2010–2019 (እ.አ.አ)
የጸሎት መልሶች
የሚያዝያ 2019 (እ.አ.አ) አጠቃላይ ጉባኤ


የጸሎት መልሶች

አብ ያውቀናል፣ ፍላጎቶቻችንን ያውቃል እንዲሁም በደምብ ይረዳናል።

የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል አንዱ አስፈላጊ እና የሚያጽናና ትምህርት የሰማይ አባታችን ለልጆቹ ፍጹም ፍቅር ያለው መሆኑ ነው። በዚያ ፍጹም ፍቅር ምክንያት እንደፍላጎታችን ብቻ ሳይሆን ማለቂያ በሌለው ጥበቡም ጭምር ይባርከናል። በነቢዩ ኔፊ በቀላሉ እንደተገለጸው “[እግዚአብሔር] ልጆቹን እንደሚወድ አውቃለሁ።”1

የዚያ ፍጹም ፍቅር አንዱ ገጽታ ሳናውቀውም ሆነ ሳንገነዘበው የሰማይ አባታችን በህይወታችን ዝርዝሮች ውስጥ መሳተፉ ነው። ከልብ በመነጨ ልባዊ ጸሎት አማካኝነት የአብን መለኮታዊ መመሪያ እና እርዳታ እንጠይቃለን። ቃል ኪዳኖቻችንን ስናከብር እና እንደአዳኛችን ለመሆን ስንጥር በመንፈስ ቅዱስ ተጽዕኖ እና መነሳሳት አማካኝነት የማያቋርጥ የመለኮታዊ ምሪት ፍሰት እንቀበላለን።2

ቅዱሳት መጻህፍት “ሳትለምኑት አባታችሁ የሚያስፈልጋችሁን ያውቃልና፣”3 እናም “ሁሉንም ነገሮች ያውቃል፣ ሁሉም ነገሮች በአይኖ[ቹ] ፊት ናቸውና” ሲሉ ያስተምሩናል።4

ነቢዩ ሞርሞን የዚህ ምሳሌ ነው። በህይወት ቆይቶ የስራውን ውጤት አላየም። ሆኖም ጌታ በጥንቃቄ እየመራው እንደነበር ተገንዝቦ ነበር። የኔፊን ትንሽ ሰሌዳዎች በመዝገቡ ውስጥ ለማካተት መነሳሳት በተሰማው ጊዜ ሞርሞን እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “እናም ይህን ለብልህ ዓላማ አደርገዋለሁ፤ በእኔ ውስጥ ያለው የጌታ መንፈስ በዝግታ ድምፅ ተናግሮኛልና። እናም አሁን፣ ሁሉንም ነገሮች አላውቅም፤ ነገር ግን ጌታ የሚመጡትን ነገሮች ሁሉ ያውቃል፤ ስለሆነም፣ እንደፈቃዱ ለማድረግ በእኔ ይሰራል።”5 ምንም እንኳን ሞርሞን 116 የእጅ ጽሁፍ ገጾች ወደፊት እንደሚጠፉ የማያውቅ የነበረ ቢሆንም ጌታ ያውቅ ነበር እናም ችግሩ ከመከሰቱ ከረዥም ጊዜ በፊት ያንን እንቅፋት የማስወገጃ መንገድ አዘጋጀ።

አብ ያውቀናል፣ ፍላጎቶቻችንን ያውቃል እንዲሁም በደምብ ይረዳናል። አንዳንድ ጊዜ ያ እርዳታ በዚያው ቅጽበት ወይም ቢያንስ መለኮታዊ እርዳታ ከጠየቅን በኋላ ወዲያው ይሰጣል። አንዳንድ ጊዜ አጅግ ልባዊ እና ተገቢ የሆኑ ፍላጎቶቻችን እኛ ተስፋ ባደረግንበት መንገድ አይመለሱም፤ ነገር ግን እግዚአብሔር የተሻሉ በረከቶች እንዳሉት እንደርስበታለን። እንዲሁም አንዳንድ ጊዜ የጽድቅ ፍላጎቶቻችን በዚህ ህይወት አይሰጡንም። የሰማይ አባታችን ለእርሱ የምናቀርባቸውን ልባዊ ልመናዎች ሊመልስ የሚችልባቸውን መንገዶች በሶስት የተለያዩ ዘገባዎች አማካኝነት በምሳሌ አስረዳለሁ።

