አጠቃላይ ጉባኤ
በማደግ ላይ ያለውን ትውልድ መደገፍ
የሚያዝያ 2024 (እ.አ.አ) አጠቃላይ ጉባኤ


በማደግ ላይ ያለውን ትውልድ መደገፍ

በምርጫዎቻቸው ላይ ትልቅ ተጽዕኖ ያለው፣ በወጣቶቹ ህይወት ውስጥ ያሉት ግንኙነቶች ናቸው።

ለእናንተ ንግግርን ለማቅረብ በምዘጋጅበት ወቅት፣ በሔለማን እና በአሞናውያን ሰዎች ብላቴና ወንድ ልጆች ታሪክ ተስቤ ነበር። ይህንን መዝገብ በማጥናት የመጽሐፈ ሞርሞን ነቢያት ወላጆችን፣ ኤጲስ ቆጶሳትን፣ እና የአጥቢያ አባላትን የማስተማር ሃይል ሊሰማኝ ችሏል።

ሔለማን፣ ወጣት አሞናውያን ሊያምኑት የሚችሉት ሰው ነበር። በጽድቅ እንዲያድጉ እና አዋቂ እንዲሆኑ ረዳቸው። ያውቁትና ይወዱት ነበር እንዲሁም “[እሱ] መሪያቸው እንዲሆን ይፈልጉ ነበር።” 1

ሔለማን እነዚህን ወጣት ወንድ ልጆች እንደ ልጆቹ ይወዳቸውና አቅማቸውን ያውቅ ነበር።2 ሽማግሌ ዴል ጂ. ረንለንድ እንዲህ ሲሉ አስተምረዋል፣ “ሌሎችን በውጤታማ ሁኔታ ለማገልገል በሰማይ አባት አይኖች ልንመለከታቸው ይገባል። በዚያ ጊዜ ብቻ ነው የነፍስን እውነተኛ ዋጋ መረዳት የምንጀምረው። የሰማይ አባት ለሁሉም ልጆቹ ያለው ፍቅር ሊሰማን የሚችለው በዚያ ጊዜ ብቻ ነው።”3 ዛሬ ኤጲስ ቆጶሳት በጥበቃቸቸው ስር ያሉትን ወጣቶች መለኮታዊ ማንነት ለመመልከት በሚያስችላቸው የማስተዋል ስጦታ ተባርከዋል።

ሔለማን በእርሱ ጥበቃ ስር የነበሩትን ወጣት ልጆች “ቆጠራቸው”4 ከእነርሱ ጋር ጠንካራ ግንኙነት መገንባትን ቅድሚያ ይሰጥ ነበር።

የሕይወትና የሞት ጉዳይ በሆነበት ጊዜ ሔለማንና ወጣቶቹ ተዋጊዎች ያሳድዷቸው የነበሩትን ተዋጊዎች አመለጧቸው። ሔለማን ከወጣቶቹ ጋር ተመካከረ፦

“እነሆ፣ በወጥመዳቸው እስከሚይዙን ወደ እነርሱም እንድንመጣ ዘንድ ቆመው እንደሆነ አናውቅም። …

“ስለዚህ ልጆቼ ምን ትላላችሁ፣ … ?”5

እነዚህ አማኝ ወጣት ወንዶች እንዲህ ሲሉ መለሱ፦ “አባታችን፣ እነሆ አምላካችን ከእኛ ጋር ነው፤ እናም እንድንወድቅ አይፈቅድም፤ ስለዚህ [እንሂድ] ።”6 ሔለማን እነዚህ ወጣት ወንድ ልጆች ያሣለፉትን ውሳኔ 7 እንዲተገብሩ8 በረዳቸው ጊዜ ቀኑን አሸንፈው ነበር።

