2014 (እ.አ.አ)
በክርስቶስ ፍቅር አለምን ሙሏት
ዲሴምበር 2014


በክርስቶስ ፍቅር አለምን ሙሏት

ስለ ገና በአል ስናስብ፣ በአብዛኛው ስጦታዎችን ስለ መስጠት እና ስለ መቀበል እናስባለን። ስጦታዎች ከፍተኛ ዋጋ የምንሰጣቸው የባህል ክፍል ሊሆኑ ይችላሉ፣ ነገር ግን የወቅቱን ክቡርነት ሊቀንሱ እናም ትርጉም ባለው መንገድ የአዳኛችንን ልደት ከማክበር ሊያውኩን ይችላል።

ከግል ልምዴ እንደማውቀው በጣም የሚታወሱት የገና በአሎች በጣም ትሁት የሆኑት ናቸው። የህፃንነቴ ስጦታዎች በዛሬ ጊዜ መለኪያዎች በእርግጠኝነት ያልተብለጨለጩ ነበሩ። አንድ አንድ ጊዜ የተሰፋ ሸሚዝ ወይም ጓንቶች ወይም ካልሲዎች ተቀብያለው። ወንድሜ እራሱ ከእንጨት የቀረጸውን ቢላ ሰጥቶኝ የነበረነትን አንድ ለየት ያለ የገና በአል አስታውሳለው።

የገና በአልን ትርጉም ያለው ለማድረግ ውድ የሆኑ ስጦታዎችን አይጠይቅም። ከ 1987 እስከ 1992 (እ.አ.አ) እንደ ሰባ ጉባኤ አባል ባገለገለው የቤተክርስቲያን ሽማግሌ ግሌን ኤል ረድ የተነገረውን ታሪክ አስታወስኩ። ከብዙ አመታት በፊት በገና በአል ዋዜማ ላይ፣ የኤጲስ ቆጶስ ግምጃ ቤትን እየተቆጣጠረ ሳለ፣ ወደ ከተማው በቅርቡ ስለመጡ ችግረኛ ቤተሰብ ከአንድ የቤተክርስቲያን መሪ ሰማ። ትንሹን የመኖሪያ ቦታቸውን ለመጎብኘት ሲሄድ፣ አንድ ባል የሌላት ወጣት እናት ከ10 አመት በታች ከሆኑ አራት ልጆች ጋር አገኘ።

የቤተሰቡ ችግርተኝነት በጣም ትልቅ ከመሆኑ የተነሳ በዛ የገና በአል እናት ለልጆቿ ስጦታዎችን መግዛት አልቻለችም ነበር፤ የገና ዛፍም እንኳን መግዛት አልቻለችም። ወንድም ረድ ከዛ ቤተሰብ ጋር ተነጋገረ እናም ሶስቱ ትንንሽ ሴት ልጆች አሻንጉሊት ወይም በእንስሳት ቅርፅ የተሰሩ መጫወቻዎችን እንደሚወዱ አወቀ። ስድስት አመት የሆነውን ወንድ ልጅ ምን እንደሚፈልግ ሲጠይቅ፣ የራበው ትንሽዬ ልጅ እንዲህ ብሎ መለሰ፣ “አንድ ጎድጓዳ ሳህን የተከካ አጃ ሾርባ እፈልጋለሁ።”

ወንድም ረድ ትንሹን ልጅ የተከካ የአጃ ሾርባ እናም ምናልባት ሌላ ነገር ቃል ገባለት። ከዛ ወደ ኤጲስ ቆጶሱ ግምጃ ቤት ሄደ እና የዛን ቤተሰብ አፋጣኝ ፍላጎት ለማሟላት ምግብና ሌሎች አቅርቦቶችን ሰበሰበ።

በዛ ጠዋት አንድ ቸር የኋለኛው ቀን ቅዱስ 50 ዶላረ “ለተቸገረ ሰው” ብላ ሰጥታው ነበር። ያንን መዋጮ በመጠቀም ወንድም ረድ ሶስቱን የራሱን ልጆች ይዞ የገና በአል ግብይት ሄደ—ልጆቹ ለተቸገሩት ልጆች መጫወቻዎችን መረጡ።

መኪናውን በምግብ፣ በአልባሳት፣ በስጦታዎች፣ በገና ዛፍ እና በአንድ አንድ ጌጣጌጦችን ከጫኑት በኋላ ረዶቹ ወደ እነዛ ቤተሰብ መኖሪያ በመኪና ተጓዙ። እዛ እናትዬዋን እና ልጆቿን የገና ዛፉን በማስተካከል አገዙ። ከዛም ከስሩ ስጦታዎችን አስቀመጡ እናም ለትንሹ ልጅ ትልቅ እሽግ የተከካ አጃ ስጦታ ሰጡት።

