ቅዱሳት መጻህፍት
ሞዛያ ፳፫


በንጉስ ኖህ ህዝብ ወደ ምድረበዳ እንዲሰደዱ የተደረጉት የአልማና የጌታ የሆኑት ሰዎች ታሪክ።

ከምዕራፍ ፳፫ እስከ ምዕራፍ ፳፬ አጠቃሎ የያዘ።

ምዕራፍ ፳፫

አልማ ንጉስ መሆንን አልተቀበለም—እንደ ሊቀ ካህን አገለገለ—ጌታ ህዝቡን ገሰጸ፣ እናም ላማናውያን የሔላምን ምድር አሸነፉ—የንጉስ ኖህ የክፉዎቹ ካህናት አለቃ የሆነው አሙሎን፣ በላማናውያን አገዛዝ ስር ገዛ። ከ፻፵፭–፻፳፩ ም.ዓ. ገደማ።

እንግዲህ አልማ የንጉስ ኖህ ወታደሮች በእነርሱ ላይ እንደሚመጡ ከጌታ ማስጠንቀቂያ በማግኘቱ፣ እናም ህዝቡ እንዲያውቀው በማድረጉ፣ ስለዚህ መንጋዎቻቸውን በአንድነት ሰበሰቡና፣ እህላቸውን ወሰዱ፣ እናም ከንጉስ ኖህ ወታደሮች ፊት ወደ ምድረበዳው ሸሹ።

እናም የንጉስ ኖህ ህዝብ እነርሱን ለማጥፋት ሊደርሱባቸው እንዳይችሉ ጌታ አበረታታቸው።

እናም በስምንት ቀን ጉዞ ወደ ምድረበዳው ተሰደዱ።

እናም ወደ ምድሩ ደረሱ፣ አዎን፣ በጣም ቆንጆና መልካም ምድር የንፁህ ውሃ ምድር ወደሆነች መጡ።

እናም ድንኳናቸውን ተከሉና፣ ምድሪቱን ማረስ ጀመሩ፣ እናም ህንፃን መገንባት ጀመሩ፣ አዎን፣ ትጉህ ነበሩም፣ እጅግ ሰሩም።

እናም አልማ በህዝቡ በመወደዱ የእነርሱ ንጉስ እንዲሆን ፈለጉ።

ነገር ግን እርሱ እንዲህ አላቸው፥ እነሆ፣ ንጉስ ይኖረን ዘንድ አስፈላጊ አይደለም፤ ምክንያቱም ጌታ እንዲህ ብሏል፥ እናንተ አንዱን ሰው ከሌላው አታስበልጡ፣ ወይም ማንም እራሱን ከሌላው በላይ ከፍ አያድርግ፣ ስለዚህ እንዲህ እላችኋለሁ ንጉስ እንዲኖራችሁ አስፈላጊ አይደለም።

ይሁን እንጂ፣ የሚቻል ከሆነ ሁልጊዜ ፃድቅ ሰው የእናንተ ንጉስ ሊሆን ቢችል ንጉስ ለእናንተ መኖሩ መልካም ይሆናል።

ነገር ግን የንጉስ ኖህንና የእርሱን ካህናት ክፋት አስታውሱ፣ እናም እኔ ራሴም በወጥመድ ተይዤ ነበርና፣ በጌታ አመለካከት ርኩስ የሆኑ በብርቱ ንስሃ እንድገባ የሚያደርጉኝን ብዙ ነገሮች ፈፅሜአለሁ፤

ይሁን እንጂ፣ ከብዙ መከራና ችግር በኋላ፣ ጌታ ጩኸቴን ሰማና፣ ለፀሎቴ መልስን ሰጠኝ፣ እናም ብዙዎቻችሁ የእርሱን እውነታ እንድታውቁ እኔን መሳሪያው አደረገኝ።