ወጣቶቹ አሞናውያን ታላቅ ምክንያት ነበራችው እናም “በሰዎቹ ድጋፍ ምክንያት” ጀግኖች ነበሩ።9 በሔለማን ይመራ የነበረው “ይህ ትንሹ ሃይል”፣ ተሞክሮ በነበራቸው የኔፋዊያን ሰራዊት ልብ ውስጥ “ታላቅ ተስፋን እና ብዙ ደስታን” አምጥቶ ነበር። 10 ዛሬ ኤጲስ ቆጶሳት በተለየ መልኩ ተሰጥኦ ያላቸውን ወጣቶች፣ አጥቢያውን እንዲባርኩ እና እስራኤልን እንዲሠበሥቡ መምራት ይችላሉ። ፕሬዚዳንት ራስል ኤም. ኔልሰን ይህ “[እነሱ] ወደ ምድር የተላኩበት ተልእኮ” እንደሆነ አስተምረዋል።11

ሔለማን፣ “በሁሉም ጊዜ በተሰጣቸው በማንኛውም ነገር ታማኝ” እንደነበሩት ልክ እንደነዚህ አሞናውያን፣ 12 በታማኝነት መሪዎቹን ተከተለ። ተግዳሮቱ ወይም ፈተናው ምንም ይሁን ምን13 ሔለማን አላማቸውን ለማሳካት ሁልጊዜ “ድፍረትን አገ[ኘ]”። “ከትንንሽ ልጆ[ቹ] ጋር እንዲዘምት” መመሪያ ሲሰጠው14 ታዟል።

ኤጲስ ቆጶሳት “ከአጥቢያው የወጣት ሴቶች ፕሬዚዳንቶች ጋር በመወያየት፣” የመሪዎቻችንን ምሪት በመከተላቸው የዛሬ ወጣቶች ተባርከዋል።15 የካስማ ፕሬዚዳንቶች ኤጲስ ቆጶሳትን እና የወጣት ሴቶች ፕሬዚዳንቶችን የወጣቶችን ሃላፊነት እንዲያሟሉ መመሪያ እንደሚሰጣቸው ያረጋግጣሉ።16

ሔለማን ቃል ኪዳኖችን አከበረ። አሞን የብላቴና ወንድ ልጆችን ወላጆች ወንጌልን ሲያስተምራቸው፣ እነዚህ ወላጆች ይህን በተከፈተ ልብ ተቀበሉት። አዲስ ለሆነው የጽድቅ ደቀመዝሙርነት ህይወታቸው የተሰጡ ከመሆናቸው የተነሳ “የአመጽ መሳሪያቸውን ለመጣል ቃል ገቡ።”17 ይህንን ቃል ኪዳን ጥሶ የድሮ የጦርነት መንገዳቸው ወደሆነው መመለስን ታሳቢ እንዲያደርጉ ያደረጋቸው ብቸኛው ነገር ኔፋዊያንን በአደጋ ውስጥ ማየታቸው ነበር።

አሞናዊያን ደህንነቱ የተጠበቀ ቤትን ለሰጧቸው ለእነዚህ ሰዎች እርዳታ ማድረግን ፈልገው ነበር። ሔለማን፣ ከሌሎቹ ጋር በመሆን፣ መቼም ላለመዋጋት የገቡትን ቃል ኪዳን እንዲጠብቁ አሳመናቸው። እነዚህ አሞናውያን በሰይፋቸው እና በቀስቶቻቸው ሊሰጡ ይችሉ ከነበረው ጥንካሬ ይልቅ እግዚአብሔር ሊሰጣቸው ይችል በነበረው ጥንካሬ ላይ ይበልጥ ተማምኖ ነበር።

ሔለማን እና ወጣት ተዋጊዎቹ አስፈሪ መከራዎች በገጠማቸው ጊዜ፣ ሔለማን ቆራጥ ነበር። “ነገር ግን እነሆ ይህ ምንም ማለት አይደለም— እግዚአብሔር እንደሚያድነን እናምናለን።”18 አንድ ጊዜ፣ እስከ ሞት በሚያደርስ ረሃብ በነበሩበት ጊዜ፣ መልሶቻቸው፣ “እግዚአብሔር እንዲያበረታቸው እና፣ እንዲያድ[ናቸው] በጸሎት ነፍሳቸውን ማፍሰስ ነበር፤ … [እናም] ጌታም እንደሚያድናቸው ማረጋገጫን በመስጠት ጎበ[ኛቸው]”፣19 “ይህም የሆነው እንዲያምኑ በተማሩት ታላቅ እምነት የተነሣ ነው።”20

