ከመፅሐፈ ሙሴ
የተመረጡ ምንባቦች
ከመፅሐፍ ቅዱስ ትርጓሜ ውስጥ ልዩ እትም፣ ከሰኔ ፲፰፻፴–የካቲት ፲፰፻፴፩ (እ.አ.አ.)፣ ለነብዩ ጆሴፍ ስሚዝ እንደተገለጡለት።
ምእራፍ ፩
[ሰኔ ፲፰፻፴ (እ.አ.አ.)]
እግዚአብሔር እራሱን ለሙሴ ገለጠ—ሙሴ ተለወጠ—እርሱም ከሰይጣን ጋር ፊት ለፊት ተጋፈጠ—ሙሴ ብዙ ሰው የሚኖርባቸው አለማትን አየ—ቁጥራቸው ታላቅ የሆኑ አለማት በወልድ ተፈጥረው ነበር—የእግዚአብሔር ስራና ክብር የሰውን ህያውነትና ዘለአለማዊ ህይወትን ማምጣት ነው።
፩ ሙሴ እጅግ በጣም ከፍ ያለ ተራራ ላይ በተነጠቀበት ጊዜ እርሱ ለሙሴ የተናገራቸው የእግዚአብሔር ቃላት፣
፪ እናም እርሱም እግዚአብሔርን ፊት ለፊት አየው፣ እናም ከእርሱም ጋር ተነጋገረ፣ እናም የእግዚአብሔር ክብርም በሙሴ ላይ ነበር፤ በዚህ ምክንያትም ሙሴ በእርሱ ፊት ለመፅናት ችሏል።
፫ እና እግዚአብሔርም ለሙሴ እንዲህ አለው፥ እነሆ፣ እኔ ሁሉን የሚገዛ ጌታ እግዚአብሔር ነኝ፣ እናም መጨረሻ የሌለውም ስሜ ነው፤ ለቀናቶቼ መጀመሪያ እና ለአመታቴም ፍጻሜ የለኝምና፤ እና ይህስ መጨረሻ የለውም አይደለምን?
፬ እናም እነሆ፣ አንተ ልጄ ነህ፤ ስለዚህ ተመልከት፣ እናም የእጄን ስራ አሳይሀለሁኝ፤ ነገር ግን ሁሉንም አይደለም፣ ስራዎቼ መጨረሻ የላቸውም፣ እና ቃላቶቼም፣ በምንም አያልቁምና።
፭ ስለዚህ የእኔን ክብር ካላየ በስተቀር ማንም ሰው ሁሉንም ስራዎቼን ማየት አይችልም፤ እናም ማንም ሰው የእኔን ክብር ሙላት አይቶ፣ እና በምድር ላይ በስጋው ለመቅረት አይችልም።
፮ ልጄ ሙሴ፣ የምትሰራልኝ ስራ አለኝ፤ እና አንተም በአንድያ ልጄ አምሳል ነህ፤ እናም አንድያ ልጄም አዳኝ ነው ይሆናልም፣ በጸጋና በእውነት ተሞልቷልና፤ ነገር ግን ከእኔ ሌላ ምንም አምላክ የለም፣ እና ሁሉም ነገሮች እኔ ዘንድ አሉ፣ ሁሉንም ነገሮች አውቃቸዋለሁና።
፯ አሁንም እነሆ፣ ልጄ ሙሴ ይህን አንድ ነገር አሳይሀለሁ፣ በአለም ውስጥ ነህና፣ እናም ለአንተም ይህን አሳይሀለሁኝ።
፰ እናም እንዲህ ሆነ፣ ሙሴም ተመለከተ፣ እና የተፈጠረበትን አለም ተመለከተ፤ እናም ሙሴም አለምንና የአለምን፣ እና የአሁን እና ተፈጥረው የነበሩትን የሰዎች ልጆችን መጨረሻ ተመለከተ፣ በእነዚህም በጣም ተደነቀ እናም ተገረመ።
፱ እና እግዚአብሔርም ከሙሴ ፊት ሄደ፣ ክብሩም በሙሴ ላይ አልነበረም፤ እና ሙሴንም ለብቻው ተትቶ ነበር። እና ለብቻው ሲተውም፣ ወደ ምድር ወደቀ።
