ቅዱሳት መጻህፍት
ሞርሞን ፱


ምዕራፍ ፱

ሞሮኒ በክርስቶስ ለማያምኑት ንሰሃ እንዲገቡ ጠራቸው—ራዕይ ስለሚሰጠው እናም ለታማኞችም ራዕዮችን እናም ምልክቶችን ስለሚሰጠው የተአምራት እግዚአብሔር አወጀ—ተአምራቶች የቆሙት እምነት ባለመኖሩ ነው—ያመኑትን ምልክቶች ይከተሉአቸዋል—ሰዎች ብልህ እንዲሆኑና ትዕዛዛቱን እንዲጠብቁ ይመከራሉ። ከ፬፻፩–፬፻፳፩ ዓ.ም. ገደማ።

እናም አሁን፣ ደግሞ በክርስቶስ ስለማያምኑት እናገራለሁ።

እነሆ፣ በመጎብኘታችሁ ቀን ታምናላችሁን—እነሆ፣ ጌታ ሲመጣ፣ አዎን በዚያ፣ በታላቁ ቀን መሬት እንደ ጥቅልል በምትጠቀለልበት ጊዜ እናም አለቶችም በታላቅ ሙቀት በሚቀልጡበት ጊዜ፣ አዎን፣ በዚያ ታላቅ ቀን በእግዚአብሔር በግ ፊት በምትቆሙ ጊዜ—እግዚአብሔር የለም ትላላችሁን?

ክርስቶስን መካዳችሁን ትቀጥሉበታላችሁ፣ ወይንም የእግዚአብሔርን በግ ለማየት ይቻላችኋል? ጥፋታችሁን እያወቃችሁ ከእርሱ ጋር ለመኖር ታስባላችሁን? ህጉን በማንኛውም እንደጣሳችሁ ነፍሳችሁ አውቃ በምትቆስል ጊዜ ከቅዱሱ ጋር በመኖር ደስተኛ መሆን እንደምትችሉ ታስባላችሁን?

እነሆ፣ የተበከለ ህሊና በፊቱ እያላችሁ ከቅዱስ እና ፍትህ እግዚአብሔር ጋር መኖር ከተኮነኑት ነፍሳት ጋር በሲዖል ከመኖር በላይ አሰቃቂ ነው እላችኋለሁ።

እነሆም፣ በእግዚአብሔር ፊት ራቁታችሁን መሆናችሁን፣ እናም ደግሞ የእግዚአብሔር ክብርና፣ የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስነት ለማየት በምትመጡበት ጊዜ፣ በእናንተ ላይ የማይጠፋን እሳት ያቀጣጥላል።

እናንተ የማታምኑ ሆይ፣ ወደ ጌታ ተመለሱ፤ ምናልባት በመጨረሻውና በዚያ በታላቁ ቀን እንከን የሌላችሁ፣ ንፁህ፣ መልካም፣ እናም በበጉ ደም የፀዳችሁ ሆናችሁ ትገኙ ዘንድ ወደ አብ በኢየሱስ ስም በኃይል ጩሁ።

እናም እናንተ የእግዚአብሔርን ራዕይ ለካዳችሁና፣ እነርሱ ተፈፅመዋል፣ ራዕዮች፣ ትንቢቶች፣ ስጦታዎችም ሆነ፣ መፈወስ፣ እናም በልሳን መናገርም ሆነ፣ በልሳን የሚናገሩትን መተርጎም ቆሟል የምትሉትን በድጋሚ እናገራችኋለሁ፤

እነሆ እኔ እንዲህ እላችኋለሁ፣ እነዚህን ነገሮች የሚክድ የክርስቶስን ወንጌል አያውቅም፤ አዎን፣ ቅዱሳን መጽሐፍትንም አላነበበም፣ ይህም ቢሆን እንኳን አልተረዱትም

እግዚአብሔር ትናንትና፤ ዛሬም እንዲሁም ለዘለዓለም አንድ እንደሆነ እናም በእርሱም የመቀያየርም ሆነ የመለወጥ ጥላ አለመኖሩን አላነበብንምን?

