ምዕራፍ ፮
ንጉስ ቢንያም የህዝቡን ስም መዘገበ እናም እነርሱን የሚያስተምሩ ካህናትን ሾመ—ሞዛያ ፃድቅ ንጉስ በመሆን ነገሰ። ከ፻፳፬–፻፳፩ ም.ዓ. ገደማ።
፩ እናም አሁን፣ ንጉስ ቢንያም ለህዝቡ ንግግሩን ከጨረሰ በኋላ፣ የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት ለመጠበቅ ቃል ኪዳን የገቡትን ሁሉ ስም መመዝገቡ ጠቃሚ እንደነበር አሰበ።
፪ እናም እንዲህ ሆነ ከትናንሽ ህፃናት በስተቀር፣ ነገር ግን ወደ ቃል ኪዳኑ ያልገባና የክርስቶስን ስም ያልለበሰ አንድም ነፍስ አልነበረም።
፫ እናም እንደገና፣ እንዲህ ሆነ ንጉስ ቢንያም እነዚህን ነገሮች ሁሉ ሲጨርስ፣ እናም ልጁን ሞዛያን በህዝቡ ላይ ገዢና ንጉስ አድርጎ ከቀድሰውና መንግስቱን በተመለከተ ሁሉንም ሃላፊነት ከሰጠው፣ ደግሞም የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት ያደምጡና ያውቁ ዘንድ እናም የፈፀሙትን መሀላ እንዲያስተውሉ ለማነሳሳት ካህናት ህዝቡን እንዲያስተምሩ ከሾማቸው በኋላ፣ ህዝቡን አሰናበተ፣ እናም ሁሉም ከየቤተሰቦቻቸው ጋር ወደየቤታቸው ተመለሱ።
፬ እናም ሞዛያ በአባቱ ቦታ መንገስ ጀመረ። እናም ንግስናውን በሰላሳ አመቱ ጀመረ፣ ይኸውም ሌሂ ኢየሩሳሌምን ለቆ ከወጣ ጊዜ በአጠቃላይ አራት መቶ ሰባ ስድስት አመት ገደማ ይሆናል።
፭ እናም ንጉስ ቢንያም ለሶስት ዓመታት ኖረ፣ እናም ሞተ።
፮ እናም እንዲህ ሆነ ንጉስ ሞዛያ በጌታ መንገድ ተራምዷል፣ የጌታን ፍርድና ስርአት አስተውሏልም፣ እናም በሁሉም ነገሮች እርሱ ያዘዘውን ጠብቋል።
፯ እናም ንጉስ ሞዛያ ህዝቡ መሬትን እንዲያርስ አደረገ። እናም ደግሞ ለህዝቡ ሸክም እንዳይሆን በሁሉም ነገር አባቱ እንዳደረገው ያደርግ ዘንድ እራሱም መሬትን ያርስ ነበር። እናም ለሶስት ዓመታት ያህል በህዝቡ ሁሉ መካከል ጠብ አልነበረም።