ምዕራፍ ፰
ሌሂ ስለ ሕይወት ዛፍ ራዕይ አየ—ከፍሬውም ተካፈለና ቤተሰቦቹም እንደዚያው እንዲያደርጉ ፈለገ—የብረት በትር፣ የጠበበና የቀጠነ መንገድና ሰዎችን የሚጋርደውን የጨለማ ጭጋግ ተመለከተ—ሳርያ፣ ኔፊና፣ ሳም፣ ፍሬውን ተካፈሉ፣ ላማንና ልሙኤል ግን ተቃወሙ። ከ፮፻–፭፻፺፪ ም.ዓ. ገደማ።
፩ እናም እንዲህ ሆነ ከሁሉም ዓይነት ዘሮች ሁሉንም የእህል ዓይነትና፣ ከሁሉም ዓይነት የፍራፍሬ ዘሮች በአንድነት ሰበሰብን።
፪ እናም እንዲህ ሆነ አባቴ በምድረበዳ በቆየበት ጊዜ እንዲህ ብሎ ተናገረን፥ እነሆ ህልምን አልሜአለሁ፣ ወይም በሌላ አባባል፣ ራዕይን አይቻለሁ።
፫ እናም እነሆ ባየሁት ነገር የተነሳ በኔፊና ደግሞም ስለሳም በጌታ የምደሰትበት ምክንያት አለኝ፣ እና እነርሱና ብዙዎቹ ዘሮቻቸው እንደሚድኑ ለመገመት ምክንያት አለኝ።
፬ ነገር ግን እነሆ ላማንና ልሙኤል፣ በእናንተ ምክንያት እጅግ እፈራለሁ፤ እነሆ በህልሜ ውስጥ ጨለማና የማያስደስት ምድረበዳ ማየቴን ተረዳሁ።
፭ እናም እንዲህ ሆነ አንድ ሰው አየሁ፣ ነጭ ልብስ ለብሶ ነበር፤ እናም መጥቶ በፊቴ ቆመ።
፮ እናም እንዲህ ሆነ እርሱም ተናገረኝ፣ እናም እንድከተለው ጋበዘኝ።
፯ እናም እንዲህ ሆነ እርሱን እንደተከተልኩት ራሴንም በጭለማ እና በማያስደስት ባድማ ውስጥ እንደነበርኩ ተመለከትኩ።
፰ እናም ለብዙ ሰዓታት በጨለማ ውስጥ ከተጓዝኩ በኋላ እንደምህረቱም ብዛት ጌታ በእኔ ላይ ምህረትን ያደርግ ዘንድ ፀለይኩ።
፱ እናም እንዲህ ሆነ ለጌታ ከፀለይኩ በኋላ፣ ትልቅና ሰፊ የሆነን ሜዳ ተመለከትኩ።
፲ እናም እንዲህ ሆነ ፍሬዋ አንድን ሰው ደስተኛ ለማድረግ መልካም የሆነችን ዛፍ ተመለከትኩ።
፲፩ እናም እንዲህ ሆነ ሄጄ ከፍሬዋ ተካፈልኩ፤ ከዚህ በፊት ከቀመስኩት ሁሉ ጣፋጭ እንደሆነች አየሁ። አዎን፣ ፍሬዋም ከዚህ በፊት ካየሁትም ንጣት ሁሉ በላይ ነጭ የሆነች ፍሬ እንደሆነች ተመለከትኩ።
፲፪ ከዚህች ፍሬ ስካፈልም ይህም ነፍሴን በደስታ ሞላው፣ ስለሆነም ቤተሰቦቼም ደግሞ ይካፈሉት ዘንድ መመኘት ጀመርኩ፤ ከሌላው ፍሬ ሁሉ በላይ አስፈላጊ እንደሆነ አውቃለሁና።
፲፫ እናም ቤተሰቤን ደግሞ ማግኘት እችል ዘንድ በዙሪያው ስመለከት፣ የወንዝ ውሃን ተመለከትኩ፤ ይወርድም ነበር፣ እና እኔ ፍሬውን ከበላሁበት ዛፍ አቅራቢያ ነበር።
፲፬ እናም ከየት እንደመጣም ለማየት ተመለከትኩ፣ ትንሽ ራቅ ብሎም ምንጩን አየሁ፤ እናታችሁ ሳርያን፣ ሳምንና፣ ኔፊን፣ በዚያው በምንጩ አየሁ፤ እነርሱም ወዴት መሄድ እንዳለባቸው እንደማያውቁ ሆነው ቆሙ።
፲፭ እናም እንዲህ ሆነ እኔ ጠቆምኳቸው፣ ወደ እኔ እንዲመጡና ከሌሎች ፍሬዎች ሁሉ በላይ መልካም የሆነውን ፍሬ፣ እንዲበሉ በከፍተኛ ድምፅ ነገርኳቸው።
፲፮ እናም እንዲህ ሆነ እነርሱ ወደ እኔ መጡና ደግሞ ፍሬውን በሉ።
፲፯ እናም እንዲህ ሆነ ላማንና ልሙኤልም እንዲመጡና ደግሞ ፍሬውን እንዲበሉ ተመኘሁ፣ ስለሆነም እንዳያቸው ዘንድ አይኖቼን ወደ ወንዙ ምንጭ ጣልኩኝ።
፲፰ እናም እንዲህ ሆነ እኔ አየሁአቸው፣ ነገር ግን እነርሱ ወደ እኔ አልመጡም፣ ፍሬውንም አልበሉም።
፲፱ እናም የብረት በትር ተመለከትኩ፣ በወንዙም ዳርቻ፣ እኔ ወደ ቆምኩበት ዛፍ ድረስ እንዲወስድ የተዘረጋ ነበር።