ትንሹ ወንድ ልጃችን በፈረንሳይ ፓሪስ ሚስዮን በሚስዮናዊነት እንዲያገለግል ተጠርቶ ነበር። ለአገልግሎት በነበረው ዝግጅት የተለመዱትን ሸሚዞች፣ ሱፎች፣ ከረባቶች እና ካልሲዎች እንዲሁም ካፖርት ለመግዛት ከእርሱ ጋር ሄድን። እንዳለመታደል ሆኖ እርሱ የፈለገው ካፖርት በእርሱ ልክ ወዲያውኑ ለመውሰድ በመጋዘኑ ውስጥ አልነበረም። ነገር ግን የመጋዘኑ ጸሃፊ ካፖርቱ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ እንደሚመጣ እና ልጃችን ወደፈረንሳይ ከመብረሩ አስቀድሞ ፐሮቮ ወደሚገኘው የሚስዮናዊ ማሰልጠኛ ማዕከል እንደሚላክ አመለከተ። የካፖርቱን ዋጋ ከፈልን ከዚያም ስለሱ ምንም ጨማሪ ነገር አላሰብንም።

ልጃችን በሰኔ ወር ወደሚስዮናዊ ማሰልጠኛ ማዕከሉ ገባ ካፖርቱም ከመሄጃው ቀን ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ በነሃሴ ወር ውስጥ መጣለት። ካፖርቱን ለብሶ አልሞከረውም ነበር፤ ነገር ግን ከልብሶቹ እና ከሌሎች እቃዎች ጋር በችኮላ ወደሻንጣው ከተተው።

ልጃችን በሚያገለግልበት ፓሪስ ክረምት ሲገባ ካፖርቱን እንዳወጣው እና እንደሞከረው ሆኖም በጣም እንዳጠረው ጻፈልን። ከፓሪስ ሌላ ካፖርት መግዛት ይችል ዘንድ ወደባንክ አካውንቱ ተጨማሪ ገንዘብ ማስገባት ነበረብን፣ እርሱም ገዛው። ትንሽ በስጨት ብዬ ሊጠቀመው ስለማይችል የመጀመሪያውን ካፖርት ለሰው እንዲሰጥ ጽፌ ነገርኩት።

በኋላም ከእርሱ ይህንን ኢሜይል ተቀበልን፦ “እዚህ በጣም በጣም ይበርዳል። … ምንም እንኳን አዲሱ ካፖርቴ ትልቅ እና ወፍራም ቢሆንም ነፋሱ በውስጣችን ሰርጎ የሚያልፍ ይመስላል። … የቀድሞውን ካፖርቴን የተሻለ ካፖርት ማግኘት ስለሚችልበት መንገድ ሲጸልይ እንደነበረ ለነገረን [በእኛ አፓርትመንት ለነበረ ሌላ ሚስዮናዊ] ሰጠሁት። ከብዙ አመታት በፊት የተለወጠ አባል የነበረ ሲሆን በሚስዮኑ እያለ የሚረዱትም እናቱ … እና ያጠመቀው ሚስዮናዊ ብቻ ነበሩ፤ እናም ካፖርቱ የጸሎት መልስ ነበር። ስለዚያ ጥልቅ ደስታ ተሰማኝ።”6

