ምዕራፍ ፫
ንጉስ ቢንያም ንግግሩን ቀጠለ—ሁሉን የሚገዛው ጌታ በጭቃ ሰውነቱ በሰዎች መካከል ያገለግላል—ለዓለም ኃጢአቶች ዋጋን ሲከፍል ደም ከሰውነቱ ቀዳዳ ሁሉ ይፈሳል—ደህንነት የሚመጣበት ብቸኛው ስም የእርሱ ነው—ሰዎች በኃጢያት ክፍያ አማካኝነት ፍጥረታዊ ሰውነታቸውን መለወጥ እናም ቅዱሳን ለመሆን ይችላሉ—የኃጢአተኞች ስቃይ እንደባህር እሳትና ዲን ይሆናል። ፻፳፬ ም.ዓ. ገደማ።
፩ እናም እንደገና ወንድሞቼ፤ ለእናንተ የምናገረው ከዚህ በላይ በመጠኑ ስላለኝ ትኩረታችሁንም እፈልጋለሁ፤ እነሆ የሚመጣውን በተመለከተ የምነግራችሁ ነገሮች አሉኝና።
፪ እናም የምናገራችሁ ነገሮች በእግዚአብሔር መልአክ ተገልፀውልኛል። እርሱም እንዲህ አለኝ፥ ንቃ፤ እናም ነቃሁ፤ እነሆ እርሱም ከፊቴ ቆመ።
፫ እናም እርሱ እንዲህ አለኝ፥ ንቃ፣ የምነግርህን ቃላት ስማ፤ እነሆም የታላቁን ደስታ የምስራች ላበስርልህ መጥቻለሁና።
፬ ጌታ ፀሎትህን ሰምቷልና፣ እናም ፅድቅህንም በሚመለከት ፈርዷልና፤ እናም አንተ ትደሰት ዘንድና፤ ለህዝብህ ትናገር ዘንድ፤ እነርሱም ደግሞ በደስታ ይሞሉ ዘንድ ልኮኛል።
፭ እነሆም፣ በኃይል ሁሉንም የሚገዛው ጌታ የነገሰው፣ የነበረው፣ እናም ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ሁሉ የሚኖረው፣ ከሰማይ በሰው ልጆች መካከል የሚመጣበት ጊዜ ይመጣል፣ ሩቅም አይደለም፣ በጭቃ ሰውነቱ ይኖራልም፤ እናም በሰዎች መካከል፣ በሽተኞችን የመፈወስ፣ ሙታንን የማስነሳት፣ ሽባዎችን እንዲራመዱ የማድረግ፣ እውሮች ማየት እንዲችሉ፣ ደንቆሮዎችም እንዲሰሙ፣ እናም ሁሉንም የበሽታ ዓይነቶችን ለማዳን አስደናቂ ስራዎችን እየሰራ ይሄዳል።
፮ እናም እርሱ ዲያብሎስን፣ ወይንም በሰው ልጆች ልብ ውስጥ የሚኖረውን እርኩስ መንፈስ ያስወጣል።
፯ እናም እነሆ፣ በፈተናና በስጋዊ ህመም፣ በርሃብ፣ በጥማትና፣ በድካም፤ ከሞት በስተቀር ሰው ሊሰቃይበት ከሚችለው የበለጠም ይሰቃያል፤ እነሆም ለህዝቡ ክፋትና እርኩሰት ጭንቀቱ እጅግ ታላቅ ሆኖ፣ ደሙም ከእያንዳንዱ የሰውነቱ ቀዳዳ ይፈሳል።
፰ እናም እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ፣ የእግዚአብሔር ልጅ፣ የሰማይና የምድር አባት፣ ከመጀመሪያው ጀምሮ የሁሉም ነገር ፈጣሪ የነበረ ተብሎ ይጠራል፤ እናም እናቱ ማርያም ተብላ ትጠራለች።
