አጠቃላይ ጉባኤ
ሰላማዊ የክርስቶስ ተከታዮች ሁኑ
የጥቅምት 2023 (እ.አ.አ) አጠቃላይ ጉባኤ


ሰላማዊ የክርስቶስ ተከታዮች ሁኑ

“ሰላማዊ የክርስቶስ ተከታዮች” በዚህ ህይወት የግል ሰላምን እንዲሁም በአስደናቂ ሁኔታ በሰማይ እንደገና መገናኘትን እንደሚያገኙ እመሰክርላችኋለሁ።

የምንኖረው “ሰላማዊ የክርስቶስ ተከታዮች”1 የተለዩ ፈተናዎች እያጋጠሟቸው ባለበት ጊዜ ላይ ነው። በኢየሱስ ክርስቶስ የሚያምኑ፣ በትህትና የሚያመልኩት እና ስለእርሱ የሚመሰክሩ ፈተናዎች፣ ሥቃይ እና መከራዎች ሁሌም ያጋጥማቸዋል።2 ባለቤቴ፣ሜሪ፣ እና እኔ ከዚህ የተለየን አይደለንም። ባለፉት ጥቂት አመታት፣ ብዙዎቹን የቅርብ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ጓደኞቻችን፣ የሚስዮን ግጓደኞቻችን፣ አንዳንዶቹ ውድ ባለቤቶቻቸውን፣ እንዲሁም የስራ ባለደረባዎች በህልፈተ ህይወት ሲለዩን ወይም ፕሬዘደንት ራስል ኤም. ኔልሰን እንዳሉት ወደ ሌላኛው የመጋረጃው ወገን ሲሸጋገሩ አይተናል። በእምነት ውስጥ አድገው የነበሩ አንዳንዶች ከቃል ኪዳኑ መንገድ ሲወጡ አይተናል።

በሚያሳዝን ሁኔታ፣ አንድ የ23 ዓመት የልጅ ልጃችን በአሰቃቂ የአንድ መኪና አደጋ ሞተ። አንዳንድ ውድ ጓደኞች፣ የቤተሰብ አባላት እና የስራ ባልደረቦች ጉልህ የጤና ችግሮችን ተቋቁመዋል።

ፈተናዎች በሚከሰቱበት ጊዜ ሁሉ እናዝናለን እንዲሁም አንዳችን የሌላውን ሸክም ለመሸከም እንጥራለን።3 ስለማይከናወኑ ነገሮች እንዲሁም ስለማይዘፈኑ ዘፈኖች እናዝናለን።4 በዚህ ምድራዊ ጉዞ መጥፎ ነገሮች በጥሩ ሰዎች ላይ ይከሰታሉ። ደቡባዊ ቺሊ በምትገኘው ማኡይ እንዲሁም በካናዳ የደረሰው አውዳሚ የእሳት አደጋ አንዳንድ ጊዜ ጥሩ ሰዎች የሚገጥሟቸው አስከፊ ክስተቶች ምሳሌዎች ናቸው።

በታላቅ ዋጋ ዕንቁ ውስጥ ጌታ ስለመንፈስ ዘላለማዊ ተፈጥሮ ለአብርሃም እንደገለፀለት እናነባለን። አብርሃም ስለ ቅድመ-ምድር ህይወታችን፣ አስቀድሞ ስለመሾም፣ ስለፍጥረት፣ አዳኙን ስለመምረጥ እና የሰው ሁለተኛ ሁኔታ ስለሆነው ስለዚህ ምድራዊ ህይወት ተምሯል።5 አዳኙ እንዲህ ሲል ተናግሯል፦

