አጠቃላይ ጉባኤ
የአዳኙ የመፈወስ ሃይል በባህሩ ደሴቶች ላይ
የጥቅምት 2023 (እ.አ.አ) አጠቃላይ ጉባኤ


የአዳኙ የመፈወስ ሃይል በባህሩ ደሴቶች ላይ

በቤተመቅደስ በረከቶች አማካኝነት አዳኙ ግለሰቦችን፣ ቤተሰቦችን እና ሐገራትን ሳይቀር ይፈውሳል።

በ1960ዎቹ አባቴ በተወለድኩባት ከተማ ሌዬ በሚገኘው የቤተክርስቲያኗ የሃዋዪ ኮሌጅ ያስተምር ነበር። ሰባቱ ታላላቅ እህቶቼ ወላጆቼ “ኪሞ” ብለው የሃዋዪ ስም እንዲያወጡልኝ አጥብቀው ጠየቁ። በሌዪ ሃዋዪ ቤተመቅደስ አቅራቢያ የኖርነው ጃፓንን ጨምሮ በኤዥያ ፓሲፊክ አካባቢ ለነበሩት ለአብዛኞቹ የቤተክርስቲያን አባላት አገልግሎት ይሰጥ በነበረበት ጊዜ ነው።1 በዚህ ጊዜ የጃፓናውያን የቅዱሳን ቡድኖች የቤተመቅደስ በረከቶችን ለመቀበል ወደ ሃዋዪ መምጣት ጀመሩ።

ከእነዚህ አባላት መካከል አንዷ ከውቧ የኦኪናዋ ደሴት የመጣችው እህት ነበረች። የሃዋዪ ቤተመቅደስ ጉዞዋ ታሪክ አስደናቂ ነው። ከተመረጠላት ባሏ ጋር በባህላዊ መንገድ በተዘጋጀ የቡድሂስት የሠርግ ሥነ ሥርዓት ጋብቻዋን የፈፀመችው ከሁለት አስርተ ዓመታት በፊት ነበር። ከጥቂት ወራት በኋላ ጃፓን በሃዋዪ ፐርል ሃርበር ላይ ጥቃት በመሰንዘር ዩናይትድ ስቴትስ ከጃፓን ጋር ጦርነት እንድትገጥም አደረገቻት። እንደሚድዌይ እና ኢዎ ጂማ ያሉ ወሳኝ ጦርነቶች ውጤት፣ የጦርነቱ ወላፈን የጃፓንን ጦር ወደ ደሴት ወደሆነችው አገሯ ወደ ኦኪናዋ የባህር ዳርቻ እንዲያፈገፍግ አደረገው።ይህም የተባበሩት ኃይሎችን ወደ ዋናው የጃፓን መሬት እንዳይዘልቁ የሚያደርገው የመጨረሻው የመከላከያ ግንባር ነበር።

በ1945 (እ.አ.አ)፣ የኦኪናዋ ጦርነት ለሦስት አስጨናቂ ወራት ተጧጧፈ። 1,300 የአሜሪካ የጦር መርከቦች ቡድን ደሴቷን ከበው በቦምብ ደበደቡ። በወታደሮች እና በሰላማዊ ዜጎች ላይ የደረሰው ጉዳት እጅግ ከፍተኛ ነበር። ዛሬ በኦኪናዋ በሚገኝ በአንድ የተከበረ ሐውልት ላይ ከ240,000 የሚልቁ በጦርነቱ የሞቱ ስማቸው የታወቀ ሰዎች ዝርዝር ተፅፎ ይገኛል።2

ይህች የኦኪናዋ ሴት፣ ባሏ እና ሁለት ትናንሽ ልጆች ከአውዳሚ ጥቃቱ ማምለጥ ያስፈልጋቸው ስለነበረ ዋሻ ውስጥ ተደበቁ። በቀጣዮቹ ሳምንታት እና ወራት ውስጥም ሊገለፅ የማይችል መከራን አሳለፉ።