፳ እናም እኔ ወደ ቆምኩበት ዛፍ ከብረት በትሩ ጋር የሚወስድ የጠበበና የቀጠነ መንገድ ተመለከትኩ፣ ይህም ደግሞ በፏፏቴውም ምንጭ፣ ዓለምን ወደሚመስለው ትልቅና ሰፊ ሜዳ ያመራል።
፳፩ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሰዎችን አየሁ፣ እኔ ወደ ቆምኩበት ዛፍ የሚያደርሰውን መንገድ ለማግኘት አብዛኞቹ ወደፊት ይገፉ ነበር።
፳፪ እናም እንዲህ ሆነ መጡ፣ እና ወደዛፉ በሚያመራው መንገድ ወደፊት ተጓዙ።
፳፫ እናም እንዲህ ሆነ የጨለማ ጭጋግ ተነሳ፣ አዎን በመንገዱ ጉዞ የጀመሩት መንገዳቸውን እስኪስቱና ተንከራተው እስኪጠፉ ድረስ እጅግ ታላቅ የጨለማ ጭጋግ ተነሳ።
፳፬ እናም እንዲህ ሆነ ሌሎች ደግሞ ወደፊት ሲጋፉ አየሁ፣ እናም እነርሱም ወደፊት መጡና የብረት በትሩን ጫፍ ያዙ፣ የብረቱን በትር ተጠግተው በጨለማው ጭጋግ ውስጥ ወደፊት መጥተው የዛፉን ፍሬ እስኪካፈሉ ድረስ ወደፊት ገፉ።
፳፭ እናም ከዛፉ ፍሬ ከተካፈሉ በኋላ ያፈሩ በመምሰል አይኖቻቸውን ወደ እዚህና ወደ እዚያ ጣሉ።
፳፮ እኔም ደግሞ አይኖቼን በዙሪያው ጣልኩኝ፣ እና ከውሃው ወንዝ ባሻገር፣ ትልቅና ሰፊ ህንፃን ተመለከትኩ፤ ከምድር ከፍ ብሎ በአየር ላይ የቆመ ይመስል ነበር።
፳፯ እናም በአረጋውያን ጎልማሳም፣ በወንድም በሴትም ሰዎች ተሞልቶ ነበር፣ አለባበሳቸውም እጅግ ያማረ ነበር፤ ፍሬውንም መጥተው ወደበሉት ላይ እጃቸውን እየጠቆሙና እየተሳለቁባቸው ነበር።
፳፰ በእነዚያ በሚያላገጡባቸውም ምክንያት፣ ፍሬውን ከቀመሱ በኋላ አፈሩ፤ ወደተከለከለውም መንገድ ገቡና ጠፉ።
፳፱ እና አሁን እኔ፣ ኔፊ፣ የአባቴን ቃላት በሙሉ አልናገርም።
፴ ነገር ግን፣ ፅሁፉን ለማሳጠር፣ እነሆ ብዙ ሌሎችም ወደፊት ሲጋፉ አየ፤ መጥተው የብረት በትሩን ጫፍ ያዙ፣ እና ወደፊት መጥተው እስኪወድቁና የዛፉን ፍሬ እስኪካፈሉና እስኪወድቁ ድረስ መንገዳቸውን ወደፊት በመቀጠል ያለማቋረጥም የብረቱን በትር አጥብቀው ያዙ።
፴፩ እና ደግሞ ሌሎችም ብዙዎች ወደትልቁና ሰፊው ህንፃ መንገዳቸውን ሲያቀኑ አየ።
፴፪ እናም እንዲህ ሆነ ብዙዎች ወደ ፏፏቴው ጥልቅ ሲመጡ፤ እና ብዙዎች ደግሞ በማይታወቅ መንገድ ገብተው ሲቅበዘበዙ ከዕይታው ጠፉ።
፴፫ እና ወደ ማይታወቀው ህንፃ የገቡት ታላቅ ብዛት ነበራቸው። ወደ ህንፃው ከገቡም በኋላ በእኔና ፍሬውን ይካፈሉ በነበሩት ላይ ደግሞ የፌዝ ጣታቸውን ይጠቁሙ ነበር፤ ነገር ግን እኛ አላደመጥናቸውም።
፴፬ እነዚህ የአባቴ ቃላት ነበሩ፥ ያደመጡዋቸው በሙሉ ጠፍተዋል።
፴፭ እና አባቴ ላማንና ልሙኤል ፍሬውን አልተካፈሉም አለ።
፴፮ እናም እንዲህ ሆነ አባቴ ብዙ የነበሩትን የህልሙን ወይንም የራዕዩን ቃላት ከተናገረ በኋላ፣ ለእኛ እንዲህ አለን፣ በራዕዩ ባየው ነገር የተነሳ፣ ለላማንና ለልሙኤል በእጅጉ ፈራላቸው፣ አዎ፣ ከጌታ ፊት እንዳይጣሉ ፈራላቸው።
፴፯ እና ምናልባት ጌታ ለእነርሱም መሐሪ እንዲሆንላቸውና እንዳይጥላቸው ዘንድ፣ የእርሱን ቃላት እንዲሰሙ በአፍቃሪ ወላጅ ሙሉ ስሜት መከራቸው፤ አዎን፣ አባቴ ለእነርሱ ሰበከላቸው።
፴፰ እናም ለእነርሱ ከሰበከላቸውና፣ ብዙ ነገሮችን ለእነርሱ ከተነበየላቸው በኋላ፣ የጌታን ትዕዛዛት እንዲጠብቁ አዘዛቸው፣ እናም ለእነርሱ መናገርን አቆመ።