እነዚህ ወጣት ወንዶች በወላጆቻቸው ተደግፈው እንደነበር ከሔለማን እንማራለን። እነዚህ ታማኝ ወላጆች ዋና ሃላፊነታቸው ልጆቻቸውን ማስተማር እንደነበረ ያውቁ ነበር። ልጆቻቸው የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት እንዲጠብቁና በፊቱም በቅንነት እንዲራመዱ አስተማሯቸው፡፡21 እናቶቻቸው፣ የማይጠራጠሩ ከሆነ እግዚአብሔር እንደሚያድናቸው አስተምረዋቸው ነበር።22 አባቶቻቸው ቃል ኪዳን የመግባት ሃያል የሆነ ምሳሌን ትተውላቸው ነበር።23 እነዚህ የቀድሞ ተዋጊዎች የጦርነትን አሰቃቂ ሁኔታዎች ያውቁ ነበር። ተሞክሮ የሌላቸው ወንድ ልጆቻቸውን በሔለማን ጥበቃ ስር እንዲሆኑ እምነታቸውን ጣሉ እንዲሁም “ብዙ ስንቆችን” በመላክ ረዷቸው።24

ሔለማን ወጣት ወንድ ልጆቹን ባገለገለበት ጊዜ ብቻውን አልነበረም። እርዳታ እና ምሪት የሚጠይቃቸው ሰዎች በዙሪያው ነበሩት። ካፒቴን ሞሮኒን እርዳታ እንዲያደርግለት ጠይቆት ነበር፣ እርዳታውንም መጣለት።

በጌታ መንግስት እያገለገለ ያለ ማንኛውም ሰው ብቻውን አያገለግልም። ጌታ በአጥቢያዎች እና በካስማዎች ባርኮናል። በእርሱ ዳግም በተመለሰ ድርጅት አማካኝነት፣ ማንኛውንም ተግዳሮት ለመጋፈጥ፣ ሃብቱ፣ ጥበቡ፣ እና ተነሳሽነቱ አለን።

ኤጲስ ቆጶስ በቡድኖች በኩል ለአጥቢያዎች መመሪያ ይሰጣል።25 በየሩብ ዓመቱ የአገልግሎት ቃለ መጠይቆች እንዲካሄዱ ይረዳል ከዚያም የሽማግሌዎች ቡድን እና የሴቶች መረዳጃ ማሕበር ቤተሰቦችን የማገልገል ሃላፊነታቸውን እንዲያሟሉ ያበረታታል። እነዚህ አመራሮች ፍላጎቶችን በመገምገም እና በመንፈሥ የተነሣሡ መፍትሄዎችን በማግኘት ዙሪያ ግምባር ቀደም ይሆናሉ። የካስማ አመራሮች የሽማግሌዎች ቡድንን እና የሴቶች መረዳጃ ማህበርን አመራሮች ስለእነዚህ ሃላፊነቶች በማስተማር ድጋፍ ይሠጣል።

ለመሪዎች እና ለወላጆች የሚያስፈልጓቸው መመሪያዎች በወንጌል ላይብረሪ እና በGospel Living apps መተግበሪያዎች ውስጥ ይገኛሉ። በእነዚህ በመንፈሥ የተነሣሡ ግብዓቶች ውስጥ፣ ቅዱሳት መጻህፍትን፣ የአሁን ዘመን ነቢያት አስተምህሮዎችን እና የአጠቃላይ መመሪያ መጽሐፍን ልናገኝ እንችላለን። በወንጌል ላይብረሪ ውስጥ የሚገኘው የወጣቶች ማውጫ[youth tab] ለቡድን እና ለክፍል አመራሮች ብዙ ግብአቶች አሉት፣26 እንዲሁም ለወጣቶች ጥንካሬ፦ ምርጫዎችን የማድረግ መመሪያ ይገኝበታል። ሁሉም የአጥቢያው አባላት እነዚህን በመንፈሥ የተነሣሡ ግብአቶች፣ ሲያጠኑ እና ከመንፈስ ቅዱስ ምሪትን ሲፈልጉ፣ ወጣቶችን በማጠናከር ረገድ ሁሉም ከጌታ ምሪትን መቀበል ይችላሉ።