እነዚህ ሊኖሩበት የሚችሉትን ምድርን እንሰራለን፤

“እና ጌታ አምላክ የሚያዛቸውን ማናቸውንም ነገሮች ሁሉ እንደሚያደርጉ ለማየት፣ በዚህ እንፈትናቸዋለን።”6

አሁን ሁላችንም የእግዚአብሔር ታላቅ የደህንነት እና ከፍ ከፍ የመደረግ ዕቅድ ክፍል ወደሆነው የክብር መንግሥት በምናደርገው የማደግ ጉዞ እዚህ በሁለተኛው ሁኔታ ላይ እንገኛለን። በመምረጥ ነፃነት ተባርከናል እንዲሁም ሥጋዊ ፈተናዎች ይገጥሙናል። ይህ ከእግዚአብሔርን ጋር ለመገናኘት እንድንዘጋጅበት የተመደበልን ጊዜ ነው።7 ኢየሱስ ክርስቶስን እና በዕቅዱ ውስጥ ያለውን ሚና በማወቃችን ተባርከናል። ዳግም የተመለሰችው የእርሱ ቤተክርስቲያን—የኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን አባል የመሆን መብት አለን። እንደ ሰላማዊ የክርስቶስ ተከታዮች የእርሱን ትዕዛዛት ለመኖር እንጥራለን። ለእርሱ ተከታዮች ቀላል ሆኖ አያውቅም። ለአዳኙም ቢሆን ምድራዊ ተልዕኮውን በታማኝነት መፈፀም ቀላል አልነበረም።

ቅዱሳት መፃህፍት ይህን በግልፅ ያስቀምጣሉ፦ “ብሉ፣ ጠጡ፣ እናም ተደሰቱ፣ ነገ እንሞታለንና”8 ወደሚለው መንገድ በማዘንበል ለፈተና እድል ፈንታ የሚሰጡ ብዙዎች ይኖራሉ። ሌሎች አማኝ ያልሆኑ ሰዎች “ቀጣዩን አዲስ ግኝት”9 እና የሰዎችን ፍልስፍና የሚከተሉ ተመሳሳይ አመለካከት ባላቸው ራሳቸውን አስፈላጊ በሚያደርጉ ቡድኖች ውስጥ ይወሸቃሉ።10 እውነቱ የት እንደሚገኝ አያውቁም።11

ሰላማዊ የክርስቶስ ተከታዮች ሁለቱንም መንገዶች አይከተሉም። እኛ ቀና እንዲሁም በምንኖርባቸው ማህበረሰቦች ውስጥ የምንሳተፍ አባላት ነን። ሁሉም የእግዚአብሄር ልጆች የክርስቶስን ትምህርቶች እንዲከተሉ እንወዳለን፣ እናካፍላለን እንዲሁም እንጋብዛለን።12 የውድ ነቢያችንን የፕሬዘደንት ኔልሰንን ምክር እንከተላለን፤ አሁንም ሆነ ሁልጊዜ የአስታራቂነት ሚናን እንመርጣለን።13 ይህ በመንፈስ የተነሳሳ አቀራረብ ከቅዱሳት መጻህፍት እና ከነቢያዊ መመሪያ ጋር አብሮ የሚሄድ ነው።

በ1829 (እ.አ.አ) ዳግም የተመለሰችው ቤተክርስቲያን ገና አልተደራጀችም ነበር፤ መጽሐፈ ሞርሞንም አልታተመም ነበር። በእግዚአብሔር መንፈስ የተገፋፉ ጥረት እያደረጉ የነበሩ ትንሽ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ቡድን ነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝን ተከተሉ። ጌታ ለአስቸጋሪ ጊዜያት የሚሆን ምክር ለጆሴፍ ገለጠለት፦ “ስለዚህ፣ አትፍሩ፣ እናንት ትንሽ መንጋዎች፣ መልካምን አድርጉ፤ ምድርና ገሀነም ቢቀናጁባችሁም፣ በእኔ ዓለት ላይ ከተገነባችሁ ሊቋቋሟችሁ አይችሉምና።”14 ደግመውም እንዲህ መከሩ፦

“ባሰባችሁት ነገር ሁሉ ወደ እኔ ተመልከቱ፣ አትጠራጠሩ፣ አትፍሩ፡፡

“እምነት ይኑራችሁ፣ ትእዛዛቴን ጠብቁ፣ እናም መንግስተ ሰማያትን ትወርሳላችሁ።”15

በግልፅ እንደሚታየው፣ ሰማያዊ ፍፃሜያችን በመከራ ስንሰቃይ አይለወጥም። በዕብራውያን መፅሐፍ ውስጥ “ምሕረትን እንድንቀበል በሚያስፈልገንም ጊዜ የሚረዳንን ፀጋ እንድናገኝ ወደ ፀጋው በድፍረት እን[ድን]ቀርብ” ተመክረናል።16 ኢየሱስ ክርስቶስ፣ “የዘላለም መዳን ምክንያት” ነው።17

