ምዕራፍ ፭
ያዕቆብ ከዜኖስ ስለለማው እና ስለዱር የወይራ ዛፍ ታሪክ ጠቀሰ—እነርሱም ከእስራኤልና ከአህዛብ ጋር የተመሳሰሉ ናቸው—የእስራኤል መበተን እና መሰባሰብ ቀድሞ ተጠቅሷል—ስለኔፋውያንና ላማናውያን እንዲሁም ስለእስራኤል ቤት ሁሉ ተጠቅሷል—አህዛብ ከእስራኤል ጋር ይዳቀላሉ—በመጨረሻም የወይኑ ስፍራ ይቃጠላል። ከ፭፻፵፬–፬፻፳፩ ም.ዓ. ገደማ።
፩ እነሆ፣ ወንድሞቼ፣ እንዲህ ሲል ለእስራኤል ቤት የተናገረውን የነቢዩ ዜኖስን ቃል ማንበባችሁን አታስታውሱምን፤
፪ የእስራኤል ቤት ሆይ አድምጡኝ፣ እናም የእኔ የጌታ ነቢይን ቃል ስሙ።
፫ እነሆም፣ ጌታ እንዲህ ይላል፥ የእስራኤል ቤት ሆይ፣ እኔ እናንተን አንድ ሰው ወስዶ በወይኑ ስፍራ ከሚንከባከበው፣ ከለማው የወይራ ዛፍ ጋር አመሳስላችኋለሁ፤ እናም አደገ፣ አርጅቶ መበስበስም ጀምረ።
፬ እናም እንዲህ ሆነ በወይኑ ስፍራ ባለቤቱ ሄዶ፣ የወይራው ዛፍ መበስበስ እንደ ጀመረ ተመለከተም፤ እናም እንዲህ አለ—ምናልባት ለጋና ለምለም ቅርንጫፎችን ያበቅል ዘንድና፣ እንዳይጠፋም እኔ እመለምለዋለሁ፣ እቆፍረዋለሁ፣ እናም እንከባከበዋለሁ።
፭ እናም እንዲህ ሆነ እንደቃሉ መለመለው፣ ቆፈረውም፣ ተንከባከበውም።
፮ እናም እንዲህ ሆነ ከብዙ ቀናት በኋላ ትናንሽና ጥቂት ለጋና ለምለም ቅርንጫፎችን ማውጣት ጀመረ፤ ነገር ግን እነሆ፣ ከዋናው ጫፍ ያለው መሞት ጀመረ።
፯ እናም እንዲህ ሆነ የወይኑ ስፍራ ባለቤት ተመለከተው፣ እናም ለአገልጋዩ እንዲህ ሲል ተናገረው—ይህንን ዛፍ ማጣት ያሳዝነኛል፤ ስለሆነም፣ ሂድና ከየዱር ወይራ ዛፍ ቅርንጫፉን ልቀም፣ ወደ እኔም አምጣው፤ እናም እኛ መጠውለግ የጀመሩትን ዋና ዋና ቅርንጫፎች እንነቅላለን፣ ይቃጠሉም ዘንድ ወደ እሳቱ እንጥላቸዋለን።
፰ እናም እነሆ፣ የወይኑ ስፍራ ጌታ እንዲህ ይላል፥ ከእነዚህ ለጋና ለምለም ቅርንጫፎች ብዙዎቹን እወስዳለሁ፣ እናም በምፈልገው ቦታ አዳቅላቸዋለሁ፤ እናም የዚህ ዛፍ ስር የሚጠፋም ከሆነ ምንም አይደለም፣ ፍሬውን ለራሴ አስቀምጣለሁ፤ ስለሆነም፣ እነዚህን ለጋና ለምለም ቅርንጫፎች እወስዳለሁ፣ እናም በፈለግሁበት ቦታ አዳቅላቸዋለሁ።
፱ አንተ የዱር የወይራ ዛፍ ቅርንጫፎችን ውሰድና፣ በእነዚያም ምትክ አዳቅላቸው፤ እናም የወይኑን ስፍራዬን እንዳያበላሹት ዘንድ፣ እኔ የመለመልኳቸውን ወደ እሳቱ እጥላቸዋለሁ፣ እናም አቃጥላቸዋለሁ።
፲ እናም እንዲህ ሆነ የወይኑ ስፍራ ጌታ አገልጋይ እንደወይኑ ስፍራ ጌታ ቃል አደረገ፣ እናም በዱሩ የወይራ ዛፍ ቅርንጫፎችን አዳቀለ።