የሰማይ አባት ከቤቱ 6 ሺህ 200 ማይልስ (10 ሺህ ኪ.ሜ) ርቆ በፈረንሳይ እያገለገለ የነበረው ይህ ሚስዮናዊ ለፓሪስ ቀዝቃዛ ክረምት በአፋጣኝ አዲስ ካፖርት እንደሚያስፈልገው ነገር ግን ሊገዛ የሚችልበት ገንዘብ እንዳልነበረው ያውቅ ነበር። በተጨማሪም የሰማይ አባት ልጃችን ፕሮቮ ዩታ ከሚገኘው የልብስ መጋዘን በጣም የሚያንሰውን ካፖርት እንደሚቀበል ያውቅ ነበር። እነዚህ ሁለት ሚስዮናውያን በፓሪስ አብረው እንደሚያገለግሉ እና ካፖርቱ አስቸኳይ ፍላጎት የነበረው የሚስዮናዊ ትሁት እና ልባዊ ጸሎት መልስ እንደሚሆን ያውቅ ነበር።

አዳኙ እንዲህ አስተማረ፦

“ሁለት ድንቢጦች በአምስት ሳንቲም ይሸጡ የለምን? ከእነርሱም አንዲቱ ያለአባታችሁ ፈቃድ በምድር ላይ አትወድቅም።

“የናንተስ የራሳችሁ ጠጉር ሁሉ እንኳ ተቆጥሮአል።

“እንግዲህ አትፍሩ ከብዙ ድንቢጦች እናንተ ትበልጣላችሁ።”7

በሌሎች ሁኔታዎች፣ ተገቢ የሆኑ ፍላጎቶቻችን እኛ ተስፋ ባደረግንበት መንገድ ሳይመለሱ ሲቀሩ በርግጥ ለእኛ ከፍተኛ ጥቅም ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ የያዕቆብ ልጅ ዮሴፍ ሊገድሉት እስኪያሴሩ ድረስ ወንድሞቹ ቀንተውበት እና በእነርሱም ተጠልቶ ነበር። ከዚያ ይልቅ ለግብጽ በባርነት አሳልፈው ሸጡት።8 እርሱ ተስፋ ባደረገበት መንገድ ጸሎቶቹ እንዳልተመለሱ የተሰማው ሰው ቢኖር ዮሴፍ ሊሆን ይችላል። እንደ እውነቱ ከሆነ፣ መጥፎ ዕድሉ ለእርሱ ታላቅ በረከቶችን አስገኝቷል እንዲሁም ቤተሰቡን ከረሃብ አድኗል። በግብጽ የታመነ መሪ ከሆነ በኋላ በታላቅ እምነት እና ጥበብ ለወንድሞቹ እንዲህ አላቸው፦

“አሁንም ወደዚህ ስለሸጣችሁኝ አትዘኑ፦አትቆርቆሩም፥ እግዚአብሔር ህይወትን ለማዳን ከእናንተ በፊት ሰዶኛልና።

“ይህ ሁለቱ ዓመት በምድር ላይ ራብ የሆነበት ነውና፥ የማይታረስበትና የማይታጨድበት አምስት አመት ገና ቀረ።

“እግዚአብሔርም በምድር ላይ ቅሬታን አስቀርላችሁ ዘንድ በታላቅ መድሃኒትም አድናችሁ ዘንድ ከእናንተ በፊት ላከኝ።

“አሁንም እናንተ ወደዚህ የላካችሁኝ አይደላችሁም፥ እግዚአብሔር ላከኝ እንጂ።”9

ኮሌጅ እያለ ትልቁ ልጃችን ከምረቃ በኋላ ወደ አስደናቂ ቋሚ ሥራ የመምራት አቅም በነበረው በጣም ተፈላጊ በሆነ የትርፍ ሰዓት የተማሪ ስራ ተቀጥሮ ነበር። በዚህ የተማሪ ስራ ለአራት አመታት በርትቶ ሰራ፣ ከፍተኛ ብቃትን አዳበረ እንዲሁም በስራ ባልደረቦቹ እና በአለቃዎቹ በጣም የተከበረ ነበር። በመጨረሻው ዓመት ማገባደጃ ላይ፣ በእግዚአብሔር የታቀደ በሚመስል መልኩ (ቢያንስ ከልጃችን እይታ አንጻር) ቋሚው የስራ መደብ ተከፈተ እናም እርሱ ዋነኛ እጩ ነበር፣ በእያንዳንዱ አመላካች እና ተስፋ በእርግጥ እርሱ ሥራውን ያገኛል።