ቤተሰቧ የሚላስ የሚቀመስ አጥቶ በረሃብ በተጎሳቆለበት፣ ጦርነቱ እየተካሄደ በነበረበት በአንድ ተስፋ አስቆራጭ ምሽት እናም ባለቤቷ ከሞት ጋር በመጋፈጡ፣ የአካባቢው ባለስልጣናት ለእርሷ እና ለሌሎች ለዚሁ ዓላማ በሰጧቸው የእጅ ቦምብ ከስቃይ ልትገላግላቸው አሰበች። ሆኖም፣ ያንን ለማድረግ እየተዘጋጀች እያለች ወደፊት ለመቀጠል ጥንካሬ የሰጣትን እግዚአብሔር እንዳለና ለእርሷ ፍቅር እንዳለው የሚያሳይ ተጨባጭ የሆነ ስሜት እንዲሰማት ያደረገ ጥልቅ የሆነ መንፈሳዊ ተሞክሮ ተከሰተ። በቀጣዮቹ ቀናት ባሏ ራሱን እንዲያውቅ አደረገች እንዲሁም ቤተሰቧን በአረም፣ ከጫካ ቅፎ በተቆረጠ ማር እና በአቅራቢያው ከሚገኝ ወንዝ በተጠመዱ ፍጥረታት መገበች። የአካባቢው ነዋሪዎች ጦርነቱ እንደተጠናቀቀ እስካሳወቋቸው ጊዜ ድረስ ባልተለመደ ሁኔታ፣ ለስድስት ወራት በዋሻው ውስጥ በፅናት ቆዩ።

ሕይወታቸውን እንደገና ለመጀመር ቤተሰቡ ወደ ቤት ሲመለስ ስለእግዚአብሄር ለማወቅ ፍለጋዋን ጀመረች። ቀስ በቀስም በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ እምነት እና የመጠመቅ ፍላጎት እንዲያቆጠቁጥ አደረገ። ይሁን እንጂ ስለኢየሱስ ክርስቶስ እና ስለጥምቀት ሳይማሩ ስለሞቱት ስለምትወዳቸው ሰዎች ተጨነቀች።ይህም እርሷን በምትወልድበት ጊዜ የሞተችውን ወላጅ እናቷን ይጨምር ነበር።

አንድ ቀን የኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን ሁለት እህት ሚስዮናውያን ቤቷ መጥተው ሰዎች ከሞቱ በኋላ ስለኢየሱስ ክርስቶስ በመንፈሳዊው ዓለም ውስጥ ሊማሩ እንደሚችሉ ሲያስተምሯት እንዴት ተደስታ እንደነበር ገምቱ። ወላጆቿ ከሞት በኋላም ኢየሱስ ክርስቶስን ለመከተል መምረጥ እንደሚችሉ እና ቤተመቅደሶች በሚባሉ የተቀደሱ ቦታዎች ለእነርሱ የምታከናውነውን የውክልና ጥምቀት መቀበል እንደሚችሉ በሚገልፀው ትምህርት ተደስታለች። እርሷ እና ቤተሰቧ ጌታን ተቀበሉ እንዲሁም ተጠመቁ።

ቤተሰቧ ጠንክሮ በመስራት መበልጸግ ጀመሩ፤ ሦስት ተጨማሪ ልጆችንም አፈሩ። በቤተክርስቲያን ታማኝ እና ንቁ ተሳታፊ ነበሩ። ከዚያም ሳይጠበቅ ባሏ ስትሮክ ያዘውና ሞተ፤ ይህም ለአምስት ልጆቿ የሚያስፈልጋቸውን ለማቅረብ የተለያዩ ሥራዎችን ለረዥም ሰ ዓታት እና ለብዙ ዓመታት እንድትሰራ አስገደዳት።

