አጠቃላይ ጉባኤ
አሁንም ፍቃደኛ ናችሁን?
የጥቅምት 2022 (እ.አ.አ) አጠቃላይ ጉባኤ


አሁንም ፍቃደኛ ናችሁን?

ኢየሱስ ክርስቶስን በፍቃደኝነት መከተል ቅዱስ ቦታዎች ለመገኘት ከምንመድበው የጊዜ ርዝመት ጋር በቀጥታ ይዛመዳል።

አንድ እሁድ ከብዙ ሳምንታት የካስማ ሃላፊነቶች በኋላ የቅዱስ ቁርባንን ለመሳተፍ ስዘጋጅ፣ የሚገርም እና ኃይለኛ ሃሳብ ወደ አዕምሮዬ መጣ።

ካህኑ ዳቦውን መባረኩን ሲጀምር፣ ከዚህ በፊት ብዙ ጊዜ የሰማኋቸው ቃላት በኃይል ወደ አዕምሮዬ እና ልቤ መጡ። እና፣ አቤቱ ዘለዓለማዊ አባት እግዚአብሔር ሆይ፣ እነርሱ የልጅህን ስም በላያቸው ላይ ለመውሰድ ፈቃደኞች መሆናቸውን፣ እና ሁልጊዜ እርሱን እንደሚያስታውሱና እርሱ የሰጣቸውን ትእዛዛት እንደሚጠብቁ ለአንተም ይመሰክሩ ዘንድ፣ በዚህም የእርሱ መንፈስ ሁልጊዜ እንዲኖራቸው ትባርከውና ትቀድሰው ዘንድ በልጅህ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እንጠይቅሃለን።1 ፍቃደኞች እንደሆንን ምን ያህል ጊዜ ነው ለእግዚአብሔር የመሰከርነው?

የእነዛን ቅዱስ ቃላት ጥቅም ሳሰላስል፣ ፍቃደኛ የሚለው ቃል በተለየ ሁኔታ አስደነቀኝ። ለአዳኝ የሃጢያት ክፍያ መስዋዕት ፍቅር እና ምስጋና እንዲሁም አብ ለቤተሰቤ እና ለእኔ ባለው የደህንነት ዕቅድ ውስጥ ያለውን ወሳኝ ሚና ጣፋጭ እና ቅዱስ ልምዶች አዕምሮዬን እና ልቤን ሞሉት። ከዛ እንዲህ የሚለውን ዘልቆ የሚገባ የውኃ ጸሎት ቃላት ሰማሁ፦ “ለአንተ ይመሰክሩ ዘንድ … እርሱን ሁሌም ያስታውሱት ዘንድ።”2 በዛ ወቅት ቃልኪዳኖቼን መጠበቅ ከመልካም ሃሳቦች በላይ እንደሆነ በግልፅ ተረዳሁ።

ከቅዱስ ቁርባን መካፈል ፍቃደኝነታችን ብቻ የሚያሳይ የሐይማኖት ስርዓት አይደለም። የክርስቶስ ማለቂያ የሌለው የሃጢያት ክፍያው እውነታን እና ሁሌም እርሱን የማስታወስ እና ትዕዛዛቱን የመጠበቅ ፍላጎት ኃይለኛ ማስታወሻ ነው። አዳኙ ላይ የማተኮር ፍቃደኝነት አስፈላጊ ከመሆኑ የተነሳ በቤተክርስቲያን ውስጥ በጣም የሚጠቀሱት ሁለት ጥቅሶች ማለትም የቅዱስ ቁርባን ጸሎቶች ዋነኛ መልዕክት ነው። የሰማይ አባት በአንድያ ልጁ አማካኝነት ለእያንዳንዳችን በፍቃደኝነት የሰጠውን እውነታ መረዳት በምላሹም ፍቃደኛ ለመሆን ከፍተኛ ጥረቶቻችንን መቀስቀስ አለበት።

መንፈሳዊ መሰረታችን በጥንካሬ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ነው የተገነባው?

