አጠቃላይ ጉባኤ
በእምነት ወደፊት ሂዱ
የሚያዝያ 2020 (እ.አ.አ) አጠቃላይ ጉባኤ።


በእምነት ወደፊት ሂዱ

በሰላም እና በጌታ በሚያድግ እምነት እባርካችኋለው።

ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ፤ ለዚህ ታሪካዊ ጉባኤ መዝጊያ ስንቃረብ፣ ምስጋናችንን ለጌታ እናቀርባለን፡፡ መዝሙሮቹ ግርማዊ፣ መልዕክቶቹ ደግሞ አነሳሽ ነበሩ።

በዚህ ጉባኤ ወቅት፣ ብዙ ጉዳዮችን ተገንዝበናል። በዚህ በሁለተኛው ምእተ ዓመት መታሰቢያ በተከበረው ላይ፣ የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል በዳግም በሙላት መመለሱ እውን መሆኑን በመናገር አዋጅ አስተዋውቀናል።

ዳግም መመለስን በሆሳዕና ጩኸት አክብረናል።

በጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ያለንን እምነት እና ለቤተክርስቲያኗ ደንባዊ መረጃና ፅሁፎችን በምስላዊ መለያ የሚገልፅ አዲስ ምልክትን እንገልፃለን።

የአሁኑ ወረርሽኝ እንዲገታ፣ አስታማሚዎች እንዲጠበቁ፣ ኢኮኖሚው እንዲጠነክር፣ እና ሕይወት ወደ ወትሮው እንዲመለስ ለመላው ዓለም የፆም እና የጸሎት ቀን ጠርተናል። ይህ ፆም በሚያዚያ 10 በመልካሙ በስቅለት እለት ይያዛል። ያ ምን አይነት ታላቅ አርብ ይሆናል!

የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስ የሃጢያት ክፍያ እና ትንሳኤ እንደገና የምናከብርበት የሚቀጥለው እሁድ የፋሲካ በዓል ነው። በሃጢያት ክፍያው ምክንያት የእርሱ የትንሳኤው ስጦታ በሕይወት ለኖረ ሁሉ ይመጣል። የዘላለማዊ ሕይወት ስጦታው በቤተመቅደሱ ውስጥ ለተደረገው ሥነ-ስርዓቶች እና ቃልኪዳኖች ታማኝ በመሆን ብቁ ለሚሆኑ ሁሉ ይመጣል።

ብዙ ከሚያነሳሱ የዚህ የሚያዝያ 2020 (እ.አ.አ) አጠቃላይ ጉባኤ እና አሁን የጀመርነው ቅዱስ ሳምንት፣ “እርሱን ስማው” በሚል በሁለት መለኮታዊ እወጃ ቃላት ይጠቃለላሉ።1 እነዛን ቃላት በተናገረው በእግዚአብሔር እና በአንድያ ልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያላችሁ ትኩረት ባነሳሳችሁ ትውስታ ውስጥ በታላቅነት እንዲያብብ እንጸልያለን። በትክክል እንድትሰሙ፣ እንድትገነዘቡ እና የአዳኙን ቃላት እንድታደምጡ እንደ አዲስ እንድትጀምሩ እንጸልያለን።2 የሚቀንስ ፍርሃት እና የሚጨምር እምነት እንደሚከተል ቃል እገባለው።

ቤታችሁን የጌታ መንፈስ መኖር የሚችልበት ትክክለኛ የእምነት መጠለያ ለማድረግ ስላላችሁ ፍላጎት አመሰግናለው፡፡ ኑ፣ ተከተሉኝ የሚለው የወንጌል የጥናት ሥራዓተ ትምህርት ሕይወታችሁን መባረኩን ይቀጥላል። በዚህ ስራ ላይ ውጤታማ ያልሆናችሁ መስሎ ሲሰማችሁ እንኳን የእናንተ ቀጣይነት ያለው ጥረታችሁ፣ ሕይወታችሁን፣ የቤተሰባችሁን ሕይወት እንዲሁም ዓለምን ይቀይራል። የበለጠ የጌታ ታታሪ ደቀመዝሙር ስንሆን፣ የትም ብንሆን ሰለ እርሱ በመቆም እና በመናገር እንጠነክራለን፡፡

አሁን ስለ ቤተመቅደስ እናውራ። በመላው ዓለም 168 ቡራኬ ያገኙ ቤተመቅደሶች አሉን። ሌሎች በተለያየ የዕቅድ ደረጃ እና ግንባታ ላይ ናቸው። አዲስ ቤተመቅደስን ለማቆም ዕቅዶች ሲተዋወቁ፣ የቅዱስ ታሪካችን አካል ይሆናል።

