አጠቃላይ ጉባኤ
ቃል ኪዳኖች እና ኃላፊነቶች
የሚያዝያ 2024 (እ.አ.አ) አጠቃላይ ጉባኤ


ቃል ኪዳኖች እና ኃላፊነቶች

የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን ከእግዚአብሔር ጋር ቃል ኪዳን በመግባት ላይ አትኩሮት እንደምትሰጥ ቤተክርስቲያን ትታወቃለች።

“ቤተክርስቲያናችሁ ከሌሎች በምን ትለያለች?” ለዚህ አስፈላጊ ጥያቄ የምሰጠው ምላሽ እኔ እየበሰልኩ ቤተክርስትያኗ ደግሞ እያደገች ስትሄድ የተለያየ እየሆነ ሄዷል። በ1932 (እ.አ.አ) በዩታ ስወለድ፣ በአብዛኛው በዩታ እና በአቅራቢያው ባሉ ግዛቶች ውስጥ የነበሩት የቤተክርስቲያናችን አባላት ቁጥር ወደ 700 ሺህ አካባቢ ነበር። በዚያን ጊዜ፣ 7 ቤተመቅደሶች ብቻ ነበሩን። ዛሬ፣ የኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን አባላት ከ17 ሚሊዮን የሚበልጡ ሲሆን፣ የሚገኙትም ወደ 170 በሚሆኑ ሃገሮች ውስጥ ነው። በዚህኛው ሚያዝያ 1፣ በብዙ ሀገራት 189 የተቀደሱ እና በእቅድ እና በግንባታ ደረጃዎች ላይ ያሉ ሌሎች 146 ቤተመቅደሶች ይገኛሉ። ስለእነዚህ ቤተመቅደሶች በአምልኳችን ውስጥ ስላላቸው አላማ እና ታሪክ እና የቃል ኪዳኖች ሚና ለመናገር ስሜት አግኝቻለሁ። ይህም ቀደምት ተናጋሪዎች በመንፈስ አነሳሽነት ያስተምሩትን ትምህርት ይጨምራል።

1.

ቃል ኪዳን የተወሰኑ ኃላፊነቶችን ለመወጣት ያለ ቁርጠኝነት ነው። የግል ቁርጠኝነት ህይወታችንን ለመቆጣጠር እና ለህብረተሰቡ መደበኛ አሠራር አስፈላጊ ነው። ይህ ሃሳብበዚህ ወቅት ተቀባይነት እያጣ ነው። አናሳ ድምጽ ያለው ቡድን ተቋማዊ ስልጣንን ይቃወማል እንዲሁም ሰዎች የግል ነፃነታቸውን ከሚወስኑ ከማንኛውም ገደቦች ነፃ እንዲሆኑ አጥብቆ ይጠይቃል። ሆኖም በተደራጁ ማህበረሰቦች ውስጥ የመኖር ጥቅሞችን ለማግኘት አንዳንድ የግል ነፃነቶችን እንደምንተው ከሺህ ዓመታት ልምድ እናውቃለን። የግለሰብ ነፃነትን መልቀቅ፣ በዋናነት በቀጥታ በሚገለጹ ወይም በተዘዋዋሪ በሚታዩ ቁርጠኝነቶች ወይም ቃል ኪዳኖች ላይ የተመሰረቱ ናቸው።

