ቅዱሳት መጻህፍት
፩ ኔፊ ፪


ምዕራፍ ፪

ሌሂ ቤተሰቡን በቀይ ባሕር በኩል ወደ ምድረበዳ ወሰደ—ንብረታቸውንም ተዉ—ሌሂ መስዋዕትን ለጌታ አቀረበ፣ እናም ወንዶች ልጆቹን ትዕዛዛትን እንዲጠብቁ አስተማረ—ላማን እና ልሙኤል በአባታቸው ላይ አጉረመረሙ—ኔፊ ታዛዥና በእምነትም የሚፀልይ ነው፣ ጌታም እርሱን ተናገረው እና በወንድሞቹም ላይ እንዲገዛ ተመረጠ። ፮፻ ም.ዓ. ገደማ።

እነሆ እናም እንዲህ ሆነ፣ ጌታ ለአባቴ ተናገረው፣ አዎን በህልሙም እንኳን እንዲህ አለው፥ ሌሂ፣ ባደረግሃቸው ነገሮች ምክንያት የተባረክህ ነህ፣ እንዲሁም አንተ ታማኝ በመሆንህና ለዚህ ሕዝብ ያዘዝኩህን ነገሮች በመግለፅህ ምክንያት እነሆም ሕይወትህን ሊያጠፉ ይፈልጋሉ።

እናም እንዲህ ሆነ፣ ጌታ አባቴን በህልሙም ጭምር ቤተሰቡን ይዞ ወደ ምድረበዳ እንዲሄድ አዘዘው

እናም እንዲህ ሆነ እርሱ ለጌታ ቃል ታዛዥ ነበር፣ ስለዚህ ጌታ እንዳዘዘው አደረገ።

እናም እንዲህ ሆነ ወደ ምድረበዳ ሄደ። እናም ቤቱን፣ የወረሰውን መሬት፣ ወርቁንና ብሩን፣ ውድና የከበሩ ነገሮቹን ተወ፣ እንዲሁም ከቤተሰቡ፣ ከስንቆችና፣ ከድንኳኖች በስተቀር ከእርሱ ጋር ምንም ሳይወስድ ወደ ምድረበዳ ሄደ

እናም በቀይ ባሕር ወዳለው ዳርቻ መጣ፤ ለቀይ ባሕር ቅርብ በሆነው ዳርቻ በምድረበዳ ውስጥ ተጓዘ፣ እናም በምድረበዳ ውስጥ እናቴን ሳርያንና ታላቅ ወንድሞቼ የነበሩት ላማን፣ ልሙኤልና ሳምን ያካተተውን ቤተሰቦቹን ይዞ ወደ ምድረበዳ ተጓዘ።

እናም እንዲህ ሆነ ለሶስት ቀን በምድረበዳ ከተጓዘ በኋላ፣ የወንዝ ውሃ ባለበት ሸለቆ አጠገብ ድንኳኑን ተከለ።

እናም እንዲህ ሆነ የድንጋይ መሠዊያን ሠራ፣ ለጌታም መስዋዕትን አደረገ፣ እናም ለጌታ ለአምላካችን ምስጋና አቀረበ።

እናም እንዲህ ሆነ የወንዙንም ስም ላማን ብሎ ጠራው፣ እና ወደ ቀይ ባሕር ይፈስ ነበር፤ ሸለቆውም በወንዙ ዳርቻ አጠገብ ጫፍ ላይ ነበር።

እናም አባቴ የወንዙ ውሃ ወደ ቀይ ባሕር ምንጭ መፍሰሱን ባየ ጊዜ ለላማን እንዲህ ብሎ ተናገረው፥ አንተ ልክ እንደዚህ ወንዝ የሁሉም ፅድቅ ምንጭ ወደሆነው ያለማቋረጥ እንድትፈስ ዘንድ ምን ያህል እመኛለሁ!

እናም ለልሙኤልም ተናገረው፥ አንተ ልክ እንደዚህ እንደሸለቆ የጌታን ትዕዛዝ በመጠበቅ ጠንካራ፣ ፅኑና፣ የማትነቃነቅ እንድትሆን እመኛለሁ!

