አጠቃላይ ጉባኤ
የእግዚአብሔርን ቤተሰብ በአጠቃላይ እይታ ሌንስ ውስጥ መመልከት
የጥቅምት 2023 (እ.አ.አ) አጠቃላይ ጉባኤ


የእግዚአብሔርን ቤተሰብ በአጠቃላይ እይታ ሌንስ ውስጥ መመልከት

በእምነት አይን አማካኝነት አርቀን እራሳችንን እና ቤተሰቦቻችንን በተስፋ እና በደስታ መመልከት እንችላለን ብዬ አምናለሁ።

የሁሉም ታናሽ የሆነችው ሴት ልጃችን በርክሊ ትንሽ ሳለች፣ ሁሉንም ነገሮች የሚያጎላውን የንባብ መነጽር መጠቀም ጀመርኩኝ። አንድ ቀን፣ በአንድነትተቀምጠን አንድ መጽሐፍ በማንበብ ላይ ሳለን፣ በፍቅር እንዲሁም በሃዘን ተመለከትኳት ምክንያቱም በቅጽበት የበለጠ ትልቅ ሰው የሆነች መሰለች። እንዲህ ብዬ አሰብኩኝ፣ “ጊዜው የት ሄደ? በጣም ትልቅ ሆናለች!”

እንባዬን ለማበስ የንባብ መነጽሩን ሳወልቅ፣ እንዲህ ተገነዘብኩኝ፣ “ውይ ትልቅ አይደለችም፣ የንባብ መነጽሩ ነው ትልቅ ያስመሰላት! ግድ የለም!”

አንዳንድ ጊዜ እኛ ማየት የምንችለው የምንወዳቸውን ሰዎች የቅርብ ርቀት የጎላ እይታ ነው። በዛሬው ምሽት እይታችሁን አስተካክላችሁ ወይም ለውጣችሁ በተለየ እይታ—ማለትም በትልቅ ምስሉ፣ በትልቁ ታሪካችሁ ላይ ትኩረትን በሚያደርገው—በዘለአለማዊ እይታ እንድትመለከቱ እጋብዛችኋለሁ።

የሰው ልጅ በመጀመሪያ ወደ ጠፈር ለመጓዝ ባደረገው ምርምር ወቅት የነበሩት ሰው አልባ መንኮራኮሮች መስኮቶች አልነበሯቸውም። ነገር ግን አፖሎ 8 ወደ ጨረቃ ለመጓዝ በነበራት ተልዕኮ ወቅት፣ የጠፈር ተመራማሪዎቹ መስኮት ነበራቸው። በጠፈር ላይ ሲንሳፈፉ መሬታችንን በመመልከት ሃይል ተደነቁ እና የመላው አለምን ትኩረት የሳበውን ይህን የሚያስደንቅ ፎቶ አነሱ! እነዚያ የጠፈር ተመራማሪዎች ሃይለኛ የሆነ ስሜት ተሰምቷቸው ስለነበረ የአጠቃላይ እይታ ውጤት የሚባል ራሱን የቻለ ስያሜ ተሰጠው።

ምስል
ምድር ከጠፈር ስትታይ

NASA

በአዲስ እይታ መመልከት ሁሉንም ነገር ይቀይራል። አንድ የጠፈር ተጓዥ ይህን አለ “ነገሮችን ሁሉም ይቻላል ብላችሁ ወደምታስቡት መጠን ያሳንሳል። … ይህን ማድረግ እንችላለን። ሰላም በምድር—ምንም ችግር የለም። ለህዝብ ያን ያህል ጉልበት … ያን ያህል ሃይል ይሰጣል።”1

እንደ ሰዎች፣ ምድራዊ የሆነ እይታ አለን፣ ነገር ግን እግዚአብሔር የአለምን ታላቅ አጠቃላይ እይታ ይመለከታል። ሁሉንም ፍጥረት፣ ሁላችንንም ይመለከታል እንዲሁም በተስፋ የተሞላ ነው።

የዚህ እይታ ስሜት እንዲሰማን፣ በዚህ ፕላኔት ገጽ ላይ በምንኖርበት ወቅትም እንኳን እግዚአብሔር እንደሚመለከተው መመልከት መጀመር ይቻላል? በእምነት አይን አማካኝነት አርቀን እራሳችንን እና ቤተሰቦቻችንን በተስፋ እና በደስታ መመልከት እንችላለን ብዬ አምናለሁ።