ምስል
ወታደር።
ምስል
የጤና ባለሙያ።
ምስል
የእሳት አደጋ ሰራተኞች።
ምስል
የሙሉ ጊዜ ሚስዮናውያን።

በማህበረሰባችን ውስጥ ያሉ የቃል ኪዳን ሀላፊነቶች አንዳንድ ምሳሌዎች እነዚህ ናቸው፦ (1) ዳኞች፣ (2) ወታደር (3) የጤና ባለሙያዎች እና (4) የእሳት አደጋ ተከላካዮች። በእነዚህ የተለመዱ ሥራዎች ውስጥ የሚሳተፉት ሁሉ የተመደቡበትን ስራ ለመወጣት—ብዙውን ጊዜ በህጋዊ መሐላ ወይም ቃል ኪዳን—ቁርጠኝነታቸውን ያሳያሉ። የሙሉ ጊዜ ሚስዮናውያኖቻችን ሁኔታም ተመሳሳይ ነው። የእነሱ ልዩ ልብስ ወይም የስም መለያ፣ ለባሹ በቃል ኪዳን ሥር መሆኑን፣ ስለሆነም የማስተማር እና የማገልገል ሀላፊነት እንዳለበት ለማመልከት የታሰበ ነው እናም በአገልግሎታቸው መደገፍ ያስፈልጋቸዋል። ከዚህ ጋር ተዛማጅ የሆነው ዓላማም፣ ለባሾቹ የቃል ኪዳን ኃላፊነታቸውን እንዲያስታውሱ ማድረግ ነው። ለባሾቹ ያሉባቸውን ልዩ ኃላፊነቶች ለማስታወስ የሚያስፈልግ አስታዋሽ ብቻ ነው እንጂ በልዩ ልብሶቻቸው ወይም ምልክቶቻቸው ላይ ምንም “አስማት” የለም። ይህ፣ የቃል ኪዳን እና የሠርግ ቀለበት ምልክቶች ለተመልካቾች ማስታወቂያ ለመስጠት ወይም የቃል ኪዳናቸውን ሀላፊነቶች ለማስታወስ ላላቸው ሚናም ይሠራል።

ምስል
የጋብቻ ቀለበቶች።

2.

ቃል ኪዳኖች የግለሰብን ሕይወት ለመቆጣጠር መሠረት ስለመሆናቸው የተናገርኩት በተለይ በሃይማኖታዊ ቃል ኪዳኖች ላይ የሚሰራ ነው። የበርካታ ሃይማኖታዊ ትስስሮች እና መስፈርቶች መሠረት እና ታሪክ በቃል ኪዳኖች ላይ የተመሰረቱ ናቸው። ለምሳሌ፣ የአብርሃማዊ ቃል ኪዳን ለብዙ ታላላቅ ሃይማኖታዊ ባህሎች መሠረታዊ ነው። ይህም እግዚአብሔርን ከልጆቹ ጋር የገባውን ቃል ኪዳን ቅዱስ ሀሳብ ያስተዋውቃል። ብሉይ ኪዳን በአብዛኛው እግዚአብሔር ከአብርሐም እና ከዘሮቹ ጋር የገባውን ቃል ጊዝዳን በብዛት ይጠቁማል።1

በብሉይ ኪዳን ዘመን የተጻፈው የመፅሐፈ ሞርሞን የመጀመሪያ ክፍል በእስራኤላውያን ታሪክ እና አምልኮ ውስጥ የቃል ኪዳኖችን ሚና በግልፅ ያሳያል። የዚያ ዘመን የእስራኤላውያን ጽሑፎች “የአይሁዶች መዝገብ [እንደሆነ] ይህም እርሱ ከእስራኤል ቤት ጋር ያደረገው የጌታን ቃል ኪዳኖች የያዘ” እንደሆነ ለኔፊ ተነግሮታል።2 የኔፊ መጽሐፍ ስለ አብርሐማዊ ቃል ኪዳን3 እና “የጌታ የቃል ኪዳን ሕዝብ”4ስለሆነው ስለ እስራኤል በተደጋጋሚ ይጠቅሣል። ከእግዚአብሔር ወይም ከሀይማኖት መሪዎች ጋር ቃል ኪዳን የመግባት ልምድ፣ በመፅሐፈ ሞርሞን ውስጥ ስለ ኔፊ፣ በግብፅ ውስጥ ስለነበረው ስለዮሴፍ ፣ ስለ ንጉሥ ቢንያም፣ ስለ አልማ እና ስለ ሻምበል ሞሮኒ በተፃፉ ጽሑፎች ውስጥ ተመዝግበዋል።5

3.

የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ሙላት ዳግም የሚመለስበት ጊዜ ሲደርስ፣ እግዚአብሔር ነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝን ጠራው። መልአኩ ሞሮኒ ለዚህ እየበሠለ በመሄድ ላይ ለነበረው ወጣት ነቢይ የሰጠውን የመጀመሪዎቹን መመሪያዎች ሙሉ ይዘት አናውቅም። “እግዚአብሔር የሚሠራው ሥራ [እንደነበረው]” እና “ለአባቶች የተገባውን የተስፋ ቃል” ጨምሮ “የዘላለማዊው ወንጌል ሙሉነት” መምጣት እንዳለበት ለጆሴፍ እንደነገረው እናውቃለን።6 ወጣቱ ጆሴፍ—ቤተክርስቲያኗን እንዲያደራጅ ከመታዘዙ በፊት እንኳን— በጥልቀት ሲያነባቸው የነበሩት ቅዱሳት መጻህፍት በመፅሐፈ ሞርሞን ውስጥ እየተረጎማቸው ስለነበሩት ቃል ኪዳኖች ብዙ ትምህርቶች እንደነበሩ እናውቃለን። ያ መጽሐፍ ለወንጌል ሙላት የዳግም መመለስ ዋና ምንጭ ነው፣ የእግዚአብሔርን የልጆቹን እቅድ ጨምሮ፣ እና መፅሐፈ ሞርሞን በቃል ኪዳኖች ማጣቀሻዎች የተሞላ ነው።

ጆሴፍ መጽሐፍ ቅዱስን በደንብ ከማወቁ የተነሳ፣ አዳኙ “ከእስራኤል ቤትና ከይሁዳ ቤት ጋር አዲስ ኪዳን [ለመግባት]”7 ስላለው ሐሳብ የሚናገረውን የዕብራውያን መጽሐፍ ጥቅስ ሳያውቅ አይቀርም። ዕብራውያንም ይህን በተጨማሪም ኢየሱስን “የአዲስ ኪዳን መካከለኛ”8 በማለት ይጠራዋል። ግልጽ በሆነ መልኩ፣ የአዳኙ ምድራዊ አገልግሎት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ዘገባ “አዲስ ኪዳን” በመባል ለ“አዲስ ቃል ኪዳን” ተመሳሳይ ቃል ስያሜ ተሰጥቶታል።

በወንጌል ዳግም መመለስ ውስጥ ቃል ኪዳኖች መሠረታዊ ነበሩ። ይህ፣ ጌታ፣ ነቢዩ ቤተክርስቲያንን ሲያደራጅ እንዲወስዳቸው ባደረገው የመጀመሪያ እርምጃዎች ላይ በግልጽ ይታይ ነበር። መፅሐፈ ሞርሞን እንደታተመ፣ ጌታ በቅርቡ የኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን በመባል የምትሠየመው ዳግም የተመለሰችው ቤተክርስቲያን እንድትደራጅ አዘዘ።9 በሚያዝያ 1830 (እ.አ.አ) የተሰጠው ራዕይ፣ ሰዎች “ለኃጢአታቸው ሁሉ ንስሐ እንደገቡ ምስክር ካደረጉ” (ይህም በክብር መመስከር ማለት ነው)፣ “እናም እርሱን እስከመጨረሻው ድረስ ለማገልገል ፈቃድ ኖሯቸው የኢየሱስ ክርስቶስን ስም በራሳቸው ለመውሰድ ፈቃደኛ ከሆኑ፣” እነርሱ “ወደ እርሱ ቤተክርስቲያን በጥምቀት ይወሰዳሉ”10 በማለት መመሪያ ይሠጣል።

ይኼው ራዕይ፣ ቤተክርስቲያኗ “ዘወትር በአንድነት በመገናኘት ጌታ ኢየሱስን ማስታወስ ዳቦና ወይንን [ውሃ]” መካፈል አስፈላጊ እንደሆነ መመሪያ ይሠጣል። የዚህ ሥርዓት አስፈላጊነት የሚታየው የሚባርከው ሽማግሌ ወይም ካህን እንዲጠቀማቸው በተሰጡት ልዩ ቃላት ላይ ነው። እርሱም የዳቦ ምልክቶችን፣ “ይህንን ዳቦ ለሚቋደሱት ነፍሳት … እነርሱ የልጅህን ስም በላያቸው ላይ ለመውሰድ ፈቃደኞች መሆናቸውን፣ እና ሁልጊዜ እርሱን እንደሚያስታውሱና እርሱ የሰጣቸውን ትእዛዛት እንደሚጠብቁ ለአንተም ይመሰክሩ ዘንድ”11 በማለት ይባርካል።

