አጠቃላይ ጉባኤ
“ይህም ቤት ለስሜ ይገንባ”
የሚያዝያ 2020 (እ.አ.አ) አጠቃላይ ጉባኤ።


“ይህም ቤት ለስሜ ይገንባ”

(ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 124፥40)

ግን፣ በቤተመቅደስ ውስጥ የምንቀበላቸው ቃል ኪዳኖች እና የሚከናወኑት ስርዓቶች ልባችንን ለማፅዳት እናም ለእግዚአብሔር ወንድ እና ሴት ልጆች መጨረሻ ዘለአለማዊ ክብር አስፈላጊ ናቸው።

ከ200 አመት በፊት በቅዱስ ጫካ ውስጥ፣ ወጣቱ ጆሴፍ ስሚዝ እግዚአብሔር የዘለአለማዊ አባትን፣ እና ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስ አየ እናም አነጋገራቸው። ከእነርሱም፣ ይህ ግርማዊ ራዕዩ በኋለኛው ቀን ውስጥ “የዘመን ፍጻሜ ሙላትን”1በማስገባት ስለአምላክ እውነተኛ ፍጥረት እና ስለሚቀጥለው ራዕይ ጆሴፍ ተማረ።

ከሶስት አመት በኋላ፣ በልባዊ ጸሎት መልስ በመስጠት፣ በመስከረም 21 ቀን፣ 1823 (እ.አ.አ) ምሽት፣ የጆሴፍ መኝታ ቤት “ብርሃኑም ከቀትር ፀሐይ እስኪበልጥ ድረስ”2በብርሀን ተሞላ። በመኝታው አጠገብም አንድ ሰው መጣ፣ ወጣት ልጁን በስም በመጥራት “እርሱ ከእግዚአብሔር … ዘንድ የተላከ መልዕክተኛ እንደሆነና ስሙም ሞሮኒ እንደሆነ”3አወጀ። ስለመፅሐፈ ሞርሞን መምጣትም ጆሴፍን አስተማረው።

እናም ከዚያ ሞሮኒ ከኪንግ ጀምስ እትም ከተጠቀመው ቋንቋ አነስተኛ ልዩነት ባለው በብሉይ ኪዳን ከሚልክያስ መጽሐፍ ጠቀሰ፤

“እነሆ፣ ታላቁና የሚያስፈራው የጌታ ቀን ከመምጣቱ በፊት በነቢዩ ኤሊያስ እጅ ክህነትን እገልጥላችኋለው። …

“እናም ለአባቶች የተገባውን የተስፋ ቃል በልጆች ልብ ይተክላል፣ እናም የልጆቹም ልብ ወደ አባቶቻቸው ይመለሳል። እንዲህ ባይሆን ኖሮ፣ መላው ምድር በምጽአቱ በጠፋ ነበር።”4

ከሁሉም ይበልጥ፣ ሞሮኒ ስለኤልያስ ተልእኮ ጆሴፍ ስሚዝን ሲያስተምርም በኋለኛው ቀናት የቤተመቅደስ እና የቤተሰብ ታሪክ ስራን አስጀመረ እናም “እግዚአብሔር ከጥንት ጀምሮ በቅዱሳን ነቢያቱ አፍ የተናገረው ነገር ሁሉ”5በዳግም የመመለስ ዋና ክፍል ነበር።

አብረን በየኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን ቤተመቅደሶች ውስጥ ስለሚገኙት ቃል ኪዳኖች፣ ስርዓቶች፣ እና በረከቶች ስንማር የመንፈስ ቅዱስ እርዳታን ለማግኘት እጸልያለሁ።

የኤልያስ መመለስ

የምጀምረውም መሰረታዊ ጥያቄን በመጠየቅ ነው፥ የኤልያስ መመለስ ለምን አስፈላጊ ነበር?

“በኋለኛው ቀን ራዕይ ኤልያስ የመልከ ጸዲቅ ክህነት የማሰር ሀይል እንዳለው ተምረናል”6 እና “እርሱም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጊዜ በፊት ይህም የነበረው የመጨረሻ ነቢይ ነበር።”7

ነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ እንደገለጸው፣ “የኤልያስ መንፈስ፣ ሀይል፣ እና ጥሪም፣ … የመልከ ጼዴቅ ክህነት ሙላት …  ቁልፍን ለመያዝ እናም በእግዚአብሔር መንግስት ውስጥ መገኘት የሚገባቸውን ስርዓቶች በሙሉ፣ እንዲሁም ለአባቶች የተገባውን የተስፋ ቃል በልጆች ልብ መተካትን፣ እናም የልጆቹም ልብ ወደ አባቶቻቸው መመለስን፣ … የማግኘት … ሀይልን መያዣ ቁልፍ እንዳላችሁ ነው።”8