ሆኖም፣ እርሱ አልተቀጠረም። ማንኛችንም ልንገነዘበው አልቻልንም። በደንብ ተዘጋጅቶ ነበር፣ ቃለ መጠይቁን በደምብ አድርጎ ነበር፣ የላቀ ብቃት ያለው እጩ ነበር፣ እንዲሁም በታላቅ ተስፋ እና ጉጉት ጸልዮ ነበር! እሱ በጣም ተበሳጭቶ እና ተስፋ ቆርጦ ነበር እናም አጠቃላዩን ነገር ሁላችንም አልተረዳነውም ነበር። እግዚአብሔር የጽድቅ ፍላጎቶቹን የከለከለው ለምንድን ነበር?

ብዙ ዓመታት ካለፉ በኋላ ነበር መልሱ በጣም ግልፅ የሆነው። ከተመረቀ በኋላ ሲያልመው የነበረውን ሥራ አግኝቶ ቢሆን ኖሮ አሁን ለዘለአለማዊ ጥቅሙ እና በረከቱ የተረጋገጠ ወሳኝ፣ ሕይወት ቀያሪ የሆነውን ዕድል ባጣ ነበር። እግዚአብሔር ፍጻሜውን ከጅምሩ ያውቃል (እንደሁልጊዜው ሁሉ) እንዲሁም በእንደዚህ ያለ ሁኔታ ውስጥ እጅግ የላቀ ውጤት ይገኝ ዘንድ የብዙ የጽድቅ ጸሎቶች መልስ አሉታዊ ነበር።

እንዲሁም አንዳንድ ጊዜ በጽድቅ፣ አጥብቀን፣ እና ተግተን የምንሻው የጸሎት መልስ በዚህኛው ሕይወት አይመለስም።

እህት ፓትሪሺያ ፓርኪንሰን የተወለደችው ከጤነኛ የማየት ችሎታ ጋር ነበር ነገር ግን ሰባት አመት ሲሆናት የማየት ችሎታዋን እያጣች ሄደች። ዘጠኝ አመት ሲሆናት እዚያው መኖርን አስፈላጊ ባደረገው ከቤቷ ወደ 90 ማይልስ (145 ኪሜ) በሚርቀው ኦግደን ዩታ በሚገኘው መስማት የተሳናቸው እና የዓይነ ስውራን ትምህርት ቤት መከታተል ጀመረች—ይህም የዘጠኝ ዓመት ልጅ ሊሰማት የሚችለውን ናፍቆት ሁሉ ይጨምር ነበር።

በ11 ዓመቷ የማየት ችሎታዋን ሙሉ በሙሉ አጥታ ነበር። ፓት በ15 ዓመቷ በአካባቢዋ በሚገኝ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለመማር በቋሚነት ወደ አገሯ ተመለሰች። ኮሌጅ ገብታ በኮሚኒኬሽን ዲስኦርደር እና በሳይኮሎጂ የመጀመሪያ ዲግሪዋን አገኘች እንዲሁም በዩኒቨርሲቲ ቅበላ ክፍል ያሉ ሃላፊዎች ከነበራቸው ጥርጣሬ ጋር በጀግንነት ትግል ካደረገች በኋላ የድህረ-ምረቃ ትምህርት ቤት ገብታ በንግግር ቋንቋ ፓቶሎጂ የማስተርስ ዲግሪ አግኝታለች። አሁን ፓት ከ53 የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ጋር ትሠራለች እንዲሁም በት/ቤቷ ዲስትሪክት ውስጥ ያሉ አራት የንግግር ቋንቋ ቴክኒሻኖችን ትቆጣጠራለች። የራስዋ ቤት እና ፓት የመጓጓዣ አገልግሎት ሲያስፈልጋት ጓደኞቿ እና ቤተሰቧ የሚነዱላት የግል መኪና አላት።

