸው ዘንድ የቁርበት ልብስ ተሰቷቸው ነበር።31 አዳኙ ለእኛ ሲል የከፈለውን መስዋዕትነት ምሳሌ ይሆን ዘንድ የቆዳ ልብስ ለመስራት አንድ እንስሳ ሳይሰዋ አልቀረም። ካፋር የሚለው ቃል የሃጢያት ክፍያ መሰረታዊ የዕብራይስጥ ቃል ሲሆን ከትርጉሞቹ መካከል አንዱ “መሸፈን” የሚል ነው።32 የቤተመቅደስ ልብሳችን አዳኙ እና የኃጢያት ክፍያው በረከቶች በህይወታችን ሁሉ እንደሚሸፍኑን ያስታውሱናል። በየቀኑ የቅዱስ ክህነት ልብስን ስንለብስ ያ ውብ ምልክት የእኛ አካል ይሆናል።

በአዲስ ኪዳን የሮሜ መጽሐፍ ውስጥ “ሌሊቱ አልፎአል ቀኑም ቀርቦአል፤ እንግዲህ የጨለማውን ሥራ አውጥተን የብርሃንን ጋሻ ጦር እንልበስ። … ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ልበሱት።”33 የሚል ቃል እናነባለን።

በህይወት ዘመኔ ሁሉ አዳኙ እና ወሰን የሌለው የኃጢያት ክፍያው በረከቶች በምድራዊ ጉዞዬ ሁሉ እንደሚሸፍኑኝ ለማስታወስ፣ የቅዱስ ክህነት ልብስ እንድለብስ ስለተሰጠኝ እድል በጣም አመስጋኝ ነኝ። በጌታ ቤት ከእግዚአብሔር ጋር የገባሁትን ቃል ኪዳን ስጠብቅ፣ እራሱ የብርሃን ጋሻ የሆነውን ክርስቶስን በምሳሌያዊ ሁኔታ እንደለበስኩትም ያስታውሰኛል። ከክፉ ይጠብቀኛል34 ኃይልን እና አቅምን ይጨምርልኛል፣35 እናም በዚህ ዓለም ጨለማ እና አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ብርሃን እና መመሪያዬ36 ይሆነኛል።

በቅዱስ ክህነት ልብስ እና ከክርስቶስ ጋር ያለው ግንኙነት ጥልቅ እና የሚያምር ምሳሌያዊ ትርጉም አለ። ቅዱሥ ልብሡን ለመልበስ ያለኝ ፈቃደኝነት37 ለእርሱ የማሣየው የእኔ ምልክት እንደሚሆን አምናለሁ።38 ይህ ለእግዚአብሔር የማሣየው የራሴ የግል ምልክት እንጂ ለሌሎች የማሣየው ምልክት አይደለም።39

ስለአዳኛችን ስለኢየሱስ ክርስቶስ በጣም አመስጋኝ ነኝ።40 ለእኛ ያደረገው የኃጢያት ክፍያ መስዋዕት እርሱ እና የሰማይ አባታችን ለእያንዳንዳችን ያላቸውን እጅግ የላቀ ፍቅር፣41 የዚያ ፍቅር እና መስዋዕት ተጨባጭ ምልክቶች—በአዳኙ እጆች፣ እግሮች እና ጎን ላይ ያሉ ምልክቶች— ከትንሣኤው በኋላም እንኳን ነበሩ።42

የቅዱስ ክህነት ልብስን መልበስ ጨምሮ ቃል ኪዳኖቼን እና ለእግዚአብሔር ያሉብኝን ግዴታዎች ስጠብቅ፣ የገዛ ህይወቴ ለአዳኙ ለኢየሱስ ክርስቶስ ያለኝ ፍቅር እና ጥልቅ ምስጋና እንዲሁም ሁል ጊዜም ከእኔ ጋር እንዲሆን ያለኝ ፍላጎት የግል ምልክት ሊሆን ይችላል።

እስካሁን ይህን ካላደረጋችሁ፣ በጌታ ቤት ከእርሱ ጋር ቃል ኪዳን በመግባት ከእግዚአብሔር ጋር የጠለቀ ግንኙነት መመሥረትን እንድትመርጡ እጋብዛችኋለሁ። በንግግራቸው የግርጌ ማስታወሻዎች ላይ ያሉትን አስደሣች ትምህርቶች ጨምሮ (አብዛኞቹ የጉባኤ ንግግሮች አሏቸው) የነቢያችንን ንግግሮች አጥኑ። ለዓመታት በተለይም የቤተክርስቲያኗ ፕሬዚዳንት ከሆኑ በኋላ ስለ ቃል ኪዳኖች ደጋግመው ተናግረዋል። ከእግዚአብሔር ጋር ቃል ኪዳኖችን በመግባት እና በመጠበቅ የእናንተ ሊሆኑ ስለሚችሉት አስደሳች በረከቶች እንዲሁም ተጨማሪ ኃይል እና አቅም ከትምህርታቸው ተማሩ።43

አጠቃላይ መመሪያ መፅሐፍ እንደሚገልጸው፣ የቤተመቅደስን ቃል ኪዳን ለማድረግ የሚስዮን ጥሪ ማግኘት ወይም ለማግባት መታጨት አያስፈልግም።44 አንድ ሰው ቢያንስ 18 ዓመት ሊሞላው፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ወይም ተመሳሳይ ትምህርት ተማሪ ያልሆነ እና ቢያንስ ለአንድ ዓመት የቤተክርስቲያኗ አባል የሆነ ሊሆን ይገባል። አስፈላጊ የሆኑ የግል ቅድስና ደረጃዎችም አሉ።45 በጌታ ቤት ውስጥ ቅዱስ ቃል ኪዳኖችን በመግባት ከሰማይ አባታችሁ እና ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ያላችሁን ግንኙነት ለማጠናከር ፍላጎት ካላችሁ፣ ከኤጲስ ቆጶሳችሁ ወይም ከቅርንጫፍ ፕሬዚዳንታችሁ ጋር እንድትነጋገሩ እና ፍላጎቶቻችሁን እንዲያውቁት እንድታደርጉ እጋብዛችኋለሁ። እነዚያን ቃል ኪዳኖች ለመቀበል እና ለማክበር እንዴት መዘጋጀት እንዳለባችሁ እንድታውቁ ይረዳችኋል።

ከእግዚአብሔር ጋር ባለን የቃል ኪዳን ግንኙነት አማካኘነት፣ የራሳችን ህይወት በሰማይ ላለው አባታችን ላለን ቁርጠኝነት እና ጥልቅ ፍቅር፣ ለእርሱ ያለን ሄሴድ 46 እንዲሁም አንድ ቀን ወደመገኛቸው ለመግባት በመዘጋጀት፣ ለማደግ እና በስተመጨረሻም እንደ አዳኛችን ለመሆን ያለን ፍላጎት፣ ህያው ምልክት ሊሆን ይችላል። የዚያ የቃል ኪዳን ግንኙነት ታላቅ በረከቶች ከሚያስከፍሉት ዋጋ ጋር ተመጣጣኝ እንደሆኑ እመሰክራለሁ። በኢየሱስ ክርስቶስ ስም፣ አሜን።