ቅዱሳት መጻህፍት
፫ ኔፊ ፲፬


ምዕራፍ ፲፬

አትፍረዱ፤ እግዚአብሔርን ጠይቁ፤ ከሃሰተኛ ነቢያት ተጠንቀቁ በማለት ኢየሱስ አዘዘ—የአባታቸውን ፈቃድ ለሚያደርጉ የደህንነትን ቃል ገብቶላቸዋል—ማቴዎስ ፯ን አነጻፅሩ። ፴፬ ዓ.ም. ገደማ።

፩ እናም አሁን እንዲህ ሆነ ኢየሱስ እነዚህን ቃላት በተናገረ ጊዜ በድጋሚ ወደ ህዝቡ ተመለሰ፣ እናም በድጋሚ አፉን ከፍቶ እንዲህ አላቸው፥ እውነት፣ እውነት እላችኋለሁ እንዳይፈረድባችሁ አትፍረዱ።

፪ በምትፈርዱበት ፍርድ ይፈረድባችኋልና፤ እናም በምትሰፍሩበትም መስፈሪያ ደግሞም ይሰፈርላችኋል።

፫ እናም በወንድማችሁ ዐይን ያለውን ጉድፍ ስለምን ታያላችሁ፤ ነገር ግን በዐይናችሁ ያለውን ምሰሶ ስለምን አትመለከቱም?

፬ ወይም ወንድማችሁን ከዐይንህ ጉድፍ ላውጣ ፍቀድልኝ እንዴትስ ትሉታላችሁ? እናም እነሆ በዐይናችሁ ምሰሶ አለ።

፭ እናንተ ግብዞች አስቀድማችሁ በዐይናችሁ ያለውን ምሰሶ አውጡ፤ እናም ከዚያም በኋላ ከወንድማችሁ ዐይን ጉድፉን ታወጡ ዘንድ አጥርታችሁ ታያላችሁ።

፮ በእግራቸው እንዳይረግጡት ተመልሰውም እንዳይነክሱአችሁ የተቀደሰውን ለውሾች አትስጡ፤ ዕንቁዎቻችሁንም በእሪያዎች ፊት አትጣሉ።

፯ ለምኑ፣ ይሰጣችኋል፤ ፈልጉ፣ ታገኛላችሁ፤ አንኳኩ፣ ይከፈትላችኋል።

፰ የሚለምን ሁሉ ይቀበላልና፣ እናም የሚፈልግም ያገኛል፤ እናም ለሚያንኳኩ ይከፈትላቸዋል።

፱ ወይም ከእናንተ ልጁ ዳቦ ቢለምነው ድንጋይ የሚሰጠው ማነው?

፲ ወይም ዓሳስ ቢለምነው እባብ ይሰጠዋልን?

፲፩ እናንተ ክፉዎች ስትሆኑ፣ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታ መስጠትን ካወቃችሁ፣ በሰማያት ያለው አባታችሁ ለሚለምኑት እንዴት አብልጦ መልካም ነገርን ይሰጣቸው?

፲፪ ስለሆነም፣ ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትወዱትን ሁሉ እናንተም ደግሞ እንዲሁ አድርጉላቸው፣ ህግም ነቢያትም ይህ ነውና።

፲፫ በጠበበው ደጅ ግቡ፣ ወደ ጥፋት የሚወስደው ደጅ ሰፊ መንገዱም ትልቅ ነውና፤ ወደ እርሱም የሚገቡ ብዙ ናቸው፤

፲፬ ምክንያቱም ወደ ህይወት የሚወስደው ደጁ የጠበበ፣ መንገዱም የቀጠነ ስለሆነ፣ የሚያገኙትም ጥቂቶች ናቸው።

፲፭ የበግ ለምድ ለብሰው ከሚመጡባችሁ፣ ነገር ግን ውስጣቸው ነጣቂ ተኩላ ከሆኑ ከሀሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ።

፲፮ ከፍሬአቸው ታውቋቸዋላችሁ። ከእሾህ ወይን፣ ወይም ከኩርንችትስ በለስ ይለቀማልን?

፲፯ መልካም ዛፍ ሁሉ መልካም ፍሬን ያፈራል፤ ክፉ ዛፍም መጥፎ ፍሬ ያፈራል።

፲፰ መልካም ዛፍ ክፉ ፍሬ ማፍራት፣ ወይንም ክፉ ዛፍ መልካም ፍሬን ማፍራት አይቻለውም።

፲፱ መልካም ፍሬ የማያደርግ ዛፍ ሁሉ ይቆረጣል፣ ወደ እሳትም ይጣላል።

፳ ስለዚህ፣ ከፍሬአቸው ታውቋቸዋላችሁ።

፳፩ በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ፣ ጌታ ሆይ፣ ጌታ ሆይ የሚለኝ ሁሉ ወደ መንግስተ ሰማያት የሚገባ አይደለም።

፳፪ በዚያ ቀን ብዙዎች ጌታ ሆይ፣ ጌታ ሆይ፣ በስምህ ትንቢትን አልተናገርንምን፣ በስምህስ አጋንንትን አላወጣንምን፣ በስምህስ ብዙ ተአምራትን አላደረግንምን? ይሉኛል።

፳፫ እናም ከቶ አላውቃችሁም፣ እናንተ አመፀኞች፣ ከእኔ ራቁ ብዬ አሳውቃቸዋለሁ።

፳፬ ስለዚህ፣ ይህን ቃሌን ሰምቶ የሚያደርገው ሁሉ፣ ቤቱን በአለት ላይ እንደሰራ እንደ ጠቢብ ሰው አመሳስለዋለሁ—

፳፭ እናም ዝናብ ወረደና፣ የጥፋት ውሀም መጣ፤ እናም ነፋስ ነፈሰና፣ ቤቱን ገፋው፤ እናም በአለትም ላይ ስለተመሰረተ አልወደቀም።

፳፮ እናም ይህንን ቃሌን ሰምቶ የማያደርገው ሁሉ ቤቱን በአሸዋ ላይ እንደሰራ ሰነፍ ሰው ይመሳሰላል—

፳፯ እናም ዝናቡ ወረደና፣ የጥፋት ውሀም መጣ፣ እናም ነፋሱ ነፈሰና፣ ቤቱን ገፋው፤ ወደቀና፣ አወዳደቁም ታላቅ ነበር።