እናም አሁን፣ ለራሳችሁ የሚለዋወጥና በእርሱም የመለዋወጥ ጥላ ያለበትን አምላክ የምታስቡ ከሆነ፣ የተአምራት አምላክ ያልሆነውን አምላክ ለራሳችሁ አስባችኋል።

፲፩ ነገር ግን እነሆ፣ ለእናንተም የተአምራት አምላክ፣ እንዲሁም የአብርሃምን አምላክ፣ እናም የይስሃቅን አምላክ፣ እናም የያዕቆብን አምላክን አሳያችኋለሁ፤ እርሱም ሰማይና ምድርን፣ እናም በውስጡም ያሉትን ነገሮች ሁሉ የፈጠረ አምላክ ነው።

፲፪ እነሆ፣ እርሱ አዳምን ፈጠረና፣ በአዳም ምክንያት የሰው ልጅ ውድቀት መጣ። እናም በሰው ልጅ መውደቅ የተነሳ፣ አብና ወልድ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ መጣ፤ እናም በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነትም ለሰው ልጅ ቤዛነት መጣ።

፲፫ እናም በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ለሰዎች ቤዛነት በመምጣቱ፣ ወደ ጌታም ፊት ተመልሰዋል፤ አዎን፣ ሁሉም ሰዎች የዳኑበት በዚህም ነው፥ የክርስቶስ ሞት ትንሣኤን አመጣ፣ ይህም መጨረሻ ከሌለው እንቅልፍ ቤዛነት አመጣ፣ መለከቱ ሲነፋ ሰዎች ሁሉ ከዚህ እንቅልፍ በእግዚአብሔር ኃይል ይነቃሉ፣ እናም ትልልቆችም ሆኑ ትንንሾች የሆኑት ይመጣሉ፣ እናም ዘላለማዊ ከሆነው የሞት ሰንሰለት በመዳንና በመፈታት፣ ይህም ሞት ጊዜአዊው ሞት ነው፣ በፍርዱ ወንበር ፊት ሁሉም ይቆማሉ።

፲፬ እናም የቅዱሱ ፍርድ በእነርሱ ላይ ይመጣል፤ ንፁህ ያልሆነውም አሁን ንፁህ ሳይሆን የሚቀርበት ጊዜ ይመጣል፤ እናም ፃድቅ የሆነው አሁንም ፃድቅ ይሆናል፤ ደስተኛ የነበረውም አሁን ደስተኛ ይሆናል፤ እንዲሁም ደስተኛ ያልነበረው አሁንም ደስተኛ አይሆንም።

፲፭ እናም አሁን፣ እናንተ ለራሳችሁ ምንም ተአምራትን መስራት የማይችል አምላክን ያሰባችሁ ሁሉ፣ እንዲህ ስል እጠይቃችኋለሁ፥ እኔ የተናገርኳቸው እነዚህ ነገሮች ሁሉ አልፈዋልን? መጨረሻው መጥቷልን? እነሆ አይደለም እላችኋለሁ፤ እናም እግዚአብሔር የተአምራት አምላክ መሆኑን አላቆመም።

፲፮ እነሆ፣ እግዚአብሔር የሰራቸው በዐይናችን ድንቅ አይደሉምን? አዎን፣ እናም ድንቅ የሆነውን የእግዚአብሔር ሥራዎች የሚገባው ማነው?

፲፯ በቃሉ ሰማይና ምድር መፈጠሩ፤ እናም ቃሉ ባለው ኃይል የሰው ልጅ ከመሬት አፈር መፈጠሩ፤ እናም በቃሉ ኃይል ተአምራት መሠራቱ ተአምር አይደለም የሚል ማነው?