“ሰላማዊ የክርስቶስ ተከታይ ለሆ[ኑት] የተሰጡትን … ከሰዎች ልጆች ጋር ባላችሁ ሰላማዊ ሂደት ምክንያት”18 የሚሉትን በልጁ ሞሮኒ የተጠቀሰውን የሞርሞን ቃላት እወዳቸዋለሁ።

እኛ በቤተክርስቲያን ሰላማዊ የክርስቶስ ተከታይ ለመሆን የምንጥር ትኩረታችንን በጌታችንና በአዳኛችን በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ስናደርግ ብሩህ ቀን ይጠብቀናል። ፈተናዎች የምድራዊ ሕይወት አካል ናቸው እንዲሁም በመላው አለም በእያንዳንዱ ሰው ህይወት ውስጥ ይከሰታሉ። ይህ በአገራት እና በግለሰቦች መካከል የሚከሰቱ ዋና ዋና ግጭቶችን ያካትታል።

የቤተክርስቲያን መሪዎች፣ “ፍትሃዊ የሆነ አምላክ በተለይ በጥሩ ሰዎች ላይ መጥፎ ነገር እንዲደርስ የሚፈቅደው ለምንድነው?” እና “ጻድቅ የሆኑ እንዲሁም ጌታን በማገልገል ላይ ያሉ ሰዎች ከእንደዚህ አይነት አሳዛኝ ሁኔታዎች ነፃ ያልሆኑት ለምንድነው?” የሚሉትን ጥያቄዎች በተደጋጋሚ ይጠየቃሉ።

ሁሉንም መልሶች አናውቅም ሆኖም ፈተናዎችን፣ ሥቃይን እና መከራዎችን በእምነት እና በራስ መተማመን እያንዳንዳችንን የሚጠብቀንን ለመጋፈጥ የሚያስችሉንን አስፈላጊ መርሆች እናውቃለን። በሥቃይ ውስጥ ማለፍን አስመልክቶ ነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ በሊበርቲ እስር ቤት ታስሮ በነበረበት ጊዜ ጌታ ከተናገረው በቅዱሳት መፃሕፍት ውስጥ ከሚገኘውንግግር የተሻለ ምሳሌ አይገኝም።

በከፊል ጌታ እንዲህ ብሏል፦

“የሲኦል መንጋጋም አፍዋን በሰፊው ብትከፍትብህ፣ ልጄ ሆይ እነዚህ ነገሮች ሁሉ ለአንተ ልምድ እንደሚሰጡህ እና ለአንተ ጥቅም እንደሆኑም እወቅ።

“የሰው ልጅ ከሁሉም በታች ወርዷል። አንተ ከእርሱ ታላቅ ነህ?

“… አትፍራ፣ እግዚአብሔር ከዘለአለም እስከ ዘለአለም ከአንተ ጋር ነውና።”19

በግለሰብ ደረጃ የሚያውቀን እና የሚወደን እንዲሁም ስቃያችንን በትክክል የሚገነዘብ የሰማይ አባት እንዳለን ግልፅ ነው። ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ አዳኛችን እና ቤዛችንነው።

ዛሬ ጥዋት ፕሬዘደንት ኤም. ራስል ባላርድ በወንጌሌን ስበኩ አዲሱ ሁለተኛ እትም ጠቀሜታ ላይ ጠንከር ያለ አጽንኦት ሰጥተዋል።20 የእርሳቸውን ጉጉት እጋራለሁ። ይህ አዲስ እትም የሚከተሉትን በኃይል በማወጅ ቅዱሳት መጻሕፍትን ያጎላል፦

“በኃጢያት ክፍያው፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ህመሞቻችንን፣ ሥቃዮቻችንን እና ድክመቶቻችንን በራሱ ላይ ወስዷል። በዚህ ምክንያት፣ ‘በስጋ ህዝቡን ከድካሙ እንዴት እንደሚረዳ ያውቃል’ (አልማ 7፥12፤ እንዲሁም ቁጥር 11ን ተመልከቱ)። “ወደ እኔ ኑ” ሲል ይጋብዘናል፣ እንዲህ ስናደርግም እረፍትን፣ ተስፋን፣ ጥንካሬን፣ እይታን እና ፈውስን ይሰጠናል (ማቴዎስ 11፥28፤ እንዲሁም ቁጥሮች 29–30ን ተመልከቱ)።

