ቅዱሳት መጻህፍት
ሞዛያ ፬


ምዕራፍ ፬

ንጉስ ቢንያም ንግግሩን ቀጠለ—ደህንነት የሚመጣው በኃጢያት ክፍያው አማካኝነት ነው—ለመዳን በእግዚአብሔር እመኑ—የኃጢአታችሁን ስርየት በእምነታችሁ አግኙ—ያላችሁን ነገር ለድሆች አካፍሉ—ሁሉንም ነገር በጥበብና በስርዓት አድርጉ። ፻፳፬ ም.ዓ. ገደማ።

እናም አሁን፣ እንዲህ ሆነ ንጉስ ቢንያም በጌታ መልአክ የተሰጠውን ቃላት ተናግሮ ሲጨርስ፣ ዙሪያ ገባውን ተመልክቶ ዐይኑን በህዝቡ ላይ አሳረፈ፣ እናም የጌታ ፍርሃት በእነርሱ ላይ በመምጣቱ የተነሳ በመሬት ላይ ወድቀው ተመለከታቸው።

እናም በስጋቸው እራሳቸውን ከመሬት ትቢያ እንኳን አሳንሰው ተመለከቱ። እናም ሁሉም በአንድ ድምፅ እንዲህ ብለው ጮሁ፥ አቤቱ ምህረትን ስጠን፣ እናም ለኃጢአታችን ይቅርታን እናገኝ ዘንድና ልባችን ንፁህ ይሆን ዘንድ የክርስቶስን የደም ክፍያ በእኛ ላይ አድርግ፤ ሰማይና ምድርን እንዲሁም ሁሉንም ነገሮች በፈጠረው በሰው ልጆች መካከል በሚመጣው በእግዚአብሔር ልጅ በክርስቶስ ኢየሱስ እናምናለንና።

እናም እንዲህ ሆነ እነዚህን ቃላት ከተናገሩ በኋላ የጌታ መንፈስ በእነርሱ ላይ መጣ፤ እና ንጉስ ቢንያም በተናገረው ቃላት መሰረት በሚመጣው በኢየሱስ ክርስቶስ ባላቸው ታላቅ እምነት የተነሳ፣ ለኃጢአታቸውም ስርየትን በመቀበል፣ እናም የህሊና ሰላምም በማግኘት በደስታ ተሞልተው ነበር።

እናም ንጉስ ቢንያም በድጋሚ አፉን ከፍቶ እንዲህ ሲል መናገር ጀመረ፥ ጓደኞቼና ወንድሞቼ፣ ወገኖቼና ህዝቤ ለእናንተ የምናገረውን ቀሪውን ቃሌን ታደምጡኝ እናም ትረዱኝ ዘንድ በድጋሚ ትኩረታችሁን እፈልጋለሁ።

እነሆም በዚህ ጊዜ የእግዚአብሔርን ቸርነት ማወቅ እናንተ ምንም እንዳልሆናችሁ፣ እናም እንደማትረቡና እንደውድቀታችሁ ሁኔታ ስሜት የሚያነቃችሁ ከሆነ—

እንዲህ እላችኋለሁ፣ የእግዚአብሔርን ቸርነት እናም ወደር የሌለውን ሀይሉንና፣ ጥበቡን፣ እንዲሁም ረዥም ፅናትና፣ እናም ለሰው ልጆች ያለውን ታጋሽነቱን፣ ደግሞም እምነቱን በጌታ ላይ ያሳረፈና፣ ትዕዛዛቱን ለመጠበቅ ትጉህ ለሆነው፣ እና እስከህይወቱ፣ ይህም ማለቴ የስጋ ሰውነት ህይወቱ መጨረሻ ድረስ በእምነት ለጸናው ደህንነት እንዲመጣለት ዘንድ፣ ከዓለም መፈጠር ጀምሮ የተዘጋጀውን የኃጢያት ክፍያ ወደማወቅ ከመጣችሁ—

