ቅዱሳት መጻህፍት
ሞርሞን ፮


ምዕራፍ ፮

ኔፋውያን ለመጨረሻው ውጊያ በከሞራ ምድር ተሰባሰቡ—ሞርሞን በከሞራ ኮረብታ ቅዱስ የሆኑትን መዛግብት ደበቃቸው—ላማናውያን ድል አደረጉ፣ እናም የኔፋውያንም ሀገር ጠፋች—በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ በጎራዴ ተገደሉ። በ፫፻፹፭ ዓ.ም. ገደማ።

እናም እንግዲህ የህዝቦቼ የኔፋውያንን ጥፋት በተመለከተ ታሪኬን እጨርሳለሁ። እናም እንዲህ ሆነ ከላማናውያን ፊት ዘመትን።

እናም እኔ ሞርሞን፣ ለላማናዊው ንጉስ ደብዳቤ ፃፍኩና፣ ከሞራ ተብሎ በሚጠራው ኮረብታ አካባቢ በከሞራ ምድር ህዝባችንን እንድንሰበስብ እንዲፈቀድልንና ከእነርሱ ጋር ለመዋጋት እንድንችል መፈለጌን ጠየቅሁ።

እናም እንዲህ ሆነ የላማናውያን ንጉስ እንደፈለግሁትም ፈቀደልኝ።

እናም እንዲህ ሆነ ወደ ከሞራ ምድር ሄድንና፣ በከሞራ ኮረብታ ዙሪያ ድንኳናችንን ተከልን፤ እናም ምድሪቱም ብዙ ውሀዎች፣ ወንዞችና፣ ምንጮች ነበሩባት፤ እናም እዚህ በላማናውያን ላይ ብልጫ እንደምንይዝ ተስፋ አደረግን።

እናም ሦስት መቶ ሰማንያ አራት ዓመታት በአለፈ ጊዜ፣ የተቀሩትን ህዝቦቻችንን በከሞራ ምድር ሰበሰብን።

እናም እንዲህ ሆነ ህዝባችንን በሙሉ በአንድነት በከሞራ ምድር በሰበሰብን ጊዜ፣ እነሆ እኔ ሞርሞን፣ ማርጀት ጀመርኩ፤ የሕዝቤም የመጨረሻው ትግል መሆኑን በማወቄና፣ በአባቶቻችን የተረከብነውን ቅዱስ የሆነ መዝገብ በላማናውያን እጅ እንዳይገባ በጌታ በመታዘዜ (ምክንያቱም ላማናውያን ያጠፏቸዋልና) ስለዚህ ይህን መዝገብ ከኔፊ ሰሌዳ ላይ ፃፍኩት፣ እናም ለልጄ ለሞሮኒ ከሰጠኋቸው ከእነዚህ ትንንሾች ሠሌዳዎች በቀር በጌታ የተሰጠኝን መዛግብት በሙሉ በከሞራ ኮረብታ ውስጥ ደበቅኋቸው

እናም እንግዲህ ህዝቦቼ ከነሚስቶቻቸውና፣ ከነልጆቻቸው፣ አሁን የላማናውያን ወታደሮች ወደ እነርሱ ሲዘምቱ ተመለከቱ፤ እናም የክፉዎችን ሁሉ ደረት በሚሞላው አሰቃቂ ሞት ፍርሀት እነርሱን ለመቀበል ይጠባበቁ ነበር።

እናም እንዲህ ሆነ እነርሱ እኛን ለመውጋት መጡና፣ በቁጥር ብዙ ስለነበሩ እያንዳንዷ ነፍስ በፍርሃት ተሞልታ ነበር።

እናም እንዲህ ሆነ ህዝቤንም በጎራዴና፣ በደጋን፣ እናም በቀስትና፣ በምሳር፣ እንዲሁም በሁሉም ዓይነት የጦር መሳሪያዎች አጠቁአቸው።

እናም እንዲህ ሆነ ሰዎቻችን ተገደሉ፤ አዎን፣ ከእኔ ጋር የነበሩት አስር ሺዎች ሳይቀሩ ተገደሉ፤ እኔ ቆስዬ በመካከላቸው ወደቅሁ፤ እናም በአጠገቤ አለፉና፣ አልገደሉኝም።

፲፩ እናም በመካከላችን ሄዱና ከሃያ አራታችን በስተቀር (ከመካከላቸውም ልጄ ሞሮኒ ነበር) ሁሉንም ህዝቦቼን ገደሉና እኛ ከሞቱት ህዝቦቻችን በመትረፋችን፣ ላማናውያን ወደ ጦር ሰፍራቸው ሲመለሱ፣ በነጋታው ከከሞራ ኮረብታ ጫፍ ላይ እኔ በፊታቸው ሆኜ እመራቸው የነበሩትን የተገደሉትን አስር ሺህ ህዝቦቼን ተመለከትን።