በቤተሰቦቿ ውስጥ ያሉ አንዳንድ ሰዎች እና ጎረቤቶቿ ወቅሰዋት ነበር። ቤተክርስቲያንን ለመቀላቀል ያደረገችውን ውሳኔ ለደረሱባት መከራዎች መንሳኤ አደረጉት። በጥልቅ ሃዘን እና በከባድ ትችት ሳትገታ፣ እግዚአብሄር እንደሚያውቃት እና የበለጠ ብሩህ ቀናት እንደሚመጡ በማመን ወደፊት ለመጓዝ ውሳኔ አድርጋ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያላትን እምነት አጽንታ ይዛለች።3

ባሏ ያለዕድሜው ከሞተ ከጥቂት አመታት በኋላ የጃፓን አባላት በቤተመቅደስ ለመሳተፍ ጥረት እንዲያደርጉ በጃፓን የሚስዮን ፕሬዚዳንት ማበረታቻ ተሰጣቸው። የሚስዮኑ ፕሬዚዳንቱ የኦኪናዋዋ እህትን እና ቤተሰቧን ብዙ እንዲጎሳቆሉ ያደረገው የኦኪናዋ ጦርነት የቀድሞ አሜሪካዊ ወታደር ነበር።4 የሆነ ሆኖ፣ ትሑቷ እህት ስለ እሱ እንዲህ ብላለለች:- “በዚያን ጊዜ ከምንጠላቸው ጠላቶቻችን አንዱ ነበር፣ አሁን ግን የፍቅርን እና የሰላምን ወንጌል ይዞ መጥቷል። ይህ ለእኔ ተዓምር ነበር።”5

መበለቷ እህት የሚስዮን ፕሬዚዳንቱን መልዕክት ስትሰማ፣ አንድ ቀን በቤተመቅደስ ውስጥ ከቤተሰቧ ጋር ለመታተም ፈለገች። ሆኖም በገንዘብ እና በቋንቋ እጥረት ምክንያት ያንን ማድረግ አትችልም ነበር።

ከዚያምብዙ አዳዲስ ምፍትሔዎች ፈለቁ። በጃፓን ያሉ አባላት የሰዎች እንቅስቃሴ በማይበዛበት ወቅት ወደ ሃዋዪ ለመብረር አንድ ሙሉ አውሮፕላን ቢከራዩ ዋጋው በግማሽ ሊቀንስ ይችላል።6 አባላት፣ የጃፓን ቅዱሳን ይዘምራሉ የሚል ርዕስ ያለው ሸክላ ቀድተው ሸጡ። አንዳንድ አባላት ቤታቸውንም ሳይቀር ሸጡ። ሌሎች ጉዞውን ለማድረግ ይችሉ ዘንድ ሥራቸውንም አቆሙ።7

ሌላው አባላት የነበሩባቸው ችግር የቤተ መቅደስ ሥርዓት ንግግሮች በጃፓንኛ የሌሉ መሆናቸው ነው። የቤተክርስቲያን መሪዎች የቤተመቅደስ ቡራኬ ሥርዓቱን ለመተርጎም ወደ ሃዋዪ ቤተመቅደስ እንዲሄድ ለአንድ ጃፓናዊ ወንድም ጥሪ ሰጡት።8 ከጦርነቱ በኋላ ፣በታማኝ የአሜሪካ ወታደሮች ተምሮ እና ተጠምቆ የተለወጠ የመጀመርያው ጃፓናዊ ነበር።9

በሃዋዪ የሚኖሩ የቤተመቅደስ ቡራኬ የተቀበሉ የጃፓን አባላት ትርጉሙን ለመጀመሪያ ጊዜ ሲሰሙ አለቀሱ። አንድ አባል እንዲህ ሲል መዝግቦ ነበር፣ “ብዙ ብዙ ጊዜ በቤተመቅደስ ተሳትፈናል። የሥርዓቱን ንግግሮች የሰማናቸው በእንግሊዝኛ ነበር። [ነገር ግን] በአፍ መፍቻ ቋንቋችን [በመስማታችን] የቤተመቅደስ ሥራ… መንፈሱ አሁን እንደሚሰማን ተሰምቶን አያውቅም።”10

