ወጣቶች
ኢየሱስ ክርስቶስ ይረዳችኋል


“ኢየሱስ ክርስቶስ ይረዳችኋል፣” ለወጣቶች ጥንካሬ፦ ምርጫ የማድረግ መመሪያ [2022 (እ.አ.አ)]

“ኢየሱስ ክርስቶስ ይረዳችኋል፣” ለወጣቶች ጥንካሬ

የኢየሱስ ክርስቶስ ምሥል።

ኢየሱስ ክርስቶስ ይረዳችኋል

መዝሙር 147፥3

ኢየሱስ ክርስቶስ ጉልበታችሁ ነው። በዚህ ህይወት እና ለዘለአለም ደስታ እንዲኖራችሁ አስፈላጊውን ሁሉ አድርጓል። እርሱን እና ወንጌሉን በመምረጥ፣ ዘለአለማዊ ደስታን ትመርጣላችሁ።

አይኖቹ የታወረ ሰውን አይን ኢየሱስ በእጁ  ሲዳስስ የሚይሳይ ሥዕል።

ጥሩ ምርጫ ለማድረግ የተቻላችሁን ለማድረግ ስትሞክሩ እንኳን፣ አንዳንድ ጊዜ ስህተትን ትሰራላችሁ። ባላደረኩት ብላችሁ የምትመኙትን ነገር ልታደርጉ ትችላላችሁ። ሁሉም ሰው እንዲህ ሊያደርግ ይችላል። ይህ በሚሆንበት ጊዜ ተስፋ መቁረጥ ወይም መቼም ጥሩ ሰው አልሆንም ብሎ ማሰብ ቀላል ነው። ነገር ግን መልካም ዜና አለ—አስደናቂ እና ተስፋ ሰጪ ዜና! እግዚአብሔር ስለሚወዳችሁ፣ ንስሐ ትገቡ እና ታድጉ ዘንድ ኃጢአታችሁን በራሱ ላይ የወሰደውን ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን ልኳል።

ዘለአለማዊ እውነት

ኢየሱስ ክርስቶስ ሊያበረታችሁ ይችላል። ምኞታችሁን፣ ሃሳባችሁን እና ተግባራችሁን እንድትቀይሩ ሊረዳችሁ ይችላል። ስትጨነቁ፣ ስትፈሩ ወይም በማንኛውም መንገድ ስትቸገሩ እርሱ ያጽናናችኋል። በሁሉም የሕይወታችሁ ዘርፍ ይረዳችኋል።

ንስሐ መግባት የኃጢአት ቅጣት አይደለም፤ አዳኙ እኛን ከኃጢአት ነፃ የሚያወጣበት መንገድ ነው። ንሰሃ መግባት ማለት መለወጥ ማለት ነው—ከሃጥያት መራቅ እና ወደ እግዚአብሔር መመለስ ነው። መሻሻል እና ይቅርታን ማግኘት ማለት ነው። የዚህ አይነት ለውጥ የአንድ ጊዜ ክስተት አይደለም፤ ቀጣይነት ያለው ሂደት ነው።

ግብዣዎች

ንስሀ ግቡ። ለማሻሻል ካለ ፍላጎት ጋር ወደ ጌታ ተመለሱ። የሆነ ስህተት ከሰራችሁ በሐቀኝነት በእግዚአብሔር ፊት እና እንደ አስፈላጊነቱ ለኤጲስ ቆጶሳችሁ እና ለጎዳችሁት ማንኛውም ሰው ስህተታችሁን አሳውቁ። ነገሮችን ለማስተካከል የተቻላችሁን አድርጉ።

ይበልጥ የተሻለ ለማድረግ እና ለመሆን በተሰጠው ስጦታ ተደሰቱ። ቀላል በማይሆንበት እና ከምትፈልጉት በላይ ረዘም ያለ ጊዜ በሚወስድበት ጊዜም እንኳ መሞከራችሁን አታቋርጡ። መሥራታችሁን እና በጌታ መታመናችሁን ቀጥሉ። በየእያንዳንዱ እርምጃዎችችሁ አዳኙ ይረዳችኋል።

ቃል የተገቡ በረከቶች

ኢየሱስ ክርስቶስ ንስሐ ስትገቡ ይቅር ይላችኋል እንዲሁም ይፈውሳችኋል። የጥፋተኝነት ስሜታችሁን በሰላምና በደስታ ይተካል። ኃጢአታችሁንም ከእንግዲህ ወዲህ አያስብም። በእርሱ ብርታት ትእዛዛቱን የመጠበቅ ፍላጎታችሁን ይጨምራል።