፲ እንዲህም ሆነ፣ ከብዙ ሰአታት በኋላ ነበር የሙሴ ተሰጥኦ ጥንካሬው እንደሰው ተመልሶ የመጣለት፤ እናም ለእራሱም እንዲህ አለ፥ አሁን፣ በዚህ ምክንያት ከዚህ በፊት እንዳላሰብኩት ሰው ምንም እንዳልሆነ አወቅሁኝ።
፲፩ ነገር ግን አሁን አይኖቼ እግዚአብሔርን አይተዋል፤ ነገር ግን በተሰጥኦ አይኖቼ ሳይሆን በመንፈሳዊ አይኖቼ ነው፣ የተሰጥኦ አይኖቼ ሊያዩት አይችሉምና፤ በእርሱ ፊት ስቆምም ጠውልጌ እና እሞት ነበርና፤ ነገር ግን ክብሩ በእኔ ላይ ነበር፤ እና ፊቱን አየሁ፣ በእርሱ ፊት ተለውጬ ነበርና።
፲፪ እንዲህም ሆነ ሙሴም እነዚህን ቃላት ሲናገር፣ እነሆ፣ ሰይጣን ሊፈትነው እንዲህ በማለት መጣ፥ የሰው ልጅ ሙሴ ሆይ፣ አምልከኝ።
፲፫ እናም እንዲህ ሆነ፣ ሙሴም ሰይጣንን ተመለከተው እና አለ፤ ማን ነህ? እነሆ፣ እኔ በአንድያ ልጅ አምሳል የሆንኩት የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ፤ እናም አመልክህስ ዘንድ ክብርህ የት አለ?
፲፬ እነሆ፣ ክብሩ በእኔ ላይ ካልሆነና በፊቱ ካልተለወጥኩኝ በስተቀር እግዚአብሔርን ማየት አልችልም። ነገር ግን በተፈጥሮአዊው ሰውነቴ አንተን ማየት እችላለሁኝ። በርግጥ፣ ይህ እውነት አይደለም?
፲፭ የአምላኬ ስም የተባረከ ይሁን፣ የእርሱ መንፈስ ከእኔ ሙሉ አልተገለለምና፣ ወይም ክብርህ የት ነው፣ ይህም ለእኔ ጭለማ ነውና? እናም በአንተና በእግዚአብሔር መካከል መፍረድ እችላለሁ፤ እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝና፥ እግዚአብሔርን አምልክ፣ እርሱንም ብቻ አገልግል።
፲፮ ከዚህ ሂድ፣ አንተ ሰይጣን፤ አታታልለኝ፤ እግዚአብሔርም እንዲህ ብሎኛልና፥ አንተ በአንድያ ልጄ አምሳል ነህ።
፲፯ ከሚነደው ጥሻ ውስጥም በጠራኝ ጊዜ ትእዛዛትንም ደግሞ እንዲህ በማለት ሰጥቶኛል፥ አምላክህን በአንድያ ልጄ ስም ጥራ፣ እናም አምልከኝ።
፲፰ ደግሞም ሙሴ አለ፥ ሌላ የምጠይቀው ነገሮች ስላሉኝ፣ እግዚአብሔርን መጥራት አላቆምም፥ ክብሩ በእኔ ላይ ነበርና፣ ስለዚህ በአንተና በእርሱ መካከል መፍረድ እችላለሁ። ከዚህ ሂድ፣ ሰይጣን።
፲፱ አሁንም፣ እነዚህን ቃላት ሙሴ ሲናገር፣ ሰይጣን በታላቅ ድምፅ ጮኸ፣ እናም በምድርም ላይ እየጮኸ ተናገረ፣ እናም እንዲህ በማለት አዘዘ፥ እኔ አንድያ ልጅ ነኝ፣ አምልከኝ።