፲፰ እናም ኢየሱስ ክርስቶስ ብዙ ተአምራትን አልሰራም የሚለው ማነው? እናም በሐዋርያቶቹ እጅ ብዙ ተአምራት ተሰርተው ነበር።

፲፱ እናም በዚያ ጊዜ ተአምራቶች ተደርገው ከሆነ፣ እግዚአብሔርስ የተአምራት አምላክ መሆኑን ለምን ያቆማል እናም ግን የማይለወጥ አምላክ ሊሆን ይችላል? እንዲሁም እነሆ እላችኋለሁ እርሱ አይለወጥም፣ የሚለወጥ ከሆነ አምላክነቱን ያቆማል፣ እናም አምላክነቱን አያቆምም፣ የተአምራትም አምላክ ነው።

እናም በሰው ልጆች መካከል ተአምራት መስራቱን ያቆመበት ምክንያት እነርሱ እምነት አጥተው በመመንመናቸው፣ እናም ከትክክለኛው መንገድ በመራቃቸውና፣ የሚያምኑበትን አምላክ ባለማወቃቸው ነው።

፳፩ እነሆ፣ እንዲህ እላችኋለሁ ምንም ባለመጠራጠር በክርስቶስ የሚያምን፣ በክርስቶስ ስም አብን ማንኛውንም ነገር ከጠየቀ ለእርሱ ይሰጠዋል፤ እናም ይህ ቃል ኪዳን ለሁሉም፣ እንዲሁም እስከ አለም ዳርቻ እንኳን ነው።

፳፪ እነሆም የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ እስከምፅአቱ ለሚቆዩትም ደቀ መዛሙርቱ፣ አዎን፣ እናም ደግሞ ለሁሉም ደቀመዛሙርት ህዝቡ እየሰሙት እንዲህ ሲል ተናገራቸው፥ ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱና፣ ለፍጥረት ሁሉ ወንጌልን ስበኩ።

፳፫ እናም ያመነና የተጠመቀም ይድናል፤ ያላመነ ግን ይኮነናል

፳፬ እናም ያመኑትን እነዚህ ምልክቶች ይከተሏቸዋል—በስሜ አጋንንትን ያወጣሉ፤ በአዲስ ልሳንም ይናገራሉ፤ መርዛማ እባቦችንም ያነሳሉ፤ እናም የሚገድልን ነገር ቢጠጡም አይጎዳቸውም፤ እጃቸውን በህመምተኞች ላይ ይጭናሉና ያድኗቸዋል፤

፳፭ እናም ምንም ሳይጠራጠር በስሜ የሚያምን ቢኖር፣ ለእርሱ እስከ ዓለም ዳርቻ ቃሌን ሁሉ ማረጋገጫ አደርግለታለሁ።

፳፮ እናም እንግዲህ፣ እነሆ፣ የጌታን ሥራ የሚቃወም ማን ነው? ንግግሩንስ የሚክድ ማን ነው? ሁሉን ቻይ በሆነው በጌታ ኃይል ላይ የሚነሳስ ማን ነው? የጌታን ሥራ የሚንቅ ማን ነው? የክርስቶስን ልጆች የሚንቅስ ማን ነው? እነሆ፣ የጌታን ሥራ የምትንቁ ሁሉ፣ ትገረማላችሁ እናም ትጠፋላችሁ።

፳፯ አቤቱ አትናቁና አትገረሙ፤ ነገር ግን የጌታን ቃላት አድምጡት፣ እናም፣ በስሙም የምትፈልጉትን ነገር አብን በኢየሱስ ስም ጠይቁት። አትጠራጠሩ፣ ነገር ግን የምታምኑ ሁኑ፣ በጥንት ጊዜ እንደነበሩት ሰዎች በእምነት ጀምሩ፤ እናም በሙሉ ልባችሁ ሆናችሁ ወደ ጌታ ፤ እናም በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ በፊቱ የራሳችሁን መዳን ፈፅሙ