ሁሉም ቤተመቅደሶቻችን ዝግ በሆኑበት ወቅት አዲስ ቤተመቅደሶችን ማስተዋወቅ የሚያስገርም ሊመስል ይችላል።

ከመቶ አመት በፊት፣ ፕሬዝዳንት ዊልፈርድ ዉድረፍ በ1893 (እ.አ.አ) በሶልት ሌክ ቤተመቅደስ የቡራኬ ጸሎት ጊዜ እንደተመዘገበው ስለ አሁን ጊዜ ያሉ ሁኔታዎችን አዩ። አንዳንዶቻችሁ በቅርቡ ስለዚህ አስደናቂ ጸሎት ፅሁፍ በመሃበራዊ ድህረገፅ ላይ አይታችሁ ይሆናል።

ከኃያል የእግዚአብሔር ነቢይ እነዚህን ልመናዎች አዳምጡ፤ “ሰዎችህ በዚህ በተቀደሰ ቤት ውስጥ የመግባት እድል ሳይኖራቸው … እና በችግሮች ተከብበው ሲጨቆኑ እና ችግር ውስጥ ሲወድቁ፣ … ወደዚህ ወዳንተ ቅዱስ ቤት ፊታቸውን ሲያዞሩ እና እንድታድናቸው፣ እንድትረዳቸው፣ ኃይልህ በእነሱ ላይ እንዲዘረጋ ሲጠይቁህ፣ በምህረት ከቅዱስ ስፍራህ ወደታች እንድትመለከት … እና ጩኸታቸውን እንድትሰማ እንለምንሃለን። ወይም በሚመጡት አመታት የሰዎችህ ልጆች በማንኛውም ምክንያት ከዚህ ቦታ በሚለዩበት ጊዜ፣ … ከመከራቸው እና ከሀዘናቸው ጥልቅ እንድታረጋጋቸው እና እንድታወጣቸው ወደ አንተ ይጮሃሉ፣ ጩኸታቸውን እንድትሰማ እና የሚጠይቁትን በረከቶች እንድትሰጣቸው በትህትና እንለምንሃለን።”3

ወንድሞችና እህቶች፣ በእኛ የጭንቀት ጊዜ ወቅት ቤተመቅደሶች ዝግ ሆነው ሳለ፣ ቃልኪዳኖቻችሁን ስታከብሩ የቤተመቅደስ ቃልኪዳኖቻችሁን እና በረከቶቻችሁን ኃይል አሁንም ልትጠቀሙባቸው ትችላላችሁ። ቤተመቅደሶች በተዘጉበት በዚህ ጊዜ ለቤተመቅደስ ብቁ የሚያደርግ ሕይወት ለመኖር ወይም ለቤተመቅደስ ብቁ ለመሆን እባካችሁ ይህንን ጊዜ ተጠቀሙበት።

ስለ ቤተመቅደስ ከቤተሰባችሁ እና ከጓደኞቻችሁ ጋር ተነጋገሩ። ኢየሱስ ክርስቶስ በቤተመቅደስ ውስጥ በምናደርገው በሁሉም ነገር መካከላዊ በመሆኑ ምክንያት፣ ስለ ቤተመቅደስ የበለጠ ስታስቡ ስለእርሱም ታስባላችሁ። ስለተባረካችሁበት ወይም ስለምትባረኩበት ኃይል እና እውቀት የበለጠ ለመማር አንብቡ እንዲሁም ጸልዩ።

ዛሬ በሚቀጥሉት አካባቢዎች ስምንት አዳዲስ ቤተመቅደሶችን የመገንባት ዕቅዶችን ስናስተዋውቅ በደስታ ነው፤ ባሂያ ብላንካ፣ አርጀንቲና፤ ታለሃሲ፣ ፍሎሪዳ፤ ሉቡምባሺ፣ የኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ፤ ፒትስበርግ፣ ፔንስልቫንያ፤ ቤኒን ሲቲ፣ ናይጄሪያ፤ ሲራከስ፣ ዩታ፤ ዱባይ፣ የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች፤ እና ሻንጋይ፣ የቻይና ሪፐብሊክ።

በሁሉም ስምንት ሥፍራዎች፣ የቤተ-ክርስቲያን የስነ ህንጻ ምሁራን ከአካባቢው ባለስልጣናት ጋር አብረው ይሰራሉ ​​እናም ቤተመቅደሱ ከእያንዳንዱ ማህበረሰብ ጋር እንዲስማማ እና ተጨማሪ ውበት እንዲሰጥ ያደርጋሉ።