አዲስ በተመለሰችው ቤተክርስቲያን የቃል ኪዳኖች ዋና ሚና፣ ጌታ ለራዕዩ የመጀመሪያ ህትመት በሰጠው መቅድም ውስጥ በድጋሚ ተረጋግጧል። በዚያ ላይ፣ ጌታ የምድር ነዋሪዎች “ከሥርዓ[ቱ] [ስለራቁ] እናም ዘላለማዊ ቃል ኪዳ[ኑን] [በማፍረሣቸው]”12ምክንያት ጆሴፍ ስሚዝን እንደጠራው አውጇል። ራዕዩም የእርሱ ትእዛዛት የተሰጡት “ዘላለማዊ ቃል ኪዳ[ኑ] ይመሰረት ዘንድ” እንደሆነ በተጨማሪ ያስረዳል።13

ዛሬ፣ ዳግም በተመለሰችው ቤተክርስቲያን የቃል ኪዳኖችን ሚና እና የአባላቶቿን አምልኮ በተመለከተ የተሻለ እንገነዘባለን። ፕሬዚዳንት ጎርደን ቢ. ሂንክሊ የእኛን ጥምቀት እና ሳምንታዊ የቅዱስ ቁርባን መካፈላችንን ውጤት ማጠቃለያ ሰጥተዋል፦ “እያንዳንዱ የተጠመቀ የዚህች ቤተክርስቲያን አባል የቅዱስ ቃል ኪዳን አካል ሆኗል። የጌታን እራት ቅዱስ ቁርባን በተቀበልን ቁጥር፣ ያንን ቃል ኪዳን እናድሳለን።”14

በዚህ ጉባኤ በብዙ ተናጋሪዎች ነቢያችን፣ ፕሬዚዳንት ራስል ኤም. ኔልሰን “ወደ [እግዚአብሔር] የሚመልሰን የቃል ኪዳኑ መንገድ15 … ከእግዚአብሔር ጋር [ያለን] ግንኙነት”15 እንደሆነ የተናገሩትን አሳስበውናል። በቤተመቅደስ ስርዐአቶቻችን ውስጥ ስለ ቃልኪዳን አስፈላጊነት አስተምረዋል እንዲሁም መጨረሻውን ከመጀመሪያው እንድንመለከት እና “ስለ ሰለስቲያል [እንድናስብ]” አሳስበውናል።16

4.

አሁን ይበልጥ ስለ ቤተመቅደስ ቃል ኪዳኖች እናገራለሁ። የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል ሙላት ዳግም ለመመለስ ያለበትን ሀላፊነት ለመወጣት፣ ነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ የነበሩትን አብዛኞቹን የመጨረሻ ዓመታት በናቩ፣ ኢሊኖይ ውስጥ ያለውን የቤተመቅደስ ግንባታ በመምራት አሳልፏል። የእርሱ ተተኪዎች በቤተመቅደሥ ውስጥ እንዲያከናውኗቸው፣ የተቀደሱ አስተምሮቶችን፣ ትምህርቶችን እና ቃል ኪዳኖችን ጌታ በእርሱ በኩል ገልጧል። የቤተመቅደሥ ቡራኬ የተቀበሉ፣ የእግዚአብሔርን የደህንነት እቅድ እንዲማሩ እና የተቀደሱ ቃል ኪዳኖችን እንዲገቡ የተጋበዙ ሠዎች ነበሩ። እነዚያን ቃል ኪዳኖች በታማኝነት የኖሩ የዘላለም ሕይወት ቃል ተገብቶላቸዋል፣ በዚያም “ሁሉም ነገሮች የእነርሱ ናቸው” እንዲሁም “በእግዚአብሔር እና በእርሱ ክርስቶስ ፊት ለዘላለም ይኖራሉ።”17