ቅዱሳን መጻህፍት ከዚህ ሃሳብ ጋር ይስማማሉ። ሞሮኒ “በእውነትም በእምነት አይን … [ስላዩ] እናም [ስለተደሰቱ] በእምነታቸው “እጅግ [ስለ]በረቱ” ሰዎች ተናግሯል።”2

በአዳኝ ላይ ባተኮረ አይን፣ ደስታ ተሰማቸው እናም ይህንን እውነት አወቁ፦ በክርስቶስ አማካኝነት ሁሉም ነገር ይሳካል። አንተ እና አንቺ እና እያንዳንዳችሁ የምትጨነቁባቸው ነገሮች በሙሉ መልካም ይሆናሉ። እናም በእምነት አይን የሚያዩ ሰዎች አሁን መልካም እንደሚሆን ይሰማቸዋል

በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ የመጨራሻ አመት ተማሪ ሳለሁ መልካም ምርጫዎችን ባለማድረጌ ምክንያት ከባድ ጊዜዎችን አሳልፌያለሁ። እናቴ ስታለቅስ አይቼ እንደነበር አስታውሳለሁ፣ እና እሷን አሳዝኜ ይሆን ብዬ አሰብኩ። በሰአቱ የእሷ እምባዎች በእኔ ተስፋ መቁረጧን እንደሚያሳይ እና በእኔ ተስፋ ካጣች ምናልባት ልመለስበት የምችልበት መንገድ የለም ስል ተጨነኩኝ ።

ነገር ግን አባቴ አርቆ እረጅሙን እይታ ማየትን ተለማምዶ ነበር። የመጨነቅ ሥሜት እንደ ፍቅር ሥሜት እንደሆነ፣ ነገር ግን አንድ አይነት እንዳይደሉ ከልምድ ተምሯል።3 ሁሉም እንደሚሳካ ለመመልከት የእምነትን አይን ተጠቀመ እናም የእርሱ በተስፋ የተሞላ አቀራረብ እኔን ቀየረኝ።

ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ስመረቅ እና ወደ ቢዋይዩ [BYU] ስሄድ፣ አባቴ ማን እንደነበርኩኝ እንዳስታውስ የሚያደርገኝ ደብዳቤዎችን ላከልኝ። የእኔ አበረታች ሆነ፣ እናም ሁሉም ሰው አበረታች ይፈልጋልና፦ “እንደሚገባው በፍጥነት እየሮጣችሁ አይደለም” የማይሏችሁ ሰዎች ፍቅር በተሞላበት መልኩ ይህን ማድረግ እንደምትችሉ እያስታወሷችሁ ነው።

አባቴ የሌሂ ህልም ምሳሌ ሆነ። ልክ እንደ ሌሂ፣ አንተ የጠፋብህን የምትወዳቸውን ሰዎች እንደማትከታተል ያውቃል። “ባላችሁበት ሆናችሁ ጥሯቸው። ወደ ዛፉ ሄዳችሁ፣ ዛፉ ጋር በመሆን፣ ፍሬውን መብላት ቀጥሉ እንዲሁም በፈገግታ ለምትወዷቸው ሰዎች ምልክት ማሳየትን በመቀጠል እና ፍሬውን መብላት የሚያስደስት ነገር እንደሆነ በምሳሌ አሳዩ።”4

ይህ የእይታ ምስል ባዘንኩባቸው ወቅቶች እራሴን ዛፉ ጋር ሳገኝ፣ ፍሬውን ስበላ እና በመጨነቄ ምክንያት ሳለቅስ ረድቶኛል፤ እናም እውነቱን ለመናገር ይህ እንዴት ነው የሚረዳው? በምትኩ፣ ተስፋ ማድረግን እንምረጥ፣ ይህም በፈጣሪያችን ላይ እንዲሁም አንዳችን በሌላው ላይ፣ አሁን ከሆንነው በበለጠ የተሻለ የመሆን ችሎታችንን የሚያቀጣጥለውን ተስፋ።

ሽማግሌ ኒል ኤ. ማክስዌል ከሞቱ ከአጭር ጊዜ በኋላ፣ አንድ ዘጋቢ የእርሳቸውን ልጅ ምን የበለጠ እንደሚናፍቀው ጠየቀ። በወላጆቹ ቤት እራት መብላትን እንደሚናፍቅ ተናገረ፣ ምክንያቱም ሁልጊዜ ከዚያ ሲመለስ አባቱ በእርሱ እንደሚያምንበት ይሰማው ስለነበረ ነው።

