ቅዱሳት መጻህፍት
ኤተር ፲፭


ምዕራፍ ፲፭

በሚሊዮን የሚቆጠሩ ያሬዳውያን በጦርነቱ ሞቱ—ሺዝ እና ቆሪያንተመር ህዝቡን በአንድነት ለመገዳደል ሰበሰቡ—የጌታም መንፈስ ከእነርሱ ጋር መሆኑን አቆመ—የያሬዳውያን ሀገር ፈጽማ ጠፋች—ቆሪያንተመር ብቻ ቀረ።

እናም እንዲህ ሆነ ቆሪያንተመር ቁስሉ እንደዳነለት፣ ኤተር ለእርሱ የተናገራቸውን ቃላት ማስታወሰ ጀመረ።

ከህዝቦቹም ወደ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉት በጎራዴው እንደተገደሉ ተመለከተ፣ እናም በልቡም ማዘን ጀመረ፤ አዎን፣ ሁለት ሚሊዮን ኃያላን ሰዎች፣ እናም ደግሞ ሚስቶቻቸው እና ልጆቻቸውም ጭምር ተገድለው ነበር።

ለሰራቸውም ክፋቶች ንሰሃ መግባት ጀመረ፤ ሁሉንም በነቢያት አንደበት የተነገሩትን ቃላቶች ማስታወስ ጀመረ፤ እናም እያንዳንዱም የተናገሩአቸው እንደተፈፀሙ ተመለከተ፤ እናም ነፍሱ አዘነች እናም መፅናናትን ለመቀበል አልቻለም።

እናም እንዲህ ሆነ ሺዝ ህዝቡን እንዲያድንለት፣ እናም ለህዝቡም ህይወት ሲል መንግስቱን እንደሚሰጠው በመፈለግ ደብዳቤ ፃፈለት።

እናም እንዲህ ሆነ ሺዝ ደብዳቤውን ሲቀበል ለቆሪያንተመር ራሱን የሰጠ እንደሆን በራሱ ጎራዴ እንደሚገድለው እናም የህዝቡንም ህይወት እንደሚያተርፍ ደብዳቤን ፃፈለት።

እናም እንዲህ ሆነ ህዝቡም ለክፋታቸው ንሰሃ አልገቡም፤ እናም የቆሪያንተመር ህዝቦች በሺዝ ህዝቦች በቁጣ ተነሳስተው ነበር፤ እናም የሺዝ ህዝብም በቆሪያንተመር ህዝቦች ላይ በቁጣ ተነሳስተው ነበር፤ ስለዚህ የሺዝ ህዝቦች ከቆሪያንተመር ህዝቦች ጋር ተዋጉ።

እናም ቆሪያንተመርም ሊሸነፍ እንደተቃረበ በተመለከተ ጊዜ በድጋሚ ከሺዝ ሰዎች ፊት ሸሸ።

እናም እንዲህ ሆነ ቆሪያንተመርም ትርጓሜውም ትልቅ፣ ወይንም ከሁሉም የሚበልጥ ማለት ወደሆነው ወደ ሪፕሊአንኩም ውኃ መጣ፤ ስለዚህ፣ ወደዚህ ውኃ በመጡ ጊዜ ድንኳናቸውን ተከሉ፤ እናም ደግሞ ሺዝ ድንኳኑን በእነርሱ አጠገብ ተከለ፤ እናም ከዚያም በሚቀጥለው ቀን ለውጊያ መጡ።

እናም እንዲህ ሆነ እጅግ የከፋ ውጊያን አደረጉ፤ በዚያም ቆሪያንተመር በድጋሚ ቆሰለ፣ እናም ብዙም ደም ስለፈሰሰው እራሱን በመሳት ወደቀ።

እናም እንዲህ ሆነ የቆሪያንተመር ወታደሮች የሺዝን ወታደሮች በኃይል አጠቁአቸው፣ ስለዚህ አሸነፉአቸው፣ እናም ከፊታቸውም እንዲሸሹ አደረጉአቸው፤ እናም እነርሱም በስተደቡብ በኩል ሸሹ፣ እናም አጋዝ ተብሎ በሚጠራም ስፍራ ድንኳናቸውን ተከሉ።

፲፩ እናም እንዲህ ሆነ የቆሪያንተመር ወታደሮችም በራማህ ኮረብታ ድንኳኖቻቸውን ተከሉ፤ እናም በዚያን ኮረብታ ነበር አባቴ ሞርሞን ቅዱስ የሆነውን መዛግብት ለጌታ የደበቀው