እርሱም ህይወታችሁን እና ልባችሁን ይቀይራል። ቀስ በቀስ፣ ታድጋላችሁ እንዲሁም እንደእርሱ መሆን ትጀምራላችሁ። ከእርሱ ጋር ያላችሁ የቃል ኪዳን ግንኙነት ወደ ኃይሉ የበለጠ እንድትደርሱ ያደርጋችኋል።

የጥያቄዎች እና መልሶች ምልክት

ጥያቄዎች እና መልሶች

እግዚአብሔር ይቅር እንዳለኝ እንዴት አውቃለሁ? እግዚአብሔር ንስሐ የገቡትን ይቅር እንደሚላቸው ቃል ገብቷል። የመንፈስ ቅዱስ ማጽናናት ሲሰማችሁ የአዳኙ የሃጢያት ክፍያ ሃይል በህይወታችሁ እየሰራ እንደሆነ ማወቅ ትችላላችሁ።

ንስሃ ለመግባት የኤጲስ ቆጶስ እርዳታ የሚያስፈልገኝ መቼ ነው? ንስሐ እንድትገቡ ለመርዳት ኤጲስ ቆጶስ የክህነት ቁልፎችን እና መንፈሳዊ ስጦታዎችን ይዟል። በማንኛውም ጊዜ የእርሱን እርዳታ እና ምክር መጠየቅ ትችላላችሁ። ለምሳሌ የንፅህና ህግን መጣስን የመሰሉ ከባድ ስህተቶችን ሰርታችሁ ከሆነ፣ከኤጲስ ቆጶሳችሁ ጋር ተገናኙ። እሱ አይኮንናችሁም። የኢየሱስ ክርስቶስ ተወካይ ስለሆነ እንዴት ሙሉ በሙሉ ንስሀ መግባት እና የአዳኙን የፈውስ እና የብርታት ሀይልን እንዴት መቀበል እንደምትችሉ ለማወቅ ይረዳችኋል።

ንስሀ ለመግባት እየሞከርኩ ነው፣ ነገር ግን ተመሳሳይ ስህተቶችን እሰራለሁ። አሁን ምን ማድረግ ይኖርብኛል? ጥሩ ልማዶችን ለማዳበር እና መጥፎዎቹንለመተው ጊዜ ስለሚወስድ ተስፋ አትቁረጡ። ወደ ክርስቶስ ተመለሱ። ጸጋው በቂ ነው። በድጋሚ ሞክሩ። ለማደግ በምታደርጉት ጥረት ውስጥ ብቻችሁን አይደላችሁም። ኢየሱስ ክርስቶስ ሁልጊዜም ከእናንተ ጋር ነው።

ኢየሱስ በከባድ ማዕበል ውስጥ የጴጥሮስን እጅ እንደያዘ የሚያሳይ ሥዕል።

ሄኖስ 1፥6 (ጥፋተኝነት ሊወገድ ይችላል)፤ ሞዛያ 4፥3 (በመንፈስ ቅዱስ በኩል፣ እግዚአብሔር ይቅር እንዳላችሁ ያሳውቃችኋል)፤ 26፥30 (በንስሐ በገባን ቁጥር አዳኙ ይቅር ይላል)፤ ኤተር 12፥27 (የአዳኙ ጸጋ ደካማ ነገሮችን ሊያጠናክር ይችላል)፤ ሞሮኒ 6፥8 (ንስሃ የገቡ ይቅር ተባሉ)፤ 10፥32 (በክርስቶስ ፍጹማን ሁኑ)፤ ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 1፥32 (ጌታ ንስሐ የገቡትን ይቅር ይላል)፤ 58፥42–43 (ንስሐ ኃጢአትን መናዘዝንና መተውን ይጨምራል) ተመልከቱ።

የቤተመቅደስ ምልክት

የቤተመቅደስ መግቢያ መታወቂያ ጥያቄዎች

በዘለአለም አባት እግዚአብሔር፣ በልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ እና በመንፈስ ቅዱስ እምነት እና ምስክርነት አለህ/አለሽ?

ስለኢየሱስ ክርስቶስ የኃጢያት ክፍያ እና እንደ አዳኝ እና ቤዛነት ስላለው ሚና ምስክርነት አለህ/አለሽ?