ይህም ጎልማሳ ልጆቻችን ከባለቤቶቻቸው ጋር ለእሁድ እራት እቤት መምጣት የጀመሩበት ጊዜ አካባቢ ነበር። በሳምንቱ ውስጥ፣ እንደ “እቤት ስትሆኑ ምናልባት ልጆቹን በመንከባከብ የበለጠ ማገዝን ሞክሩ” ወይም “ጥሩ አዳማጭ መሆንን አትርሱ” አይነት በእሁድ ለእነርሱ ላስታውሳቸው የምፈልጋቸውን ነገሮች ዝርዝር በአእምሮዬ እየያዝኩኝ ነበር።

የወንድም ማክስዌልን ሃሳብ ሳነብ፣ ዝርዝሮቹን በመጣል ያንን ድምጽ ዝም አስባልኩት፣ ስለሆነም ያደጉ ልጆቼን በእያንዳንዱ ሳምንት ለዚያች አጭር ጊዜ ሳያቸው፣ እያደረጓቸው በነበሩት ብዙ አወንታዊ ነገሮች ላይ አተኮርኩኝ። ከተወሰኑ አመታት በኋላ ታላቁ ልጃችን ራየን በሞተ ጊዜ፣ የአብሮነት ቆይታችን አስደሳች እና የበለጠ አወንታዊ በመሆኑ አመስጋኝ መሆኔን አስታውሳለሁ።

ከምንወደው ሰው ጋር መስተጋብር ከመፈጸማችን በፊት፣ “ላደርገው ወይም ልናገረው ያለው ነገር የሚረዳ ነው ወይስ የሚጎዳ?” የሚለውን ጥያቄ መጠየቅ እንችላለን። የምንናገራቸው ቃላት ታላቅ ውጤት ከሚያስከትሉ ነገሮች መካከል ናቸው፤ የቤተሰብ አባላት ደግሞ “ስለ እኔ የምታስቡትን ጻፉ!” እያሉ ከፊታችን እንደሚቆሙ ልክ እንደ የሰው የጥቁር ሰሌዳዎች ናቸው። እነዚህ መልእክቶች፣ የታሰበባቸውም ሆኑ ያልታሰበባቸው ተስፋን ያዘሉ እና የሚያበረታቱ መሆን አለባቸው።5

ስራችን በከባድ ችግር ውስጥ ያሉ ሰዎች መጥፎዎች ወይም የሚያሳዝኑ መሆናቸውን ማስተማር አይደለም። ውስን በሆኑ ጊዜዎች ማስተካከያ መስጠት እንደሚያስፈልግ ሊሰማን ይችላል፣ ነገር ግን ብዙ ጊዜ የምንወዳቸውን ሰዎች በሚነገር እና በማይነገር መልኩ ለመስማት የሚጓጉትን መልእክቶች እንንገራቸው፦ “እናንተ በውስጡ ስላላችሁበት፣ ቤተሰባችን ሙሉነት ይሰማዋል።” “ምንም ይሁን ምን ቀሪውን ህይወታችሁን በሙሉ ትወደዳላችሁ።”

እያንዳንዳችን በእውነት የሚያስፈልገን ነገር ከምክር ይልቅ ርህራሄ፤ ከማስተማር ይልቅ ማዳመጥ፤ የሚሰማ እና “እነርሱ አሁን ያሉትን ብናገር እንዴት ሊሰማኝ ይችላል?” ብሎ ራሱን የሚጠይቅ ሰው ነው።

አስታውሱ፣ ቤተሰቦች የተሳሳቱ እርምጃዎች እና የተሳሳቱ ስሌቶች ሊገኙ የሚችሉበት ብቻ ሳይሆኑ፣ በእርግጥም የሚገኙበት እንደሆነ የምናውቅበት እግዚአብሔር ሰጠሽ ላቦራቶሪ ናቸው። በህይወታችን መጨረሻ ላይ እነዚያ ግንኙነቶች እንዲሁም እነዚያ አስቸጋሪ ወቅቶች እንደ አዳኙ የበለጠ ለመሆን የረዱን ነገሮች መሆናቸውን ማየት መቻላችን አያስገርምምን? እያንዳንዱ አስቸጋሪ መስተጋብር ጥልቅ በሆነ ደረጃ ማለትም በእግዚአብሔር መሰል ደረጃ መልኩ ለማፍቀር የመማር እድል ነው።6

የቤተሰብ ግንኙነቶች እዚህ ለመማር የመጣንበትን ትምህርቶች እንደሚያስተምሩን እንደ ሀይለኛ አጋጣሚዎች ለመመልከት ወደ አዳኝ በመዞር አይታችንን እናስተካክል።

