“በጉዞአችሁ የእግዚአብሔርን ብርሃን ተከተሉ፣” ለወጣቶች ጥንካሬ፦ ምርጫዎችን የማድረግ መመሪያ፣ [2022 (እ.አ.አ)]
“በጉዞአችሁ የእግዚአብሔርን ብርሃን ተከተሉ፣” ለወጣቶች ጥንካሬ
በጉዞአችሁ የእግዚአብሔርን ብርሃን ተከተሉ
ገላትያ 5፥25
ነገሮችን በግልፅ ማየት ስትችሉ የተሻሉ ምርጫዎችን ታደርጋላችሁ። ለዚያም ነው ብርሃን በጣም አስፈላጊ የሆነው ፦ ብርሃን ትክክለኛውን መንገድ ለማየት ቀላል ያደርጋል። የሰማይ አባት መልካሙን እና ክፉውን፣ ትክክል እና ስህተት የሆነውን በግልፅ ለመለየት እንዲረዳችሁ የሰማይ ብርሃን የሆነውን—የመንፈስ ቅዱስ ስጦታን ሰጥቷችኋል።
ዘለአለማዊ እውነቶች
በጥምቀት ጊዜ ከሰማይ አባት እና ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር አስደሳች የቃል ኪዳን ግንኙነት ትገባላችሁ። በቤተመቅደስ ውስጥ፣ ያንን ግንኙነት የሚያጠናክሩ ተጨማሪ ቃል ኪዳኖችን ትገባላችሁ። በየሳምንቱ በቅዱስ ቁርባን ጊዜ ቃል ኪዳኖቻችሁን ታድሳላችሁ። ትእዛዛትን ለመጠበቅ ፈቃደኛ መሆናችሁን ትገልፃላችሁ፣ እንዲሁም ጌታ መንፈስ ቅዱስ የዘወትር አጋራችሁ እንዲሆን እድል በመስጠት ይባርካችኋል። ይህም እርሱ ለእናንተ ከሰጣችሁ ታላቅ ስጦታዎች አንዱ ነው።
ጥሩ ምርጫ ማድረግ መንፈስን የመሰማት ችሎታችሁን ያሻሽላል። በዚህ ዓለም ውስጥ ብዙ ጥሩ እና ጠቃሚ ነገሮች አሉ። በምትበሉትና በምትጠቱት ነገር ሰውነታችሁ እንደሚጎዳ ሁሉ፣ የምታነቡት፣ የምታዩት እና የምትሰሙት ነገሮች በአእምሮአችሁ እና በመንፈሳችሁ ላይ እጅጉ ተጽዕኖ ያድሩባችኋል።
ግብዣዎች
በየቀኑ ለጌታ ጊዜ ስጡ። ከእርሱ ተማሩ። ሁልጊዜ እርሱን አስታውሱ። ወደ ሰማይ አባት ጸልዩ። ቅዱሳት መጻህፍትንና የኋለኛው ቀን ነቢያትን ቃላት አጥኑ። ከዚያም በተማራችሁት መሠረት ለመኖር ጣሩ።
መንፈስን የሚያነሳን፣ የሚያነቃቃን እና የሚጋብዘን ነገር ፈልጉ። ምን ማየት፣ ማንበብ፣ ማዳመጥ ወይም መሳተፍ እንዳለባችሁ ምርጫን ስታደርጉ ምን እንደሚሰማችሁ አስቡ። ጥሩ ሀሳቦችን ይጋብዛል? በተቀደሱ ነገሮች ላይ ከሚያፌዝ ወይም ሥነ ምግባር ከጎደለው ነገር ራቁ። እንደ አመጽ፣ አልኮል እና ጎጂ እጾች አይነት ውሳኔዎቻችሁን ወይም ለመንፈስ ያላችሁን ስሜት በሚያደበዝዝ በማንኛውም ነገሮች ውስጥ አትሳተፉ። ቪዲዮን ወይም መጫወቻን ለማጥፋት፣ ከፊልም ወይም ከዳንስ ለመውጣት፣ ሙዚቃን ለመቀየር ወይም ከመንፈስ ጋር ከማይጣጣም ከማንኛውም ነገር ለመራቅ ድፍረት ይኑራችሁ።
ማህበራዊ ሚዲያን ለማነሳሳት ተጠቀሙበት። ማህበራዊ ሚዲያ ኃይለኛ የመገናኛ መሳሪያ ሊሆን ይችላል። የምትጠቀሙት ከሆነ፣ በብርሃን፣ በእምነት እና በእውነት ላይ አተኩሩ። ሕይወታችሁን ሌሎች ሰዎች እያጋጠሟቸው ካሉ ነገሮች ጋር አታነጻጽሩ። ብቁነታችሁ የሰማይ ወላጆች ልጅ በመሆን ላይ የሚመካ ነው እንጂ ከማህበራዊ ሚዲያ የሚመጣ እንዳልሆነ አስታውሱ።
ጤናማ ልምዶችን እና እውነተኛ እና ዘላቂ ግንኙነቶችን ፈልጉ። የቴክኖሎጂ እና የሚዲያ አጠቃቀማችሁ ከቤተሰብ እና ከጓደኞች ጋር በአካል የምታሳልፉትን ጊዜ እንዳይሻማ ተጠንቀቁ። ማህበራዊ ሚዲያ እና ሌሎች ቴክኖሎጂዎች በምላሹ ብዙ ጥቅም ሳይሰጡ አብዛኛውን ጊዜአችሁን ሊወስዱ ይችላሉ። ከምናባዊው ዓለም እረፍት ውሰዱ እንዲሁም በእውነተኛ ህይወት ካሉ ሰዎች ጋር ተገናኙ።