መንፈሳዊ መሰረታችን ጥልቅ ካልሆነ ወይም ሰው ሰራሽ ከሆነ፣ ፍቃደኝነታችንን በማህበረሰብ ዋጋ ጥቅም ትንተና ወይም ግላዊ ያለመመቸት ላይ መሰረት ለማድረግ ልንገፋ እንችላለን። እና ቤተክርስቲያኗ በዋነኛነት ያረጁ ወይም በፖለቲካ የተሳሳቱ ማህበራዊ ፖሊሲዎች፣ የማይመስሉ ግላዊ እና የጊዜ ገደቦች አሏት የሚሉትን ወሬዎች የምንቀበል ከሆነ፣ ስለ ፍቃደኝነት የሚኖሩን ድምደሜዎች ችግር ይኖርባቸዋል። የፍቃደኝነትን መርህ ከማህበራዊ ሚዲያ አቅራቢዎች ወይም ከቲክ ቶክ ሰዎች ጋር በአወንታዊ መንገድ እንዲሄድ መጠበቅ የለብንም። የሰዎች አመለካከት ብዙ ጊዜ ከመለኮታዊ እውነታ ጋር አይዛመድም።

ቤተክርስቲያኗ እግዚአብሔርን የሚወዱ እና ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ለመከተል ፍቃደኛ የሆኑ ፍፁም ያልሆኑ ሰዎች መሰብሰቢያ ቦታ ናት። ያ ፍቃደኝነት ኢየሱስ ክርስቶስ በመሆኑ እና የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ በመሆኑ እውነታ ላይ የተመሰረተ ነው። ይህ መለኮታዊ እውነታ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ብቻ ነው ሊታወቅ የሚችለው። ስለሆነም፣ ፍቃደኝነታችን የመንፈስ ቅዱስ ተፅዕኖ በሚገኝባቸው ቅዱስ ቦታዎች ለመኘት ከምንመድበው የጊዜ ርዝመት ጋር በቀጥታ ይዛመዳል።

ትርጉም ባለው ንግግር ላይ ከአፍቃሪ የሰማይ አባት ጋር በመወያየት የበለጠ ጊዜ ስናሳልፍ እና የሌሎችን ሃሳቦች መሻት ላይ ጥቂቀት ጊዜ ስናባክን መልካም ይሆናል። የቀን ተቀን የዜና ምንጫችንን ወደ ቅዱስ መጽሐፍቶች እና የእርሱ ህያው ነብያት የትንቢት ቃላት ለመቀየር መምረጥም እንችላለን።

ሰንበትን በመባረክ፣ ሃቀኛ አስራትን በመክፈል፣ ወቅታዊ የቤተመቅደስ መግቢያ መታወቂያን በመያዝ፣ ቤተመቅደስን በመካፈል እና የቤተመቅደስ ቅዱስ ቃልኪዳኖቻችንን በማክበር ላይ የምናስቀምጠው ጠቀሜታ የፍቃደኝነታችን እና የቁርጠኝነታችን ኃይለኛ ጠቋሚዎች እና ማረጋገጫዎች ናቸው። በክርስቶስ ያለንን እምነት ለማጠንከር ሰው ሰራሽ ከሆነ በላይ የሆነ ሙከራ ለማድረግ ፍቃደኞች ነን?

የሰማይ አባት ፍፁም በሆነ መልኩ ይወደናል፣ ነገር ግን ያ መውደድ ከብዙ ሃላፊነቶች ጋር ይመጣል። አዳኙን በፍቃደኝነት የሕይወታችን ማዕከል እንድናደርገው ይጠብቅብናል። አዳኙ በሁሉም ነገሮች ለአብ በፍቃደኝነት በመታዘዝ ለእኛ ፍፁም የሆነ ምሳሌ ነው። እርሱ “መንገድ፣ እውነት፣ እና ህይወት” ነው።3 ለሀጢያቶቻችን በፍቃደኝነት ቤዛ ሆነ። እርሱ በፍቃደኝነት ሸክማችንን አቀለለ፣ ፍርሃታችንን አበረደ፣ ጥንካሬ ሰጠን እንዲሁም በጭንቀት እና በሃዘን ወቅት ወደ ልባችን ሰላምን እና መረዳትን አመጣ።

ቢሆንም በኢየሱስ ክርስቶስ ማመን ምርጫ ነው። “ከማመን በላይ የበለጠ ለመፈለግ ባንችለልም” 4 በእርሱ ቃላት የእምነት ጉዟችንን የምንጀምርበት ወይም የምናስተካክልበት መነሻ ቦታ አለን። የእርሱ ቃላት በልባችን ውስጥ እንደ ፍሬ ከተተከለ እና በታላቅ እንክብካቤ ከተመገበ፣ ስር ይሰዳል እና እምነታችን በእርግጠኝነት ያድጋል እና የተግባር እና የኃይል መመሪያ ይሆናል። መፅሐፈ ሞርሞን እምነትን ለማሳደግ እና ለመመለስ በጣም ትልቁ ግብዓታችን ነው። ፍቃደኝነት የእምነት ማቀጣጠያ ነው።