፲፩ እናም የወይኑ ስፍራ ጌታ እንዲቆፍርና እንዲመለምል፣ እናም እንዲንከባከበው ለአገልጋዩ እንዲህ አለው—ይህንን ዛፍ ማጣት ያሳዝነኛል፣ ስለሆነም፣ ምናልባት እንዳይጠፋ ስሮቹን ለማዳን እችል ዘንድ፣ ለእኔ ለራሴ እነርሱን አስቀር ዘንድ ይህን ነገር አድርጌአለሁ።
፲፪ ስለሆነም፣ መንገድህን ሂድ፣ ዛፉን ጠብቅ፣ እናም በቃሌ መሰረት ተንከባከበው።
፲፫ እናም ይህን ራቅ ባለው በወይን አትክልት ስፍራዬ፣ በምፈልገው በማንኛውም ቦታ፣ አስቀምጠዋለሁ፣ ይህም አንተን አያሳስብህም፤ እናም ይህን የማደርገው የተፈጥሮ ቅርንጫፎቹን ለራሴ አድን ዘንድ፣ እናም ደግሞ ለራሴ ፍሬውን ለማከማቸት ነው፤ ምክንያቱም ይህን ዛፍና ፍሬውን ማጣት ያሳዝነኛል።
፲፬ እናም እንዲህ ሆነ የወይኑ ስፍራ ጌታ መንገዱን ሄደ፣ እናም ተፈጥሮአዊውን የለማውን የወይራ ዛፍ ቅርንጫፎች ራቅ ባለው የወይን ስፍራ፤ እንደፈቃዱና ደስታው አንዳንዱን በአንድ፣ እናም አንዳንዱን በሌላ ቦታ ደበቀው።
፲፭ እናም እንዲህ ሆነ ረጅም ጊዜ አለፈ፣ የወይኑ ስፍራ ጌታም ለአገልጋዩ እንዲህ አለው—ና ወደ ወይኑም ስፍራ እንሰራ ዘንድ እንሂድ።
፲፮ እናም እንዲህ ሆነ የወይኑ ስፍራ ጌታና ደግሞ አገልጋዩ ወደ ወይኑ ስፍራ ለመስራት ሄዱ። እናም እንዲህ ሆነ አገልጋዩ ለጌታው እንዲህ አለው፥ እነሆ፣ በዚህ ተመልከት፣ ዛፉን ተመልከት።
፲፯ እናም እንዲህ ሆነ የወይኑ ስፍራ ጌታ የዱር የወይራው ቅርንጫፎች የተዳቀሉበትን ዛፍ አየም ተመለከተም፤ እናም ዛፉ ማበብና ፍሬ ማፍራት ጀመሯል። እርሱም መልካም እንደሆነ አየ፤ እናም ፍሬው እንደተፈጥሮው ፍሬ ነበር።
፲፰ እናም ለአገልጋዩ እንዲህ አለው፥ እነሆ፣ የዱር ቅርንጫፎቹ የዛፉን ስር እርጥበት ወስደውታል፣ ስለዚህ ስሩም የበለጠ ጥንካሬን አግኝቷል፤ እናም የእዚያ ስር ብዙ ጥንካሬ ስለነበረው የዱር ቅርንጫፎች የለሙ ፍሬዎች አፍርተዋል። አሁን፣ እነዚህን ቅርንጫፎች ባናዳቅላቸው ኖሮ ዛፉ ይሞት ነበር። እናም አሁን፣ እነሆ፣ ዛፉ ያፈራቸውን ፍሬ አከማቻለሁ፤ እናም ለወቅቱም ፍሬውን ለራሴ አከማቻለሁ።
፲፱ እናም እንዲህ ሆነ የወይኑ ስፍራ ጌታ ለአገልጋዩ እንዲህ አለው፥ ና ራቅ ወዳለው የወይኑ ስፍራ እንሂድ፣ እናም ፍሬውን ለራሴ በወቅቱ አከማቸው ዘንድ፣ የተፈጥሮው ቅርንጫፍ ብዙ ፍሬ ደግሞ እንዳላመጣ እንመልከት።
፳ እናም እንዲህ ሆነ ባለቤቱ የተፈጥሮ ቅርንጫፎቹን ወደ ደበቀበት ስፍራ ሄዱ፣ እናም እርሱ ለአገልጋዩ፥ እነዚህን ተመልከት አለው፤ የመጀመሪያው ብዙ ፍሬ እንደሚያስገኝም ተመለከተ፤ እናም መልካም እንደሆነ ደግሞ ተመለከተ። ለአገልጋዩም እንዲህ አለው፥ ፍሬውን ውሰድና ለራሴ አስቀምጠው ዘንድ ለወቅቱ አከማቸው፤ እነሆም፣ ለረጅም ጊዜ ተንከባክቤዋለሁ፣ እናም ብዙ ፍሬን አስገኝቷል።
