ቅዱሳት መጻህፍት
፩ ኔፊ ፯


ምዕራፍ ፯

የሌሂ ወንዶች ልጆች ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሰው እስማኤልንና ቤተሰቦቹን አብረዋቸው እንዲጓዙ ጋበዙአቸው—ላማንና ሌሎቹ አመፁ—ኔፊ ወንድሞቹን በጌታ እምነት እንዲኖራቸው መከራቸው—በገመድ አሰሩት እናም የእርሱን ጥፋት አቀዱ—በእምነት ሀይል እርሱ ነፃ ሆነ—ወንድሞቹ ይቅርታን ጠየቁ—ሌሂና አብረውት የነበሩትም የሚቃጠለውን መስዋዕት አቀረቡ። ከ፮፻–፭፻፺፪ ም.ዓ. ገደማ።

እና አሁን ይህንን እንድታውቁት እፈልጋለሁ፣ አባቴ፣ ሌሂ፣ ስለ ዘሩ መተንበይን ከጨረሰ በኋላ እንዲህ ሆነ፤ ሌሂ ቤተሰቦቹን ብቻ ወደ ምድረበዳ መውሰድ እንደማይገባው ነገር ግን ወንድ ልጆቹ ሴት ልጆችን ለሚስትነት እንዲወስዱና፣ ለጌታ ዘርን በቃልኪዳኑ ምድር እንዲያሳድጉ ጌታ በድጋሚ ነገረው።

እናም እንዲህ ሆነ እኔ፣ ኔፊና፣ ወንድሞቼ፣ ተመልሰን ወደ ኢየሩሳሌም ምድር መሄድ እንዳለብን፣ እናም እስማኤልንና ቤተሰቡን ወደ ምድረበዳ እንድናመጣቸው ጌታ አዘዘው

እናም እንዲህ ሆነ እኔ፣ ኔፊ፣ እንደገና ከወንድሞቼ ጋር፣ ወደ ኢየሩሳሌም ለመመለስ ወደ ምድረበዳ ወጣን።

እናም እንዲህ ሆነ ወደ እስማኤል ቤት ድረስ ሄድን፣ በእስማኤልም ፊት ታላቅ ሞገስን በማግኘታችን፣ የጌታን ቃል ለእርሱ ተናገርን።

እናም እንዲህ ሆነ ጌታ የእስማኤልንና የቤተሰዎቹን ልብ ከማራራቱ የተነሳ ወደ ምድረበዳ ወደ አባታችን ድንኳን ከእኛ ጋር ተጓዙ።

እናም በምድረበዳ ስንጓዝ፣ እነሆ ላማንና ልሙኤል፣ ሁለቱ የእስማኤል ሴት ልጆች፣ ሁለቱ የእስማኤል ወንዶች ልጆቹና ቤተሰቦቻቸው በእኛ ላይ አዎን፣ በእኔ፣ በኔፊና፣ በሳም፣ በአባታቸው በእስማኤልና በሚስቱና በሌሎች ሶስት ሴቶች ልጆቹ ላይ አመፁ።

እናም በዚህ በአመፃቸው የተነሳ ወደ ኢየሩሳሌም ምድር ለመመለስ ፈለጉ።

እና አሁን እኔ፣ ኔፊ፣ በልባቸው ጠጣርነት በማዘን፣ እንዲህ ስል ተናገርኳቸው፥ አዎን፣ ለላማንና ለልሙኤልም እንኳ፤ እነሆ እናንተ የእኔ ታላቅ ወንድሞቼ ናችሁ፣ እንዴት በልባችሁ ጠጣር፣ በአዕምሮአችሁ እውር ሆናችሁ፣ እና እኔ ታናሽ ወንድማችሁ ለእናንተ ልናገርና፣ አዎን፣ እና ምሳሌን ላስቀምጥላችሁ ይገባኛልን?

እንዴት ነው የጌታን ቃል ያላዳመጣችሁት?

እንዴት ነው የጌታን መልአክ ማየታችሁን የረሳችሁት?

፲፩ አዎ፣ ጌታ ከላባን እጅ ሲያወጣን፣ እና ደግሞ መዝገቦቹን እንድናገኝ ሲል ምን ታላላቅ ነገሮችን እንዳደረገልንስ እንዴት ረሳችሁት?