ስጋዊ ህይወት በመለኮታዊ መልኩ ቀላል አይደለም እና አንዳንዴም ከአቅም በላይ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ፣ “እኛ ደስታ እንዲኖረን ነው”!5 በአዳኙ እና ቃልኪዳኖቻችን ላይ ማተኮር ዘላቂ ደስታ ያመጣል! የስጋዊ ህይወት አላማ ፍቃደኛ መሆናችንን ማረጋገጥ ነው። “የሕይወት ታላቁ ስራ እና የደቀ መዝሙርነት ዋጋ፣ የጌታን ፍቃድ መማር እና መተግበር ነው።”6 እውነተኛ ደቀ መዝሙርነት ወደ ደስታ ሙላት ይመራል። የደቀ መዝሙርነትን ዋጋን ለመክፈል ፍቃደኞች ነን?

የቃልኪዳኑ መንገድ የሚከናወኑ ተግባራት ዝርዝር አይደለም፣ የመንፈሳዊ እድገት እና ለጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ያለንን ቁርጠኝነት ማጠንከሪያ ሂደት ነው። የእያንዳንዱ ትዕዛዝ፣ መርህ፣ ቃልኪዳን እና ሥርዓት ዋነኛ አላማ፣ እምነትን መገንባት እና በክርስቶስ ማመን ነው። ሕይወታችንን በክርስቶስ ላይ የማተኮር ውሳኔአችን ቋሚ መሆን አለበት—መስፈርት ያለው፣ በሁኔታዎች የሚለዋወጥ፣ ወይም ስው ሰራሽ መሆን የለበትም። “በሁሉም ጊዜ በሁሉም ነገርና፣ በም[ንኖር]በት ቦታዎች ሁሉ የእግዚአብሔር ምስክር በመሆን ለመቆም” ከፍቃደኝነታችን የመዝናኛ ቀናት ወይም የእረፍት ቀናትን ለመውሰድ አንችልም።7 የመንፈስ ቅዱስ አብሮነት በጣም ውድ በመሆኑ ምክንያት ደቀ መዝሙርነት እርካሽ አይደለም።

በእርግጥ፣ ጌታ ስለ አስሩ ደናግላን ሲያስተምር ስለ እኛ ቀን እያሰበ ነበር። ብልሆች ስለነበሩት ስለአምስቱ እንዲህ አለ፦ “መንፈስ ቅዱስን እንደመሪያቸው ወስደዋል እናም አልተታለሉም፣” 8 የሞኞቹ ፋኖስ ደግሞ ዘይት በማጣቱ የተነሳ “ጠፍቷል።”9 ምናልባት የኔፊ ቃላት እነዚህን የቀድሞ ታማኝ የቤተክርስቲያን አባሎች በጥሩ ሁኔታ ይገልፃል፦ “እናም እርሱ ሌሎችን ያረጋጋልና፣ ቀስ ብሎም ወደ ስጋዊ ደህንነት አባብሏቸው እንዲህ ይላሉ፥ በፅዮን ሁሉም መልካም ነው”10

ስጋዊ ደህንነት ማለት ክርስቶስን ሳይሆን ዓለማዊ ነገሮችን መፈለግ እና በእነዛ ላይ ማመን ማለት ነው—በሌላ አባባል፣ በመንፈሳዊ መነፅር ሳይሆን በምድራዊ መነፅር መመልከት ማለት ነው። መንፈስ ቅዱስ “ነገሮች በርግጥ እንዳሉ እናም ነገሮች በርግጥ እንደሚሆኑ” የማየት ችሎታ ይሰጠናል።11 “በመንፈስ ቅዱስ ኃይል የሁሉንም ነገሮች እውነታ [እናውቃለን]” 12 እናም አንታለልም። ክርስቶስን የሕይወታችን ማዕከል እናደርገዋለን እና የእርሱን ትዕዛዛ በመታዘዝ ፍቃደኝነታችንን እናሳያለን፣ አይነስውር ሆነን ሳይሆን፣ ነገር ግን ማየት ስለምንችል።13