፳፩ እናም እንዲህ ሆነ አገልጋዩ ለጌታው አለው፥ ይህንን ዛፍ ወይም የዛፉን ቅርንጫፍ ለመትከል እዚህ ለምን መጣህ? እነሆም ከወይኑ ስፍራ ሁሉ ያልለማ ነበርና።
፳፪ እናም የወይኑ ስፍራ ጌታም አለው፥ እኔን አትምከረኝ፤ መጥፎ የመሬት ቦታ እንደነበረ አውቃለሁ፤ ስለሆነም፣ እንዲህም ብዬሃለሁ፣ ይህን ለረጅም ጊዜ ተንከባክቤዋለሁ፣ እናም ብዙ ፍሬን እንዳስገኘ ተመልክተሃል።
፳፫ እናም እንዲህ ሆነ የወይኑ ስፍራ ጌታ ለአገልጋዩ እንዲህ አለው፥ እዚህ ተመልከት፤ እነሆ ሌላ የዛፉን ቅርንጫፍ ደግሞ ተክያለሁ፤ እናም አንተ ይህ መሬት ከመጀመሪያው የበለጠ መጥፎ መሆኑን ታውቃለህ። ነገር ግን ዛፉን ተመልከት። ለረጅም ጊዜ ተንከባክቤዋለሁ፣ እናም ብዙ ፍሬን አስገኝቷል፤ ስለዚህ፣ ሰብስበውና ለራሴ አስቀምጠው ዘንድ ለወቅቱ አከማቸው።
፳፬ እናም እንዲህ ሆነ የወይኑ ስፍራ ጌታ ለአገልጋዩ በድጋሚ አለው፥ ወደዚህ ተመልከት፣ እናም እኔ የተከልኩትን ሌላ ቅርንጫፍ ደግሞ ተመልከት፤ እነሆ እኔ ደግሞ ተንከባክቤዋለሁ፣ ይህም ፍሬን አስገኝቷል።
፳፭ እናም ለአገልጋዩ አለው—ወደዚህ ተመልከት፣ እናም የመጨረሻውን ተመልከት። እነሆ፣ ይህን በመልካሙ መሬት ቦታ ላይ ተክየዋለሁ፣ ለዚህ ለረጅም ጊዜም ተንከባክቤዋለሁ፣ እናም የለማውን ፍሬ በግማሹ ክፍል ብቻ አስገኝቷል፤ ሌላው የዛፉ ክፍልም የዱር ፍሬ አፍርቷል፣ እነሆ ይህን ዛፍ እንደሌሎቹ ተንከባክቤዋለሁ።
፳፮ እናም እንዲህ ሆነ የወይን ስፍራው ጌታ ለአገልጋዩ አለ—መልካም ፍሬ የማያፈሩትን ቅርንጫፎች ንቀላቸውና ወደ እሳቱ ጣላቸው።
፳፯ ነገር ግን እነሆ፣ አገልጋዩም አለ—እንግረዘው፣ እንኮትኩተውም፣ እናም ለትንሽ ጊዜ እንንከባከበው፣ ምናልባት በወቅቱ የምታከማቸውን መልካም ፍሬን ያመጣልህ ይሆናል።
፳፰ እናም እንዲህ ሆነ የወይኑ ስፍራ ጌታና የወይን ስፍራው ጌታ አገልጋይ የአትክልቱን ስፍራ ፍሬዎች በሙሉ ተንከባከቡት።
፳፱ እናም እንዲህ ሆነ ረጅም ጊዜ አለፈ፣ እናም የወይኑ ስፍራ ጌታ ለአገልጋዩ እንዲህ አለው—ና፣ በወይኑ ስፍራ እንደገና እንሰራ ዘንድ ወደ ወይኑ ስፍራ እንሂድ። እነሆም፣ ቀኑ ቀርቧል፣ እናም የመጨረሻው በፍጥነት ይመጣል፣ ስለሆነም፣ ለራሴ ለወቅቱ የሚሆን ፍሬ ማከማቸት አለብኝ።
፴ እናም እንዲህ ሆነ የወይኑ ስፍራ ጌታና አገልጋዩ ወደ ወይኑ ስፍራ ሄዱ፤ የተፈጥሮ ቅርንጫፎቹ ወደ ወደቁበትና፣ የዱር ቅርንጫፎቹ ወደተዳቀሉለት ዛፍም ሄዱ፣ እናም እነሆ ሁሉም ዓይነት ፍሬዎች ዛፉ እንዲያዘነብል አደረጉት።