፲፪ እናም እንዲህ ሆነ ከኤተር በስተቀር ከሞት የተረፉትን ሰዎች በሙሉ በአንድ ላይ በምድሪቱ ላይ ሰበሰቡአቸው።

፲፫ እናም እንዲህ ሆነ ኤተር የህዝቡን ሥራ ሁሉ ተመለከተ፤ እናም በቆሪያንተመር በኩል የነበሩትም ሰዎችም ከቆሪያንተመር ወታደሮች ጋር በአንድነት ተሰባስበው እንደነበር ተመለከተ፤ እናም በሺዝ በኩል የነበሩትም ሰዎችም በሺዝ ወታደሮች በኩል በአንድ ላይ ተሰባስበው ነበር።

፲፬ ስለሆነም፣ እናም በምድሪቷ ፊት ላይ የነበሩትን ሁሉ ያገኙ ዘንድ፣ እናም ለመቀበል የሚችሉትን ጥንካሬዎች ሁሉ ለመቀበል፣ ህዝቡን ለዓራት አመታት ሰበሰቡአቸው።

፲፭ እናም እንዲህ ሆነ ሁሉም እያንዳንዳቸው ከነሚስቶቻቸው፣ እናም ከነልጆቻቸው ከፈለጉት ወታደሮች ጋር በተሰበሰቡበት ጊዜ—ወንዶች፣ ሴቶች እና ልጆች የጦር መሳሪያ በመታጠቅ፤ ጋሻዎችን፣ እናም የደረት ኪሶችን፣ እናም ኮፍያን በመታጠቅ፣ እናም ማንኛውንም ዓይነት የጦር አልባሳትን በመልበስ—እያንዳንዱም ከሌላው ጋር ለመዋጋት ዘመቱ፤ እናም ቀኑን ሙሉ ተዋጉ፣ ሆኖም ግን አላሸነፉም።

፲፮ እናም እንዲህ ሆነ ምሽት በሆነም ጊዜ ደክመው ነበር፣ እናም ወደ ጦር ሰፈራቸውም ተመለሱ፤ እናም ወደ ጦር ሰፈራቸውም ከተመለሱ በኋላ፣ ለሞቱት ወገኖቻቸው ይጮኹ፣ እንዲሁም ያለቅሱ ነበር፤ እናም ጩኸታቸው እናም ለቅሶአቸውታላቅ በመሆኑ አየሩን እጅግ የሚሰነጥቅ ታላቅ ኃይል ነበረው።

፲፯ እናም እንዲህ ሆነ በሚቀጥለውም ቀን ዳግም ለውጊያ ሄዱ፣ እናም ያም ቀን ታላቅና አስፈሪ ነበር፤ ይሁን እንጂ አላሸነፉም፣ እናም በድጋሚ ምሽት በሆነበት ጊዜም ህዝቦቻቸው ስለሞቱባቸው አካባቢውን በጩኸትና በልቅሶ ረበሹት።

፲፰ እናም እንዲህ ሆነ ቆሪያንተመርም በድጋሚ ለውጊያ ወደእርሱ እንዳይመጣ፣ ነገር ግን መንግስቱን እንዲይዝ፣ እናም የህዝቡን ህይወት እንዲያተርፍለት በመጠየቅ ለሺዝ ደብዳቤ በድጋሚ ፃፈለት።

፲፱ ነገር ግን እነሆ፣ የጌታ መንፈስ ከእነርሱ ጋር መሆኑን አቆመ፣ እናም ሰይጣንም በሰዎች ልብ ሙሉ ስልጣን ነበረው፤ ልባቸውን በማጠጠራቸው፣ አዕምሮአቸውን በማሳወራቸው እንዲጠፉ ዘንድ ተስፋ ቆርጠው ነበርና፤ ስለሆነም በድጋሚ ወደጦርነት ሄዱ።