ይህም ቅዱስ የማተም ስልጣን አስፈላጊ የሆነው “በምድር የምታስረው ሁሉ በሰማያት የታሰረ [እንዲሆን]፣ እና በምድርም የምትፈታው ሁሉ በሰማያት የተፈታ [እንዲሆን]”9ነው።

ጆሴፍም እንዲህ አብራራ፣ “ይህን ትውልድ ለማዳን እግዚአብሔር እንዴት ይመጣል? እርሱም ነቢዩ ኤልያስን ይልካል። … ኤልያስም የአባቶችን ልብ ከልጆች ጋር፣ እናም የልጆችን ከአባቶች ጋር የሚተሳሰርበትን ቃል ኪዳን ይገልጻል።”10

ኤልያስ በመለወጫ ተራራ ላይ ከሙሴ ጋር መጣ እናም ይህን ስልጣን ለጴጥሮስ፣ ለያዕቆብ፣ እና ለዮሀንስ ሰጣችው።11 ኤልያስም በሚያዝያ 3 ቀን 1836 (እ.አ.አ) በከርትላንድ ቤተመቅደስ ውስጥ ከሙሴ ጋር መጣ እናም ያን አይነት የክህነት ቁልፍ ለጆሴፍ ስሚዝ እና ለኦሊቨር ካውደሪ ሰጠ።12

በ1836 (እ.አ.አ) የማተም ስልጣን በኤልያስ በዳግም መመለሱ አለም ለአዳኝ ዳግም መመለስ ለመዘጋጀት እና ታላቅ የሆነ እና አለም አቀፋዊ የቤተሰብ ታሪክ ምርምር ፍላጎትን ለማነሳሳት አስፈላጊ ነበር።

ልብን መቀየር፣ መመለስ፣ እናም ማጥራት

ልብ የሚባለው ቃል በመደበኛ ስራዎች ውስጥ ከ1 ሺህ በላይ ለሚሆን ጊዜ ጥቅም ላይ ውሏል። ይህም ቀላል ግን ታላቅ የሆነ ቃል የግለሰብን ውስጣዊ ሥሜት የሚጠቁም ነው። የፍላጎታችን፣ የፍቅራችን፣ አላማችን፣ ምክንያታችን፣ እና ጠባያችን ሙላት የሆነው ልባችን ማን እንደሆንን ያስረዳናል እናም ምን እንደምንሆን ይወስናል። የጌታ ስራ ምንነት በወንጌል ቃል ኪዳኖች እና በክህነት ስርዓቶች በኩል መለወጥ፣ መቀልበስ፣ እና ልብን ማንጻት ነው።

ቅዱስ ቤተመቅደሶችን የምንገነባው ወይም የምንገባባቸው ማስታወሻ የሚሆን የግል ወይም የቤተሰብ ልምምዶችን ለማግኘት ብቻ አይደለም። ግን፣ በቤተመቅደስ ውስጥ የምንቀበላቸው ቃል ኪዳኖች እና የሚከናወኑት ስርዓቶች ልባችንን ለማፅዳት እናም ለእግዚአብሔር ወንድ እና ሴት ልጆች መጨረሻ ዘለአለማዊ ክብር አስፈላጊ ናቸው።

የቤተሰብ ታሪክን ምርምር በማከናወን፣ የልጆችን ልቦች ወደ አባቶች በመመለስ፣ በልጆች ልብ ውስጥ የአባቶች፣ እንዲሁም ለአብርሐም፣ ለይስሐቅ፣ እና ለያዕቆብ፣ የተገባን ቃል ኪዳን መትከል፣ እና በወኪልነት የቤተመቅደስ ስርዓቶችን መፈጸም በመጋረጃው ሁለት በኩል ግለሰቦችን የሚባርኩ ስራዎች ናቸው። በዚህ ስራ በቅንነት ስንሳተፍ፣ እግዚአብሔርን እና ጎረቤቶቻችንን የማፍቀር እና የማገልገል ትእዛዛትን ማክበራችን ነው።13 እናም እንዲህ አይነት አገልግሎት በእውነትም “እንድንሰማው!”14 እና ወደ አዳኝ እንድንመጣ15ይረዳናል።