፴፩ እናም እንዲህ ሆነ የወይን ስፍራው ጌታ ከፍሬው እያንዳንዱን አይነት፣ ከትንሽ እስከትልቅ፣ ቀመሰ። የወይኑ ስፍራ ጌታም እንዲህ አለ፤ እነሆ፣ ለረጅም ጊዜ ይህን ዛፍ ተንከባክበናል፣ እናም ለወቅቱ የሚሆን ብዙ ፍሬንም ለራሴ አከማችቻለሁ።
፴፪ ነገር ግን እነሆ፣ በዚህ ጊዜ ብዙ ፍሬን አስገኝቷል፣ እናም ከዚህ ውስጥ ምንም መልካም የሆነ የለም። እናም እነሆ፣ ከሁሉም ዓይነት መጥፎ ፍሬዎች አሉ፤ በብዛት ብንሰራበትም፣ ለእኔ ምንም ጥቅም አያስገኝልኝም፤ እናም አሁን ይህንን ዛፍ በማጣቴ አሳዝኖኛል።
፴፫ እናም የወይኑ ስፍራ ጌታ ለአገልጋዩ አለው—እኔ እንደገና መልካሙን ፍሬ ለራሴ አስቀምጥ ዘንድ በዛፉ ላይ ምን ማድረግ ይሻለናል?
፴፬ እናም አገልጋዩ ለጌታው አለው፥ እነሆ፣ እነርሱን ከዱሩ የወይራ ዛፍ ቅርንጫፎች ላይ ስላዳቀልክ ስሩን ተንከባክበዋል፣ ስለዚህ በህይወት ቆይተዋል እናም አልጠፉም፤ ስለሆነም፣ አሁንም አንተ መልካም መሆናቸውን ተመልክተሃል።
፴፭ እናም እንዲህ ሆነ የወይኑ ስፍራ ጌታ ለአገልጋዩ እንዲህ አለው፥ ዛፉ ለእኔ ምንም አይጠቀመኝም፣ እናም መጥፎ ፍሬን እስከሰጠ ድረስ ስሩም ምንም አይጠቀመኝም።
፴፮ ይሁን እንጂ፣ ስሩ መልካም እንደሆነ አውቃለሁና፣ ለራሴ ዓላማ እነርሱን አድኛለሁ፤ እናም እስከአሁን ባላቸው ጥንካሬም የተነሳ ከዱር ቅርንጫፎቹ መልካም ፍሬን ሰጡ።
፴፯ ነገር ግን እነሆ የዱር ቅርንጫፎቹ አደጉና፣ የዚያ ስሩ ሊሸከማቸው አልቻለም፤ እናም ስሩ የዱር ቅርንጫፎቹን መሸከም ስላቃተው እርሱ መጥፎ ፍሬን አፈራ፤ እርሱም ብዙ መጥፎ ፍሬዎችን በማፍራቱ መጥፋት እንደ ጀመረ ትመለከታለህ፤ እናም ስለዚህ እርሱን ለማዳን አንድ ነገር ካላደረግን ወደ እሳት እንዲጣል በፍጥነትም ይበስላል።
፴፰ እናም እንዲህ ሆነ የወይኑ ስፍራ ጌታ ለአገልጋዩ አለው—ራቅ ወዳለው የወይኑ ስፍራ እንሂድና፣ የተፈጥሮ ቅርንጫፎቹም ደግሞ መጥፎ ፍሬን እንደሚያፈሩ እንመልከት።
፴፱ እናም እንዲህ ሆነ ራቅ ወዳለው ወደ ወይኑ ስፍራ ሄዱ። እናም እንዲህ ሆነ የተፈጥሮ ቅርንጫፎቹ ፍሬ ደግሞ እንደተበሰበሰ ተመለከቱ፤ አዎን፣ የመጀመሪያውና ሁለተኛው ደግሞ የመጨረሻውም፤ እናም ሁሉም በስብሰዋል።
፵ እናም የመጨረሻው የዱር ፍሬ መልካሙን ፍሬ ያፈራውን የዛፍ ክፍል አሸንፎታል፣ እንዲሁም ቅርንጫፉ ጠውልጓልና ሞቷል።
፵፩ እናም እንዲህ ሆነ የወይኑ ስፍራ ጌታ አለቀሰ፣ እናም ለአገልጋዩ አለው፥ ለወይኑ ስፍራዬ ከዚህ የበለጠ ምን ማድረግ እችላለሁ?
