ምዕራፍ ፱
መልዕክተኞች ዋናው ዳኛ በፍርድ ወንበሩ ላይ ሞቶ አገኙት—እነርሱም ታሰሩ፣ በኋላም ተለቀቁ—በመንፈስ በመነሳሳት ኔፊ ሴአንቱም ገዳይ መሆኑን አሳወቀ—ኔፊ በጥቂቶች ነቢይ ተብሎ ተቀባይነትን አገኘ። ከ፳፫–፳፩ ም.ዓ. ገደማ።
፩ እነሆ እንዲህ ሆነ ኔፊ እነዚህን ቃላት በተናገረ ጊዜ ከእነርሱ ጋር የነበሩ አንዳንድ ሰዎች ወደ ፍርድ ወንበሩ ሮጡ፤ አዎን አምስት ነበሩ፤ እናም በተጓዙ ጊዜ በመካከላቸው እንዲህ ሲሉ ተናገሩ፥
፪ እነሆ፣ አሁን ይህ ሰው በእርግጥ ነቢይ መሆኑን፣ እናም እንደዚህ ያሉ ድንቅ ነገሮችን እንዲተነብይ እግዚአብሔር እንዳዘዘው በእርግጥ እናውቃለን። እነሆ፣ እርሱ አዞታል ብለን አናምንም፤ አዎን፣ ነቢይ ነው ብለንም አናምንም፤ ይሁን እንጂ፣ ስለዋናው ዳኛ ይሞታል በማለት የተናገረው ይህ ነገር እውነት ከሆነ ሌሎች የሚናገራቸው ቃላት እውነት ናቸው ብለን እናምናለን።
፫ እናም እንዲህ ሆነ በኃይል ሮጡና፣ ወደ ፍርድ ወንበሩ መጡ፤ እናም እነሆ፣ ዋናው ዳኛ በመሬት ላይ ወድቋልና ከነደሙም ተኝቷል።
፬ እናም አሁን እነሆ፣ ይህንን በተመለከቱ ጊዜ እጅግ ተገርመው ነበር፤ ስለዚህ በመሬት ላይ ወደቁ፤ ምክንያቱም ኔፊ ስለዋናው ዳኛ የተናገራቸውን ቃላት አላመኑም ነበር።
፭ ነገር ግን አሁን፣ በተመለከቱ ጊዜ አመኑ፣ እናም ኔፊ የተናገረው ቅጣት ሁሉ በህዝቡ ላይ ይመጣል የሚል ፍርሃት በእነርሱ ላይ ሆነ፤ ስለዚህ ተንቀጠቀጡ፣ እናም በመሬት ላይ ወደቁ።
፮ እንግዲህ፣ ዳኛው በተገደለበት ጊዜ ወዲያው—ምስጢራዊ ልብስ በለበሰው ወንድሙ ተወግቶ፣ እናም እርሱም ሸሸና፣ አገልጋዮቹ ሮጡ፣ እናም ለህዝቡ በመካከላቸው ግድያ እንደነበረ ድምፃቸውን ከፍ በማድረግ ተናገሩ፤
፯ እናም እነሆ ህዝቡ በአንድነት በፍርድ ወንበሩ ስፍራ ራሳቸውን ሰበሰቡ—እናም እነሆ በመገረም በመሬት ላይ የወደቁትን አምስት ሰዎች ተመለከቱ።
፰ እናም እንግዲህ እነሆ፣ በኔፊ የአትክልት ስፍራ በአንድነት ስለተሰበሰቡት ሰዎች ህዝቡ ምንም አያውቅም ነበር፤ ስለዚህ እርስ በርሳቸውም እንዲህ ተባባሉ፥ እነዚህ ሰዎች ዳኛውን የገደሉት ናቸው፣ እናም ከእኛ እንዳይሸሹ እግዚአብሔር መቷቸዋል።
፱ እናም እንዲህ ሆነ ያዙአቸውና፣ አሰሩአቸው፣ ወደ ወህኒ ቤትም ጣሉአቸው። እናም ዳኛው ስለመገደሉና፣ ገዳዩ ተወሰደና ወደ ወህኒ ቤት እንደተጣሉ ዜናው በሁሉም ስፍራ ተሰራጨ።
፲ እናም እንዲህ ሆነ በሚቀጥለው ቀን በተገደለው በዋናው ዳኛ ቀብር ላይ ለማዘን፣ እናም ለመፆም ህዝቡ በአንድ ላይ እራሱን ሰበሰበ።
፲፩ እናም እነዚህ በኔፊ የአትክልት ስፍራ የነበሩት፣ እናም ቃሉን የሰሙት ዳኞች ደግሞም በቀብሩ ላይ በአንድነት ተሰብስበው ነበር።
