ምዕራፍ ፲፯
ኢየሱስ ህዝቡ ስለቃሉ እንዲያገናዝቡ እናም እንዲፀልዩ አዘዘ—በሽተኞቻቸውን ፈወሰ—ለመፃፍ በማይቻል ቋንቋ ስለህዝቡ ፀለየ—ህፃናቶቻቸውን መላዕክት አስተማሩአቸው እናም በእሳት ተከበቡ። ፴፬ ዓ.ም. ገደማ።
፩ እነሆ፣ እንግዲህ እንዲህ ሆነ ኢየሱስ እነዚህን ቃላት በተናገረ ጊዜ ወደ ህዝቡ በድጋሚ ዙሪያውን ተመለከተ፤ እናም እንዲህ ሲል ተናገራቸው፥ እነሆ ጊዜዬ ቀርቦአል።
፪ በዚህ ጊዜ በአባቴ ለእናንተ እንድናገር የታዘዝኩትን ቃሌን በሙሉ ልትረዱ እንደማትችሉ ደካሞች መሆናችሁን አስተውላለሁ።
፫ ስለዚህ፣ ወደቤታችሁ ሂዱና፣ ስለተናገርኳችሁ ነገሮች አሰላስሉ፤ እናም ትረዱና ለሚቀጥለው ቀን አእምሮአችሁን ታዘጋጁ ዘንድ በስሜ አብን ጠይቁት፣ እናም እኔም በድጋሚ እመጣለሁ።
፬ ነገር ግን አሁን ወደ አባቴ፣ እናም ደግሞ ራሴን ለጠፉት የእስራኤል ነገዶች ለማሳየት እሄዳለሁ፤ ምክንያቱም እነርሱ ለአብ አልጠፉምና፣ እርሱም የት እንደወሰዳቸው ያውቃልና።
፭ እናም እንዲህ ሆነ ኢየሱስ እንዲህ በተናገረ ጊዜ፣ ዐይኑን በድጋሚ በህዝቡ ላይ በዙሪያው ያደርግ ነበር፤ እናም እንባ እያነቡ መሆናቸውንና፣ እርሱ ከእነርሱ ጋር ትንሽ እንዲቆይ የሚፈልጉ በመምሰል በእርሱ ላይ ያተኮሩ ይመስሉ እንደነበር ተመለከተ።
፮ እናም እርሱ እንዲህ አላቸው፥ እነሆ፣ ስለእናንተ አንጀቴ በርህራሄ ተሞልቷል።
፯ ከእናንተ መካከል በሽተኞች አሉን? ወደዚህ ስፍራ አምጡአቸው። ከእናንተ መካከል ድውይ፣ ወይንም ዐይነስውር፣ ወይንም ሽባ፣ ወይንም ለምፃም፣ ወይንም ሰውነታቸው የሰለለ፣ ወይንም ደንቆሮ፣ ወይንም በተመሳሳይ የሚሰቃዩ አሉን? ወደ እዚህ ስፍራ አምጡአቸው እናም ለእናንተ ከአንጀቴ ርህራሄ ስላለኝ እፈውሳቸዋለሁ፤ ውስጤም በምህረት ተሞልቷል።
፰ በኢየሩሳሌም ለነበሩት ወንድሞቻችሁ ምን እንዳደረግሁ እንዳሳያችሁ እንደምትፈልጉ እገነዘባለሁ፣ ምክንያቱም እናንተን እንድፈውሳችሁ እምነታችሁ በቂ መሆኑን አይቻለሁና።
፱ እናም እንዲህ ሆነ ይህንን በተናገረ ጊዜ፣ ህዝቡ በሙሉ በአንድ ልብ ከበሽተኞቻቸው፣ እንዲሁም ከሚሰቃዩትና፣ ከሽባዎቹ፣ እናም ከዐይነ ስውሮቹና፣ ከዲዳዎቹና፣ በሁሉም ዐይነት በሽታ ከሚሰቃዩ ሰዎች ጋር ሄዱ፤ እናም ወደ እርሱም በቀረቡ ጊዜ እያንዳንዳቸውን ፈወሳቸው።
፲ እናም እነርሱም በሙሉ፣ የተፈወሱትም ሆኑ ጤነኛዎቹ፣ በእግሩ ስር ሰገዱና፣ አመለኩት፤ እናም በእንባቸው እግሩ እስከሚታጠብ ድረስ ብዙዎች ወደ እርሱ ቀርበው እግሩን ሳሙት።
፲፩ እናም እንዲህ ሆነ ህፃናት ወደ እርሱ እንዲመጡ አዘዘ።