፵፪ እነሆ፣ የወይኑ ስፍራ ፍሬ ከዚህ በስተቀር ሁሉም እንደበሰበሱ አውቃለሁ። እናም በአንድ ወቅት መልካም ፍሬን ያመጣው ደግሞ አሁን በስብሷል፤ እናም አሁን የወይኔ ስፍራ ዛፎች በሙሉ ያለመቆረጥና ወደ እሳት ያለመጣል በስተቀር ለምንም መልካም አይደሉም።
፵፫ እናም እነሆ ይህ የመጨረሻው የጠወለገ ቅርንጫፍ፣ በመልካሙ መሬት ላይ አዎን፣ ከሌላው ከወይን ስፍራዬ መሬት ክፍሎች ሁሉ በላይ ምርጥ በሆነው ላይ እንኳን ነበር የተከልኩት።
፵፬ እናም ይህን ዛፍ በቦታው እተክል ዘንድ ይህን ምድር የሚያበላሹትንም ደግሞ ስቆርጥ ተመልክተሃል።
፵፭ እናም የዚህ ዛፍ ክፍል መልካም ፍሬን ሲያፈራና፣ ከፊሉም የዱር ፍሬን ሲያፈራ ተመልክተሃል፤ እናም ቅርንጫፎቹን መልምዬ ወደ እሳቱ ባለመጣሌ፣ እነሆ፣ እነርሱ መልካሙን ቅርንጫፍ አሸንፈውት እንዲጠወልግ አደረጉት።
፵፮ እናም አሁን፣ እነሆ፣ ለወይኑ ስፍራዬ ሁሉንም አይነት ጥንቃቄ ብንወሰድም፣ በዚያ ያሉት ዛፎች በስብሰዋል፣ ስለዚህ መልካም ፍሬን አልሰጡም፤ እናም እነዚህን ለማዳን፣ የእነዚህን ፍሬዎች በወቅቱ ለእኔ ለማከማቸት ተስፋ አድርጌ ነበር። ነገር ግን፣ እነሆ፣ እነርሱ ልክ እንደዱር የወይራ ዛፍ ሆነዋል፣ መቆረጥና ወደ እሳት የሚጣሉ ከመሆን በስተቀር ምንም ዋጋ የሌላቸው፤ እናም እነርሱን ማጣቴ አሳዝኖኛል።
፵፯ ነገር ግን በወይኑ ስፍራዬ ውስጥ ከዚህ የበለጠ ምን ማድረግ እችላለሁ? እናም እንዳልንከባከብ እጄን ሰበሰብኩኝን? አይደለም፣ ተንከባክቤዋለሁ፤ ኮትኩቼዋለሁ፤ እንዲሁም ከርክሜዋለሁ፤ ፍግም አፍስሻለሁ፤ ቀኑን ሙሉ እጄን ዘርግቻለሁም፣ መጨረሻው ተቃርቧልም። እናም የወይን ስፍራዬን ዛፎች ሁሉ መቁረጤና፣ እንዲቃጠሉ ወደ እሳቱ መጣሌ አሳዝኖኛል። የወይን ስፍራዬን ያበላሸው ማን ነው?
፵፰ እናም እንዲህ ሆነ አገልጋዩ ለጌታው አለው—የወይኑ ስፍራህ ትልቅነት አይደለም—በዚያ ያሉት ቅርንጫፎች መልካም የሆኑትን ስሮች አላሸነፉምን? እናም ቅርንጫፎቹ ስሩን በማሸነፋቸው የተነሳ እነሆ ጥንካሬን ለራሳቸው በማድረግ ከስሩ ጥንካሬ የበለጠ በፍጥነት አድገዋል። እነሆ፣ እላለሁ፣ የወይኑ ስፍራ ዛፍህ የተበላሸው ለዚህ አይደለም እንዴ?
፵፱ እናም እንዲህ ሆነ የወይኑ ስፍራ ባለቤት ለአገልጋዩ አለው፥ የወይን ስፍራ መሬት እንዳያቆሽሽ እንሂድና የወይኑን ስፍራ ዛፍ እንቁረጥ ወደ እሳት እንጣላቸውም፣ የምችለውን ያህል አድርጌአለሁና። ለወይኑ ስፍራዬ ከዚህ የበለጠ ምን ማድረግ እችላለሁ?
