2023 (እ.አ.አ)
ቤተሰቦች ዘለአለማዊ ናቸው
ጥር 2023 (እ.አ.አ)


“ቤተሰቦች ዘለአለማዊ ናቸው፣“ ሊያሆና፣ጥር 2023 (እ.አ.አ)

ወርሀዊ የሊያሆና መልዕክት፣ ጥር 2023 (እ.አ.አ)

ቤተሰቦች ዘለአለማዊ ናቸው

ምስል
የሚስቁ ቤተሰብ

ቤተሰብ የህብረተሰብ እና የቤተክርስቲያኗ መሰረታዊ ክፍል ነው። የኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን አባላት ቤተሰቦች ዘለአለማዊ ሊሆኑ እንደሚችሉ ያምናሉ። በምድር ያሉ ቤተሰቦቻችንን ለማጠናከር እንሰራለን። የዘለአለም ቤተሰብን በረከት እንደምንቀበልም እምነት አለን።

የእግዚአብሔር ቤተሰብ

ሁሉም ሰዎች የሰማይ ወላጆች መንፈሳዊ ወንድ እና ሴት ልጆች ናቸው። እኛ ሁላችንም የእግዚአብሔር ቤተሰብ ክፍል ነን። ሁላችንም መለኮታዊ ተፈጥሮ እና ፍጻሜ አለን። በጽድቅ ከኖርን የእርሱ ቤተሰብ አካል በመሆን ከሰማይ አባታችን ጋር ለዘለአለም ለመኖር መመለስ እንችላለን።

ምስል
አዲስ ተጋቢዎች በቤተመቅደስ በር ላይ

የሠርግ ፎቶ በጆሴፍ ካሉባ

የዘለአለም ቤተሰቦች

ወንድ እና ሴት በቤተመቅደስ ውስጥ ሲጋቡ እና ቃል ኪዳኖቻቸውን ሲጠብቁ ጋብቻቸው የዘለአለም ይሆናል። ይህ የቤተመቅደስ ሥርዓት መታተም ተብሎ ይጠራል። ወላጆቻቸው ከታተሙ በኋላ የተወለዱ ልጆች በዚያ ቃል ኪዳን የተወለዱ ናቸው። ወላጆቻቸው ከመታተማቸው በፊት የተወለዱ ልጆች ከእነርሱ ጋር በቤተመቅደስ ውስጥ ሊታተሙና ለዘለአለም ቤተሰብ ሊሆኑ ይችላሉ። በትውልዶቻቸው ውስጥ ያሉ ቤተሰቦቻቸው አንድ ላይ መታተም ይችሉ ዘንድ የቤተክርስቲያኗ አባላት የቤተሰብ ታሪክን እና የቤተመቅደስ ስራን ይሰራሉ። ኢየሱስ ክርስቶስ እና የኃጢያት ክፍያው የዘለአለም ቤተሰብ በረከትን የሚቻል ያደርጋል።

ጋብቻ

በወንድ እና በሴት መካከል የሚደረግን ጋብቻ ያቋቋመው እግዚአብሔር ነው። የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ባሎች እና ሚስቶች አንዳቸው ለአንዳቸው ታማኝ እንዲሆኑ እንዲሁም ለጋብቻ ቃል ኪዳናቸው ታማኝ እንዲሆኑ ያስተምራል። በሀሳብ፣ በንግግር፣ እና በድርጊት እውነተኛ መሆን አለባቸው። ጋብቻ በእኩልነት ላይ የተመሰረተ ጥምረት ነው እናም ባለትዳሮች እርስ በርስ መበረታታት፣ መጽናናት እና መረዳዳት ይኖርባቸዋል።

ምስል
ወላጆች ከጨቅላ ልጅ ጋር

ወላጆች እና ልጆች

እግዚአብሔር አዳምን እና ሔዋንን ልጆች እንዲወልዱ አዘዛቸው። የቤተክርስቲያን መሪዎች ይህ ትዕዛዝ አሁንም በሥራ ላይ እንደሆነ አስተምረዋል። ወላጆች ልጆቻቸውን በፍቅር እና በጽድቅ ለማሳደግ በጋራ ይሰራሉ (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 68፥25–28 ይመልከቱ)። ልጆች ወላጆቻቸውን እንዲያከብሩ እና እንዲታዘዙ ትምህርት ተሰጥቷቸዋል (ዘጸዓት 20፥12 ይመልከቱ)።

ማስተማር እና መማር

ወላጆች ልጆቻቸው እግዚአብሔርን እንዲወዱ እና ትዕዛዛቱን እንዲያከብሩ ያስተምሯቸዋል። የቤተሰብ ህይወት ደስታ እንዲሰማን እንዲሁም ትዕግስትን እና ራስ ወዳድነትን እንድንማር እድል ይሰጠናል። እነዚህ ባህርያት ይበልጥ እግዚአብሔርን እንድንመስል ይረዱናል እንዲሁም እንደ ቤተሰብ ለዘለአለም በደስታ ለመኖር ያዘጋጁናል።

ቤተሰቦችን ማጠንከር

ውጤታማ ቤተሰብን መገንባት ስራን፣ ትጋትን እና ትዕግሰትን ይጠይቃል። እንደ እምነት፣ ጸሎት፣ ይቅር ባይነት፣ ፍቅር፣ ሥራ እና ጤናማ መዝናኛ ያሉ የወንጌል መርሆዎች በቤተሰብ ህይወት ውስጥ ደስታን እንድናገኝ ሊረዱን ይችላሉ። ቤተሰቦቻችንን እንዴት ማጠንከር እንዳለብን ለማወቅ እንድንችል የግል መገለጥ ልንቀበልም እንችላለን።

ምስል
የኢየሱስ ክርስቶስ ምስል

የክርስቶስ ምስል፣ በሄንሪክ ሆፍማን

ለሁሉም የተዘጋጁ በረከቶች

እዚህ ምድር ላይ የጥሩ ቤተሰብ አባል የመሆን እድል የሚያገኘው ሁሉም ሰው አይደለም። ሆኖም፣ የእርሱን ትዕዛዛት የሚጠብቁ ሁሉ የዘለአለም ቤተሰብ በረከቶችን ሁሉ እንደሚቀበሉ እግዚአብሔር ቃል ገብቷል። በእርሱ መታመን እንችላለን እንዲሁም በእርሱ ጊዜ እምነት ሊኖረን ይችላል፡፡