ከሁሉም በላይ ቅዱስ የሆኑት ቃል ኪዳኖች እና የክህነት ስርዓቶች ለመቀበል የሚቻሉት በቤተመቅደስ—በጌታ ቤት፣ ውስጥ ነው። በቤተመቅደስ ውስጥ የምንማረው እና የምናደርጋቸው ሁሉም ነገሮች የኢየሱስ ክርስቶስን መለኮታዊነት እና በሰማይ አባት ታላቅ የደስታ እቅድ የእርሱን ክፍል ያጎላሉ።

ከውስጥ ወደ ውጪ

ፕሬዘደንት እዝራ ታፍት ቤንሰን “የሰውን ህያውነትና ዘለአለማዊ ህይወትን ለማምጣት”16አዳኝ የሚጠቀመውን አስፈላጊ ንድፍ ገልጸዋል። እንዲህም አሉ፣ “ጌታ የሚሰራው ከውስጥ ወደ ውጪ ነው።. አለም የሚሰራው ከውጪ ወደ ውስጥ ነው። አለም ሰውን ከቆሻሻው ስፍራ ያወጣል። ክርስቶስ ቆሻሻ ስፍራን ከህዝብ ያወጣል፣ እና ከዚያም ራሳቸውን ከቆሻሻ ስፍራ ውስጥ ያወጣሉ። አለም ሰዎችን አካባቢያቸውን በመቀየር ይቀርጻል። ክርስቶስም ሰዎች ይቀይራል፣ ከዚያ እነርሱም አካባቢያቸውን ይቀይራሉ። አለም የሰው ባህርይን ይቀርጻል፣ ነገር ግን ክርስቶስ የሰውን ፍጥረት ይቀይራል።”17

ቃል ኪዳኖች እና የክህነት ስርዓቶች ሁልጊዜም በሚቀጥለው መንፈሳዊ ለውጥ እና ዳግም መወለድ ሂደት ዋና ክፍል ናቸው፤ እነርሱም ጌታ ከእያንዳንዳችን ጋር ከውስጥ ወደ ውጪየሚሰራባቸው መንገድ ናቸው። በፅናት የሚከበሩ፣ ሁልጊዜ የሚታወሱ፣ እና “በሕያው እግዚአብሔር መንፈስ … ሥጋ በሆነ በልብ ታቦት”18 የተጻፉ ቃል ኪዳኖች፣ አላማን እና በስጋዊነት እና ዘለአለማዊ በረከቶችን ማረጋገጫ ይሰጣሉ። በብቁነት የተቀበሉ እና የሚታወሱ ስርዓቶች አምላካዊ ሀይል ወደ ህይወታችን የሚያመጣውን የሰማይ መንገድ በዘላቂነት ይከፍታሉ።

ወደ ቤተመቅደስ የምንመጣው ከአለም ክፉዎች ለመደበቅ ወይም ለማምለጥ አይደለም። ነገር ግን፣ ወደ ቤተመቅደስ የምንመጣው የአለም ክፉን ለማሸነፍ ነው። የክህነት ስርአቶችን በመቀበል እና ቅዱስ ቃል ኪዳኖችን በመጠበቅ ወደ ህይወታችን “የአምላክ አይነት ሀይልን”19 ስንጋብዝ፣ የስጋዊነት ፈተናዎችን እና ችግሮችን እንዲሁም መልካምን ለመስራት እና ለመሆን ከራሳችን በላይ በሆነ ጥንካሬ20 እንባረካለን።

የዚህ ቤት ታዋቂነት ይስፋፋል

የዚህ ዘመን የመጀመሪያው ቤተመቅደስ የተገነባው በከርትላንድ፣ ኦሀዮ ነበር እናም የተቀደሰውም በመጋቢት 27 ቀን 1836 (እ.አ.አ) ነበር።

ከተቀደሰ አንድ ሳምንት በኋላ ለነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ በተሰጠው ራዕይ ውስጥ፣ ጌታ እንዳወጀው፣

“በሀይላቸው ይህን ቤት ለስሜ የገነቡት ህዝቦቼ ልብ ይደሰት።

“አዎን፣ በሚፈሱት በረከቶች እና አገልጋዮቼ በዚህ ቤት ውስጥ በተቀበሉት መንፈሳዊ ስጦታዎች ምክንያት የሺዎች እና የአስር ሺዎች ልብ በእጅጉ ይደሰታሉ።

“እና የዚህ ቤት ዝናም በውጪ አገሮች ይስፋፋል፤ እና ይህም በህዝቤ ራሶች ላይ የሚፈሰው የበረከት መጀመሪያም ነው።”21

እባካችሁ የሺዎች እና የአስር ሺዎች ልብ በእጅጉ ይደሰታሉ እና የዚህ ቤት ዝናም በውጪ አገሮች ይስፋፋልየሚሉትን ሀረጎች ላይ ትኩረት አድርጉ። በ1836 (እ.አ.አ) ቤተክርስቲያኗ ትንሽ አባላት እና አንድ ቤተመቅደስ በሚኖርባት ጊዜ እነዚህ አዋጆች አስደናቂ ነበሩ።