፶ ነገር ግን እነሆ፣ አገልጋዩ ለወይኑ ስፍራ ጌታ አለው—ለትንሽ ጊዜ አቆየው።
፶፩ እናም ጌታውም አለ፥ አዎን፣ ለትንሽ ጊዜ እተወዋለሁ፣ ምክንያቱም የወይን ስፍራዬን ዛፎች ማጣት ያሳዝነኛልና።
፶፪ ስለሆነም፣ ራቅ ባለው የወይኑ ስፍራዬ የተከልኩትን የእነዚህን ቅርንጫፎች እንውሰድ፣ እናም ከመጡበት ዛፍ ላይ እናዳቅላቸው፣ እናም ፍሬያቸው መራራ ከሆኑት እነዚያ ቅርንጫፎች እንመልምል፣ እናም የዛፉ የተፈጥሮ ቅርንጫፎችን በምትኩ እናዳቅል።
፶፫ እናም ይህን የማደርገው ዛፉ እንዳይጠፋና፣ ምናልባት ስሩን ለራሴ አላማ አድነው ዘንድ ነው።
፶፬ እናም እነሆ፣ በፈለኩበት ቦታ የተከልኩት የተፈጥሮ ቅርንጫፍ ስሮች እስከአሁን በህይወት ናቸው፤ ስለሆነም፣ ለራሴ ዓላማ ደግሞ አድናቸው ዘንድ፣ ከዚህ ዛፍ ቅርንጫፎችን እወስዳለሁ፣ እናም በተፈጥሮ ቅርንጫፉ ላይ አዳቅላቸዋለሁ። አዎን፣ ደግሞ ለራሴ ስሮቹን ለመጠበቅና፣ በብቁ ጠንካራ ሲሆኑ መልካም ፍሬ ወደእኔ እንዲያመጡልኝ ዘንድ፣ እናም በወይኑ ስፍራዬ ፍሬም እደሰት ዘንድ የእናት ዛፋቸው ቅርንጫፎችን በእነርሱ ላይ አዳቅላለሁ።
፶፭ እናም እንዲህ ሆነ የዱር ከሆነው የተፈጥሮ ዛፉ ቅርንጫፎቹን ወሰዱ፣ እናም ደግሞም ዱር ወደሆነው ተፈጥሮአዊ በሆነው ዛፍ ላይ አዳቅሉት።
፶፮ እናም ደግሞ የዱር የሆነውን የተፈጥሮ ዛፍ ወሰዱ፣ በእናታቸው ዛፍ ላይም ተዳቀሉ።
፶፯ እናም የወይኑ ስፍራ ጌታ ለአገልጋዩ አለው፥ ከሁሉም በላይ መራራ ከሆኑት በስተቀር የዱር ቅርንጫፎቹን ከዛፎቹ ላይ አትመልምል፣ እናም በእነርሱም ላይ እኔ በተናገርኩት መሰረት አዳቅላቸው።
፶፰ እናም የወይኑን ስፍራ ዛፎች እንደገና እንንከባከባቸዋለን፣ ቅርንጫፎቹንም እንከረክማለን፤ እናም ከዛፎቹ ውስጥ እነዚያን መጥፋት የሚገባቸውን የበሰሉትን ቅርንጫፎች እናለመልማለን፣ ወደ እሳትም እንጥላቸዋለን።
፶፱ እናም ይህን የማደርገው በመልካምነታቸው ምክንያት የዛፉ ስር ይጠነክራል ብዬ ነው፤ እናም በቅርንጫፎቹ መቀያየር የተነሳ መልካሙ መጥፎውን ያሸንፋል።
፷ እናም የተፈጥሮ ቅርንጫፎቹንና ስሩን በማዳኔና፣ የተፈጥሮ ቅርንጫፎቹን ወደ እናታቸው ዛፍም በድጋሚ በማዳቀሌና፣ የእናታቸው ዛፍን ስር በማዳኔ፣ ምናልባት የወይኑ ስፍራዬ ዛፎች በድጋሚ መልካም ፍሬን ያስገኛሉ፤ እናም በወይኑ ስፍራዬም ፍሬ ድጋሚ ደስታን እንዳገኝና፣ ምናልባት የመጀመሪያውን ፍሬ ስሩንና ቅርንጫፎቹን በማዳኔ እጅግ ደስታ እንዲሰማኝ—