ይህ አይነቱ ሰው ከዓለም መፈጠር ጀምሮ፣ ከአዳም ውድቀት በኋላ ለነበሩት፣ ወይም ለአሉት፣ ወይም እስከ አለም መጨረሻ ድረስ ስለሚኖሩት፣ ለሰው ልጆች ሁሉ በተዘጋጀው የኃጢያት ክፍያ ደህንነትን ይቀበላል እላለሁ።

እናም ደህንነት የሚገኝበት መንገድ ይህ ነው። እናም ከዚህ ከተነገረው በስተቀር ሌላ ደህንነት የለም፤ እኔ ከተናገርኳችሁ ሁኔታ በቀር ሰዎች የሚድኑበት ሌላ መንገድ የለም።

በእግዚአብሔር እመኑ፤ እርሱ እንዳለ፣ እናም እርሱ በሰማይም በምድርም ያሉትን ሁሉንም ነገሮች እንደፈጠረ እመኑ፤ በሰማይና በምድር ሁሉ ጥበብና ሀይል እንዳለው እመኑ፤ ጌታ ሊረዳቸው የሚችለውን ነገሮች ሁሉ ሰው እንደማይረዳቸው እመኑ።

እናም እንደገና፤ ለኃጢአታችሁ ንስሃ መግባትና፣ መተው፣ እንዲሁም በእግዚአብሔር ፊት ትሁት መሆን እንዳለባችሁ እመኑ፤ ይቅር እንድትባሉ ከልባችሁም ጠይቁ፤ እናም አሁን፣ እነዚህን ነገሮች ሁሉ ካመናችሁ መፈፀማችሁን አረጋግጡ።

፲፩ እናም እንደገና በፊት እንደተናገርኳችሁ እናገራችኋለሁ፣ የእግዚአብሔርን ክብር ለማወቅ የምትመጡ ከሆነ፣ እንዲሁም ቸርነቱንና ታጋሽነቱን ካወቃችሁና ፍቅሩን ከቀመሳችሁ፣ ነፍሳችሁ እጅግ እንድትደሰት የሚያደርገውን ለኃጢአታችሁ ስርየትን ከተቀበላችሁም፣ የእግዚአብሔርን ታላቅነትና የራሳችሁን ከንቱነት፣ ወደ እናንተ የማትረቡ ፍጥረት ያለውን የእርሱን ጥሩነትና ትዕግስት፣ እናም የጌታንም ስም ቀን በቀን በመጥራትና በመልአኩ አፍ በተነገረለት ወደፊት በሚመጣው እምነት አፅንታችሁ በመቆም በጥልቅ ትህትና እንኳን ራሳችሁን እንድታዋርዱ እንድታስታውሱትና ሁልጊዜም በማስታወስ እንድትይዙት እፈልጋለሁ።

፲፪ እናም እነሆ፣ እላችኋለሁ ይህንን የምታደርጉ ከሆነ ሁልጊዜ ትደሰታላችሁ፣ በእግዚአብሔር ፍቅር ትሞላላችሁም፣ ሁልጊዜ የኃጢአታችሁን ስርየት ታገኛላችሁም፤ እናም እናንተን በፈጠረው ክብር እውቀት፣ ወይንም ትክክለኛና እውነተኛ በሆነው እውቀት ታድጋላችሁ።

፲፫ እናም በሰላም ለመኖርና፣ ለእያንዳንዱ ሰው የሚገባውን ለመስጠት እንጂ፣ እርስ በርሳችሁ የመጎዳዳት ሃሳብ አይኖርባችሁም።

፲፬ እናም ልጆቻችሁ ተርበው አለበለዚያም ተራቁተው እንዲሄዱ አትፈቅዱም፤ የእግዚአብሔርንም ህግ እንዲተላለፉ፣ እርስ በርሳቸውም እንዲጣሉ እናም በአባቶቻችን ክፉ መንፈስ ተብሎ የተነገረለትን የፅድቅ ሁሉ ጠላት የሆነውንና የኃጢያት አለቃ የሆነውን ዲያብሎስን እንዲያገለግሉ አትፈቅዱም።

