ቅዱሳት መጻህፍት
፩ ኔፊ ፳


ምዕራፍ ፳

ጌታ ዓላማውን ለእስራኤል ገለጠ—እስራኤልም በመከራ እቶን ተመረጠች፣ እናም ከባቢሎን ትወጣለች—ኢሳይያስ ፵፰ን አነጻፅሩ። ከ፭፻፹፰–፭፻፸ ም.ዓ. ገደማ።

፩ እናንተ በእስራኤል ስም የተጠራችሁ እናንተ ከይሁዳ ውኃ ይሁን ከጥምቀት ውኃ የወጣችሁ፣ በጌታ ስም የምትምሉ፣ በእውነት ሳይሆን፣ በፅድቅ ሳይሆን የእስራኤልን አምላክ የምትጠሩ የያዕቆብ ቤት ሆይ ይህን ስሙ እናም አድምጡ።

፪ ይሁን እንጂ በቅድስት ከተማ ስም እራሳቸውን ይጠራሉ፣ ነገር ግን የሰራዊት ጌታ በሆነው በእስራኤል አምላክ ላይ አይደገፉም፤ አዎን፣ የሰራዊት ጌታ የእርሱ ስም ነው።

፫ እነሆ የቀድሞውን ነገሮች ከጥንት ጀምሮ ተናግሬአለሁ፤ ከአፌም ወጥተዋል፣ አሳይቼአቸዋለሁ። በድንገትም አሳየኋቸው።

፬ እናም ይህንን ያደረግሁት አንተ እልከኛ፣ አንገትህም የብረት ጅማት፣ ግንባርህም ናስ እንደሆነ ስለማውቅ ነው፤

፭ እናም ጣኦቴ ይህን አድርጓል፣ የተቀረፀው ምስሌ፣ ቀልጦ የተሰራው ምስሌ እነዚህን አዘዘኝ እንዳትል ፈርቼ አስቀድሜ ነግሬህ ነበር፤ ሳይሆንም አስተምሬህ ነበር።

፮ ይህን ሁሉ ተመልክተሀልና ሰምተሀል፤ እናም አንተ አትናገራቸውምን? አዲስ ነገሮች፣ እንዲሁም የተደበቁትንም ነገሮች፣ ከዚህ ጀምሮ አሳይቼህ ነበር፣ እና አንተ አላወቅሀቸውም።

፯ እነርሱም አሁን እንጂ ከጥንት ጀምሮ አልተፈጠሩም፣ አንተም እነሆ፥ አውቄአቸዋለሁ እንዳትል ስለእነዚህ ከመስማትህ በፊት ለአንተ ተገልጠውልህ ነበር።

፰ አዎን እናም አልሰማህም፣ አዎን አላወቅህም፤ አዎን ጆሮህም በዚያን ጊዜ አልተከፈተም፣ ምክንያቱም አንተ ፈፅሞ ወንጀለኛ እንደሆንክ ከማህፀንም ጀምሮ ህግን ተላላፊ ተብለህ እንደተጠራህ አውቃለሁና።

፱ ይሁን እንጂ ስለስሜ ቁጣዬን አዘገያለሁ፣ ስለምስጋናዬም ስል እንዳላጠፋህ ዘንድ እለይሃለሁ።

፲ ምክንያቱም እነሆ አንጥሬሀለሁ፣ በመከራም እቶን መርጬሀለሁ።

፲፩ ስለእኔ አዎን ስለራሴ ይህን አደርገዋለሁ፣ ምክንያቱም ስሜ እንዲነቀፍ አልፈቅድም፣ እናም ክብሬንም ለሌላ አልሰጥም።

፲፪ ያዕቆብ ሆይ፣ የጠራሁህም እስራኤል ሆይ ስሙኝ፣ ምክንያቱም እኔ ነኝና፤ እኔ የፊተኛው እናም ደግሞ እኔ መጨረሻው ነኝ።

፲፫ እጄም ደግሞ የምድርን መሰረት መስርታለች፣ ቀኝ እጄም ሰማያትን ዘርግታለች። ጠራኋቸው እናም በአንድ ላይ ቆሙ።

፲፬ እናንተ ሁሉ በአንድ ላይ ተሰብስባችሁ አድምጡ፤ ከእነርሱ እነዚህን ነገሮች ያወጀላቸው ማን ነው? ጌታ እርሱንም ወድዶታል፤ አዎን እርሱም በእነርሱ የተናገረውን ቃል ይፈፅማል፣ እርሱም እንደሚያስደስተው በባቢሎን ላይ ያደርጋል፣ ክንዱም በከለዳውያን ላይ ይሆናል።

፲፭ ደግሞም ጌታ እንዲህ ይላል፤ እኔ ጌታ አዎን እኔ ተናገርኩ፤ አዎን እርሱን እንዲያውጅ ጠራሁት፣ አምጥቼውማለሁ፣ መንገዱንም ቀና ያደርጋል።

፲፮ ወደ እኔ ቅረቡ፣ እኔ በስውር አልተናገርኩም፤ ከጥንት ጀምሮ፣ ከታወጀበት ጊዜ አንስቶ እኔ ተናገርኩ፣ እናም ጌታ እግዚአብሔርና መንፈሱ ልከውኛል።

፲፯ እናም መዳኒትህ፣ የእስራኤል ቅዱስ ጌታ እንዲህ ይላል፤ የሚረባህን ነገር የማስተምርህ፣ በምትሄድበትም መንገድ የሚመራህ እኔ ጌታህ እግዚአብሔር ልኬዋለሁ።

፲፰ አቤቱ ትዕዛዛቴን ብትሰማ ኖሮ ሰላምህ እንደወንዝ፣ ፅድቅህም እንደባህር ሞገድ ይሆን ነበር።

፲፱ ዘርህም ደግሞ እንደ አሸዋ በሆነ ነበር፤ የሆድህም ትውልድ እንደባህር ጠጠር በሆነ ነበር፤ ስሙም ከፊቴ ባልጠፋ ወይም ባልፈረሰ ነበር።

፳ ከባቢሎን ውጡ፣ ከከለዳውያንም ኮብልሉ፣ በእልልታ ድምፅ ተናገሩ፣ ይህንም ተናገሩ እስከምድር ዳርቻ ድረስ አውሩ፤ ጌታ ባርያውን ያዕቆብን ታድጎታል በሉ።

፳፩ እናም አልተጠሙም ነበር፤ በበረሃ ውስጥ መራቸው፤ ውሃውንም ከዓለቱ ውስጥ አፈለቀላቸው፤ ዓለቱንም ደግሞ ሰነጠቀውና ውኃው ፈለቀ።

፳፪ እናም ይህንን ሁሉና፣ ደግሞ ታላቅ ነገር ቢያደርግም፣ ለክፉዎች ሰላም የላቸውም ይላል ጌታ።