እንዲሁም አባላት እያደገ ባለው ትውልድ ላይ ባተኮሩ ጊዜ መላው አጥቢያ ይጠናክራል እንዲሁም ይባረካል። ጉድለቶቻችን እና ድክመቶቻቻን እንዳሉ ሆነው፣ የሰማይ አባታችን፣ በመንፈስ ቅዱስ አጋርነት በኩል ሌሎችን እንድንረዳ እያንዳንዳችንን ጋብዞናል። የመንፈስ ቅዱስን ምሪት ስንከተል እንደምናድግ እና ንጹህ እንደምንሆን ያውቃል።27 ጥረቶቻችን ፍጹም አለመሆናቸው ችግር የለውም። ከጌታ ጋር ስንጣመር፣ ጥረቶቻችን እርሱ ለወጣቶች ሊያደርገው ከሚችለው ነገር ጋር እንደሚስማሙ ማመን እንችላለን።

ወጣቶቹን በመርዳት አኳያ መንፈስ ቅዱስ የሚሰጠውን መመሪያ በመከተል፣ በህይወታቸው ውስጥ የሰማይ አባት ፍቅር ምስክሮች እንሆናለን። ከጌታ የሚመጡ ምሪቶችን መተግበር የፍቅር እና የመተማመን ግንኙነቶችን ይገነባሉ። በምርጫዎቻቸው ላይ ትልቅ ተጽእኖ ያላቸው፣ በወጣቶቹ ህይወት ውስጥ ያሉት ግንኙነቶች ናቸው።

ሌሎችን ስለማገልገል የሚሰጡ የመንፈሥ ምሪቶችን በመፈለግ እና በመተግበር ሂደት ላይ ከእኛ ጋር ሲሳተፉ ወጣቶች የራዕይን ቅደም ተከተል ይማራሉ። ወጣቶቹ ይህን በመንፈሥ የተነሣሣ ምሪት እንዲያገኙ ጌታን ሲጠይቁ፣ ከእርሱ ጋር ያላቸው ግንኙነት እና እምነት ጠንካራ ይሆናል።

ሙሉ ለሙሉ ሳንቆጣጠራቸው እርዳታን እና መመሪያን በመስጠት በወጣቶች ላይ ያለንን እምነት እንገልጻለን።28 ያለ እኛ ተሣትፎ ወጣቶቹ አንድ ላይ በመመካከር እንዲማሩ በምንፈቅድበት ጊዜ፣ ተነሳሽነት ያለውን ትምህርት በመምረጥ እና እቅዳቸውን ተግባራዊ በማድረግ እውነተኛ የደስታ እና የእድገት ተሞክሮ ይኖራቸዋል።

ፕሬዚዳንት ሔንሪይ ቢ. አይሪንግ እንዲህ በማለት አስተምረዋል፦ “በጣም ወሳኝ የሆነው፣ እነርሱ በእውነትም ማን እንደሆኑ እና ምን መሆን እንደሚችሉ [ከእናንተ] መማራቸው ነው። የእኔ ግምት፣ ይህንን በቃል ከሚሰጡ ትምህርቶች ያን ያህል እንደማይማሩት ነው። ከእናንተ የማንነት፣ እነሱ ማን ናቸው ብላችሁ ከምታስቡት እና ማን ሊሆኑ ይችላሉ ብላችሁ ከምታስቡት ስሜቶች ያገኙታል።29

ወጣቶቻችን በድፍረታቸው፣ በእምነታቸው እና በአቅማቸው ያስደንቁናል። ሙሉ በሙሉ የሚሳተፉ የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀመዛሙርት ለመሆን ሲመርጡ፣ የእርሱ ወንጌል በልባቸው ውስጥ ይቀረፃል። እርሱን መከተል ለማድረግ ያህል ብቻ የሚያደርጉት ነገር ሳይሆን የማንነታቸው አካል ይሆናል።