፷፩ ስለሆነም፣ በወይኑ ስፍራ በምንችለው በትጋት እንድንሰራ፣ መንገዱን እንድናዘጋጅ ሂድ፣ እናም አገልጋዮችን ጥራ፣ ከሌሎቹ ፍሬዎች ሁሉ በላይ መልካምና ድንቅ የሆነውን ተፈጥሮአዊውን ፍሬ እንደገና አስገኛለሁ።
፷፪ ስለሆነም፣ በዚህ በመጨረሻው ጊዜ እንሂድና በምንችለው እንስራ፣ እነሆም መጨረሻው ተቃርቧልና፣ እናም ይህ የወይኑ ስፍራዬን የምመለምልበት የመጨረሻ ጊዜ ነው።
፷፫ ቅርንጫፎችን አዳቅል፤ እናም የመጀመሪያ ይሆኑ ዘንድ ከመጨረሻዎቹ ጀምሩ፣ የመጀመሪያዎቹም የመጨረሻ ይሆኑ ዘንድ፣ ሁሉንም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንንከባከባቸው ዘንድ፣ ያረጁትንና ወጣቶቹን፣ የመጀመሪያዎቹንና የመጨረሻዎቹን፣ እና የመጨረሻዎቹንና የመጀመሪያዎቹን፣ ዛፎቹን ኮትኩቷቸው።
፷፬ ስለዚህ፣ ቆፍሩአቸውና መልምሉአቸው፣ እናም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ፍግ አድርጉባቸው፣ ምክንያቱም መጨረሻው ቀርቧልና። እናም እነዚህ በመጨረሻ የተዳቀሉት ካደጉ፣ እንዲሁም የተፈጥሮ ፍሬን ካፈሩ፣ እነርሱም ያድጉ ዘንድ ለእነርሱ መንገድን ታዘጋጃላችሁ።
፷፭ እናም ማደግ ሲጀምሩ በመልካሙ ጥንካሬውና ባለው መጠን መሰረት መራራ ፍሬ የሚያፈሩትን ቅርንጫፎች ታስወግዳላችሁ፤ እናም ስሩ ለተዳቀሉት እጅግ ጠንካራ እንዳይሆንባቸው፣ እናም በእዚያ የተዳቀሉት እንዳይጠፉና፣ የወይኑ ስፍራዬን ዛፎች እንዳላጣ፣ መጥፎውንም ሁሉ በአንዴ አታስወግዱም።
፷፮ የወይኑ ስፍራ ዛፎቼን ማጣት ያሳዝነኛልና፤ ስለሆነም፣ ስሩና ቅርንጫፉ በጥንካሬ እኩል እንዲሆን፣ መልካሙ መጥፎውን እስኪያሸንፈው፣ እናም የወይኑ ስፍራዬን ቦታ አንዳያበላሹት መጥፎው ተቆርጦ ወደ እሳት እስከሚጣል ድረስ፣ መልካሙ በሚያድግበት መሰረት መጥፎውን ታስወግዳላችሁ፤ እና እንደዚህም መጥፎውን ከአትክልት ስፍራዬ ጠርጌ አስወግደዋለሁ።
፷፯ እናም የተፈጥሮውን ዛፍ ቅርንጫፎች በተፈጥሮው ዛፍ ላይ በድጋሚ አዳቅለዋለሁ፤
፷፰ እናም የተፈጥሮውን ዛፍ ቅርንጫፎች በዛፉ የተፈጥሮ ቅርንጫፎች ላይ አዳቅላለሁ፤ እና እንደዚህ ተፈጥሮአዊውን ፍሬ ያፈሩ እንዲሁም አንድ ይሆኑ ዘንድ በድጋሚ እነርሱን በአንድነት አመጣቸዋለሁ።
፷፱ እናም መጥፎው ይጣላል፣ አዎን፣ ከአትክልት ስፍራዬ መሬት ሁሉም እንኳን፤ እነሆም፣ ወይኑ ስፍራዬን ይህን አንዴ ብቻ እከረክመዋለሁ።
፸ እናም እንዲህ ሆነ የወይኑ ስፍራ ባለቤት አገልጋዩን ላከ፤ እናም አገልጋዩ ሄደና ጌታው እንዳዘዘው አደረገ፣ ሌሎች አገልጋዮቹንም አመጣ፤ እናም እነርሱ ጥቂት ነበሩ።