፳፰ በሙከራ ጊዜያችሁም ብልህ ሁኑ፤ የጎደፉ ነገሮችን በሙሉ ከላያችሁ ላይ አራግፉ፤ ለምኞቶቻችሁ ማስፈፀሚያ በክፉ አትጠይቁ፤ ነገር ግን ወደ ፈተና እንዳትገቡ ዘንድ፣ ነገር ግን እናንተ እውነተኛውን እናም ህያውን እግዚአብሔር ታገለግሉ ዘንድ በማይነቃነቀው ፅናታችሁ ጠይቁ።

፳፱ ብቁ ሳትሆኑ እንዳትጠመቁም ተጠንቀቁ፤ የክርስቶስንም ቅዱስ ቁርባን ብቁ ሳትሆኑ ላለመቁረስ ተጠንቀቁ፤ ነገር ግን ሁሉንም ነገሮች ስታደርጉ በብቁነት ማድረጋችሁን ተመልከቱ፣ ስታደርጉም በህያው እግዚአብሔር ልጅ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አድርጉት፤ እናም ይህን ካደረጋችሁና፣ እስከመጨረሻ ፅኑ ከሆናችሁ በምንም ዓይነት እናንተ አትጣሉም።

እነሆ፣ ሙታን ሆኜ እንደምናገረው እናገራችኋለሁ፤ ምክንያቱም እናንተ የእኔ ቃል እንደሚኖራችሁ አውቃለሁ።

፴፩ በጉድለቶቼ ምክንያት አትኮንኑኝ፣ አባቴንም በጉድለቶቹ አትኮንኑት፣ ከእርሱም በፊት ሲጽፉ የነበሩትንም አትኮንኑአቸው፤ ነገር ግን እግዚአብሔር እኛ ከነበርነው የበለጠ ብልህ ለመሆን ትማሩ ዘንድ ፍፁም አለመሆናችንን ስለገለፀላችሁ ምስጋና አቅርቡለት እንጂ።

፴፪ እናም አሁን፣ እነሆ፣ በመካከላችን በንግግራችን ስርዐት መሰረት የተላለፉልንና የቀየርናቸው የተለወጡ ግብፃውያን ተብለው በሚጠሩት ፊደላት እንደችሎታችን ይህንን መዝገብ ፅፈናል።

፴፫ እናም ሰሌዳዎቻችን በበቂ ሁኔታ ትልቅ ቢሆኑ ኖሮ በዕብራውያን እንፅፈው ነበር፤ ነገር ግን ዕብራውያንም ደግሞ በእኛ ተለውጧል፤ እናም በዕብራውያን መፃፍ ብንችል ኖሮ፣ እነሆ፣ በመዛግብቶቻችን ውስጥ ስህተት አታገኙም ነበር።

፴፬ ነገር ግን ጌታ የፃፍናቸውን ነገሮች ያውቃል፣ እናም ደግሞ ማንም ሌላ ሰው ቋንቋችንን አያውቅም፤ እናም ምክንያቱም ማንም ሌላ ሰው ቋንቋችንን ባለማወቁ፣ ስለዚህ እርሱም የሚተረጉምበትን መንገድ አዘጋጅቷል።

፴፭ እናም እነዚህ ነገሮች እምነት አጥተው የመነመኑትን ወንድሞቻችንን ደም ከልብሶቻችን ላይ እናነፃ ዘንድ የተፃፉ ናቸው።

፴፮ እናም እነሆ፣ ወንድሞቻችንን በተመለከተ እነዚህን ነገሮች፣ አዎን፣ ክርስቶስን ወደማወቅ ይመለሱ ዘንድ፣ የፈለግናቸው በምድሪቱ ይኖሩ በነበሩት ቅዱሳን ሁሉ ፀሎት መሰረት ነው።

፴፯ እናም ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስም ፀሎታቸው እንደ እምነታቸው እንዲመለስላቸው ያድርግ፤ እግዚአብሔር አብም ከእስራኤል ቤት ጋር የገባውን ቃል ኪዳን ያስታውስ፤ እናም በክርስቶስ ስም ባላቸው እምነት በኩል ለዘለዓለም ይባርካቸው። አሜን።