፲፪ እናም ደግሞ በልጄ ሞሮኒ ይመሩ የነበሩ አስር ሺህ የሚሆኑ ህዝቦቼን ተመለከትናቸው።

፲፫ እናም እነሆ አስር ሺህ የሚሆኑ የጊድጊዶና ሰዎች ወድቀዋል፣ እናም እርሱም ደግሞ በመካከላቸው ነበር።

፲፬ እናም ላማም ከአስር ሺዎቹ ጋር ወድቋል፤ ጊልጋልም ከአስር ሺዎቹ ጋር ወድቋል፤ እናም ሊምሀም ከአስር ሺዎቹ ጋር ወድቋል፤ ዬኔዩም ከአስር ሺዎች ጋር ወድቋል፤ እናም ቁሜኒሀምና፣ ሞሮኒሃም፣ አንቲዩነምና፣ ሺብሎም፣ እናም ሼምና፣ ጆሹ፣ እያንዳንዳቸው ከአስር ሺዎቻቸው ጋር ወደቁ።

፲፭ እናም እንዲህ ሆነ ከእያንዳንዳቸው አስር ሺዎች ጋር በጎራዴ የተገደሉ አስር መሪዎች ነበሩ፤ አዎን፣ ከእኔ ጋር ከነበሩት ከሃያ አራቱ፣ እናም ደግሞ በሃገሪቱ በስተደቡብ ካመለጡት ጥቂቶችና፣ ወደ ላማናውያንን ከከዱት ጥቂቶች በስተቀር፣ ሁሉም ህዝቦቼ ወድቀዋል፤ እናም ሥጋቸውና፣ አጥንታቸው፣ እንዲሁም ደማቸው በምድረ ገፅ ላይ ሆኖ፣ በምድሪቱ ላይ እንዲበሰብሱና፣ እንዲበላሹ እናም ወደ እናት ምድርም እንዲመለሱ በገዳዮቻቸው እጅ ተተዉ።

፲፮ እናም ነፍሴ ሕዝቤ በመገደሉ በጭንቀት ተከፈለች፣ እናም እንዲህ ስል ጮኽኩ፥

፲፯ እናንተ መልከ መልካሞች ሆይ፣ ከጌታ መንገድ እንዴት ልትለዩ ቻላችሁ! እናንተ መልከ መልካሞች ሆይ፣ እናንተን ለመቀበል ክንዶቹን ዘርግቶ የቆመውን ኢየሱስን እንዴት ልትቃወሙት ቻላችሁ!

፲፰ እነሆ፣ ይህንን ባታደርጉ ኖሮ፣ አትወድቁም ነበር። ነገር ግን እነሆ፣ ወድቃችኋል እናም ስለሞታችሁ እተክዛለሁ።

፲፱ እናንተ መልከ መልካም ወንዶችና ሴት ልጆች ሆይ፤ አባቶችና እናቶች ሆይ፣ እናም ባሎችና ሚስቶች ሆይ፤ እናንተ መልከ መልካም የሆናችሁ፣ እንዴት ልትወድቁ ቻላችሁ!

ነገር ግን እነሆ፣ እናንተ ጠፍታችኋል፣ እናም የእኔ ሀዘን እናንተን ሊመልሳችሁ አይችልም።

፳፩ እናም ሟች የሆነው ሰውነታችሁ በቅርቡ ህያው የሚሆንበት ቀን ይመጣል፤ እናም ይህ ሰውነት ዛሬ የሚበሰብስ የሆነው በቅርቡ የማይበሰብስ ሰውነት በመሆን ይለወጣል፤ እናም በስራችሁ መሰረት ሊፈረድባችሁ በክርስቶስ የፍርድ ወንበር ፊት መቆም ይኖርባችኋል፤ እናም እናንተ ፃድቅ ብትሆኑ፣ ከዚያም ከእናንተ በፊት ካለፉት አባቶቻችሁም ጋር የተባረካችሁ ትሆናላችሁ።

፳፪ አቤቱ ከዚህ ታላቅ ጥፋት በፊት ንሰሃ በገባችሁ ኖሮ። ነገር ግን እነሆ፣ እናንተ አልፋችኋል፣ እናም አብ፣ አዎን ዘለአለማዊው የሰማይ አባት የእናንተን ሁኔታ ያውቃል፤ እናም እርሱም እንደ ፍርዱና ምህረቱ ያደርግላችኋል።