አጠቃላይ ጉባኤ
ምስጋና ለሰውየው
የጥቅምት 2023 (እ.አ.አ) አጠቃላይ ጉባኤ


ምስጋና ለሰውየው

በዚህ በመጨረሻው ዘመን በነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ ምክንያት አሁን የምናውቀውን ሁሉ ለማወቅ በመቻላችን ምን ያህል ተባርከናል።

ውድ ወንድሞችና እህቶች፣ በዚህ ጠዋት ከእናንተ ጋር በመገኘቴ ክብር ይሰማኛል። ጌታ እንዲባርከኝ እጸልያለሁ።

ዓይኖቼ እንደ ቀድሞው አይደሉም። ሄድኩኝና የዓይን ሐኪሙ ጋር ቀረብኩ፣ ከዚያም “ቴሌፕሮምተሩን ማየት አልቻልኩም” አልኩት።

እርሱም እንዲህ አለኝ፣ “አይኖችዎ አርጅተዋል። ከዚህ በኋላ የማየት ችሎታቸው ሊሻሻል አይችልም።”

ስለዚህ፣ የምችለውን ያህል አደርጋለሁ።

በአእምሮዬ ውስጥ ያሉትን አንዳንድ ነገሮችን ላካፍላችሁ እፈልጋለሁ። ባለፉት ጥቂት ወራት ነቢዩ ጆሴፍን በአእምሮዬ ውስጥ አሰላስለው ነበር። የዚህ የዘመኑ ፍፃሜ ነቢይ የመሆን አስደናቂ ሀላፊነቱን ቁጭ ብዬ አሰላስያለሁ።

እንደ የኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን አባላት፣ ኃጢአቱ እንዲሰረይ ምን ማድረግ እንዳለበት ለማወቅ የፈለገ ልጅ፣ በፓልማይራ፣ ኒው ዮርክ በሚገኘው መኖሪያው አቅራቢያ ወዳሉት የዛፎች ቁጥቋጦ ለመግባት ድፍረት አግኝቶ፣ እና እዚያ ለጸሎት ተንበርክኮ፣ እና በራሱ መግለጫ ለመጀመሪያ ጊዜ ጮክ ብሎ ለጸለየው ትንሽ ልጅ፣ ጆሴፍ ስሚዝ ምን ያህል አመስጋኞች ነን ብዬ አስባለሁ (ጆሴፍ ስሚዝ—ታሪክ 1፥14 ይመልከቱ)።

በዚያ አጋጣሚ፣ ጆሴፍ ቅዱስ ቁጥቋጦ ብለን በምንጠራው ስፍራ ተንበርክኮ፣ ሰማያት ተከፈቱ። ከቀትር ፀሐይ የበለጠ ብሩህ የሆኑ ሁለት ሰዎች በፊቱ ታዩ። “እንደኛውም እንዲህ አለ፣ “[ጆሴፍ፣] ይህ የምወደው ልጄ ነው። አድምጠው!” (ጆሴፍ ስሚዝ—ታሪክ 1፥17)። እንደዚህም የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ሙላት በዳግም መመለስ ተጀመረ።

አዳኛችን እና ቤዛችን ኢየሱስ ብላቴናውን ጆሴፍን አነጋግሮት ስለነበር እና አሁን የምንኖርበትን የዘመን ፍጻሜ ስለከፈተ፣ “ከያህዌ ጋር የተነጋገረ ሰው ይመስገን!” ብለን እንዘምራለን። (“Praise to the Man,” Hymns, no. 27). ስለጆሴፍ ስሚዝ እና በ1820 በፓልማይራ፣ ኒው ዮርክ በሚገኘው ቤቱ አቅራቢያ ወደዚያ የዛፍ ቁጥቋጦ ለመግባት ስለነበረው ድፍረት ጌታን እናመሰግናለን።

ስለምናውቃቸው አስደናቂ ነገሮች እና ስላሉን ነገሮች ሁሉ እያሰብኩ ነበር። የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ፣ ዛሬ ጠዋት ለእናንተ የምመሰክረው እኛ የምናውቀውን ሁሉ ለማወቅ የተባረክንበት ምክንያቱም የዚህ የዘመን ፍጻሜ ነብይ ጆሴፍ ስሚዝ ስላለን ነበር።

ስለ ህይወት ዓላማ፣ ስለማንነታችን ግንዛቤ አለን።

እግዚአብሔር ማን እንደሆነ እናውቃለን፤ አዳኙ ማን እንደሆነ እናውቃለን፣ ምክንያቱም በልጅነቱ ወደ ዛፎች ቁጥቋጦ የገባ፣ ለኃጢአቱ ይቅርታ የሚፈልግ ጆሴፍ ስላለን።

በዚህ በኋለኛው ቀን የሰማይ አባታችን እና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እራሳቸውን እንደገለጡ እና ጆሴፍ የዘለአለም ወንጌልን ሙላት በዳግም ለመመለስ መነሳቱን ማወቅ በዚህ አለም ውስጥ ያለ ማንም ሰው ሊያውቀው ከሚችለው በላይ እጅግ የከበረ እና አስደናቂ የሆነ ነገር ይመስለኛል።