በናቩ ቤተመቅደስ ውስጥ ያነበሩት የቡራኬ ሥርዓቶች የተከናወኑት፣ ቀደምት ሰፋሪዎች ተባረው በስተ ምዕራብ ራቅ ወዳሉ ተራሮች ታሪካዊ ጉዟቸውን ከመጀመራቸው አስቀድሞ ነበር። በናቩ ቤተመቅደስ ውስጥ በቤተመቅደሥ ቡራኬያቸው ከክርስቶስ ጋር በመታሰራቸው የተቀበሉት ሃይል አስደናቂ ጉዟቸውን ለማድረግ እና በምዕራብ ለመቋቋም ጥንካሬ እንደሰጣቸው ከእነዚያ ሰፋሪዎች ብዙ ምስክርነቶች አሉን።18

በቅዱስ ቤተመቅደሥ ውስጥ የቤተመቅደሥ ቡራኬ የተቀበሉ ሰዎች ከልብስ ስር በመለበሱ ምክንያት ከውጪ የማይታይ የቤተመቅደስ ልብስ መልበስ አለባቸው። የቤተመቅደስ ቡራኬ የተቀበሉ አባላትን፣ ስለገቧቸው ቅዱስ ቃል ኪዳኖች እና በቅዱሱ ቤተመቅደሥ ውስጥ ቃል ስለተገቡላቸው በረከቶች ያስታውሷቸዋል። እነዚያን ቅዱስ ዓላማዎች ለማሳካት ሲባል፣ የግድ አስፈላጊ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ በስተቀር የቤተመቅደስ ልብሶችን ያለማቋረጥ እንድንለብስ ታዝዘናል። ቃል ኪዳኖች “የዕረፍት ቀን” ስለሌላቸው፣ የአንድ ሰው የቤተመቅደስን ልብስ አለመልበስ የሚዛመዱትን ሀላፊነቶች እና በረከቶች እንዳለመቀበል ሊታይ ይችላል። በአንጻሩ፣ የቤተመቅደስ ልብሳቸውን በታማኝነት የሚለብሱ እና የቤተመቅደስ ቃል ኪዳናቸውን የሚጠብቁ ሰዎች የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዝሙርነታቸውን በዘላቂነት ያረጋግጣሉ።

ምስል
የቤተመቅደሶች ካርታ

የኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን በአለም ዙሪያ ቤተመቅደሶችን እየገነባች ነው። አላማቸውም የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳን ልጆች በቤተመቅደስ አምልኮ እና በቃል ኪዳን በሚቀበሏቸው ቅዱስ ሀላፊነቶች እና ሀይሎች እንዲሁም በልዩ በረከቶች ከክርስቶስ ጋር የመገናኘትን በረከቶች ለመባረክ ነው።

ምስል
የሳዎ ፖሎ ብራዚል ቤተመቅደስ

የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን ከእግዚአብሔር ጋር ቃል ኪዳን በመግባት ላይ አትኩሮት እንደምትሰጥ ቤተክርስቲያን ትታወቃለች። ቃል ኪዳኖች በደህንነት እና በዘለዓለማዊ ህይወት ከፍ ከፍ በመደረግ ሥርዓቶች የሚገኙ ናቸዋ። የጥምቀት ሥርዓት እና ተያይዞ ያለው ቃል ኪዳን ወደ ሰለስቲያል መንግሥት ለመግባት አስፈላጊ መስፈርቶች ናቸው። የቤተመቅደስ ሥርዓቶች እና ተዛማጅ ቃል ኪዳኖች ከሁሉም “የእግዚአብሔር ስጦታዎች” የላቀውን የዘላለም ህይወት ለማግኘት በሰለስቲያል መንግስት ውስጥ ከፍ ከፍ ለመደረግ አስፈላጊ መስፈርቶች ናቸው።19 ያ የኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን ትኩረት ነው።

የዚህች ቤተክርስትያን ራስ ስለሆነው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እመሰክራለው፣ እንዲሁም ቅዱስ ቃል ኪዳኖቻቸውን ለመጠበቅ ለሚፈልጉ ሁሉ በረከቶቹን እጥራለሁ። በኢየሱስ ክርስቶስ ስም፣ አሜን።