በኋላ በዚያው ዓመት፣ 161 ጎልማሶች እና ልጆች ወደ ሃዋዪ ቤተመቅደስ ለመሄድ ከቶኪዮ ጉዟቸውን ጀመሩ። አንድ ጃፓናዊ ወንድም ስለጉዞው እንዲህ ያስታውሳል፦“ከአውሮፕላኑ ውስጥ ሆኜ ፐርል ሃርበርን ስመለከትና ሀገራችን ታህሳስ 7 ቀን 1941 (እ.አ.አ) በእነዚህ ሰዎች ላይ ያደረገችውን ባስታወስኩኝ ጊዜ ልቤ ፈራ። ይቀበሉናል? ሆኖም፣ ይግረምህ ብሎ፣ በሕይወቴ አይቼ የማላውቀውን ታላቅ ፍቅርና ደግነት አሳዩኝ።”11

ምስል
የጃፓን ቅዱሳን በአበባ የአንገት ጉንጉን አቀባበል ተደርጎላቸዋል።

የጃፓን ቅዱሳን እንደደረሱ ለእነርሱ ባህል እንግዳ በሆነው መተቃቀፍ እና ጉንጭ ላይ በመሳሳም ስፍር ቁጥር በሌላቸው የአበባ ጉንጉን አንገት ላይ በማጥለቅ የሃዋዪ አባላት ተቀበሏቸው። የጃፓን ቅዱሳን፣ በሃዋዪ ካሳለፏቸው 10 ለዋጭ ከሆኑት ቀናት በኋላ፣ በሃዋዪ ቅዱሳን በተዘመረው “አሎሃ ኦ” የሚል መዝሙር ተሰነባብተዋል።12

ለጃፓን አባላት በተዘጋጀው ሁለተኛው የቤተመቅደስ ጉዞ ውስጥ የኦኪናዋ መበለት ተካታለች። በቅርንጫፏ ያገለገሉ እና በጠረጴዛዋ ላይ ብዙ ምግብ የተመገቡ ሚስዮናውያን ላደረጉት ለጋሽ ስጦታ ምስጋና ይግባቸውና የ10,000-ማይል (16,000-ኪ.ሜ) ጉዞውን አደረገች። በቤተመቅደስ፣ ለእናቷ የውክልና ጥምቀት በተጠመቀች እና ከሞተው ባሏ ጋር በታተመች ጊዜ የደስታ እምባ አነባች።

በ1980 (እ.አ.አ) የቶኪዮ ጃፓን ቤተመቅደስ 18ኛው ቤተመቅደስ ሆኖ እስኪመረቅ ድረስ ከጃፓን የሚደረጉ የቤተመቅደስ ጉዞዎች በመደበኛነት ቀጥለው ነበር። በዚህ አመት ህዳር ወር 186ኛው ቤተመቅደስ በኦኪናዋ ጃፓን ይመረቃል። ይህች ሴት እና ቤተሰቧ ከተሸሸጉበት በማዕከላዊ ኦኪናዋ ውስጥ ካለው ዋሻ ብዙም በማይርቅበት ቦታ ላይ ይገኛል።13

ይህችን የኦኪናዋ ድንቅ እህት በአካል ባልግገናኛትም፣ ያሳደረችው ተፅዕኖ በማውቃቸው እና በምወዳቸው ታማኝ ትውልዶቿ አማካኝነት ቀጥሏል።14

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት በፓስፊክ ውቅያኖስ የተሳተፈው የቀድሞ ወታደር የነበረው አባቴ፣ ወጣት ሚስዮናዊ በመሆን በጃፓን ለማገልገል ጥሪ ሲሰጠኝ በጣም ተደሰቶ ነበር። ጃፓን የደረስኩት የቶኪዮ ቤተመቅደስ ተመርቆ ብዙም ሳይቆይ ነበር፤ እናም ለቤተመቅደስ ያላቸውን ፍቅር በገዛ አይኔ አይቻለሁ።