ሔለማን፣ ወጣት አሞናውያን፣ ደፋር የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀመዝሙር እንዴት እንደሚኖር መመልከት እንዲችሉ ረድቷቸዋል። ዛሬ የክርስቶስ ደቀመዛሙርት እንዴት እንደሚኖሩ በማሳየት ለወጣቶች ብርቱ ምሳሌዎች መሆን እንችላለን። አማኝ ወላጆች በልጆቻቸው ህይወት ውስጥ እነዚህ ምሳሌዎች እንዲኖሯቸው እየጸለዩ ነው። ምንም አይነት ፕሮግራም የአፍቃሪ፣ ቃል ኪዳን ጠባቂ ጎልማሶችን ተጽዕኖ ሊተካ አይችልም።

የካህናት ቡድን ፕሬዚዳንት እንደመሆኑ፣ ኤጲስ ቆጶሱ፣ እንዴት ታማኝ ባል እና አፍቃሪ አባት30 መሆን እንደሚችሉ ለወጣቶች ምሳሌ በመሆን ጥበቃ በማድረግ፣ አስፈላጊ ነገሮችን በማቅረብ እና በጽድቅ መንገዶች በመምራት ረገድ ሊያስተምራቸው ይችላል።31 ኤጲስ ቆጶሳት፣ ወጣቶች ላይ ጠንካራ ትኩረት በማድረግ፣32 ለብዙ ትውልዶች የሚቆይ ተጽዕኖ ይኖራቸዋል።

የዛሬ ወጣቶች በጣም ክቡር ከሆኑት33 የሰማይ አባት መንፈሶች መካከል ተጠቃሽ ናቸው። በቅድመ ምድራዊ ህይወት ውስጥ ታማኝ የእውነት እና የነጻ ምርጫ ጠባቂዎች ነበሩ።34 በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ባላቸው ጠንካራ ምስክርነት አማካኝነት እስራኤልን ለመሰብሰብ በእነዚህ ቀናት ውስጥ ተወልደዋል። እያንዳንዳቸውን እንዲሁም ታላቅ አቅማቸውን ያውቃል። ዕድገት እያደረጉ በሚሄዱበት ጊዜ ይታገሣል። ያድናቸዋል እንዲሁም ይጠብቃቸዋል። ይፈውሳቸዋል እንዲሁም ይመራቸዋል። ያነሳሳቸዋል። እኛ ወላጆቻቸው እና መሪዎቻቸው እነርሱን ለመደገፍ ዝግጁ ነን። ቀጣዩን ትውልድ በምናሳድግበት ወቅት የምትረዳን የአዳኙ ቤተክርስቲያን አለችን።

በጆሴፍ ስሚዝ በኩል የተመለሰችው፣ አሁን ደግሞ በፕሬዚዳንት ረስል ኤም. ኔልሰን የምትመራው የክርስቶስ ቤተክርስቲያን ወጣቶች በነዚዚህ የኋለኞቹ ቀናት ታላቅ የሆነውን ዓላማቸውን እንዲያሳኩ ለመርዳት የተመሰረተች እንደሆነ ምስክርነቴን አካፍላለሁ። በኢየሱስ ክርስቶስ ስም፣ አሜን።

ማስታወሻዎች

  1. አልማ 53፥19

  2. “ምርጫችሁ ከሆነ፣ የምትፈልጉ ከሆነ፣ … ትልቅ፣ አዲስ እና ግርማዊ ከሆነ አንድ ነገር፣ ትልቅ አካል መሆን ትችላላችሁ! … ጌታ ወደዚህች አለም ከላካቸው ከሚያውቀው ምርጦች መካከል አንዱ ናችሁ። ይበልጥ አስተዋይ እና ብልህ የመሆን ችሎታ አላችሁ እንዲሁም ቀደም ካሉት ከየትኛውም ትውልዶች ይበልጥ በአለም ላይ ተጽእኖ አላችሁ። ረስል ኤም ኔልሰን፣ “Hope of Israel [የእስራኤል ተስፋ]” [worldwide youth devotional [አለም አቀፍ የወጣቶች መንፈሳዊ ትምህርት]፣ ሰኔ 3፣ 2018 (እ.አ.አ)]፣ የወንጌል ቤተመጻህፍት።