፳ እንዲህም ሆነ ሙሴም በጣም መፍራት ጀመረ፤ እናም ሲፈራም፣ የሲኦልን መራራነትን አየ። ይህም ቢሆን እግዚአብሔርን በመጥራት ጥንካሬን ተቀበለ፣ እና እንዲህም በማለት አዘዘ፥ ሰይጣን ከእኔ ዘንድ ሂድ፣ የክብር አምላክ የሆነውን ይህን አንድ እግዚአብሔርን ብቻ አመልካለሁና።
፳፩ አሁንምሰይጣን መንቀጥቀጥ ጀመረ፣ እናም ምድርም ተንቀጠቀጠች፤ እናም ሙሴም ጥንካሬን ተቀበለ፣ እና እንዲህም በማለት እግዚአብሔርን ጠራ፥ ሰይጣን፣ በአንድያ ልጅ ስም፣ ከዚህ ሂድ።
፳፪ እንዲህም ሆነ ሰይጣን በታላቅ ድምጽ በማልቀስና በመጮኽ፣ እናም በጥርስ ማፏጨት አነባ፤ እናም ከዚያ እንዲሁም ከሙሴ ዘንድም ሄደ ሙሴም አላየውም።
፳፫ አሁንም ስለነዚህ ነገሮች ሙሴ ምስክርነትን ሰጠ፤ ነገር ግን በተንኮል ምክንያት ይህ በሰው ልጆች መካከል አልተገኘም።
፳፬ እንዲህም ሆነ ሰይጣን ከሙሴ ፊት ሲሄድ፣ ሰለአብና ወልድ ምስክር በሚሰጠው መንፈስ ቅዱስ በመሞላት፣ ሙሴ አይኑን ወደሰማይ አነሳ፤
፳፭ እና የእግዚአብሔርን ስም በመጥራት የእርሱን ክብር እንደገና አየ፣ ይህም በእርሱ ላይ አርፎ ነበርና፤ እና እንዲህም የሚል ድምፅንም ሰማ፥ ሙሴ የተባረክ ነህ፣ እኔ፣ ሁሉን የሚገዛው፣ መርጬሀለሁና፣ እና ከብዙ ውሀዎች በላይ ጠንካራ ትሆናለህ፣ እንደ አምላክ እንደሆንክ አይነት ትእዛዝህን ያከብሩታልና።
፳፮ እናም አስተውል፣ እስከመጨረሻዎቹ ቀናትህም ድረስ እኔ ከአንተ ጋር ነኝ፤ አንተ ህዝቤን፣ እንዲሁም የተመረጠውን እስራኤልን፣ ከባርነት ቀንበር ታድናቸዋለህና።
፳፯ እንዲህም ሆነ ድምጹም እየተናገረ እያለ፣ ሙሴ አይኑን ዞር ዞር አደረገ እና ምድርን፣ አዎን ሁሉንም፣ አየ፤ እና በእግዚአብሔር መንፈስ ለይቶ በማወቅም ያላየው አንድ የመጨረሻ ትንሽ መጠንም አልነበረም።
፳፰ እናም በዚያ ነዋሪዎችንም ደግሞ አየ፣ እና ያላየው አንድም ነፍስ አልነበረም፤ እና እነርሱንም በእግዚአብሔር መንፈስ ለይቶ አወቃቸው፤ እናም ቁጥራቸውም ታላቅ፣ እንዲሁም እንደ ባህር ዳርቻ እንደሚገኙ አሸዋ ተቆጥረው አያልቁም ነበር።
፳፱ እና ብዙ መሬቶችንም አየ፤ እና እያንዳንዱም መሬት ምድር ተብለው ተጠርተው ነበር፣ እናም በእነዚህ ላይ ነዋሪዎች ነበሩ።
፴ እንዲህም ሆነ ሙሴም እንዲህ በማለት እግዚአብሔርን ጠራ፥ እባክህ ንገረኝ፣ እንዴት እነዚህ ነገሮች እንዲህ ሆኑ እናም በምን እነዚህን ሰራሀቸው?