፲፪ አዎን፣ ጌታ ለሰዎች ልጆች፣ በእርሱ ታማኝ እስከሆኑ ድረስ፣ ሁሉንም ነገሮች በፈቃዱ ለማድረግ እንደሚችል እንዴት እረሳችሁ? ስለዚህ ለእርሱ ታማኞች እንሁን።

፲፫ እኛም ለእርሱ ታማኞች ከሆንን የቃልኪዳኗን ምድር እናገኛለን፤ እናም ወደ ፊት አንድ ቀን የኢየሩሳሌምን መጥፋት በተመለከተ የጌታ ቃል እንደሚሟላ እናንተ ታውቃላችሁ፤ ሁሉም ስለኢየሩሳሌም መጥፋት ጌታ የተናገራቸው ነገሮች መፈጸም አለባቸውና።

፲፬ እነሆም የጌታ መንፈስ ከእነርሱ ጋር መስራትን በቅርብ ያቆማል፤ እነሆ እነርሱ ነቢያትን ተቃውመዋልኤርምያስን ወደ ወህኒ ጨምረዋል። እናም ከምድሪቱ እስከማባረር ድረስም የአባቴን ህይወት ለማጥፋት ፈልገዋል።

፲፭ አሁንም እነሆ እላችኋለሁ ወደ ኢየሩሳሌም ብትመለሱ እናንተም ደግሞ ከእነርሱ ጋር ትጠፋላችሁ። አሁንም በምርጫችሁ ወደ ምድሪቱም ሂዱ፣ እናም እኔ ለእናንተ የተናገርኩትን ቃላቶች አስታውሱ፣ የምትሄዱ ከሆነ ትጠፋላችሁ፤ ይህንንም እናገር ዘንድ የጌታ መንፈስ ገፋፍቶኛልና።

፲፮ እናም እንዲህ ሆነ እኔ ኔፊ እነዚህን ቃላት ለወንድሞቼ ስናገር በእኔ ተቆጡ። እነሆም እንዲህ ሆነ በእጃቸው ያዙኝ፣ እነሆ፣ እጅግ ተናደው ነበር፣ እና በምድረበዳ ውስጥ ትተውኝ በዱር አውሬ እንድበላ ዘንድ ህይወቴን ለማጥፋት ስለፈለጉ በገመድም አሰሩኝ

፲፯ ነገር ግን እንዲህ ሆነ ለጌታ እንዲህ ብዬ ፀለይኩ፥ አቤቱ ጌታ በአንተ ባለኝ እምነት መሰረት ከወንድሞቼ እጅ ታድነኛለህ፤ አዎን የታሰርኩበትንም እስር እበጣጥሰው ዘንድ ጥንካሬን ስጠኝ።

፲፰ እናም እንዲህ ሆነ እነዚህን ቃላት በተናገርኩ ጊዜ እስሩ ከእጆቼና ከእግሬ ላይ ተፈታ፣ እናም ከወንድሞቼ ፊት ቆምኩና፣ እንደገና ተናገርኳቸው።

፲፱ እናም እንዲህ ሆነ እነርሱ እንደገና በእኔ ላይ ተቆጡ፣ እናም እጃቸውን ሊያሳርፉብኝ ፈለጉ፤ ነገር ግን እነሆ ከእስማኤል ሴት ልጆች አንዷ፣ አዎን፣ ደግሞም እናቷና ከእስማኤል ወንዶች ልጆች አንዱ፣ የእኔ ወንድሞች ልባቸው እስኪራራ ድረስ ለመኑዋቸው፤ ህይወቴንም ለማጥፋት መፈለጋቸውን አቆሙ።

እናም እንዲህ ሆነ እነርሱ በክፋታቸው፣ ምክንያት አዘኑ፣ ስለዚህ በእኔ ላይ ባደረጉት ነገር ይቅርታ እንዳደርግላቸው በፊቴ አጎንብሰው ለመኑኝ።

፳፩ እናም እንዲህ ሆነ እነርሱ ባደረጉት ነገር ሁሉ በእውነት ይቅርታ አደረኩላቸው፣ እናም ይቅር ይላቸው ዘንድ ለጌታ ለአምላካቸው እንዲፀልዩ መከርኳቸው። እናም እንዲህ ሆነ እነርሱም እንዲሁ አደረጉ። እናም ወደ ጌታ ከፀለዩ በኋላ እንደገና ወደአባታችን ድንኳን ጉዞአችንን አደረግን።

፳፪ እናም እንዲህ ሆነ ወደ አባታችን ድንኳን ወረድን። እናም እኔና ወንድሞቼና የእስማኤል ቤት ሁሉ ወደ አባቴ ድንኳን ከወረድን በኋላ እነርሱ ለጌታ ለአምላካቸው ምስጋናን አቀረቡ፤ መስዋዕትንና የሚቃጠለውንም መስዋዕት አቀረቡለት።