  3. ዴል ጄ ረንለንድ፣ ”በእግዚአብሔር አይኖች በኩል፣” ሊያሆና፣ ጥቅምት 2015 (እ.አ.አ)።

  4. አልማ 56፥55

  5. አልማ 56፥43-44

  6. አልማ 56፥46

  7. “የሰማዩ አባታችን የወላጅነት አላማው ልጆቹ ትክክለኛውን ነገር እንዲያደርጉ ማድረግ አይደለም፤ ይልቁንስ የእርሱ ልጆች ትክክለኛውን ነገሮች እንዲመርጡ ማድረግ ነው” (ዴል ጄ. ረንለንድ “Choose You This Day [ይህንን ቀን ምረጡ]፣” ሊያሆና፣ ህዳር 2018፣ (እ.አ.አ) 104)።

  8. “እንዲተገብሩ በመጋበዝ እና በመፍቀድ፣ ቤተክርስቲያኗ ተአምራዊ በሆነ መንገድ ወደፊት ትጓዛለች” [ዴቭድ ኤ. ቤድናር፣ 2020 (እ.አ.አ) የቤተመቅደስ እና የቤተሰብ አመራር መመሪያ፣ የካቲት 27፣ 2020 (እ.አ.አ)]።

  9. አልማ 53፥22

  10. አልማ 56፥17

  11. ረስል ኤም. ኔልሰን፣ “የእስራኤል ተስፋ፣” የወንጌል ቤተመጻህፍት።

  12. አልማ 53፥20

  13. አልማ 58፥12

  14. አልማ 56፥30

  15. አጠቃላይ መመሪያ መጽሃፍ፤ በኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን ውስጥ ማገልገል7.1.2፣ የወንጌል ቤተመጻህፍት።

  16. አጠቃላይ መመሪያ መጽሃፍ6.7.2 ይመልከቱ።

  17. አልማ 23፥7

  18. አልማ 58፥37

  19. አልማ 58፥10-11

  20. አልማ 57፥26

  21. አልማ 53፥21

  22. አልማ 56፥47

  23. አልማ 23፥724፥17–19ን ይመልከቱ።

  24. አልማ 56፥27

  25. አጠቃላይ መመሪያ መጽሃፍ7.1.1 ይመልከቱ።

  26. “ዘላለማዊ እውነትን በምንፈልግበት ጊዜ፣ የሚከተሉት ሁለት ጥያቄዎች ሃሳቡ ከእግዚአብሔር ወይም ከሌላ ምንጭ የመጣ እንደሆነ ለማወቅ ይረዱናል። ሃሳቡ በቅዱሳን መጻሕፍቶች ውስጥ እና በህያው ነቢያት ትምህርት ይሰጥባቸዋልን? ሃሳቡ በመንፈስ ቅዱስ ምስክርነት የተረጋገጠ ነውን? እግዚአብሔር እውነትን በነቢያት በኩል ይገልጣል፣ እናም መንፈስ ቅዱስ እነዛን እውነቶች ለእኛ ያረጋግጣል እናም እንድንጠቀምባቸው ይረዳናል” [ጆን ሲ. ፒንግሪ ቀዳማይ “ዘለአለማዊ እውነታ፣” ሊያሆና፣ ህዳር 2023 (እ.አ.አ)]።

  27. ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 4፥2-4ን ይመልከቱ።

  28. “[የእኛ] ወጣቶቻችን በጌታ ስራ በጣም የተጨናነቁ ካልሆኑ፣ ከሞላ ጎደል በአለምም የተጨናነቁ ይሆናሉ። … አንድን ሰው ጸሎት እንዲያቀርብ ወይም ቅዱስ ቁርባንን እንዲያሳልፍ በመጥራት ብቻ ስንትን የዲያቆናት እና የአስተማሪዎች የምልአተ ጉባኤ አባላትን ያካትታል? ወንድሞች፣ እነዚህ በእውነትም ልዩ መንፈሶች ናቸው እና እድሉ ከተሰጣቸው አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን መስራት ይችላሉ!” (ኒልኤ. ማክስዌል፣ “እያደገ ላለው ትውልድ፣” ኢንሳይን፣ ግንቦት 1985 (እ.አ.አ)።