፱ እናም እነሆ፣ በስሙ በማመን ደህንነት ለሰው ልጆች ይመጣ ዘንድ የእርሱ ወደ ሆኑት መጣ፤ እናም ከዚህ ሁሉ በኋላ እንኳን እንደ ሰው ይቆጥሩታል፣ ዲያብሎስ አለው ብለው ይናገራሉም፤ ይገርፉታልም፣ እንዲሁም ይሰቅሉታል።
፲ እርሱም በሶስተኛው ቀን ከሞት ይነሳል፤ እናም እነሆ ዓለምን ሊፈርድ ይቆማል፤ እናም እነሆ በሰው ልጆች ላይ ጻድቃዊው ፍርድ ይመጣ ዘንድ እነዚህ ሁሉ ይሆናሉ።
፲፩ እነሆም፣ እናም ደግሞ በአዳም መተላለፍ ለወደቁት ኃጢአተኞች፣ እነርሱን በተመለከተ ያለውን የእግዚአብሔር ፈቃድ ሳያውቁ ለሞቱት፣ ወይም ባለማወቅ ኃጢያትን ለፈፀሙት የእርሱ ደም የኃጥያቶች ክፍያ ይሆናል።
፲፪ ነገር ግን በእግዚአብሔር ላይ ማመፁን ለሚያውቅ ወዮ ወዮለት! እንደነዚያ ላሉት ደህንነት በንስሃ እና በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እምነት ካልሆነ በቀር አይመጣምና።
፲፫ እናም ጌታ እግዚአብሔር ለሁሉም ወገን፣ ሀገርና፣ ቋንቋ፣ እነዚህን ነገሮች እንዲናገሩ ቅዱሳን ነቢያቱን በሰው ልጆች ሁሉ መካከል ልኳል፤ በዚህም ማንኛውም ክርስቶስ ይመጣል በማለት የሚያምን ለኃጢአቱ ስርየትን ያገኛል፣ እርሱም በመካከላቸውም እንደመጣም ዓይነት በታላቅ ደስታ ሃሴት ይሆናሉ።
፲፬ ይሁን እንጂ ጌታ እግዚአብሔር ሕዝቡ አንገተ ደንዳና እንደሆኑ ተመልክቷል፣ እናም ህግን፣ እንዲሁም የሙሴንም ሕግ መስርቶላቸዋል።
፲፭ እናም የእርሱን መምጣት በተመለከተ ብዙ ምልክቶችንና፣ ተዓምራትንና፣ ምሳሌዎችንና ጥላውን አሳይቷቸዋል፤ እናም ደግሞ መምጣቱን በተመለከተ ቅዱሳን ነቢያትም ነግረዋቸዋል፤ ይሁን እንጂ እነርሱ ልባቸውን አጠጥረዋል፣ በደሙ ክፍያም ካልሆነ በቀር የሙሴ ሕግ ምንም የማይጠቅም መሆኑን አልተገነዘቡትም።
፲፮ እናም ምንም እንኳን ህጻናት ኃጢያትን መስራት የሚችሉ ቢሆኑም ሊድኑ አይችሉም ነበር፤ ነገር ግን እነርሱ የተባረኩ ናቸው እላችኋለሁ፤ እነሆም፣ በአዳም፣ ወይም በፍጥረት እንደወደቁም፣ የክርስቶስ ደም ለኃጢአታቸው ክፍያ እንዲሁም ያደርጋል።
፲፯ እናም ከዚህ በተጨማሪ፣ እንዲህ እላችኋለሁ፣ ሁሉን በሚችለው ጌታ በክርስቶስ ስም ካልሆነ በስተቀር ለሰው ልጆች ደህንነት እንዲመጣ የሚሰጥ ምንም ስም ወይም መንገድ፣ ወይም ዘዴ የለም።