ዛሬ በ2020 (እ.አ.አ) 168 አገልግሎት እየሰጡ ያሉ ቤተመቅደሶች አሉን። 49 ተጨማሪ ቤተመቅደሶች እየተገነቡ ናቸው ወይም እንደሚገነቡ ማስታወቂያ ተሰጥቷል። የጌታ ቤት “በባህር ደሴቶች”22 ላይ እናም ከዚህ በፊት ለቤተመቅደስ ብቁ ይሆናሉ ተብሎ በማይገመትባቸው አገሮችና ቦታዎች ላይ እየተገነቡ ናቸው።

አሁን የቤተመቅደስ ቡራኬ ስርዓቶች በ88 ቋንቋዎች ይገኛሉ እናም ብዙ የእግዚአብሐርን ልጆችን ለመባረክ ቤተመቅደሶች ሲገነቡም ተጨማሪ ብዙ ቋንቋዎችም ይገኛሉ። በሚቀጥለው 15 አመት፣ የቤተመቅደስ ስርዓቶች የሚገኙባቸው ተጨማሪ ቋንቋዎች በእጥፍ ያድጋሉ።

በዚህ አመት የ18 ቤተመቅደሶችን ግንባታ እንጀምራለን። በንፅፅርም፣ ከቤተክርስቲያኗ በ1830 (እ.አ.አ) ከመደራጀቷ ጀምሮ የቶክዮ ጃፓን ቤተመቅደስ በ1980 (እ.አ.አ) በፕሬዘደንት ስፔንሰር ደብሊው. ኪምባል እስከተቀደሰ ጊዜ ድረስ፣ 18 ቤተመቅደሶችን ለመገንባት 150 አመት ፈጅቶ ነበር።

ምስል
ስድስት ቤተ መቅደሶች

በፕሬዘደንት ራስል ኤም. ኔልሰን ህይወት ውስጥ ስለነበረው የቤተመቅደስ ስራ ፍጥነት አስቡ። ፕሬዘደንት ኔልሰን በመስከረም 9 ቀን 1924 (እ.አ.አ) በተወለዱበት ጊዜ፣ ቤተክርስቲያኗ አገልግሎት እየሰጡ የነበሩ ስድስት ቤተመቅደሶች ነበሩ።

ምስል
26 ቤተ መቅደሶች

ከ60 አመታት በኋላ፣ በሚያዝያ 7 ቀን 1984 (እ.አ.አ) እንደ ሐዋሪያ ሲሾሙም፣ 26 ቤተመቅደሶች በአገልግሎት ላይ ነበሩ፣ ይህም በ60 አመት የ20 ቤተመቅደሶች እድገት ነበር ማለት ነው።

ምስል
159 ቤተ መቅደሶች

ፕሬዘደንት ኔልሰን እንደ ቤተክርስቲያኗ ፕሬዘደንት የድጋፍ ድምጽ በተሰጣችው ጊዜም፣ 159 ቤተመቅደሶች በአገልግሎት ላይ ነበሩ፣ ይህም የአስራ ሁለቱ ሐዋሪያት ምልዓተ ጉባኤ አባል ሆነው ባገለገሉበት 34 አራት አመታት ውስጥ የ133 ቤተመቅደሶች እድገት ማለት ነው።

ምስል
በአገልግሎት ላይ ያሉ እና የተተዋወቁ ቤተ መቅደሶች

በጥር 14 ቀን 2018 (እ.አ.አ) የቤተክርስቲያኗ ፕሬዘደንት ከሆኑ በኋላ፣ ፕሬዘደንት ኔልሰን 35 አዳዲስ ቤተመቅደሶች እንደሚገነቡ አስታውቀዋል።

አሁን ከሚገኙት ቤተመቅደሶች ዘጠና ስድስት ከመቶ የሚሆኑት የተቀደሱት በፕሬዘደንት ኔልሰን ህይወት ጊዜ ውስጥ ነበር፣ ሰማንያ አራት ከመቶ የሚሆኑትም የተቀደሱት እንደ ሐዋሪያ ከተሾሙ በኋላ ነበር።

ከሁሉም በላይ አስፈላጊ በሆኑት ላይ ሁልጊዜም አተኩሩ

በዳግም እንደተመለሰችው የጌታ ቤተክርስቲያን አባላት፣ በኋለኛው ቀናት ላይ ስራው በተፋጠነ እርምጃ እንዴት እንደሚሄድ በመመልከት እንደነቃለን። ተጨማሪ ቤተመቅደሶችም እየመጡ ናቸው።