፲፪ ስለዚህ ህፃናት ልጆቻቸውን አመጡና በእርሱ ዙሪያም አስቀመጡአቸው፣ እናም ኢየሱስ በመካከላቸው ቆመ፤ እናም ህፃናት በሙሉም ወደ እርሱ እንዲቀርቡ ህዝቡ ቦታ ለቀቀ።
፲፫ እናም እንዲህ ሆነ ሁሉም በመጡ ጊዜ፣ እናም ኢየሱስ በመካከላቸው በቆመ ጊዜ ህዝቡ በመሬት ላይ እንዲንበረከክ አዘዘ።
፲፬ እናም እንዲህ ሆነ በመሬት ላይ በተንበረከኩም ጊዜ፣ ኢየሱስም በውስጡ እንዲህ ሲል ቃተተ፥ አባት ሆይ የእስራኤል ቤት በሆኑት ሰዎች ኃጢያት አዝኜአለሁ።
፲፭ እናም እነዚህን ቃላት በተናገረ ጊዜ እርሱም ደግሞ በመሬት ላይ ተንበረከከ፤ እናም እነሆ ወደ አብ ፀለየ፣ የፀለየባቸውም ነገሮች ምንም ሊፃፉ አይቻሉም፣ የሰሙትም ሰዎች መስክረዋልም።
፲፮ እናም በዚህም ሁኔታ መስክረዋል፥ ከዚህ በፊት ዐይን ያላየውን፣ ጆሮም ያልሰማውን፤ ኢየሱስ ወደ አብ ሲናገር ያየናቸው እናም የሰማናቸው ነገሮች ታላቅና አስደናቂ ነገሮችን ነው፤
፲፯ እናም አንደበት ሊናገረው አይችልም፣ እንዲሁም በማንም ሰው ሊፃፍ አይችልም፤ ኢየሱስ ሲናገር እኛ እንዳየናቸውና እንደሰማናቸው ያሉ ታላቅና አስደናቂ ነገሮች የሰው ልብ ሊገምተው አይቻለውም፤ እናም ወደ አብ ለእኛ ሲፀልይ በሰማነው ጊዜ ነፍሳችን የተሞላችበትን ዐይነት ደስታ ማንም ሊገምተው አይቻለውም።
፲፰ እናም እንዲህ ሆነ ኢየሱስ ወደ አብ መፀለይን በጨረሰ ጊዜ ተነሳ፤ ነገር ግን የህዝቡ ደስታ ታላቅ ስለነበረ እነደተሸነፉም ሆኑ።
፲፱ እናም እንዲህ ሆነ ኢየሱስ ተናገራቸውና፣ እንዲነሱ አዘዛቸው።
፳ እነርሱም ከመሬቱ ላይ ተነሱ፤ እናም እንዲህ ሲል ተናገራቸው፥ እናንተ በእምነታችሁ የተባረካችሁ ናችሁ። እናም እንግዲህ እነሆ፣ ደስታዬ ሙሉ ነው።
፳፩ እናም እነዚህን ቃላት በተናገረ ጊዜ አለቀሰ፤ ህዝቡም ስለማልቀሱ መሰከሩ፣ አንድ በአንድም ህፃናቶቻቸውን ወሰዳቸውና፣ ባረካቸውም፣ ስለእነርሱም ወደ አብ ፀለየ።
፳፪ እናም ይህንንም ሲያደርግ በድጋሚ አለቀሰ፤
፳፫ እናም ለህዝቡ ተናገረና፣ እንዲህ አላቸው፥ ህፃናቶቻችሁን ተመልከቱ።
፳፬ እናም ለመመልከት ዐይኖቻቸውን በሰማይ ላይ አደረጉና፣ ሰማያት ሲከፈቱ ተመለከቱ፣ እናም መላዕክቱ ልክ በእሳት መካከል እንደሆነ ከሰማይ ሲወርዱ ተመለከቱ፤ እነርሱም ወርደው ህፃናቱን ከበቡአቸው፣ በእሳቱም ተከበቡ፤ እናም መላዕክት አገለገሉአቸው።
፳፭ እናም ህዝቡ ተመለከቱና ሰሙ እናም መሰከሩ፤ ሁሉም እያንዳንዱ ለራሱ ስለተመለከተና ስለሰማ ምስክርነታቸውም እውነት መሆኑን ያውቃሉ፤ እናም በቁጥርም ሁለት ሺህ አምስት መቶ ነፍሳት ገደማ ነበሩ፤ እነርሱም ወንዶች፣ ሴቶችና፣ ህፃናት ነበሩ።