“በክርስቶስ ደስታን ማግኘት፣” ለወጣቶች ጥንካሬ፦ ምርጫዎችን የማድረግ መመሪያ [2022 (እ.አ.አ)]
“በክርስቶስ ደስታን ማግኘት፣” ለወጣቶች ጥንካሬ
በክርስቶስ ደስታን ማግኘት
ምርጫዎች ዋጋ አላቸው። በወንጌል ትምህርቶች ላይ የተመሰረቱ ምርጫዎች ወደ የሰማይ አባታችሁ እና ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ እንድትቀርቡ የሚያደርጉ እርምጃዎች ናቸው። ኢየሱስም “ደስታችሁም እንዲፈጸም ይህን ነግሬአችኋለሁ” (ዮሃንስ 15፥11) በማለት ተናግሯል። በእያንዳንዱ እርምጃ ወደ እርሱ፣ ወደ መንፈስ የበለጠ ትቀርባላችሁ እንዲሁም ከእግዚአብሔር ጋር ያላችሁ የቃል ኪዳን ግንኙነት እየጠነከረ ይሄዳል።
ነገር ግን ይህ ማለት መንገዱ ከችግር ነጻ ይሆናል ማለት አይደለም። ማንም ሰው ፍጹም በሆነ ቀጥተኛ መስመር ስለማይሄድ፣ አቅጣጫችሁን ያለማቋረጥ ፈትሹ እንዲሁም የእግዚአብሔርን ትእዛዛት አክብሩ። ከእግዚአብሔር ጋር የገባችኋቸውን ቃል ኪዳኖች ጠብቁ፣ ተጨማሪም ለማድረግ ተዘጋጁ። ቃል ኪዳኖች እናንተን ከሰማይ አባት እና ከአዳኙ ጋር ያገናኛሉ። እነዚህም በሕይወታችሁ ውስጥ የእግዚአብሔርን ኃይል ይጨምራሉ እንዲሁም የዘለአለምን ሕይወት እንድትቀበሉ ያዘጋጃችኋል።
ሊሆኑ ከሚችሉት ምርጫዎች ሁሉ፣ በጣም አስፈላጊው ኢየሱስ ክርስቶስን የመከተል ምርጫ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ የወጣቶች ጥንካሬ ነው። የእርሱ ወንጌል ወደ ሰማይ አባታችሁ የሚመልሳችሁ አስደሳች መንገድ ነው።