“በኢየሱስ ክርስቶስ እና በኃጢያት ክፍያው ላይ ስንመካ፣ በፈተናዎቻችን፣ በበሽታዎቻችን እና በህመሞቻችን እንድንታገስ ሊረዳን ይችላል። በደስታ፣ በሰላም፣ እና በመፅናኛ ለመሞላት እንችላለን። በህይወት ሚዛናዊ ያልሆኑ ነገሮች በሙሉ በኢየሱስ ክርስቶስ የኃጢያት ክፍያ በኩል ትክክል ለመሆን ይችላሉ።”21

በደስታ ሰላማዊ የክርስቶስ ተከታዮች ልንሆን እንችላለን።

አባታችን ለልጆቹ ያለው የደስታ እቅድ የቅድመ ምድር እና ምድራዊ ህይወትን ብቻ ሳይሆን በሞት ከተለየናቸው ጋር የሚደረግን ታላቅ እና አስደናቂ የሆነ እንደገና መገናኘትን ጨምሮየዘላለም ህይወት የማግኝትንም አቅም ያካትታል። ስህተቶች ሁሉ ይስተካከላሉ እንዲሁም በፍፁም ግልጽነት እና ሥህተት አልባ እይታ እና ግንዛቤ እናያለን።

የቤተክርስቲያን መሪዎች ይህንን አመለካከት ባለሶስት ገቢር ተውኔቱ ከጀመረ በኋላ ከገባ ሰው ጋር አነጻጽረውታል።22 ስለአብ እቅድ እውቀት የሌላቸው ሰዎች በመጀመሪያው ገቢር ወይም በቅድመ ምድር ሕይወት ምን እንደተከሰተ እና እዚያ የተቋቋሙትን ዓላማዎች አይገነዘቡም ወይም በሦስተኛው ገቢር የሚመጣውን የአብ እቅድ አስደናቂ ፍጻሜ ማብራሪያ እና ዓላማ አይገነዘቡም።

ብዙዎች በእርሱ አፍቃሪ እና ሁሉን አቀፍ ዕቅዱ ውስጥ የራሳቸው ባልሆነ ጥፋት፣ ተጎጂ የሆኑ የሚመስሉት፣ በመጨረሻ የዚያ ተጽዕኖ የሚደርስባቸው ባለመሆኑ አድናቆት አያሳዩም።23

ቅዱሳት መጻህፍት በግልጽ ያስቀምጡታል፦ጻድቅ የሆኑ፣ አዳኙን የሚከተሉ እና ትዕዛዛቱን የሚጠብቁ ሰላማዊ የክርስቶስ ተከታዮች ይባረካሉ። በህይወት ያሉበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን ጻድቅ ለሆኑ ሰዎች በጣም አስፈላጊ ከሆኑት ቅዱስ ጽሁፋዊ ጥቅሶች አንዱ ንጉሥ ቢንያም ለሕዝቡ ያደረገው ንግግር ክፍል ነው። ትእዛዛትን በታማኝነት የሚጠብቁ በዚህ ህይወት በሁሉም ነገር የተባረኩ ናቸው እንዲሁም፣ “ለዘለአለም በማያልቀው ደስታ ከእግዚአብሔር ጋር ይኖሩ ዘንድ፣ መንግስተ ሰማይ ትቀበላቸዋለች።” ሲል ተስፋ ሰጥቷል።24

ሁላችንም ማለት በሚቻል ሁኔታ በህይወታችን አንዳንድ በከፍተኛ ሁኔታ የሚጎዱ አካላዊ እና መንፈሳዊ አውሎ ነፋሶች እንዳጋጠሙን እንገነዘባለን። የሰማይ አፍቃሪ አባት እና የእርሱ የተመለሰች ቤተክርስቲያን መሪ የሆነው ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ እኛን ለማዘጋጀት፣ ስለሚመጡ አደጋዎች እኛን ለማስጠንቀቅ እንዲሁም ለማዘጋጀት እና ለመጠበቅ መመሪያ ሊሰጡን ቅዱሳት መጻህፍትን እና ነቢያትን ሰጥተውናል። አንዳንድ መመሪያዎች አፋጣኝ እርምጃ መውሰድን ይጠይቃሉ እና አንዳንዶቹ ወደፊት ለሚመጡት ለብዙ አመታት ጥበቃ ያደርጋሉ። ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች ክፍል 1የጌታ መግቢያ “የነቢያትን ቃል እንድንሰማ” ይመክረናል።25