እናም እንዲህ ሆነ በዚያን ቀን በሙሉ ተዋጉ፤ እናም ምሽት ሲሆን ጎራዴአቸውን ይዘው ተኙ።

፳፩ እናም በሚቀጥለው ቀንም ምሽት እስከሚሆን ድረስ ተዋጉ።

፳፪ እናም ምሽቱ ሲመጣ ልክ ወይን ጠጥቶ እንደሰከረ ሰው በቁጣ ሰክረው ነበር፤ እናም ጎራዴአቸውን ይዘው በድጋሚ ተኙ።

፳፫ እናም በሚቀጥለው ቀን በድጋሚ ተዋጉ፤ እናም ምሽቱም በመጣም ጊዜ ከቆሪያንተመር ሰዎች ከሃምሳ ሁለቱ እናም ከሺዝ ሰዎች ስልሳ ዘጠኙ በስተቀር በጎራዴ ተመትተው ወደቁ።

፳፬ እናም እንዲህ ሆነ በዚያን ምሽትም ጎራዴአቸውን እንደያዙ ተኙ፣ እናም በሚቀጥለው ቀን በድጋሚ ተዋጉ፣ እናም ቀኑን ሙሉ በኃይል፣ በጎራዴአቸው እና በጋሻዎቻቸው ተዋጉ።

፳፭ እናም ምሽት በሆነም ጊዜ ሠላሳ ሁለት የሺዝ ሰዎች፣ እንዲሁም ሃያ ሰባት የቆሪያንተመር ሰዎች ብቻ ነበሩ።

፳፮ እናም እንዲህ ሆነ ምግባቸውን በልተው ተኙ፣ እናም በሚቀጥለውም ቀን ለሞት ተዘጋጁ። እናም እነርሱም እንደሰዎች ጥንካሬ ትላልቅ እና ኃያላን ሰዎች ነበሩ።

፳፯ እናም እንዲህ ሆነ ለሦስት ሰዓታትም ተዋጉ፣ እናም ደም ስለፈሰሳቸው እራሳቸውን ሳቱ።

፳፰ እናም እንዲህ ሆነ የቆሪያንተመር ሰዎች ለመራመድ የሚያስችላቸውን በቂ ብርታት ባገኙ ጊዜ ህይወታቸውን ለማትረፍ ሊሸሹ ነበር፤ ነገር ግን እነሆ ሺዝ ተነሳ፣ እናም ደግሞ የእርሱ ሰዎች ተነሱ፣ እናም ቆሪያንተመርን ለመግደል አለበለዚያም በጎራዴው እንደሚጠፋ በቁጣው ማለ።

፳፱ ስለሆነም፣ እነርሱን ተከተላቸው፣ እናም በሚቀጥለው ቀን ደረሰባቸው፤ እናም በድጋሚ በጎራዴ ተዋጉ። እናም እንዲህ ሆነ ከቆሪያንተመር እና ከሺዝ በስተቀር ሁሉም በጎራዴው በወደቁ ጊዜ፣ እነሆ፣ ሺዝ ደም ስለፈሰሰው እራሱን ስቶ ነበር።

እናም እንዲህ ሆነ ቆሪያንተመር ጎራዴውን በመመርኮዝ ለጊዜ ትንሽ አረፈ፣ እናም የሺዝን እራስ ቆረጠ።

፴፩ እናም እንዲህ ሆነ የሺዝን ራስ በመምታት ከቆረጠ በኋላ፣ ሺዝ በእጆቹ በመመርኮዝ ተነሳ፣ እናም ወደቀ፤ እናም ለመተንፈስ ከታገለም በኋላ ሞተ።

፴፪ እናም እንዲህ ሆነ ቆሪያንተመር በመሬቱ ላይ ወደቀ፣ እናም ህይወት የሌለውም መሰለ።

፴፫ እናም ጌታ ኤተርን ተናገረው፤ እናም እንዲህ አለው፥ ወደፊት ሂድ። እናም እርሱም ወደ ፊት ሄደ፣ እናም የጌታ ቃል በሙሉ መፈፀሙንም ተመለከተ፤ እናም ታሪኩንም ጨረሰ፤ (እኔም መቶኛውን ክፍል አልፃፍኩም) እናም የሊምሂ ሰዎች እንዲያገኙት በማድረግም ደበቀው።

፴፬ እንግዲህ በኤተር የተፃፉት የመጨረሻዎቹ ቃላት እነዚህ ናቸው፥ ጌታ እኔ እንድቀየር ከፈቀደ ወይንም በስጋ የጌታን ፈቃድ እንድፈጽም ቢያደርግ፣ እኔ በእግዚአብሔር መንግስት የምድን ከሆነ ሌላው ምንም አይደለም። አሜን።