፸፩ እናም የወይኑ ስፍራ ጌታ አላቸው፥ ሂዱና በአቅማችሁ በወይኑ ስፍራ ስሩ። እነሆም ይህ የወይኑን ስፍራዬን የምንከባከብበት የመጨረሻ ጊዜ ነው፤ መጨረሻው ቀርቦ ደርሷልና፣ ወቅቱም በፍጥነት ይመጣል፤ እናም በአቅማችሁ ከእኔ ጋር ከሰራችሁ በቅርቡ ለሚመጣው ጊዜ ለራሴ ባከማቸሁት ፍሬ ደስታ ይኖራችኋል።
፸፪ እናም እንዲህ ሆነ አገልጋዮቹ ሄዱና በአቅማቸው ሰሩ፤ የወይኑ ስፍራ ጌታ ደግሞም ከእነርሱ ጋር ሰራ፤ እናም በሁሉም ነገሮች የወይኑን ስፍራ ጌታ ትዕዛዛት ተቀበሉ።
፸፫ እናም በወይኑ ስፍራ እንደገና የተፈጥሮ ፍሬ መሆን ጀመረ፣ እናም የተፈጥሮ ቅርንጫፎች ማደግና እጅግም መፋፋት ጀመሩ፤ የዱር ቅርንጫፎች መመልመልና መጣል ጀመሩም፤ እነርሱም ስራቸውና ጫፋቸው በጥንካሬው መሰረት እኩል እስኪሆኑ ጠበቁት።
፸፬ እናም መጥፎው ከወይኑ ስፍራ እስከሚጣልና ጌታው ዛፎቹ እንደገና የተፈጥሮ ፍሬ እንዲያፈሩ ለራሱ እስኪያድን ድረስ፣ በወይኑ ስፍራ ጌታ ትዕዛዛት መሰረት እንደዚህ በሙሉ ትጋት ሰሩ፤ እነርሱም እንደ አንድ አካል ሆኑ፤ ፍሬዎቹም እኩል ነበሩ፤ እናም የወይኑ ስፍራ ጌታ ከመጀመሪያው ጀምሮ ለእርሱ እጅግ ውድ የሆነውን የተፈጥሮ ፍሬ ለራሱ አድኗል።
፸፭ እናም እንዲህ ሆነ የወይኑ ስፍራ ጌታ ፍሬው መልካም መሆኑንና፣ የወይኑንም ስፍራ ከእንግዲህ እንዳልበሱበሱ ባየ ጊዜ አገልጋዮቹን ጠራቸውና እንዲህ አላቸው፥ እነሆ፣ ለመጨረሻ ጊዜ የወይኑን ስፍራዬን ተንከባክበናል፤ እንደ ፍቃዴ እንዳደረኩም ተመልክታችኋል፤ እናም የተፈጥሮ ፍሬን አድኜዋለሁ፣ ልክ መጀመሪያ እንደነበረም መልካም ነው። እናንተም የተባረካችሁ ናቸሁ፤ በወይኑ ስፍራዬ ከእኔ ጋር በትጋት በመስራታችሁ፣ ትዕዛዛቴንም በመጠበቃችሁና፣ የወይኑ ስፍራዬ ከእንግዲህ እንዳይበሰብስ፣ በድጋሚ ተፈጥሮአዊ ፍሬን በማምጣታችሁና፣ መጥፎው ስለተጣለ፣ እነሆ በወይን ስፍራዬ ፍሬ የተነሳ እናንተ ከእኔ ጋር ደስታ ይኖራችኋል።
፸፮ እነሆም ለረጅም ጊዜ በፍጥነት ለሚመጣው ወቅት የወይኑን ስፍራዬን ፍሬ ለራሴ አከማቻለሁ፤ እናም ለመጨረሻ ጊዜ የወይኑን ስፍራዬን ተንከባከብኩት፣ ከረከምኩትም፣ እናም ኮተኮትኩት፣ ፍግም አደረግሁበት፤ ስለዚህ፣ በተናገርኩት መሰረት ከፍሬው ለራሴ ለረጅም ጊዜ አከማቻለሁ።
፸፯ እናም መጥፎው ፍሬ በድጋሚ በወይኑ ስፍራዬ በሚወጣበት ጊዜ ጥሩውና መጥፎው እንዲሰበሰቡ አደርጋለሁ፤ እናም መልካሙን ለራሴ አስቀምጣለሁ፣ መጥፎውንም ወደ ራሱ ስፍራ እጥለዋለሁ። ከዚያም በኋላ ወቅቱ እንዲሁም መጨረሻው ይመጣል፤ እናም የወይኑን ስፍራዬን በእሳት እንዲቃጠል አደርገዋለሁ።