የቤተመቅደስ ቃል ኪዳኖች ከሰማይ አባታችን ለልጁ ለኢየሱስ ክርስቶስ ታማኝ ተከታዮች የተሰጡ ስጦታዎች ናቸው። የሰማይ አባታችን በቤተመቅደስ አማካኝነት ግለሰቦችን እና ቤተሰቦችን ከአዳኙ ጋር እንዲሁም እርስ በርሳቸው ያጣምራል።

ፕሬዚዳንት ራስል ኤም ኔልሰን ባለፈው ዓመት እንዲህ ሲሉ ተናግረዋል፦

በጥምቀት ገንዳ እና በቤተመቅደስ ውስጥ ቃል ኪዳን የሚገባ—እና ቃል ኪዳኑን የሚያከብር—እያንዳንዱ ሰው የኢየሱስ ክርስቶስን ሀይል የማግኘት ተጨማሪ ችሎታ አለው።

ቃል ኪዳኖችን በመጠበቅ የሚገኘው ሽልማት የሰማይ ሀይል ነው—ያም ሀይል መከራዎቻችንን፣ ፈተናዎቻችንን፣ እና ከባድ ሀዘኖቻችንን በተሻለ ሁኔታ እንድንቋቋም ያጠናክረናል። ይህም ሀይል መንገዳችንን ያቀልልናል።”15

በቤተመቅደስ በረከቶች አማካኝነት አዳኙ ግለሰቦችን፣ ቤተሰቦችን እና ከዚህ በፊት ደመኛ ጠላቶች የነበሩ ሐገራትን ሳይቀር ይፈውሳል። ከሞት የተነሳው ጌታ፣ ግጭት ለበዛባቸው እርሱን ለሚያከብሩ ማህበረረሰቦች፣ “ነገር ግን ስሜን ለ[ሚ]ፈሩ፣ ለእ[ነርሱ] የፅድቅም ልጅ ፈውስን በክንፎቹ ይዞ ይነሳል” ሲል ተናግሯል።16

“የአዳኛችን እውቀት በሁሉም ሃገር፣ ነገድ፣ ቋንቋ እና ሕዝብ መካከል የሚሰራጭበት ጊዜ እንደሚመጣ”17 እናም “በባህር እና በደሴቶች ያሉትንም” እንደሚያካትት18፣ የተነገረውን የጌታ ቃል ኪዳን እየተፈጸመ እንደሆነ ምስክር በመሆኔ አመስጋኝ ነኝ።

ስለኢየሱስ ክርስቶስ እንዲሁም በዚህ በኋለኛው ቀን ስላሉት ነቢያቱ እና ሐዋርያቱ እመሰክራለሁ። ሰማያዊው ሃይል በምድር የታሰረውን በሰማይም እንደሚያስር ምስክርነቴን እሰጣለሁ።

የአዳኙ ሥራ ያ ነው፤ ቤተመቅደሶች የእርሱ ቅዱስ ቤቶች ናቸው።

በማያወላውል እምነት እነዚህን እውነቶች በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አናገራለሁ፣ አሜን።

ማስታወሻዎች

  1. የሌዬ ሃዋዪ ቤተመቅደስ በ1919 (እ.አ.አ) በፕሬዘዳንት ሄበር ጄ. ግራንት ተቀድሷል። እንደ ሐዋርያ፣ በ1901 በጃፓን ቤተክርስቲያንን ከፈተ። ይህም አምስተኛው ተግባራዊ ቤተመቅደስ እና ከአህጉራዊ ዩናይትድ ስቴትስ ውጭ የተገነባ የመጀመሪያው ቤተመቅደስ ነበር።