፲፭ ነገር ግን በእውነትና በጥሞና መንገድ እንዲራመዱ ታስተምሯቸዋላችሁ፣ እርስ በርሳቸው እንዲዋደዱ እንዲሁም አንደኛው ሌላኛውን እንዲያገለግል ታስተምሯቸዋላችሁ።

፲፮ እናም ደግሞ፣ እናንተ ራሳችሁ የእናንተን እርዳታ ፍለጋ የቆሙትን ትረዷቸዋላችሁ፤ ፍላጎት ላላቸው ቁሳቁሳችሁን ትሰጧቸዋላችሁ፤ እናም ለማኙም እናንተን የሚለምነው በከንቱ እንዲሆንና፣ እንዲጠፋ ማስወጣትን አትፈቅዱም።

፲፯ ምናልባት እንዲህ ትላላችሁ፥ ይህ ሰው ስቃይን በራሱ ላይ አምጥቷል፣ ስለሆነም እጄን እሰበስባለሁ፣ እናም እንዳይቸገር ከእንጀራዬም ሆነ ከአለኝ ነገር አልሰጠውም ምክንያቱም ቅጣቶቹ ትክክል ናቸውና—

፲፰ ነገር ግን እላችኋለሁ፣ ሰው ሆይ፣ ማንም ይህንን ያደረገ ንስሃ ለመግባት ታላቅ ምክንያት ይኖረዋል፤ እናም በፈፀመው ነገር ንስሃ ካልገባ በስተቀር ለዘለዓለም ይጠፋል፣ እናም በእግዚአብሔር መንግስት ቦታ አይኖረውም።

፲፱ እነሆም ሁላችንስ ለማኞች አይደለንምን? ሁላችንም ባሉን ቁሳቁሶች ሁሉ፣ በምግብና በልብስ፣ እንዲሁም በወርቅና፣ በብር፣ እናም ከሁሉም አይነት ባሉን ሀብቶች በአንዱስ ፍጡር፣ እንዲሁም በእግዚአብሔር ጥገኞች አይደለንምን?

እናም እነሆ፣ በዚህ ጊዜም እንኳን ቢሆን፣ ስሙን ጠርታችኋልም፣ ለኃጢአታችሁ ስርየትን ለምናችኋልም። እናም በከንቱ እንድትለምኑ ፈቅዷልን? አይደለም፤ መንፈሱን በላያችሁ ላይ አፍስሷል፤ እናም ልባችሁ በደስታ እንዲሞላ አድርጓል፣ እንዲሁም ስለዚህ ደስታችሁም እጅግ ታላቅ ሆኖ፣ መናገርም እንዳትችሉ አንደበታችሁን እንዲዘጋ አድርጓል።

፳፩ እናም አሁን፣ ለህይወታችሁና ላላችሁና ለሆናችሁት ሁሉ የምትመኩበት እናንተን የፈጠረው እግዚአብሔር ትክክለኛ የሆነውን ማንኛውንም ነገር በእምነት፣ አገኛለሁ በማለት አምናችሁ የምትጠይቁትን ከሰጣችሁ፣ አቤቱ ያላችሁን ነገሮች አንዳችሁ ለሌላኛችሁ እንዴት መካፈል ይገባችኋል።

፳፪ እናም አንድ ሰው እንዳይጠፋ ካላችሁ ሀብት እንድታካፍሉት የሚጠይቃችሁን ከፈረዳችሁበት፣ ከኮነናችሁት፣ የእናንተ ሳይሆን ህይወታችሁም እንኳን የእርሱ የሆነው የእግዚአብሔር የሆነውን ሀብታችሁን በመያዛችሁ ኩነኔያችሁም ምን ያህል ትክክል ይሆናል፤ ነገር ግን፣ ለሰራችኋቸው ነገሮችም ንሰሃን እናም ልመናን አላቀረባችሁም።