እናትዬዋ አነባች፣ ልጆቹ ተደሰቱ እናም ሁሉም የገና መዝሙር ዘመሩ። በዛ ምሽት የረድ ቤተሰብ ለእራት ሲሰበሰቡ፣ ለሌላ ቤተሰብ የገና ደስታን ስላመጡ እንዲሁም ትንሹ ልጅ አንድ ጎድጓዳ ሳህን የተከካ የአጃ ሾርባ እንዲቀበል ለማግውዝ ስለቻሉ ምስጋና አቀረቡ።1

ክርስቶስ እና የመስጠት መንፈስ

የሰማይ አባታችን የልጁን ልደት ለማክበር የመረጠውን ቀላሉን ነገር ግን ክብር ያለውን መንገዶች አስቡ። በዛ በተቀደሰ ምሽት፣ መልአክቶች ለሀብታሞች ሳይሆን ለእረኞች ተገለፁ። ልጅ ክርስቶስ በትልቅ ቤት ውስጥ ሳይሆን በግርግም ውስጥ ተወለደ። በሀር ሳይሆን በመጠቅለያ ጨርቅ ተጠቀለለ።

የዛ የመጀመሪያው የገና በአል ቀለል ማለት የአዳኙን ሕይወት ጠቆመ። ምንም እንኳን መሬትን ቢፈጥርም፣ በግርማዊ ግዛቶች እና በክብር ውስጥ ቢራመድም፣ በአብ ቀኝ እጅ ቢቆምም፣ የሚረዳ እንደሌለው ልጅ ወደ ምድር መጣ። ሕይወቱ የትሁት ባላባትነት ሞዴል ነበር፣ እና በድሆች፣ በታመሙት፣ ባዘኑት እና ሸክማቸው በከበደ መሀል ሄደ።

ምንም እንኳን ንጉስ ቢሆንም፣ ስለ ክብርም ሆነ ስለሰዎች ሀብት አልተጨነቀም። ሕይወቱ፣ ቃሎቹ እና የቀን ለቀን ተግባሮቹ ቀለል ያሉ ነገር ግን ታላቅ የሆኑ የክብር ሀውልቶች ነበሩ።

እንዴት መስጠት እንዳለበት ፍፁም በሆነ ሁኔታ ያወቀው ክርስቶስ ኢየሱስ የመስጠትን መንገድ አስቀመጠልን። በብቸኝነትና በሀዘን ልባቸው ለከበደ ሰዎች፣ ርህራሄንና መፅናናትን ያመጣል። በህመምና በስቃይ አካላቸውና አእምሮአቸው ለተጎዱ ሰዎች፣ ፍቅርንና ፈውስን ያመጣል። ነፍሳቸው በሀጢያት ለተጫነ ሰዎች፣ ተስፋን፣ ይቅርታን እና መዳንን ያቀርባል።

አዳኛችን በእኛ መሀል ቢሆን፣ ሁሌም በነበረበት ቦታ የዋሆችን፣ አዛኞችን፣ ትሁቶችን፣ በጭንቀት ላይ ያሉትን እና የመንፈስ ድሆችን እያገለገለ እናገኘው ነበር ። በዚህ የገና በአል ወቅትና ሁሌም እሱ እንደሚወደው በመውደድ ለእርሱ እንስጥ። የልደቱን ትሁት ክብር፣ ስጦታዎች እና ሕይወት እናስታውስ። በቀላል የደግነት፣ የልግስና እና የርህራሄ ተግባሮች አማካኝነት በፍቅሩ ብርሀን እና የመፈወስ ኃይሉ አለምን እንሙላት።

ማስታወሻ

  1. ግሌን ኤል ረድ Pure Religion: The Story of Church Welfare since 1930 (እ.አ.አ) (1995), 352–53፤ እነዲሁም ግሌን ኤል ረድ፣ “A Bowl of Oatmeal,”Church News፣ ታህሳስ 2፣ 2006 (እ.አ.አ)፣ 16።

ከዚህ መልእክት ማስተማር

ፕሬዘደንት ኡክዶርፍ የአዳኙን የመስጠት መንገድ መከተል እዳለብን አስተማሩ። የምትጎበኙትን ሰዎች ተራ በተራ አዳኙ የሰጣቸውን ስጦታ እዲጠሩ መጠየቅን አስቡ፣ እናም ያንን ስጦታ ሌሎችን ለማገልገል እንዴት መጠቀም እንደሚችሉ ተወያዩ። ለምሳሌ፣ አንድ አባል በሙዚቃ ስልጠና ተባርኮ ከነበረ፣ እሱ ወይም እሷ ወደ አንድ አንድ ጎረቤቶች በመሄድ የገና መዝሙር መዘመር ይችላል/ትችላለች። ከምትጎበኟቸው ሰዎች ጋር የትኛውን ስጦታ ለማካፈል፣ እንዴት ማካፈል እንደሚችሉ እና ለማን ማካፈል እንዳለባቸው እንዲያውቁ መንፈሳዊ ማነሳሻ ለመጠየቅ በፀሎት እንዲበረከኩ ማቅረብ ትችላላችሁ ። በምትቀበሉት ማንኛውም መንፈሳዊ ማነሳሻ ላይ ክትትል አድርጉ።