ምስል
እህት ፓትሪሺያ ፓርኪንሰን

10 ዓመት ሲሆናት ፓት እየቀነሰ የመጣውን ዕይታዋን ለማከም ሌላ ሕክምና እንድታደርግ ቀጠሮ ተይዞላት ነበር። ወላጆቿ ሁልጊዜ የአንድን የህክምና ሂደት በተመለከተ ምን ሊደረግ እንደሆነ በትክክል ይነግሯት ነበር፤ ሆኖም በሆነ ምክንያት በተለይ ስለዚህ ህክምና ሂደት አልነገሯትም። ለህክምናው ቀጠሮ ተይዞላት እንደነበር በነገሯት ጊዜ በእናቷ ቃላት ፓት “ተረብሻ ነበር።“ ፓት ወደሌላኛው ክፍል ሮጠች በኋላም ተመልሳ መጣችና ትንሽ ቁጣ ባዘለ ድምጽ ወላጆቸቿን እንዲህ አለቻቸው፣ “ምን እንደሆነ እኔ ልንገራችሁ። እኔ አውቀዋለሁ፣ እግዚአብሔር ያውቀዋል እናንተም ልታውቁት ትችሉ ይሆናል። ቀሪውን ህይወቴን አይነ ስውር ልሆን ነው!”

ከብዙ አመታት በፊት ፓት በዚያ ይኖሩ የነበሩ የቤተሰብ አባላትን ለመጠየቅ ወደ ካሊፎርኒያ ተጉዛ ነበር። የሶስት አመት ዕድሜ ካለው የወንድሟ ልጅ ጋር በደጅ ሳሉ አንዲህ አላት፣ “አክስቴ ፓት፣ የሰማይ አባት አዳዲስ አይኖች እንዲሰጥሽ ለምን አትጠይቂውም? ምክንያቱም የሰማይ አባትን ብትጠይቂው የፈለግሺውን ይሰጥሻል። እርሱን መጠየቅ አለብሽ።”

ፓት በጥያቄው እንደተደነቀች ተናገረች ነገር ግን እንዲህ መለሰች፣ “ደህና፣ አንዳንድ ጊዜ የሰማይ አባት በዚያ መንገድ አይሰራም። አንዳንድ ጊዜ አንድ ነገር እንድትማር ይፈልጋል እናም በዚህ ምክንያት የፈለከውን ሁሉ አይሰጥህም። አንዳንድ ጊዜ መጠበቅ ይኖርብሃል። የሰማይ አባት እና አዳኙ ለእኛ ጥሩ የሆነውን እና የሚያስፈልገንን የበለጠ ያውቃሉ። ስለዚህ የፈለከውን ነገር ሁሉ በፈለግክበት ቅጽበት አይሰጡህም።”

ፓትን ለብዙ አመታት አውቃታለሁ እናም በቅርቡ ሁልጊዜ ቀና እና ደስተኛ የመሆኗን እውነታ እንደማደንቅ ነገርኳት። አንዲህ መለሰች “ደህና ከእኔ ጋር በቤት አልነበርክም አይደል፣ ነበርክ እንዴ? ጥሩ ጊዚያት አሳልፊያለሁ። በጣም ከባድ የመንፈስ ጭንቀት ነበረብኝ እናም ብዙ አልቅሻለሁ።” ሆኖም እንዲህ ስትል አከለች፣ “እይታዬን ማጣት ከጀመርኩበት ጊዜ ጀምሮ እንግዳ ነገር ነበር፣ ነገር ግን የሰማይ አባት እና አዳኙ ከቤተሰቤ እና ከእኔ ጋር መሆናቸውን አውቂያለሁ። በምንችለው ከሁሉም በተሻለው መንገድ ይዘነዋል እናም እንደ እኔ አስተያየት በትክክል ይዘነዋል። በራሴ በቂ ስኬታማ ሰው ሆኛለሁ እናም በአጠቃላይ ደስተኛ ሰው ነኝ። በሁሉም ነገር ውስጥ ተጽዕኖ ያደርግ እንደነበረ አስታውሳለሁ። አይነ ስውር በመሆኔ እናደድ እንደሆነ ለሚጠይቁኝ እንዲህ እመልሳለሁ፣ ‘በማን ነው የምናደደው? የሰማይ አባት በዚህ ነገር ከእኔ ጋር ነው፤ ብቻዬን አይደለሁም። በሁሉም ጊዜ ከእኔ ጋር ነው።’”