፲፩ በላማንና በልሙኤል አንገተ ደንዳናነት ምክንያት እርሱ ይህንን ተናግሯል፤ እነሆም እነርሱ በአባታቸው ላይ በብዙ ነገሮች አጉረምርመዋል፣ ምክንያቱም እርሱ ባለራዕይ ሰው ስለነበረ፣ እና የውርስ ምድራቸውንና ወርቃቸውንና፣ ብራቸውንና፣ የከበሩ ነገሮቻቸውን ትተው በምድረበዳ እንዲጠፉ ከኢየሩሳሌም ምድር እንዲወጡ ስላደረገ ነበር። እናም እርሱ ይህን ያደረገው በከንቱ የልቡ ሀሳብ ምክንያት ነው አሉ።

፲፪ እናም ላማንና ልሙኤል ታላቅ በመሆናቸው በአባታቸው ላይ አጉረመረሙ። እና ይህንን ያጉረመረሙት የዚያን የፈጠራቸውን አምላክ ሥራዎች ስላላወቁ ነበር።

፲፫ እንደ ነቢያት ቃል ታላቋ ከተማ ኢየሩሳሌም እንደምትጠፋ አላመኑም ነበር። እናም እነርሱ ልክ በኢየሩሳሌም የአባቴን ሕይወት ለማጥፋት እንደፈለጉት አይሁዶች ነበሩ።

፲፬ እናም እንዲህ ሆነ አባቴ በልሙኤል ሸለቆ ውስጥ በመንፈስ በመሞላቱ ምክንያት ሰውነታቸው እስኪንቀጠቀጥ ድረስ በኃይል ተናገራቸው። እናም እርሱን ለማናገር ድፍረት እስኪያጡ ድረስ ዝም አሰኛቸው፤ ስለዚህ እርሱ እንዳዘዛቸው አደረጉ።

፲፭ እናም አባቴ በድንኳን ውስጥ ኖረ።

፲፮ እናም እንዲህ ሆነ እኔ፣ ኔፊ፣ እጅግ ወጣት ነበርኩ፣ ሆኖም በአቋሜ ትልቅ ነበርኩ፣ እናም የእግዚአብሔርን ሚስጥሮች የማወቅ ፍላጎቴ ትልቅ ነበር፣ ስለዚህ፣ ወደ ጌታ ጮህኩ፤ እናም እነሆ እርሱ ጎበኘኝ፣ እኔም አባቴ የተናገራቸውን ቃላት ሁሉ እንዳምን ዘንድ ልቤንም አባባው፤ ስለዚህ፣ እኔ እንደ ወንድሞቼ በእርሱ ላይ አላመፅኩም።

፲፯ እናም ጌታም በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት ለእኔ ስለገለፃቸው ነገሮች እንዲያውቅ በማድረግ ሳምን አነጋገርኩት። እናም እንዲህ ሆነ በእኔ ቃላት አመነ።

፲፰ ነገር ግን እነሆ ላማንና ልሙኤል የእኔን ቃላት አላዳመጡም፤ እናም በልባቸው ጠጣርነት የተነሳ አዝኜ ለእነርሱ ወደ ጌታ ጮህኩ።

፲፱ እናም እንዲህ ሆነ ጌታ እንዲህ ሲል ተናገረኝ፥ በእምነትህ የተነሳ በትሁት ልብህ አጥብቀህ ፈልገኸኛልና አንተ ኔፊ የተባረክህ ነህ።

እና ትዕዛዛቴን እስከጠበቅህ ድረስ ትበለፅጋለህ፣ ወደ ቃል ኪዳንም ምድር፣ አዎን እንዲያውም እኔ ወደ አዘጋጀሁልህ ምድር፣ አዎን ከሌሎች ምድር ሁሉ በላይ ወደተመረጠች ምድር ትመራለህ።

፳፩ እናም ወንድሞችህ በአንተ ላይ እስከዐመፁ ድረስ ከጌታ ፊት ይለያሉ

፳፪ እናም አንተ ትዕዛዛቴን እስከጠበቅህ ድረስ በወንድሞችህ ላይ አለቃና መምህር ትሆናለህ።

፳፫ እነሆ እነርሱ በእኔ ላይ በሚያምፁበት ጊዜ በከባድ እርግማን እረግማቸዋለሁ፣ እናም እነርሱ በእኔም ላይ ካላመፁ በቀር፣ በዘሮችህ ላይ ምንም ኃይል አይኖራቸውም።

፳፬ እናም እነርሱ በእኔ ላይ የሚያምፁም ከሆነ፣ ለማስታወስ እንዲያነሳሷቸው፣ ለዘርህ የሚያውኩ ጅራፍ ይሆናሉ።