ምዕራፍ ፫
በልባቸው ንፁህ የሆኑ የሚያስደስተውን የእግዚአብሔርን ቃል ይቀበላሉ—የላማናውያን ፅድቅ ከኔፋውያን ይልቃል—ያዕቆብ ሳያገቡ ስለሚያመነዝሩ፣ ስለዝሙትና ስለማንኛውም ኃጢያት አስጠነቀቀ። ከ፭፻፵፬–፬፻፳፩ ም.ዓ. ገደማ።
፩ ነገር ግን እነሆ፣ እኔ ያዕቆብ፣ በልባችሁ ንፁህ ለሆናችሁ እናገራለሁ። በአዕምሮ ፅኑነት ወደ እግዚአብሔር ተመልከቱ፣ በታላቅ እምነትም ወደእርሱ ፀልዩ፣ እርሱም በመከራችሁ ያፅናናችኋል፣ እናም ምክንያታችሁን ይማፀናል፣ ጥፋታችሁንም ለሚመኙ ፍርድን ይልካል።
፪ አቤቱ በልባችሁ ንፁህ የሆናችሁ ሁሉ፣ ራሳችሁን አቅኑና አስደሳቹን የእግዚአብሔርን ቃል ተቀበሉ፣ እናም ፍቅሩንም ተቋደሱ፤ አዕምሮአችሁ ፅኑ ከሆነ፣ ይህን ለዘለአለም ለማድረግ ትችላላችሁና።
፫ ነገር ግን፣ እናንተ በልባችሁ ንፁህ ያልሆናችሁ በዚህ ቀን በእግዚአብሔር ፊት የቆሸሻችሁ ወዮ፣ ወዮላችሁ፤ ንስሀ ካልገባችሁ ምድሪቱ በእናንተ ምክንያት የተረገመች ትሆናለችና፤ እናም ላማናውያን እንደ እናንተ ባይቆሽሹም፣ ይሁን እንጂ በከባድ እርግማን ተረግመዋል፣ እስከምትጠፉም እንኳን ይጎዱአችኋል።
፬ እናም እናንተ ንስሀ ካልገባችሁ፣ የርስት ምድራችሁን እነርሱ የሚወርሱበት ጊዜ በፍጥነት ይመጣል፣ እናም ጌታ እግዚአብሔር ፃድቃንን ከመካከላችሁ ያወጣል።
፭ እነሆ፣ የእናንተ ወንድሞች፣ በቆሻሻነታቸውና በቆዳቸው ላይ በመጣው እርግማን የተነሳ የጠላችኋቸው ላማናውያን፣ ከእናንተ የበለጠ ፃድቃን ናቸው፤ ምክንያቱም እነርሱ አንድ ሚስት ብቻ እንዲኖራቸው እናም ምንም ዕቁባት እንዳይኖራቸው፣ እናም በመካከላቸውም ዝሙት እንዳይፈጸም ዘንድ ለአባታችን የተሰጠውን የጌታን ትዕዛዝ አልረሱምና።
፮ እናም አሁን፣ ይህንን ትዕዛዝ ለመጠበቅ ይጥራሉ፤ ስለሆነም፣ ይህንን ትዕዛዝ ለመጠበቅ ጥረት የተነሳ ጌታ እግዚአብሔር እነርሱን አያጠፋም፣ ነገር ግን ለእነርሱ መሀሪ ይሆናል፤ እናም አንድ ቀን የተባረኩ ህዝቦች ይሆናሉ።
፯ እነሆ፣ ባሎቻቸው ሚስቶቻቸውን ይወዳሉ፣ ሚስቶቻቸውም ባሎቻቸውን ይወዳሉ፤ እናም ባሎቻቸውና ሚስቶቻቸው ልጆቻቸውን ይወዳሉ፤ እንዲሁም የእነርሱ አለማመንና ወደ እናንተ ያላቸው ጥላቻ በአባቶቻቸው ክፋት የተነሳ ነው፤ ስለሆነም፣ በታላቁ ፈጣሪያችሁ አመለካከት እናንተ ምን ያህል ከእነርሱ የተሻላችሁ ናችሁ?
፰ ወንድሞቼ ሆይ፣ ከእነርሱ ጋር በእግዚአብሔር ዙፋን ፊት ስትቀርቡ እናንተ ለኃጢኣታችሁ ንስሀ ካልገባችሁ የእነርሱ ቆዳ ከእናንተ የበለጠ ይነጣል በማለት እፈራለሁ።
፱ ስለሆነም፣ የእግዚአብሔር ቃል የሆነ ትዕዛዝ እሰጣችኋለሁ፣ ቆዳቸው በመጥቆሩ ምክንያት ከእንግዲህ አትሰድቧቸውም፤ በመቆሸሻቸውም ምክንያት አትሰድቧቸውም፤ ነገር ግን የራሳችሁን መቆሸሽ ታስታውሳላችሁ፣ እናም የእነርሱ መቆሸሽ የመጣው በአባቶቻቸው የተነሳ መሆኑን አስታውሱ።
፲ ስለሆነም፣ በፊታቸው ባስቀመጣችሁት ምሳሌም የተነሳ የልጆቻችሁን ልብ እንዴት እንዳሳዘናችሁ ታስታውሳላችሁ፤ እናም ደግሞ በመቆሸሻችሁ የተነሳ፣ ልጆቻችሁን ወደ ጥፋት ታመጣላችሁ፣ እናም በመጨረሻው ቀን ኃጢአታቸው በራሳችሁ ላይ ይቆለላሉ።
፲፩ ወንድሞቼ ሆይ፣ ቃሌን አድምጡ፤ የነፍሳችሁን ስሜት አነቃቁ፤ ከሞት እንቅልፍ ትነቁ ዘንድ ራሳችሁን ነቅንቁ፤ እናም የዲያብሎስ መልዕክተኛ በመሆን የሁለተኛው ሞት ከሆነው እሳትና ዲን ራሳችሁን እንዳትጥሉ ከሲዖል ህመም ራሳችሁን ፍቱ።
፲፪ እናም አሁን እኔ ያዕቆብ፣ የሚያስከትሉትን ክፉ ነገሮች በመንገር ከዝሙትና ከአመንዝራነት፣ እንዲሁም ከማንኛውም አይነት ኃጢያት እነርሱን በማስጠንቀቅ ለኔፊ ህዝብ ብዙ ነገሮችን ተናገርኳቸው።
፲፫ እናም አሁን ቁጥራቸው ታላቅ እየሆኑ የመጡት የዚህ ህዝብ ነገር አንድ መቶኛ ክፍል ድርጊቶችም በእነዚህ ሰሌዳዎች ሊፃፍ አይቻልም፤ ነገር ግን አብዛኛው ድርጊታቸውና፣ ጦርነታቸው፣ እናም ፀባቸው፣ እንዲሁም የነገስታቶቻቸው የንግስ ታሪክ በትልቁ ሰሌዳ ላይ ተፅፈዋል።
፲፬ እነዚህ ሰሌዳዎች የያዕቆብ ሰሌዳዎች ይባላሉ፣ እናም የተሰሩት በኔፊ እጅ ነው። እናም እነዚህን ቃላት መናገሬን አቆማለሁ።