፲፰ እነሆም እርሱ ይፈርዳል፣ ፍርዱም ፍፁም ነው፤ እናም በህፃንነቱ የሞተ ህፃን አይጠፋም፤ ነገር ግን ሰዎች እራሳቸውን ትሁትና፣ እንደ ህፃናት ካላደረጉ፣ እናም ሁሉን በሚችለው ጌታ በክርስቶስ የደም ካሣ ውስጥና በኩል ደህንነት እንደነበረ፣ እንደሚሆንና፣ እንደሚመጣ ካላመኑ በቀር ኩነኔን ይጎነጫሉ።
፲፱ ተፈጥሮአዊው ሰው ከአዳም ውድቀት ጀምሮ ለእግዚአብሔር ጠላት ነው፣ እናም እርሱም ለመንፈስ ቅዱስ ግብዣ ፈቃደኛ ካልሆነና፣ ተፈጥሮአዊው ሰውነቱን ካልቀየረ እናም በጌታ በክርስቶስ የኃጢያት ክፍያ አማካኝነት ቅዱስ ካልሆነና፣ እንደልጅ ሁሉን የሚቀበል፣ የዋህ፣ ትሁት፣ ትዕግስተኛ፣ በፍቅር የተሞላ፣ ልጅ ከአባቱ ተቀባይ እንደሚሆን፣ ጌታ ብቁ ነው ብሎ የሚያደርስበትን ሁሉንም ነገሮች ለመቀበል ፈቃደኛ ካልሆነ እስከመጨረሻው ለዘለዓለም የእግዚአብሔር ጠላት ይሆናል።
፳ እናም ከዚህ በተጨማሪ፣ እላችኋለሁ፣ የአዳኛችን እውቀት በሁሉም ሀገር፣ ነገድ፣ ቋንቋ እና ህዝብ መካከል የሚሰራጭበት ጊዜ ይመጣል።
፳፩ እናም እነሆ፣ ያ ጊዜ ሲመጣ፣ ሁሉን በሚችለው በጌታ እግዚአብሔር ስም ንስሃ እና እምነት በኩል፣ ትናንሽ ልጆች ካልሆኑ በቀር፣ በእግዚአብሔር ፊት እንከን የሌለበት አይገኝም።
፳፪ እናም በዚህ ጊዜም እንኳን ቢሆን፣ ጌታ አምላክህ ያዘዘህን ነገሮች ለሕዝባችሁ ስታስተምር፣ እኔ በነገርኩህ ቃላት መሰረት ካልሆነ በስተቀር ከእንግዲህ በእግዚአብሔር ፊት ያለ እንከን አይሆኑም።
፳፫ እናም አሁን ጌታ እግዚአብሔር ያዘዘኝን ቃላት ተናግሬአለሁ።
፳፬ እናም ጌታ እንዲህ ይላል፥ እነዚህ በፍርድ ቀን ለዚህ ሕዝብ እንደ ብሩህ ምስክር ሆነው ይቆማሉ፤ ስለዚህ ማንኛውም ሰው በስራው መሰረት፣ መጥፎም ሆነ መልካም፣ ይፈረድበታል።
፳፭ እናም እነርሱ ደግመው ሊመለሱበት በማይችሉበት በስቃይና መጨረሻ በሌለው አሰቃቂ በሆነ ሁኔታ በጌታ ፊት እንዲሸማቀቁ በሚያደርጋቸው በራሳቸው ክፋትና እርኩሰት ክፉዎች አስተያየት ላይ ይመደባሉ፤ ስለዚህ ለእራሳቸው ነፍስ ኩነኔን ይጎነጫሉ።
፳፮ ስለዚህ፣ ፍርዱ አዳም የተከለከለውን ፍሬ በመመገቡ መውደቅ እንዳለበት ለመካድ እንደማይችል እነርሱንም ሊክድ ስለማይችሉ፣ ከእግዚአብሔር የቁጣ ዋንጫ ጎንጭተዋል፤ ስለዚህ ምህረት ከእንግዲህ ለዘለዓለም በእነርሱ ላይ ጥያቄ ሊኖረው አይችልም።
፳፯ እናም ስቃያቸው ነበልባሉ የማይጠፋ፣ እና ጢሱ ለዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ወደ ላይ እንደሚያርገው እንደ እሳቱ ባህርና ዲን ነው። እንደዚህም ጌታ እኔን አዞኛል። አሜን።