በዱባይ ውስጥ የቤተመቅደስ እቅድ የመጣው ምስጋና በሚገባው የልግስና ጥሪያቸው ምላሽ ነው፣ እኛም በምስጋና ተቀብለናል።

ለሻንጋይ የዕቅዱ ምንነት በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ከሁለት አስርተ ዓመታት በላይ፣ በህዝባዊ ሪፐብሊክ ቻይና ውስጥ ያሉ የቤተመቅደስ ብቁ የሆኑ አባላት በሆንግ ኮንግ ቻይና ቤተመቅደስ ተሳትፈዋል። ግን በሐምሌ ወር 2019 ይህ ቤተመቅደስ ለረጅም ጊዜ ከታቀደ እና እጅግ አስፈላጊ ለሆነ እድሳት ተዘግቷል።

በሻንጋይ፣ መጠነኛ የሆነ የብዙ አገልግሎት የመሰብሰቢያ ቦታ የቻይና አባላት በቤተ መቅደስ ስነ ስርአቶች መሳተፋቸውን እንዲቀጥሉ በህዝባዊ ሪፐብሊክ ቻይና ውስጥ ለራሳቸው እና ለቅድመ አያቶቻቸው መንገድን ያመቻቻል።4

በእያንዳንዱ ሀገር ይህች ቤተክርስቲያን አባላቶች ህጉን እንዲያከብሩ፣ እንዲታዘዙ እና እንዲደግፉ ታስተምራቸዋለች፡፡5 የቤተሰብን አስፈላጊነት፣ ጥሩ ወላጅ መሆን እና አርአያ ዜጎች ስለ መሆን እናስተምራለን። የቻይና ህዝብ ሪፐብሊክ ህጎችን እና ደንቦችን ስለምናከብር፣ ቤተክርስቲያኗ ሰባኪ ሚስዮናውያንን እዚያ፣ አትልክም እኛም አሁን እንዲሁ አናደርግም።

የባዕድ አገር እና የቻይና ምእመናን በተናጥል መገናኘታቸውን ይቀጥላሉ፡፡ እዚያ ያለው የቤተክርስቲያኗ ህጋዊ አቋም አልተለወጠም፡፡ የመጀመሪያው የመገልገያ ቦታ አጠቃቀም፣ እና መግቢያ በቀጠሮ ብቻ ይሆናል። በሻንጋይ የሚገኘው የጌታ ቤት ከሌሎች አገሮች ለመጡ ቱሪስቶች የመድረሻ ቦታ አይሆንም

እነዚህ አዲስ ስምንት ቤተመቅደሶች በሁለቱም የመጋረጃ ክፍሎች የብዙ ሰዎችን ሕይወቶች ይባርካሉ። ቤተመቅደሶች የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል በሙሉነት የመመለስ ዘውድ ክፍሎች ናቸው። በእግዚአብሔር መልካምነት እና ቸርነት የቤተመቅደስ በረክቶችን በሁሉም ቦታለልጆቹ እያቀረበ ነው።

መመለሱ ሲቀጥል፣ በምድር ስለሚገኘው ቤተመንግስቱ እግዚአብሔር ብዙ ታላቅ እና አስፈላጊ ነገሮችን መግለጡን እንደሚቀጥል አውቃለው።6 ያ ቤተመንግስት የኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን ነው

ውድ ወንድሞች እና እህቶች፣ ለእናንተ ያለኝን ፍቅር እገልፃለው። በዚህ የውጥረት እና የመጠራጠር ወቅት፣ የተሰጠኝን ስልጣን በመጠቀም በላያችሁ ላይ ሐዋርያዊ በረከትን አበረክትላችኋለው።

በሰላም እና በጌታ በሚያድግ እምነት እባርካችኋለው።7

ንስሃ ለመግባት እና በየቀኑ ትንሽ እንደ እርሱ ለመሆን ፍላጎት እንዲኖራችሁ እባርካችኋለው።8

ነቢዩ ዮሴፍ ስሚዝ የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል በሙሉነት የመመለስ ነቢይ እንደሆነ እንድታውቁ እባርካችኋለው።

በመካከላችሁ ወይም በምትወዱት ሰዎች መካከል በሽታ ካለ፣ ከጌታ ፍቃድ ጋር የሚስማማ የፈውስ በረከቴን እተውላችኋለው።

ለእያንዳንዳችሁ ያለኝን ፍቅር በድጋሜ እየገልፅኩኝ እባርካችኋለው፣ በኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ስም፣ አሜን።