፲፪ እናም እንዲህ ሆነ በህዝቡ መካከል እንዲህ በማለት ጠየቁ፥ ዋናው ዳኛ መሞቱን በተመለከተ ለመጠየቅ የተላኩት አምስቱ የት አሉ? እናም መለሱና እንዲህ አሉ፥ ልከናችኋል ስላላችኋቸው ስለእነዚህ አምስቱ ምንም አናውቅም፤ ነገር ግን ገዳዮች የሆኑ ወደ ወህኒ ቤት የጣልናቸው አምስት አሉ።
፲፫ እናም እንዲህ ሆነ ዳኞቹ እነዚህ ወደእነርሱ እንዲመጡ ፈለጉ፤ እናም አመጡዋቸውና፣ እነርሱም የተላኩት አምስቱ እንደነበሩ ተመለክቱ፤ እናም እነሆ ጉዳዩን በተመለከተ ለማወቅ ዳኞቹ ጠየቁአቸውና፣ ያደረጉትን በሙሉ እንዲህ በማለት ነገሩአቸው፥
፲፬ ሮጥን፣ እናም ወደ ፍርድ ወንበሩ መጣንና፣ ኔፊ እንደመሰከራቸው ሁሉንም ነገሮች ስንመለከት፣ መሬት እስከምንወድቅም ድረስ ተገረምን፤ እናም ከመገረማችን በተመለስን ጊዜ፣ እነሆ ወደ ወህኒ ቤት ጣሉን።
፲፭ እንግዲህ፣ የዚህን ሰውዬ ግድያ በተመለከተ ማን እንዳደረገው አናውቅም፤ እናም እስከዚህ ብቻ ነው የምናውቀው፤ ሮጥንና እንደ ፍላጎታችሁ መጣን፣ እናም እንደ ኔፊ ቃላት መሞቱን ተመለከትን።
፲፮ እናም አሁን እንዲህ ሆነ ዳኞቹ ጉዳዩን ለህዝቡ ገለፁና፣ በኔፊም ላይ እንዲህ ሲሉ ጮኹ፥ እነሆ ይህ ኔፊ ዳኛውን ለመግደል ከአንድ ሰው ጋር ተስማምቶ ይሆናል፣ ከዚያም እኛን ወደ እርሱ እምነት ለመለወጥ እራሱን ታላቅ ሰው ለማድረግ፣ በእግዚአብሔር የተመረጠና ነቢይ ያደርግ ዘንድ ይህን ለእኛ ይናገራል።
፲፯ እናም እንግዲህ እነሆ፣ ይህንን ሰው እናገኘዋለን፣ ስህተቱንም ይናዘዛል፣ እናም የዚህን ዳኛ እውነተኛ ገዳይ እንድናውቀው ያደርገናል።
፲፰ እናም እንዲህ ሆነ በቀብሩ ቀን አምስቱ ነፃ ወጡ። ይሁን እንጂ፣ በኔፊ ላይ በሚናገሩት ቃላት ዳኞቹን ገሰፁአቸው፣ እናም ዳኞቹም ዝም እንዲሉ እስከሚያደርጉአቸው ድረስ አንድ በአንድ ተከራክሯዋቸው።
፲፱ ይሁን እንጂ፣ ኔፊ እንዲወሰድና፣ እንዲታሰር፣ እናም በህዝቡ ፊት እንዲመጣ አደረጉትና፣ እርሱን በሞት እንዲቀጣ ለመክሰስ፣ እንዲቃረናቸው በተለያየ መንገድ ይጠይቁት ጀመር—
፳ እንዲህም አሉት፥ አንተ ከሌሎች ተባባሪ ነህ፤ ግድያውንስ የፈፀመው ይህ ሰው ማን ነው? አሁን ንገረንና ጥፋትህን ተቀበል፤ እንዲህም አሉት፤ እነሆ ገንዘብ ይኸውና፤ እናም ደግሞ የምትነግረንና፣ ከእርሱ ጋር የተስማማህበትን የምታሳውቀን ከሆነ ህይወትህን እናተርፍልሃለን።
፳፩ ነገር ግን ኔፊ እንዲህ አላቸው፥ እናንተ ሞኞች ሆይ በልባችሁም ያልተገረዛችሁ፤ እውሮች እናም አንገተ ደንዳና የሆናችሁ፣ ጌታ አምላካችሁ በዚህ በኃጢያት መንገዳችሁ እንድትሄዱ ለምን ያህል ጊዜ እንደሚፈቅድላችሁ ታውቃላችሁን?