፲፩ ይሁን እንጂ፣ በዚህ አልኮራም ለመኩራት ብቁም አይደለሁምና።

፲፪ እናም አሁን በንጉስ ኖህ ተጨቁናችኋል፣ እናም በእርሱና በካህናቱ ባርነት ስር ሆናችኋል፣ በእነርሱም ወደ ጥፋት ተወስዳችኋል እላለሁ፤ ስለዚህ በኃጢያት እስራት ታስራችሁ ነበር።

፲፫ እናም አሁን ከዚህ ሰንሰለት በእግዚአብሔር ኃይል ተለቅቃችኋል፤ አዎን፣ ከንጉስ ኖህና ከህዝቡ እጅ እንኳን፣ እናም ደግሞ ከክፋት ሰንሰለት ነፃ እንደወጣችሁ፣ እንዲሁም በእዚህ ነፃነት ፀንታችሁ እንድትቆሙ ደግሞ እፈልጋለሁ፣ እናም ማንም ሰው በእናንተ ላይ ገዢ እንዲሆን አትፍቀዱ።

፲፬ እናም ደግሞ የእግዚአብሔር ሰው ሆኖ በእርሱ ጎዳና የሚራመድና ትዕዛዛቱን የሚጠብቅ ካልሆነ በቀር ማንም የእናንተ መምህርም ሆነ አገልጋይ እንዲሆን አትፍቀዱ።

፲፭ ማንም ሰው ጎረቤቱን እንደራሱ አድርጎ እንዲወድ፣ በመካከላቸውም ምንም ፀብ እንዳይኖር አልማ ህዝቡን እንዲህ አስተማረ።

፲፮ እናም አሁን፣ አልማ ሊቀ ካህንና የቤተክርስቲያናቸውም መስራች ነበር።

፲፯ እናም እንዲህ ሆነ በእርሱ በኩል ከእግዚአብሔር ካልሆነ በቀር ማንም ለመስበክም ሆነ ለማስተማር ስልጣንን አልተቀበለም ነበር። ስለዚህ ሁሉንም የእነርሱን ካህናትንና መምህራኖቻቸውን ሾመ፤ እናም ማንም ትክክለኛ ሰው ካልሆነ በቀር አልተሾመም ነበር።

፲፰ ስለዚህ ህዝባቸውን ጠበቁ፣ እናም ከፅድቅነት ጋር የተገናኙ ነገሮችን መገቧቸው

፲፱ እናም እንዲህ ሆነ በምድሪቱ እጅግ መበልፀግ ጀመሩ፤ እናም ምድሪቱን ሔላም ብለው ጠሯት።

እናም እንዲህ ሆነ በሔላም ምድር ተባዙ እጅግም በለፀጉ፤ እናም የሔላም ከተማ ብለው የሰየሟትን ከተማ ቆረቆሩ።

፳፩ ይሁን እንጂ ጌታ ህዝቡን መግሰፅ ተገቢ መሆኑን አየ፣ አዎን፣ ትዕግስታቸውንና እምነታቸውን ፈተነ።

፳፪ ይሁን እንጂ—እምነቱን በእርሱ ያደረገ በመጨረሻው ቀን ከፍ ይላል። አዎን እናም ለዚህ ህዝብም እንደዚህ ነበር።

፳፫ እነሆም ወደ ባርነት እንደመጡ አሳያችኋለሁ፤ እናም ጌታ አምላካቸው፣ አዎን የአብርሃምና የይስሐቅ እናም የያዕቆብ አምላክ፣ ካልሆነ በቀር ማንም ሊያድናቸው አይቻለውም።

፳፬ እናም እንዲህ ሆነ፣ እርሱ አዳናቸው፣ ታላቁን ኃይሉንም አሳያቸው፣ እናም ደስታቸው ታላቅ ነበር።

፳፭ እነሆም፣ እንዲህ ሆነ በሔላም ምድር በነበሩበት ጊዜ፣ አዎን፣ በሔላም ከተማ፣ በዙሪያው ያለውን መሬት በሚያርሱበት ጊዜ፣ እነሆ የላማናውያን ወታደሮች በምድሪቱ ዳርቻ ነበሩ።