ብሪገም ያንግ የተስፋ ቃል እንደሰጡት፣ “ይህን ስራ ለማከናወን አንድ ብቻ ሳይሆን ብዙ ሺህ ቤተመቅደሶች ያስፈልጋሉ፣ እናም ሺህ ወይም አስር ሺህ ወንዶች እና ሴቶች ወደእነዚያ ቤተመቅደሶች ይሄዳሉ እናም ጌታ እስከሚገልጽ ድረስ ሊኖሩ ለነበሩትም በውክልነት ያገለግላሉ።”23

በሚገባም ሁኔታ፣ የአዲስ ቤተመቅደስ መገንባት ማስተዋወቅ የታላቅ ደስታ ምንጭ እና ጌታን ምስጋና የምንሰጥበት ምክንያት ነው። ይህም ቢሆን፣ ዋናው ትኩረታችን በቦታው የትነት ወይም ውበት ላይ ብቻ ሳይሆን ልባችንን ለመቀየር እና ለአዳኝ ያለንን አምልኮ ጥልቅ ለማድረግ በሚችሉት ቃል ኪዳኖች እና ስርዓቶች ላይ መሆን ይገባዋል።

በዳግም እንደተመለሰችው የጌታ ቤተክርስቲያን አባላት መሰረታዊ ግዴታችንም (1) “እርሱን ለማድመጥ!”24 እና በቃል ኪዳኖችና ስነስርዓቶች በኩል ልባችንን ማስቀየር፣ እናም (2) በመጋረጃው ሁለት በኩል ለሚገኙት የሰው ዘር በሙሉ በመለኮት የተመደበውን የቤተመቅደስ በረከቶች የማቅረብ ሀላፊነት በደስታ ማሟላት ነው። በእርሱ መመሪያ እና እርዳታ እነዚህን ቅዱስ ሀላፊነቶች ለማሟላት እንችላለን።

ፅዮንን መገንባት

ነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ አወጀ፤

“የጽዮን መገንባት በየዘመናቱ የእግዚአብሔር ህዝብን ፍላጎት ያነሳሳ ጉዳይ ነው፤ ይህ ነብይ፣ ቀሳውስት እና ነገሥታት ልዩ በሆነ አስደሳችነት የኖሩበት መሪ ሃሳብ ነው፤ እኛ የምንኖርበትን ቀን በጉጉት እየተጠባበቁ ነበር፤ እናም በሰማያዊ እና በደስታ ሙሉ ጥበቃ ተሞልተው ስለዚህ ቀናችን ዘምረዋል እናም ተንብየዋል፤ ነገር ግን ሳያዩት ሞተዋል፤ … ይህም የኋለኛው ቀን ግርማን ለመመልከት፣ በጉጉት ለመጠበቅ እና ወደፊት ለመግፋት ለመርዳት ለእኛ ተትቷል። “25

“ሰማያዊ ክህነትም ከምድራዊው ጋር እነዚህን ታላቅ አላማዎችን ለማሟላት ይጋራል፤ … ያም እግዚአብሔር እና መላዕክት ባለፉት ትውልዶች በደስታ ይጠብቁት የነበረ ስራ ነው፤ … የጥንት ቅድመ አባቶችን እና ነቢያትን ነፍሳት ያነሳሳ፤ የጨለማን ሀይል ለማፍረስ፣ ምድርን ለማሳደስ፣ ለእግዚአብሔርም ክብርን ለመስጠት፣ እና የሰው ቤተሰብ ደህንነት ለመሆን እጣ ፈንታ የነበረውም ስራ ነበር።”

አብ እና ወልድ ወደ ጆሴፍ ስሚዝ እንደመጡ እና ኤልያስ የማተም ስልጣንን በዳግም እንደመለሰ እመሰክራለሁ። ቅዱስ የቤተመቅደስ ቃል ኪዳኖች እና ስርዓቶች “እርሱን እንድናዳምጥ!”27 እኛን ያጠናክሩናል እናም ልባችንን ያነጻሉ እናም የአምላክነት ሀይልንም በህይወታችን ውስጥ እንቀበላለን። ይህ የኋለኛው ቀን ስራ የጭለማን ሀይል እንደሚያጠፋ እና የሰው ቤተሰብን ደህንነት እንደሚያመጣ እመሰክራለሁ። ስለእነዚህ እውነቶች የምመሰክረው በጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ስም ነው፣ አሜን።