በተጨማሪም ክፍል 1 “ለሚመጣው ተዘጋጁ፣ ተዘጋጁ” ሲል ያስጠነቅቀናል።26 ጌታ ለሚያጋጥማቸው ፈተናዎች እንዲዘጋጁ ለህዝቡ ዕድል ይሰጣል።

ጌታ በጥር 14 ቀን 1847 (እ.አ.አ) በዊንተር ኳርተርስ ለፕሬዘደንት ብሪገም ያንግ ኃይለኛ መገለጥ ሰጠው።27 ይህ መገለጥ ጌታ ለሚመጣው እንዲዘጋጁ ለህዝቡ ዕድል እንደሚሰጥ የሚጠቁም ልዩ ምሳሌ ነው። ታማኝ ቅዱሳን ወደ ሶልት ሌክ ሸለቆ ተራራ መጠለያ የሚያደርጉትን ስደት ጀምረው ነበር። የናቩ ቤተመቅደስን በተሳካ ሁኔታ ገንብተው የነበረ ሲሆን የተቀደሱ የማዳን ሥርዓቶችንም ተቀብለው ነበር። ከሚዙሪ የተባረሩ ሲሆን አሳዳጆቻቸው በአስፈሪው የክረምት ወቅት ከናቩ አስወጥተዋቸውም ነበር። ብሪገም የተቀበለው መገለጥ እንዴት ለስደት ዝግጅት እንደሚደረግ ተግባራዊ ምክር ሰጥቷል። ጌታ ድሆችን፣ መበለቶችን፣ አባት የሌላቸውን እና የቅዱሳን ዋና ክፍል አደገኛውን ጉዞ እያደረጉ በነበሩበት ጊዜ በሞርሞን ባታሊዮን ውስጥ እያገለገሉ የነበሩትን ሠዎች ቤተሰቦች በመንከባከብ ላይ ልዩ ትኩረት አድርጓል።

በጽድቅ እንድንኖር ከተሰጡ ከሌሎች ምክሮች በተጨማሪ፣ ጌታ ዛሬም ተግባራዊ በመሆን በሚቀጥሉ ሁለት መርሆች ላይ አጽንዖት ሰጥቷል።

በመጀመሪያ ፣ “ጌታን በዝማሬ፣ በሙዚቃ፣ በእልልታ፣ እና በምስጋና ጸሎት እና በምስጋና [እንዲያመልኩ] አበረታታቸው።28

ሁለተኛ፣ “የከፋቸው ቢሆኑም፣ ነፍሶቻቸው ይደሰቱ ዘንድ፣ ጌታ አምላካቸውን በልመና እንዲጠሩ” ጌታ መከራቸው።29

እነዚህ ሁለት ምክሮች ለራሳችን ዘመን የሚሆኑ ታላቅ ምክሮች ናቸው። በምስጋና፣ በሙዚቃ እና ምስጋና በመስጠት የተሞላ ህይወት በተለየ ሁኔታ የተባረከ ነው። ደስተኛ መሆን እና በጸሎት አማካኝነት በሚገኝ ሰማያዊ እርዳታ መደገፍ ሰላማዊ የክርስቶስ ተከታዮች ለመሆን ጠቃሚ መንገድ ነው። ሁልጊዜ ደስተኛ ለመሆን መጣር ድባቴን ለማስወገድ ይረዳል።

የማስተዋል መዝሙሩ የመጨረሻው መስመር የመጨረሻውን መልስ በሚያምር ሁኔታ ያስተላልፋል፦ “ሰማይ መፈወስ የማይችለው ሀዘን ምድር የላትም።”30

እንደጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያነቴ፣ ሰላማዊ የክርስቶስ ተከታዮች በዚህ ህይወት የግል ሰላምን እንዲሁም በአስደናቂ ሁኔታ በሰማይ እንደገና መገናኘትን እንደሚያገኙ እመሰክርላችኋለሁ። የአዳኙን አምላክነት እና የኃጢያት ክፍያውን እውነታ ትክክለኛ ምስክርነቴን እሰጣለሁ። አዳኛችን እና ቤዛችን ነው። በኢየሱስ ክርስቶስ ስም፣ አሜን።