  29. ሔንሪይቢ አይሪንግ፣ “Teaching is a moral act [ማስተማር የእሴት ተግባር ነው]” [የብሪገም ያንግ ዩኒቨርሲቲይ መንፈሳዊ ትምህርት፣ ነሐሴ 27, 3, 1991 (እ.አ.አ)]፣ speeches.byu.edu

  30. የአሮናዊ ክህነት ቡድን ጭብ፣” የወንጌል ቤተመጻህፍትን ይመልከቱ።

  31. ቤተሰብ፦ ለአለም የተላለፈ አዋጅ፣” የወንጌል ቤተመጻህፍትን ይመልከቱ።

  32. “ኤጲስ ቆፖጶች ወጣት ወንዶች ባላቸው የክህነት ሃላፊነቶች በተመለከተ ታላቅ ማብራሪያዎችን እና አትኩሮቶችን እንዲያደርጉ እንዲሁም በምልአተ ጉባኤ ሃላፊነታቸው እንደሚረዳቸው ተስፋ እናደርጋለን። አቅሙ ያላቸው የወጣት ወንዶች አማካሪዎች የአሮናዊ ክህነት ስልጣን ምልአተ ጉባኤ አመራርን እና የኤጲስ ቆጵስን አመራር ለመርዳት ይጠራሉ። ወጣቶቻችን ላይ ባለው ቆራጥ ትኩረት ምክንያት ብዙ ወጣት ወንዶች እና ወጣት ሴቶች ለፈተናው ብቁ እንደሚሆኑ እና በቃል ኪዳኑ መንገድ ላይ እንደሚቆዩ እናምናለን፣” (Quentin L. Cook, “Adjustments to Strengthen Youth,” ሊያሆና፣ ሕዳር 2019 (እ.አ.አ)፣ 41።)

  33. “የሰማይ አባታችን ብዙዎቹን ክቡር መንፈሶች፣ ምናልባትም እጅግ በጣም ምርጦቹን ቡድን፣ ለዚህ መጨረሻ ደረጃ በማዘጋጀት አስቀምጣል። እነዛ ክቡራን መንፈሶች—እነዛ ምርጦቹ ተጨዋቾች፣ እነዛ ጀግኖች— እናንተ፣ ናችሁ!” (ረስልኤም. ኔልሰን፣ “Hope of Israel [የእስራኤል ተስፋ]፣” የወንጌል ቤተመጻህፍት)።

  34. “የምትወዱት/ዷት ወጣት በነጻ ምርጫ እና በእምነት በኩል ደፋር ከሆኑት ተዋጊዎች መካከል አንዱ/ዷ ሆኖ/ና ይሆናል። … ለራሳቸው በመምረጥ ባላቸው ቁርጠኝነት በኩል በምናሳያቸው ባህሪይ ልንረዳ እንችላለን። በቅድመ ህይወት ውስጥ ለግል ነጻ ምርጫ እና ሊያመጣላቸው የሚችለውን ታላቅ የደስታ በረከት የሚያውቁ ታማኝ ተዋጊዎች መካከል አንዱ እንደሆኑ እንደምናያቸው ወይም እንደማናያቸው ይታወቃቸዋል። በቅድመ ህይወት ውስጥ እንደ ታማኝ ተዋጊዎች ልናያቸው ከቻልን፣ በተጨማሪም የእነሱን የነጻነት ይገባኛል ጥያቄ የእነሱን አቅም እንደማሳያ፣ ለእነሱ ደስታን የሚያመጣውን የነጻ ምርጫ ሃይልን እየፈተኑ መሆኑን የሚያመላክት አድርገን ልንመለከተው እንችላለን፣ (ሔንሪይ ቢ. አይሪንግ፣ “A Life Founded in Light and Truth [በብርሃን እና በእውነት ውስጥ የተገኘ ህይወት]” [የብሪይገም ያንግ ዩኒቨርሲትይ መንፈሳዊ ትምህርት፣ነሐሴ፣፣ 15 2000 (እ.አ.አ)]፣ speeches.byu.edu)።