፳፮ አሁን እንዲህ ሆነ የአልማ ወንድሞች ከእርሻቸው ሸሹ፣ እናም በሔላም ከተማ እራሳቸውን በአንድ ላይ ሰበሰቡ፤ እናም በላማናውያን አቋም እጅግ ፈርተው ነበር።

፳፯ ነገር ግን አልማ ወደፊት ሔደና ከእነርሱ ጋር ቆመ፣ እናም እንዳይፈሩ፣ ነገር ግን ጌታ አምላካቸው ማስታወስ እንዳለባቸውና እርሱ እንደሚያድናቸው አበረታታቸው።

፳፰ ስለዚህ ፍርሃታቸውን ዋጡት፣ እናም እነርሱንና ሚስቶቻቸውን፣ እናም ልጆቻቸውን ያተርፉላቸው ዘንድ የላማናውያንን ልብ እንዲያራራ ወደ ጌታ መጮኽ ጀመሩ።

፳፱ እናም እንዲህ ሆነ ጌታ የላማናውያንን ልብ አራራ። እናም አልማና ወንድሞቹ ወደ እነርሱ ሔዱና፣ እራሳቸውን አሳልፈው ሰጡአቸው፤ እናም ላማናውያን የሔላምን ምድር ያዙ።

አሁን ከንጉስ ሊምሂ በኋላ የሚሄዱት ላማናውያን ወታደሮች ለብዙ ቀናት በምድረበዳው ተሰወሩ።

፴፩ እናም እነሆ፣ የንጉስ ኖህን ካህናት አሙሎን በተባለ ስፍራ አገኙአቸው፤ እናም የአሙሎንን ምድር የራሳቸው አደረጉ፣ ምድሪቱንም ማረስ ጀመሩ።

፴፪ አሁን የካህናቱ መሪ ስም አሙሎን ነበር።

፴፫ እናም እንዲህ ሆነ አሙሎን ላማናውያንን ተማፀነ፣ እናም ደግሞ የላማናውያን ሴት ልጆች የሆኑትን ሚስቶቻቸውን፣ ባሎቻቸውን እንዳያጠፉባቸው ከወንድሞቻቸው ጋር እንዲማፀኑ ላከ።

፴፬ እናም ላማናውያን በሚስቶቻቸው ምክንያት ለአሙሎንና ለወንድሞቹ ርህራሄ ነበራቸው፣ እናም አላጠፉአቸውም።

፴፭ እናም አሙሎንና ወንድሞቹ ከላማናውያን ጋር አንድ ሆኑና፣ የኔፊን ምድር ለመፈለግ በተጓዙበት ወቅት በአልማና በወንድሞቹ የተያዘውን የሔላምን ምድር አገኙ።

፴፮ እናም እንዲህ ሆነ ወደ ኔፊ ምድር የሚወስደውን መንገድ የሚያሳዩአቸው ከሆነ ህይወታቸውንና ነፃነታቸውን እንደሚሰጡአቸው ላማናውያን ለአልማና ለወንድሞቹ ቃል ገቡ።

፴፯ ነገር ግን አልማ ወደ ኔፊ ምድር የሚወስደውን መንገድ ካሳያቸው በኋላ ላማናውያን ቃላቸውን አልጠበቁም፤ ነገር ግን በአልማና በወንድሞቹ ላይ በሔላም ምድር ዙሪያ ጠባቂዎች አስቀመጡ።

፴፰ እናም የተቀሩት ወደ ኔፊ ምድር ሔዱ፤ እናም ግማሾቹ ወደ ሔላም ምድር ተመለሱ፣ ደግሞም ትተዋቸው የሄዱትን ጠባቂዎቹ ሚስቶቻቸውንና ልጆቻቸውን አመጡ።

፴፱ እናም የላማናውያን ንጉስ ለአሙሎን በሔላም ምድር በነበረው ህዝቡ ላይ ንጉስና ገዢ እንዲሆን ፈቀደለት፤ ይሁን እንጂ ከላማናውያን ንጉስ ፈቃድ የሚቃረን ምንም ነገር የማድረግ ስልጣን አይኖረውም።