፳፪ አቤቱ፣ ንስሃ ካልገባችሁ በዚህ ጊዜ በሚጠብቃችሁ ታላቅ ጥፋት የተነሳ በሰቆቃ መጮህ እንዲሁም ማዘን አለባችሁ።
፳፫ እነሆ ዋና ዳኛችን የሆነውን ሲኤዞራምን ከሚገድለው ሰውዬ ጋር ተስማምቻለሁ ብላችኋል። ነገር ግን እነሆ፣ እንዲህ እላችኋለሁ፥ ይህ የሆነበት መንስኤ ስለዚህ ነገር ታውቁ ዘንድ ስለመሰከርኩ ነው፤ አዎን፣ በመካከላችሁ ያለውን ክፋትና እርኩሰት የማወቄ ለምስክር እንዲሆንላችሁ ነው።
፳፬ እናም ይህንን በማድረጌ ይህንን ነገር እንዲፈጽም ከአንድ ሰው ጋር እንደተስማማሁ ተናገራችሁ፤ አዎን፣ ይህን ምልክት ስላሳየኋችሁ በእኔ ተቆጣችሁ፣ እናም ህይወቴን ለማጥፋት ፈለጋችሁ።
፳፭ እናም አሁን እነሆ ሌላ ምልክት አሳያችኋለሁ፣ እናም በዚህ ነገር እኔን ለማጥፋት እንደምትፈልጉም አያለሁ።
፳፮ እነሆ እንዲህ እላችኋለሁ፥ የሲኤዞራም ወንድም ወደሆነው ወደ ሴአንቱም ቤት ሂዱ፤ እናም እንዲህ በሉት—
፳፯ ስለዚህ ህዝብ ብዙ ክፉ የሚተነብየው አስመሳዩ ነቢይ፣ ኔፊ፣ ወንድምህን ሲኤዞራምን በመግደል ከአንተ ጋር ተስማምቷልን?
፳፰ እናም እነሆ እርሱ ግን አይደለም ይላችኋል።
፳፱ እናም እናንተ እንዲህ ትሉታላችሁ፥ ወንድምህን ገድለኸዋልን?
፴ እናም እርሱ በፍርሃት ይቆማል፣ ምን ማለት እንዳለበትም አያውቅም። እናም እነሆ ይክድላችኋል፤ የተገረመ ለመምሰልም ይሞክራል፤ ይሁን እንጂ በዚህ ነገር ተጠያቂ አለሆኑንም ለእናንተ ይናገራል።
፴፩ ነገር ግን እነሆ ትመረምሩታላችሁ፤ እናም በልብሱም ጫፍ ላይ ደም ታገኛላችሁ።
፴፪ እናም ይህን በተመለከታችሁ ጊዜ እንዲህ ትላላችሁ፥ ይህ ደም ከየት መጣ? የወንድምህ ደም መሆኑንስ አናውቅምን?
፴፫ እናም ከዚያን በኋላ ይንቀጠቀጣል፣ እናም ሞት በላዩ ላይ የመጣ ይመስል ይገረጣል።
፴፬ እናም እንዲህ ትሉታላችሁ፥ በፍርሃትህና ፊትህ በመገርጣቱ፣ እነሆ፣ ጥፋተኛ መሆንህን እናውቃለን።
፴፭ እናም ታላቅ ፍርሃት በላዩ ላይ ይመጣል፤ እናም ለእናንተ ይናዘዝላችኋል፣ ይህንን ግድያ መፈፀሙንም ከእንግዲህ አይክድም።
፴፮ እናም ከዚያ በኋላ በእግዚአብሔር ከተሰጠኝ ኃይል በስተቀር ስለጉዳዩ እኔ ኔፊ ምንም አላውቅም በማለት ይነግራችኋል። እና ከዚያም እኔ ታማኝ ሰው መሆኔንና፣ ከእግዚአብሔር ወደ እናንተ የተላኩ መሆኔን ታውቃላችሁ።
፴፯ እናም እንዲህ ሆነ ሄዱና፣ ኔፊ እንደተናገራቸው አደረጉ። እናም እነሆ እርሱ የተናገራቸው ቃላት እውነት ነበሩ፤ በቃላቱ መሰረትም ካደ፤ በቃላት መሰረትም ተናዘዘ።
፴፰ እናም እርሱም ራሱ በእውነት ገዳይ መሆኑ ተረጋገጠ፤ ስለዚህ አምስቱ እናም ደግሞም ኔፊ ተለቀቁ።
፴፱ እናም የኔፊን ቃላት ያመኑ ጥቂት ኔፋውያን ነበሩ፤ እናም ጥቂቶች አምስቱ በወህኒ ቤት በነበሩበት ወቅት በመለወጣቸው በእነርሱ ምስክርነት ያመኑ ነበሩ።
፵ እናም እንግዲህ ኔፊ ነቢይ ነበር ብለው የተናገሩ በህዝቡ መካከል ጥቂት ነበሩ።
፵፩ እናም ሌሎችም እንዲህ ሲሉ የተናገሩ ነበሩ፥ እነሆ እርሱ አምላክ ነው፤ አምላክ ባይሆን ኖሮ ሁሉንም ነገሮች ሊያውቃቸው አይቻለውም ነበር። እነሆም፣ የልባችንን ሀሳብ ነግሮናልና ደግሞ ነገሮችንም ነግሮናል፤ እናም የዋናው ዳኛችን እውነተኛ የሆነውንም ገዳይ እንኳን እንድናውቀው አድርጓል።