  2. ከመጋቢት 2፣ 2023(እ.አ.አ) ጀምሮ፣ በመታሰቢያ ሐውልቱ ላይ 241,281 ስሞች ተጽፈዋል።

  3. ጎርደን ቢ. ሂንክሊ, “Keep the Chain Unbroken” (Brigham Young University devotional, Nov. 30, 1999)ይመልከቱ።

  4. ድዌይን ኤን አንደርሰን በኦኪናዋ ጦርነት ቆስሏል። ከ1962 እስከ 1965 በጃፓን የሚስዮን ፕሬዝዳንት ሆኖ አገልግሏል እና ከ1980 እስከ 1982 የቶኪዮ ጃፓን ቤተመቅደስ የመጀመሪያ ፕሬዝዳንት ነበር።

  5. እኔና ባለቤቴ በቶኪዮ የሚስዮን መሪዎች ሆነን ስናገለግል የቤተሰቧን አባላት አገኘኋቸው። ይህንን መረጃ ከግል ቤተሰቧ ታሪክ መዝገቦች ሰጥተውኛል።

  6. Dwayne N. Andersen: An Autobiography for His Posterity(2001), 102–5, Church History Library ይመልከቱ።

  7. Dwayne N. Andersen, 104፣ ይመልከቱ።

  8. Edward L. Clissold, “Translating the Endowment into Japanese,” Stories of the Temple in Laie, Hawaii, comp ይመልከቱ። Clinton D. Christensen (2019), 110–13።

  9. ተርጓሚው፣ ታትሱ ሳቶ፣ በሐምሌ 7፣ 1946(እ.አ.አ) በዩኤስ ወታደር በሲ ኤሊዮት ሪቻርድስ ተጠመቀ። የታጹ ሚስት፣ ቺዮ ሳቶ፣ በዚያው ቀን በቦይድ ኬ. ፓከር ተጠመቀች። በተናጠል፣ ኒል ኤ. ማክስዌል በኦኪናዋ ጦርነት ተዋግቷል፣ እና ኤል. ቶም ፔሪ የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ በጃፓን ወደ ባህር ዳርቻ ከሄዱት የመጀመሪያዎቹ የባህር ኃይል መካከል አንዱ ነበር። ሽማግሌ ፓከር፣ ማክስዌል እና ፔሪ የአስራ ሁለቱ ሐዋርያት ቡድን አባላት እንዲሆኑ ተጠርተዋል።

  10. In Clissold, “Translating the Endowment into Japanese,” 112።

  11. In Dwayne N. Andersen, “1965 Japanese Excursion,” Stories of the Temple in Lā‘ie, Hawai‘i, 114.

  12. Andersen, “1965 Japanese Excursion,” 114, 117፣ ይመልከቱ።

  13. በዚህ የጥቅምት 2023 አጠቃላይ ጉባኤ ክፍለ ጊዜ በኋላ ላይ፣ ፕሬዘደንት ራስል ኤም ኔልሰን፣ የኦሳካ ጃፓን ቤተመቅደስን ጨምሮ 20 አዳዲስ ቤተመቅደሶችን አስታውቀዋል፣ ይህም በጃፓን አምስተኛው ቤተመቅደስ ይሆናል።

  14. ከ2018 እስከ 2021 (እ.ኤ.አ.) በቶኪዮ በነበረብ ምስዮናዊ አገልግሎት በኮቪድ ወረርሽኝ ፈታኝ ሁኔታዎች ውስጥ፣ ቤተሰቧ ለእኔ እና ለቤተሰቤ ፍቅር እና እንክብካቤ አድርገውልናል፣ ለዚህም ለዘላለም አመስጋኞች ነን።

  15. ራስል ኤ. ኔልሰን፣ ““አለምን ማሸነፍ እና እረፍትን ማግኘትሊያሆና, ህዳር 2022 (እ.አ.አ)፣ 96።

  16. 3 ኔፊ 25፥2

  17. ሞዛያ 3፥20

  18. 2 ኔፊ 29፥7