፳፫ እላችኋለሁ፣ ለዚህ ሰው ወዮለት ያለው ነገር ከእርሱ ጋር ይጠፋልና፣ እናም አሁን፣ የዚህን ዓለም ነገሮች ለአሉአቸው ባለጠጋዎች እነዚህን ነገሮች እናገራለሁ።

፳፬ እናም እንደገና ባይኖራቸውም፣ ግን በህይወት እንዲቆዩ በመጠኑም ለሚኖራቸው ድሆች እንደገና እንዲህ እላለሁ፤ ማለቴም እናንተ ስለሌላችሁ ለድሆች ለማትሰጡት ነው፤ በልባችሁ ስለሌለኝ አይደለም የማልሰጠው፣ ነገር ግን ቢኖረኝ ኖሮ እሰጥ ነበር እንድትሉ እፈልጋለሁ።

፳፭ እናም አሁን፣ ይህንን በልባችሁ የምትሉ ከሆነ ከበደል የነፃችሁ ትሆናላችሁ፣ አለበለዚያ ግን ትኮነናላችሁ፣ እናም ኩነኔአችሁ የእናንተ ያልሆነውን በመመኘታችሁ ትክክል ነው።

፳፮ እናም አሁን፣ ለእናንተ ለተናገርኳቸው ለእነዚህ ነገሮች ሲባል—ይህም ማለት በእግዚአብሔር ፊት ከበደል ነፅታችሁ ትራመዱ ዘንድ ከቀን ወደ ቀን ለኃጢአታችሁ ስርየትን እንድታገኙ—የራሳችሁን ነገር ለድሃ እንድትሰጡ፣ እያንዳንዱ ሰው ባለው መጠን፣ የተራቡትን በመመገብ፣ የታረዙትን በማልበስ፣ የታመሙትን በመጎብኘት እናም እንደፍላጎታቸው ለነፍሳቸውም ሆነ ለስጋቸው ደህንነት በቂ እርዳታን እንድትለግሱ እፈልጋለሁ።

፳፯ እናም እነዚህ ነገሮች ሁሉ በጥበብና በዕቅድ እንደተደረጉ ተመልከቱ፣ ሰው ከአቅሙ በላይ ፈጥኖ መሮጡ አስፈላጊ አይደለምና። እናም እንደገና፣ ሽልማቱን ያሸንፍ ዘንድ ትጉህ መሆኑ አስፈላጊ ነው፣ ስለዚህ፣ ሁሉም ነገሮች በስርዓት መደረግ አለባቸው።

፳፰ እናም ማንም ከእናንተ መካከል ከጎረቤቱ የተበደረ የተበደረውን ነገር በስምምነቱ መሰረት መመለስ እንዳለበት እንድታስታውሱ እፈልጋለሁ፣ አለበለዚያ ኃጢያትን ትፈፅማላችሁ፤ እናም ምናልባት ጎረቤቶቻችሁንም ደግሞ ኃጢያት እንዲፈፅሙ ታደርጋላችሁ።

፳፱ እናም በመጨረሻም፣ ኃጢያት ልትፈፅሙ የምትችሉባቸውን ነገሮች ሁሉ ልነግራችሁ አልችልም፤ ምክንያቱን መቁጠር የማልችለው ብዙ መንገዶችና ዘዴዎች ስለሚኖሩ ነው።

ነገር ግን ይህን ያህል ልነግራችሁ እችላለሁ፣ ራሳችሁን፣ ሀሳባችሁንናቃላችሁን፣ እናም ድርጊታችሁን የማታስተውሉና፣ የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ የማትጠብቁ፣ እናም የሚመጣውን ጌታችንን በተመለከተ የሰማችሁትን እስከ ህይወታችሁ መጨረሻ በእምነት የማትቀጥሉ ከሆናችሁ፣ መጥፋት ይገባችኋል። እናም አሁን፣ ሰው ሆይ፣ አስታውስ፣ እናም አትጥፋ።