ይህን አምነን እንቀበል፣ በወደቀው አለም ውስጥ፣ ፍጹም የትዳር አጋር፣ ወላጅ፣ ወንድ ወይም ሴት ልጅ፣ የልጅ ልጅ፣ አስተማሪ ወይም ጓደኛ መሆን የሚቻልበት መንገድ የለም—ነገር ግን መልካም ለመሆን የሚቻልባቸው በሚሊዮን የሚቆጠሩ መንገዶች አሉ።7 ዛፉ ጋር እንቆይ፣ የእግዚአብሔርን ፍቅር እንቋድስ እንዲሁም ለሌሎች እናካፍለው። በዙሪያችን ያሉትን ሰዎች በመርዳት፣ አብረን ከፍ እንላለን።

በሚያሳዝን ሁኔታ፣ ፍሬውን የመብላት ትውስታ በራሱ በቂ አይደለም፤ እይታችንን በሚያስተካክል እና ከሰማይ አጠቃላይ እይታ ጋር በሚያገናኝ መልኩ በተደጋጋሚ መቋደስ ይኖርብናል፣ ይህንንም የምናደርገው፣ ጨለማውን ለማባረር በብርሃን የተሞሉትን ቅዱሳት መጻህፍት በመክፈት፤ ተራ ጸሎታችን ወደ ሃይለኛ እስቀሚቀየር ድረስ በጉልበታችን ተንበርክከን በመቆየት ነው። በዚህ ጊዜ ነው ልቦች የሚለሰልሱት እና እግዚአብሔር እንደሚመለከተው መመልከት የምንጀምረው።

በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት፣ ምናልባት የእኛ ታላቅ ስራ ከምናፈቅራቸው ጋር ሊሆን ይችላል— በእርኩስ አለም ውስጥ ከሚኖሩ መልካም ሰዎች። የእኛ ተስፋ እራሳቸውን የሚያዩበትን መንገድ እና እውነትኛ ማንነታቸውን ይቀይራል። እናም በዚህ የፍቅር እይታ አማካኝነት ማን እንደሚሆኑ ያዩታል።

ነገር ግን እኛ ወይም የምንወዳቸው ሰዎችበአንድ ላይ ወደ ቤት እንድንመለስ የማይፈልግ ጠላት አለ። እናም ጊዜ እና ውስን በሆኑ አመታት በተገደበ ፕላኔት ላይ ስለምንኖር8 እርሱም በጣም እውነት የሚመስልን ድንጋጤ ያስፋፋል። አቅርበን ስናይ ከፍጥነታችን በበለጠ አቅጣጫችን አስፈላጊ እንደሆነ ለማየት ያስቸግራል።

አስታውሱ፣ “ፈጥናችሁ ለመሄድ ከፈለጋችሁ፣ ብቻችሁን ሂዱ። እረጅም እርቀት ለመጓዝ ከፈለጋችሁ በአንድ ላይ ሂዱ።”9 ደስ የሚለው፣ የምናመልከው እግዚአብሔር በጊዜ የተገደበ አይለደም። እርሱም የምንወዳቸው ሰዎች በእውነት ማን እንደሆኑ፣ እኛ በእውነት ማን እንደሆንን ይመለከታል።10 ስለሆነም እርስ በእርስ ታጋሾች እንድንሆን ተስፋ በማድረግ እርሱ ለእኛ ትእግስት አለው።

ጊዜያዊ ቤታችን የሆነችው ምድር የሃዘን ደሴት እንደሆነች የሚሰማን ጊዜያት እንዳሉ አምናለሁ—አንደኛው ዓይኔ የእምነት ሌላኛው አይኔ ደግሞ እያነባ የነበረባቸውን ወቅቶችን አሳልፌአለው።11 ይህንን ስሜት ታውቃላችሁን?