ሞኞቹ ደናግላንስ? የመንፈሳዊ ፋኖስ ዘይትን ለመሸከም ፍቃደኞች ያልነበሩት ለምንድን ነው? ዝም ብለው እያዘገዩ ነበርን? ምናልባት ሳይመቻቸው ቀርቶ ወይም አላስፈላጊ መስሏቸው ይሆናል። ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን፣ የክርስቶስን ወሳኝ ሚና በተመለከተ ተታለው ነበር። ይህ የሰይጣን መሰረታዊ ማታለያ ነበር እና ለዚህ ነበር የምስክርነታቸው ፋኖስ በመጨረሻ በመንፈሳዊ ዘይት ማጣት የተነሳ መጥፋት የቻለው። ይህ ምሳሌ ለእኛ ምሳሌያዊ አባባል ነው። ብዙዎች የእርሱን ቤተክርስቲያን ከመተዋቸው ከረዥም ጊዜ አስቀድመው አዳኙን እና ቃልኪዳናቸውን ይተዋሉ።

“በሰው ልጆች ልብ ውስጥ ይቆጣል እናም ጥሩ በሆነው ነገር ለቁጣ እንዲነሳሱ” ሰይጣን በሚቆጣበት ቀን በጥንት ነብያት በተተነበየ ታይቶ በማይታወቅ ጊዜ ውስጥ እንኖራለን።14 እጅግ ብዙዎቻችን በክርስቶስ መለኮታዊ ማንነት እና እምነት ላይ ጠላት በሆነው በኮምፒተር የታገዘ መዝናኛ እና መልዕክት በተጥለቀለቀ ዓለም ውስጥ እንኖራል።

በህፃን ልጅ ሕይወት ውስጥ በጣም ኃይለኛ መንፈሳዊ ተፅዕኖ ያለው ነገር የራሳቸውን ቅዱስ ቃልኪዳኖች በታማኝነት የሚጠብቁ የአፍቃሪ ወላጆች እና የአያቶች የጽድቅ ምሳሌ ነው። አላማ ያላቸው ወላጆች “ለሃጢያታቸው ስርየት ወዴት መመልከት እንዳለባቸው ያውቁ ዘንድ” 15 ልጆቻቸው በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እምነት እንዲኖራቸው ያስተምራሉ። ተራ እና ቋሚ ያልሆነ የቃልኪዳን ጥበቃ ወደ ተራ መንፈሳዊነት ይመራል። መንፈሳዊ ጉዳቱ ብዙ ጊዜ በልጆቻችን እና የልጅ ልጆቻችን ላይ ታላቅ ይሆናል። ወላጆች እና አያቶች፣ አሁንም ፍቃደኞች ነን?

ፕሬዚዳንት ራስል ኤም ኔልሰን እንዳስተማሩት “በሚመጡት ቀናት ያለ መንፈስ ቅዱስ መመሪያ፣ ምሪት፣ መጽናኛ እና ቋሚ ከሆነ ተጽዕኖ በመንፈሳዊነት ተቋቁመን ለመቀጠል አይቻልም” ብለዋል፡፡16 ይህ ፋኖሶቻችንን እንድናሳምር እና የመንፈሳዊ ዘይት ይዞታችንን እንድንጨምር ግልፅ እና ያልተሳሳተ ማስጠንቀቂያ ነው። ሕያው ነብያትን ለመከተል አሁንም ፍቃደኞች ነን? በፋኖሳችሁ ውስጥ ያለው የመንፈስ ዘይት መጠናችሁ ምንድን ነው? በግላዊ ሕይወታችሁ ውስጥ ምን ዓይነት ለውጦች ቀጣይነት ያለው የመንፈስ ቅዱስ ተፅዕኖ እንዲኖራችሁ ያስችላችኋል?

ዛሬ፣ ልክ እንደ ኢየሱስ ጊዜ፣ ወደ ኋላ የሚመለሱ የደቀ መዝሙርነትን ዋጋ የማይቀበሉ ይኖራሉ። ከባድ እና ጥላቻ የተሞላበት ነቀፋ በአዳኙ ቤተክርስቲያን እና እርሱን በሚከተሉት ላይ እየጨመረ ነው፣ ደቀ መዝሙርነታችን መንፈሳዊ የጀርባ አጥንታችንን ለማስተካከል እና ለማጠንከር እና እንዳንሰማቸው ታላቅ ፍቃደኝነትን ይጠይቃል።17

መንፈሳዊ መሰረታችን በጥንካሬ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ከተገነባ፣ አንወድቅም እናም መፍራት የለብንም።

“እነሆ፣ ጌታ ልብን እና መልካም ፈቃድ ያለውን አዕምሮ ይሻል፤ እናም ፍቃድ ያለው እና ታዛዥ የሆነው በእነዚህ የመጨረሻዎቹ ቀናት የፅዮን ምድርን በረከት ይበላሉ።”18

ሁላችንም ሁልጊዜ ፍቃደኞች እንሁን። በቅዱሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ስም፣ አሜን።