ቃል የተገቡ በረከቶች
መንፈሱ ሁል ጊዜ ከእናንተ ጋር ሊኖር ይችላል። መንፈስ ቅዱስ ስለ ሰማይ አባት እና ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ይመሰክርላችኋል። እርሱም ያፅናናችኋል፣ ይመራችኋል፣ ያስጠነቅቃችኋል እንዲሁም ይቀድሳችኋል። እውነትን እንድታውቁና በዓለም ውስጥ ያለውን መልካም ነገር እንድታስተውሉ ይረዳችኋል።
ጥያቄዎች እና መልሶች
ከመንፈስ ቅዱስ የመጣ ስሜት እየተሰማኝ እንደሆነ እንዴት ማወቅ እችላለሁ? የመንፈስ ስሜትን ለመገንዘብ ጊዜን፣ ልምምድን እና ትዕግስትን ይጠይቃል። እርሱም ለተለያዩ ሰዎች በተለያየ መንገድ ይናገራል። የአንድን ሰው ምስክርነት በማዳመጥ የሚሰማችሁን ሰላማዊ ስሜት ወይም የተሳሳተ ምርጫ ካደረጋችሁ በኋላ የሚሰማችሁን ያልተረጋጋ ስሜት የመሳሰሉትን ቀላል ነገሮች ችላ አትበሉ። መንፈስ የሚናገርባቸውን የተለያዩ መንገዶች ለማግኘት ቅዱሳት መጻህፍትን አጥኑ፣ ስለእነርሱ ጸልዩእንዲሁም የመንፈስ ስሜት የሚያሰማችሁ አጋጣሚዎችን ፈልጉ።
የብልግና ምስል ምንድን ነው? ለምንስ ይህን ማስወገድ አለብኝ? የብልግና ምስል፣ በምስሎች ወይም በቃላት፣ ጾታ ስሜትን ለመቀስቀስ የተነደፈ መግለጫ ነው። የብልግና ምስሎች ቪዲዮዎችን፣ ሥዕሎችን፣ መጻሕፍትን እና ሙዚቃዎችን ጨምሮ በተለያዩ መንገዶች ይመጣሉ። እንዲሁም በጓደኞች መካከል የተላኩ መልዕክቶች ወይም ምስሎች ሊሆኑ ይችላሉ። የብልግና ምሥሎች የተቀደሱ ነገሮችን ማለትም ሥጋዊ አካላችንንና የጾዊ ስሜታችንን ያንቋሽሻሉ። ሳታስቡ የብልግና ምሥሎች ሊያጋጥሟችሁ ይችላሉ። ሆን ብላችሁ ሆነ ሳታውቁ የብልግና ምሥሎችን ከተመለከታችሁ ወዲያውኑ መመልከታችሁን አቁሙ። እንዲሁም ወላጅን ወይም ሌላ ታማኝ አዋቂን ለማንጋገር ትፈልጉም ይሆናል። ሆን ብሎ የብልግና ምስሎችን መመልከት ኃጢአት ነው እንዲሁም መንፈስን የመሰማት ችሎታን ይጎዳል። ራስን መግዛትን ያዳክማል እንዲሁም ራሳችሁንእና ሌሎችን የምታዩበትን መንገድ ያዛባል። ኢየሱስ ክርስቶስ የብልግና ምስሎችን መመልከት እንድትቋቋሙ እና ንስሐ እንድትገቡ የመርዳት ኃይል አለው። ወደ እርሱ ተመለሱ፣ ከጨለማ ራቁ። ኤጲስ ቆጶሳችሁ በአዳኙ በኩል ጥንካሬን እና ይቅርታን እንድታገኙ ሊረዳችሁ ይችላል።
አሞጽ 5፥14 (መልካምን ፈልጉ)፤ ገላትያ 5፥22–23 (የመንፈስ ፍሬዎች)፤ ሞሮኒ 7፥18–19 (የክርስቶስ ብርሃን)፤ ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 6፥23 (ጌታ ሰላም ይናገራል)፤ 20፥77፣ 79 (የቅዱስ ቁርባን ጸሎቶች) ተመልከቱ።
የቤተመቅደስ መግቢያ መታወቂያ ጥያቄዎች
ጌታ እንዲህ ብሏል ሁሉም ነገሮች በፊቴ “በንጽህና ይሰሩ” (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 42፥41). በአስተሳሰብህ/ሽ እና በባህሪህ/ሽ ውስጥ የሥነ–ምግባር ንጽህና እንዲኖርህ/ርሽ ጥረት ታደርጋለህ/ታደርጊያለስሽ? የንጽህና ህግን ታከብራለህ/ታከብሪያለሽ?
የሰንበትን ቀን በቤትም ሆነ በቤተክርስቲያን ቅዱስ አድርጎ ለመጠበቅ፤ በስብስባዎች ለመገኘት፤ ቅዱስ ቁርባን ለመቀበል ለመዘጋጀት እና በብቁነት ለመውሰድ፤ እንዲሁም ህይወትህን/ህይወትሽን ከወንጌል ህግጋት እና ትዕዛዛት ጋር አስማምተህ/ሽ ለመኖር ትጥራለህ/ትጥሪያለሽ?