፴፩ እናም እነሆ፣ የጌታ ክብር በሙሴ ላይ አርፎ ነበር፣ ስለዚህ ሙሴ በእግዚአብሔር ፊት ቆመ፣ እና ከእርሱም ጋር ፊት ለፊት ተነጋገረ። እናም ጌታ አምላክ ለሙሴ እንዲህ አለው፤ በራሴ አላማ እነዚህን ነገሮች ሰርቼአለሁ። ይህም ጥበብ ነው እናም ይህም በእኔ ዘንድ ይቀራል።
፴፪ እና በሀይሌ ቃልም፣ እንዲሁም በጸጋና በእውነት በተሞላው አንድያ ልጄ እነዚህን ፈጠርኩኝ።
፴፫ እና ለመቁጠር የማይቻል አለማትንም ፈጠርኩኝ፤ እና የፈጠርኳቸውም ለራሴ አላማ ነው፤ እና አንድያ ልጄ በሆነው ወልድም እነዚህን ፈጠርኳቸው።
፴፬ ከሁሉም የመጀመሪያ ሰውንም በትርጉም ብዙ የሚባለውን አዳም ብዬ ጠራሁት።
፴፭ ነገር ግን ስለዚህ ምድርና በዚህ ስለሚኖሩት ታሪክ ብቻ ነው የምሰጥህ። እነሆ፣ በሀይሌ ቃል ያለፉ ብዙ አለማት አሉ። እና አሁን የሚኖሩ ብዙዎችም አሉ፣ እና በሰው ለመቆጠር የሚያዳግቱ ናቸው፤ ነገር ግን ሁሉም ነገሮች በእኔ የሚቆጠሩ ናቸው፣ የእኔ ናቸው እና አውቃቸዋለሁና።
፴፮ እንዲህም ሆነ ሙሴ ለጌታ እንዲህ ብሎ ተናገረ፥ እግዚአብሔር ሆይ፣ ለአገልጋይህ ርህራሄ ይሰማህ፣ እና ስለዚህ ምድርና ኗሪዎቿ እናም ስለሰማያት ንገረኝ፣ ከዚያም አገልጋይህ ይረካል።
፴፯ እናም ጌታ እግዚአብሔር ለሙሴ እንዲህ ሲል ተናገረ፣ ሰማያት፣ እነርሱም ብዙ ናቸው፣ እና በሰው ሊቆጠሩም አይችሉም፤ ነገር ግን በእኔ ይቆጠራሉ፣ የእኔ ናቸውና።
፴፰ እና አንድ ምድር ስታልፍ፣ እና የዚያም ሰማያት እንዲሁም ሌላ ይመጣል፤ እናም ለስራዬ እና ለቃላቶቼ ምንም መጨረሻ የላቸውም።
፴፱ እነሆ፣ የሰውን ህያውነት እና ዘለአለማዊ ህይወት ማምጣት ስራዬ እና ክብሬ ይህ ነው።
፵ አሁንም፣ ልጄ ሙሴ፣ ስለቆምክባት ምድር በሚመለከት እነግርሀለሁ፤ እና የምናገራቸውንም ነገሮች ጻፍ።
፵፩ እናም የሰው ልጆች ቃላቴን እንደማይረባ በሚመለከቱበትና ከጻፍካቸው ውስጥ ብዙ ቃላትን በሚያወጡበት ጊዜ፣ እነሆ፣ እንደ አንተ አይነት ሌላንም አስነሳለሁ፤ እና እነዚህም ከሚያምኑት ሰው ልጆች ጋር ሁሉ መካከል እንደገና ይገኛሉ።
፵፪ (እነዚህ ቃላት ለሙሴ የተነገሩትም በተራራ ላይ ነው፣ የዚህም ስም በሰዎች ልጆች አይታወቅም። አሁንም እነዚህ ለእናንተም ተነግረዋል። ከሚያምኑት ሌላ በስተቀር ለማንም አታሳይ። እንዲህም ይሁን። አሜን።)