መፅሐፈ ሞርሞን አለን። መፅሐፈ ሞርሞን ለቤተክርስቲያኗ አባላት እንዴት ያለ የከበረ እና ድንቅ ስጦታ ነው። ይህም ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ ስለመሆኑ ሌላ ምስክር ነው። እኛ ይህን ያገኘንበት ምክንያት ጆሴፍ ሰሌዳዎችን ለመቀበል፣ ከሰማይ መነሳሳትን በመቀበል በእግዚአብሔር ስጦታና ኃይል ተርጉሞ መጽሐፉን ለዓለም ለመስጠት ብቁ ስለነበር ነው።

ምንም እንኳን የዛሬ ጠዋት መልእክቴ ቀላል ቢሆንም፣ ጥልቅ ነው፣ እንዲሁም በነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ እና በእነዚያ እርሱን በደገፉት ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንዲሁም በወጣትነቱ እሱን በደገፉት እና ለመደገፍ ፈቃደኛ በነበሩት ሠዎች ሁሉ ፍቅር የተሞላ ነው።

ዛሬ ጠዋት ለእናቱ ክብር መስጠት እፈልጋለሁ። ጆሴፍ በቅዱስ ቁጥቋጦው ከነበረው ከዚያ ልምድ ተመልሶ ወደ ቤት ሲመጣ እና ለእናቱ የሆነውን ነገር ሲነግራት፣ ሉሲ ማክ ስሚዝ እርሱን ማመኗ ምንኛ አስደናቂ እንደሆነ ሁልጊዜ አስብ ነበር።

የኢየሱስ ክርስቶስን ዘላለማዊ ወንጌል ሙላት በምድር ላይ እንደገና ለመመለስ ጌታ ነቢይ እንዲሆን ለእርሱ በሰጠው በዚህ ታላቅ ሀላፊነት ስለደገፉት አባቱ እና ወንድሞቹ እና እህቶቹ እንዲሁም ቤተሰቦቹ አመስጋኝ ነኝ።

ስለዚህ ዛሬ ጠዋት ምስክርነቴ ኢየሱስ ክርስቶስ የአለም አዳኝ እና ቤዛ እንደሆነ እንደማውቅ ነው። የሰማይ አባታችን እና ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደተገለጡ እና ጆሴፍን እንዳነጋገሩት እንዲሁም ነቢይ እንዲሆን እንዳዘጋጁት አውቃለሁ።

ብዙዎቻችሁም እንደምታደርጉ፣ ስለ ህይወታችን አላማ፣ ለምን እዚህ እንዳለን፣ በዕለት ተዕለት ህይወታችን ውስጥ ምን ለማድረግ እና ለማከናወን መሞከር እንዳለብን የምናውቀውን በማወቃችን ያን ያህል በመባረካችን እገረማለሁ። ቀን በቀን እኛ ራሳችንን ለማዘጋጀት፣ ትንሽ የተሻልን ለመሆን፣ ትንሽ ደግ ለመሆን፣ በእርግጠኝነት ወደ ሰማይ አባታችን እና ወደ ጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ለመመለስ ለሚመጣው ለዚያ ቀን ትንሽ የበለጠ ለመዘጋጀት እየሞከርን ነው።

ያም ጊዜ ለእኔ በመጠኑ ቀረብ ያለ ነው። በቅርብ 95 አመት ይሞላኛል። ልጆቼ አንዳንድ ጊዜ ከዚያ እድሜ በላይ እንደሆንኩኝ እንደሚሰማቸው ይነግሩኛል፣ ግን ያም ምንም አይደለም። ማድረግ የምችለውን ያህል እያደረኩኝ ነው።

ነገር ግን ለ50 ዓመታት፣ ወንድሞች እና እህቶች፣ እንደ የቤተክርስቲያኗ አጠቃላይ ባለስልጣን በተመደብኩበት ስራ ምክንያት በአለም ዙሪያየመጓዝ እድል አግኝቻለሁ። ይህም ግሩም በረከት ነበር። ሁሉንም የዓለም ክፍሎች ወደማየት ተቃርቤ የነበረ ይመስለኛል። በዓለም ዙሪያ ካሉ የቤተክርስቲያኗ አባላት ጋር ተገናኝቻለሁ።

እንዴት እንደምወዳችሁ። ፊቶቻችሁን መመልከት፣ በፊታችሁ መገኘት እንዲሁም ለጌታ እና ለኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ዳግም መመለስ ያላችሁን ፍቅር መሰማቱ እንዴት ያለ አስደሳች ተሞክሮ ነበር።

የሰማይ አባታችን አሁን ይጠብቀን እንዲሁም ሁሉንም የጉባኤ ሂደቶች ይባርክ። እናም በአጠቃላይ ጉባኤያችን በመገኘታችን ምክንያት የጌታ መንፈስ በልባችን ውስጥ ይትረፈረፍ፣ እንዲሁም —እርሱን ለማገልገል እና ትእዛዛቱን ለመጠበቅ እና የበለጠ እንደ እርሱ ለመሆን ስንጥርለኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል—ለተወደደው አዳኛችን፣ ለጌታ ለኢየሱስ ክርስቶስ ያለን ፍቅር ይጨምር። በዚህ አለም የትም ብትሆኑ እግዚአብሔር ይባርካችሁ። የጌታ መንፈስ ከእኛ ጋር ይሁን። በዚህ ጉባኤ ክፍለ-ጊዜ አብረን ስናመልክ የሰማይ ኃይል ይሰማን።

ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ እንደ ሆነ እንደማውቅ ምስክርነቴን እተውላችኋለሁ። እርሱ አዳኛችን እና ቤዛችን ነው። እውነተኛ ጓደኛችንም ነው። በተቀደሰው በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አሜን።