ማክሰኞ ዕለት እንደዚያ ተሰምቶኝ ነበር።

በምትኩ በቤተሰቦቻችን ውስጥ ተአምራቶች እንደሚፈፀሙ ቃል የገቡትን የነቢያችንን ታማኝ አቋም መምረጥ እንችላለን? ይህን ካደረግን፣ ብጥብጥ ቢጨምርም እንኳን፣ ደስታችን ይጨምራል። ሁኔታዎቻችን ምንም ይሁኑ ምን፣ የአጠቃላይ እይታ ውጤት አሁን መለማመድ እንደሚቻል ቃል ገብቶልናል።12

በዚህ የእምነት አይን አሁን መኖር፣ ወደዚህ ፕላኔት ከመምጣታችን በፊት የነበረንን እምነት እንደገና መልሶ የሚያስገኝልን ወይም የሚያስተጋባ ነው። “በሃይላችን ያሉትን ነገሮች ሁሉ በደስታ [እንድናደርግ] ከዚያም … [እንድንቆም]” በመፍቀድ 13 የወቅትን ያልተረጋገጠ ነገር እንዳላየ ያልፋል።

በህይወታቹ ውስጥ አሁን ከባድ የሆነ ፣ የተጨነቃችሁበት መፍትሄ ሊያገኝ ያልቻለ ነገር አለን? የእምነት አይን ከሌለ፣ እግዚአብሔር በነገሮች ላይ ያለውን ቁጥጥር ያጣ ሊመስል ይችላል፣ እናም ያ እውነት ነውን?

ወይም የእናንተ ትልቅ ፍርሃት ይህንን ከባድ ጊዜ በራሳችሁ የምታሳልፉ ስለሚመስላችሁ ሊሆን ይችላል፣ ነገር ግን ያ ማለት እግዚአብሔር ተዋችሁ ማለት ሊሆን ነው እና ያ እውነት ነውን?

አዳኙ በእርሱ የኃጢያት ክፍያ አማካኝነት ማንኛውንም የምታሳልፉትን አስቻጋሪ ፈተና ወደ በረከት የመቀየር ችሎታ እንዳለው ምስክርነቴ ነው። እርሱም “በማይለወጥ ቃል ኪዳን” ይህን የተስፋ ቃል ይሰጣል፦ እርሱን ለማፍቀር እና ለመከተል ስንጥር፣ “[የተሰቃየንባቸው] ነገሮች ሁሉ [ለጥቅማችን] አብረው ይሰራሉ።”14 ሁሉም ነገሮች።

የቃል ኪዳኑ ልጆች በመሆናችን፣ ይህንን የተስፋ ስሜት አሁን መጠየቅ እንችላለን!

ቤተሰቦቻች ፍጹም ባይሆኑም፣ ምንም ይሁን ምን አይነት ፍቅር ማለትም ለውጥን የሚደግፍ እና እድገትን እና መመለስን የሚፈቅድ ፍቅር ቋሚ፣ የማይለወጥ እስኪሆን ድረስ ለሌሎች ያለንን ፍቅር ፍጹም ማድረግ እንችላለን።

ውዶቻችንን መልሶ ማምጣት የአዳኙ ስራ ነው። የእርሱ ስራ እና የእርሱ ሰአት ነው። ተስፋን እና ወደቤት የሚመጡበትን ልብን መስጠት የእኛ ስራ ነው። “ለመኮነን [የእግዚአብሔር] ስልጣን እንዲሁም ለማዳን ሃይሉ የለንም፣ ነገር ግን የእርሱን ፍቅር ለመለማመድ ስልጣኑ ተሰጥቶናል።”15 ፕሬዘደንት ኔልሰን ሌሎች ከእኛ ፍርድ ይልቅ ፍቅራችንን እንደሚፈልጉ አስተምረዋል። “በቃላችን እና በድርጊታችን ውስጥ የሚታየውን የኢየሱስ ክርስቶስ ንጹህ ፍቅር ሊሰማቸው ይገባል።”16

ልቦችን የሚቀይረው ነገር ፍቅር ነው። ከሁሉም የሚበልጥ ነገሮችን የማድረግ ንፁህ ምክንያት ነው እንዲሁም ሌሎች ሊሰማቸው ይችላል። ከ50 አመታት በፊት የተሰጡትን እነኚህን ነቢያዊ ቃላት አጥብቀን እንያዝ፦ “ለመጣር ካላቆመ በስተቀር፣ ምንም ቤት ወዳቂ አይደለም።”17 በእርግጥ፣ ከሁሉም የበለጠ እና ከሁሉም ለሚበልጥ ረጅም ጊዜ የሚወዱ ሰዎች ያሸንፋሉ!