በዚህ ሁኔታ፣ የፓት እይታዋን የማግኘት ፍላጎት በዚህኛው ህይወት አይመለስም። ነገር ግን ከአባቷ የተማረችው መፈክር “ይህም ያልፋል” የሚል ነው።10

ፕሬዚዳንት ሄንሪ ቢ. አይሪንግ “አብ በአሁኑ ሰአት ስለናንተ፣ ስለስሜታችሁ እንዲሁም በዙሪያችሁ ስላሉት ሰዎች መንፈሳዊ እና ስጋዊ ፍላጎቶች ያውቃል” ሲሉ ተናግረዋል።11 ይህ ታላቅ እና አጽናኝ እውነት እኔ በገለጽኳቸው በሶስቱ ተሞክሮዎች ውስጥ ሊገኝ ይችላል።

ወንድሞች እና እህቶች አንዳንድ ጊዜ ጸሎቶቻችን ተስፋ ባደረግነው ውጤት መሰረት በፍጥነት ይመለሳሉ። አንዳንድ ጊዜ አጅግ ልባዊ እና ተገቢ የሆኑ ፍላጎቶቻችን እኛ ተስፋ ባደረግነው መንገድ አይመለሱም፣ ሆኖም በጊዜ ሂደት እግዚአብሔር እኛ መጀመሪያ ካሰብናቸው የተሻሉ በረከቶች እንደነበረው እንማራለን። እንዲሁም አንዳንድ ጊዜ ለእግዚአብሔር የምናቀርባቸው የጽድቅ ልመናዎቻችን በዚህ ህይወት አይሰጡንም።12 ሽማግሌ ኒየል ማክስዌል እንዳሉት፣ “እምነት እንዲሁም በእግዚአብሔር ጊዜ ማመንን ያካትታል።”13

በራሱ መንገድ እና በራሱ ጊዜ የሰማይ አባት አንደሚባርከን እንዲሁም ሁሉንም ስጋቶቻችንን፣ ፍትህ ማጣታችንን እና ብስጭቶቻችንን እንደሚፈታ ማረጋገጫ አለን።

ንጉስ ቢንያምን ለመጥቀስ፦ “እናም በተጨማሪ፣ የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት የሚጠብቁትን የተባረከና አስደሳቹን ሁኔታ እንድትገነዘቡ እፈልጋለሁ። እነሆም እነርሱ በሁሉም ነገሮች፣ ለጊዜያዊም ሆነ ለመንፈሳዊ፣ የተባረኩ ናቸውና፤ እናም እስከ መጨረሻው በታማኝነት ከዘለቁ፣ ለዘለአለም በማያልቀው ደስታ ከእግዚአብሔር ጋር ይኖሩ ዘንድ፣ መንግስተ ሰማይ ትቀበላቸዋለች። አቤቱ አስታውሱ፤ እነዚህ ነገሮች እውነት መሆናቸውን አስታውሱ፣ ምክንያቱም ጌታ እግዚአብሔር ተናግሮታልና።”14

እግዚአብሔር ጸሎቶቻችንን እንደሚሰማ አውቃለሁ።15 ሁሉን እንደሚያውቅ አፍቃሪ አባት ጸሎቶቻችንን በደምብ፣ ማለቂያ በሌለው ጥበቡ እና ለእኛ ከፍተኛ ጥቅም እና በረከት በሚሆኑ መንገዶች እንደሚመልስ አውቃለሁ። ስለዚህ የምመሰክረው በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ነው፣ አሜን።