አቅጣጫውን በመጠቆም እና የምንውዳቸው ሰዎች በዚያ አቅጣጫ ይጓዛሉ ብለን ተስፋ እያደረግን፣ የሚጓዙበትን መንገድ የሚመርጡት ራሳቸው መሆኑ እያወቅን በምድራዊ ቤተሰቦች ውስጥ፣ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር አድርጎ የነበረውን ነገር እያደረግን ነን።

እናም በመጋረጃው ሌላኛው ወገን በሞት ሲሄዱ እና ወደዚያ አፍቃሪ ወደ ሆነው የሰማይ ቤታቸው ሲቀርቡ፣18 እዚህ በመወደዳቸው ምክንያት ተመሳሳይ ስሜት እንደሚሰጥ አምናለሁ።

ያንን የአጠቃላይ እይታ እንጠቀም እና የምንወዳቸውን እና አብረናቸው የምንኖረውን ሰዎች በሂህች ውብ ፕላኔት ላይ እንደተሰጡን ጓደኞች እንመልከት።

እናንተ እና እኔ? ይህን ማድረግ እንችላለን! መታገስ እና ተስፋ ማድረግ እንችላለን! ዛፉ ጋር መቆየት፣ እና በፈገግታ ፍሬውን መቋደስ እና በአይናችን ውስጥ ያለውን የክርስቶስ ብርሃን በእነሱ የጨለማ ሰአቶች ሌሎች የሚተማመኑበት እንዲሆን መፍቀድ እንችላለን። በገጽታዎቻችን ላይ ብርሃንን ሲመለከቱ፣ ወደ እሱ ይሳባሉ። ከዚያም ትኩረታቸውን ዋና የፍቅር እና የብርሃን ምንጭ ወደሆነው “ወደሚያበራ[ው] የንጋት ኮከብ” ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ በድጋሚ እንዲያደርጉ መርዳት እንችላለን።19

ይህ ሁሉም እኛ ከምናስበው በበለጠ ሁኔታ እንደሚሳካ ምስክርነቴን እሰጣለሁ። የእምነትን አይን በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ በማድረግ፣ መጨረሻ ላይ ሁሉም ነገር መልካም እንደሚሆን እንመልከት እናም አሁን መልካም እንደሚሆን ይሰማን። በኢየሱስ ክርስቶስ ስም፣ አሜን።

ማስታወሻዎች

  1. Anousheh Ansari, in “The Overview Effect and Other Musings on Earth and Humanity, According to Space Travelers,” cocre.co.

  2. ኤተር 12፥19፤ አትኩሮት ተጨምሮበታል።

  3. See Jody Moore, “How to Say Hard Things,” Better than Happy (podcast), Sept. 18, 2020, episode 270.

  4. ሮናልድ ኢ. ባርታለሚው፣ በፈቃድ ተጠቅሜአለሁ፤ ደግሞም 1 ኔፊ 8፥1011፥21–22ን ይመልከቱ።

  5. See James D. MacArthur, “The Functional Family,” Marriage and Families, vol. 16 (2005), 14.

  6. እኛ “… በዚህ ፍቅር [እንሞላ] ዘንድ በሀይል ልባችን በመጸለይ]” ይህ እንዲቻል ለማድረግ እንችላለን (ሞሮኒ 7፥48)።

  7. ጂል ቸርችል ብላዋለች የተባለው አሳጥሮ የተጻፈ።

  8. See Richard Eyre, Life before Life: Origins of the Soul … Knowing Where You Came from and Who You Really Are (2000), 107.

  9. ባህላዊ ምሳሌ።

  10. ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 93፥24፣ 26ን ይመልከቱ።

  11. Robert Frost, “Birches,” in Mountain Interval (1916), 39 ተመልከቱ።

  12. ራስል ኤም. ኔልሰን፣ “ደስታ እና መንፈሳዊ ደህንነት፣” ሊያሆና፣ ህዳር 2016 (እ.አ.አ)፣ 81–84፤ ደግሞም ራስል ኤም. ኔልሰን፣ “እግዚአብሔር ያሸንፍ፣” ሊያሆና፣ ህዳር 2020 (እ.አ.አ)፣ 92–95 ይመልከቱ።

  13. ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 123፥17

  14. ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 98፥3፤ አትኩሮት ተጨምሮበታል።

  15. Wayne E. Brickey, Inviting Him In: How the Atonement Can Change Your Family (2003), 144.

  16. ራስል ኤም. ኔልሰን፣ “አስታራቂዎች ይፈለጋሉ፣” ሊያሆና፣ ግንቦት 2023 (እ.አ.አ.)፣ 100።

  17. Teachings of Presidents of the Church: Harold B. Lee (2000), 134.

  18. See Paul E. Koelliker, “He Truly Loves Us,” Liahona, May 2012, 18.

  19. ራዕይ 22፥16