ስርዓቶች እና አዋጆች
የዳግም መመለስ አዋጅ


የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ሙላት በዳግም መመለስ

ለሁለት መቶኛ አመት መታሰቢያ የሚሆን ለአለም የተላለፈ አዋጅ

ይህ አዋጅ በሶልት ሌክ ስቲ፣ ዩታ ውስጥ በሚያዝያ 5፣ 2020 (እ.አ.አ) በነበረው በ190ኛው አመታዊ አጠቃላይ ጉባኤ ላይ በፕሬዘደንት ራስል ኤም. ኔልሰን እንደ መልእክታቸው ክፍል የተነበበ ነበር።

እግዚአብሔር በሁሉም አገሮች የሚኖሩትን ልጆቹን እንደሚያፈቅር በክብር እናውጃለን። እግዚአብሔር አብም የውድ ልጁን፣ የኢየሱስ ክርስቶስን፣ መለኮታዊ ውልደት፣ የማይነጻጸር ህይወት፣ እና ፍጻሜ የሌለው የኃጢያት ክፍያ መስዋዕትን ሰጥቶናል። በአብ ሀይል፣ ኢየሱስ ከሞት እንደገና ተነሳ እናም በሞት ላይ ድልን አገኘ። እርሱ አዳኛችን፣ ምሳሌአችን፣ እና ቤዛችን ነው።

ከሁለት መቶ አመታት በፊት፣ በ1820 (እ.አ.አ) በውብ የጸደይ ጠዋት፣ ወጣቱ ጆሴፍ ስሚዝ የትኛዋን ቤተክርስቲያን አባል ለመሆን እንደሚገባው በመፈለግ፣ በኒው ዮርክ፣ ዩ.ኤስ.ኤ. ውስጥ በቤቱ አጠገብ ወዳለው ጫካ ለመጸለይ ገባ። ስለ ነፍሱ ደህንነት በሚመለከት ጥያቄ ነበረው እናም እግዚአብሔር እንደሚመራው አምኖ ነበር።

ለጸሎቱ መልስ እግዚአብሔር አብ እና ልጁ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ለጆሴፍ እንደተገለጡ እና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደተተነበየው “[የነገሮችን] ሁሉ [መታደስ]” (የሐዋሪያት ስራ 3፥21) እንደተጀመሩ በትህትና እናውጃለን። በዚህም ራዕይ፣ የመጀመሪያዎቹ ሐዋሪያትን ሞት ተከትሎ፣ የክርስቶስ የአዲስ ኪዳን ቤተክርስቲያን ከምድር እንደጠፋች ተማረ። ጆሴፍ በዚህች መመለስ መሳሪያ ይሆናል።

በአብ እና በኢየሱስ ክርስቶስ አመራር፣ የሰማይ መልእክተኞች ጆሴፍን ለማስተማር እና የኢየሱስ ክርስቶስን ቤተክርስቲያንን እንደገና ለማቋቋም እንደመጡም እናረጋግጣለን። በትንሳኤ የተነሳው መጥምቁ ዮሀንስ ለኃጢአት ስርየት በመጥለቅ የማጥመቅን ስልጣን በዳግም መለሰ። ከመጀመሪያዎቹ አስራ ሁለት ሐዋሪያት ሶስቱ—ጴጥሮስ፣ ያዕቆብ፣ እና ዮሀንስ—ሐዋሪያነትን እና የክህነት ስልጣን ቁልፎችን በዳግም መለሱ። ሞትን በማሸነፍ ቤተሰቦችን በዘለአለማዊ ግንኙነት ለዘለአለም የማጣመር ስልጣንን በዳግም የመለሰው ኤልያስንም ጨምሮ፣ ሌሎችም መጡ።

ጆሴፍ ስሚዝ የጥንት መዝገቦች፣ የሆነውን መፅሐፈ ሞርሞን—ሌላኛው የኢየሱስ ክርስቶስ ምስክርነትን ለመተርጎም የእግዚአብሔር ስጦታ እና ሀይል እንደተሰጠውም በተጨማሪም እንመሰክራለን። የዚህ ቅዱስ ፅሁፍ ገጾችም ኢየሱስ ክርስቶስ በምዕራብ ክፍለ አለም ውስጥ የኖሩትን ሰዎች ከትንሳኤው በኋላ በግል ያገለገለበትን ታሪክ ያካትታሉ። ይህም ስለህይወት አላማ ያስተምራል እናም የዚህ አላማ ማእከላዊ የሆነውን የክርስቶስን ትምህርት ያስተምራል። እንደ መፅሐፍ ቅዱስ ተጓዳኝ ፅሁፍም፣ የሰው ዘር በሙሉ የአፍቃሪ የሰማይ አባት ወንድ እና ሴት ልጆች እንደሆኑ፣ እርሱ ለህይወታችን መለኮታዊ እቅድ እንዳለው፣ እና ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ዛሬም ልክ እንደ ጥንት ቀናት እንደሚናገር መፅሐፈ ሞርሞን ይመሰክራል።

በሚያዝያ 6፣ 1830 (እ.አ.አ) የተደራጀችው የኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን የክርስቶስ በዳግም የተመለሰችው የአዲስ ኪዳን ቤተክርስቲያን እንደሆነችም እናውጃለን። ይህችም ቤተክርስቲያን የማዕዘን አለቷ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም ህይወት እና መፈጸሚያ በሌለው የኃጢያት ክፍያውና በእውን ትንሳኤው ላይ የተተከለች ናት። ኢየሱስ ክርስቶስ እንደገናም ሐዋሪያትን ጠርቷል እና ለእነርሱም የክህነት ስልጣንን ሰጥቷቸዋል። እርሱም መንፈስ ቅዱስንና የደህንነት ስርዓቶችን ለመቀበል፣ እና የሚጸና ደስታን ለማግኘት እንችል ዘንድ ወደ እርሱ እና ወደ ቤተክርስቲያኑ እንድንመጣ ሁላችንንም ይጋብዛል።

ይህ በዳግም መመለስ በእግዚአብሔር አብ እና በውድ ልጁ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ከተጀመረ ሁለት መቶ አመታት አልፈዋል። እነዚህ የተተነበዩባቸው ድርጊቶች እውቀትንም በአለም ዙሪያ ውስጥ ብዙ ሚልዮን ሰዎች ተቀብለዋቸዋል።

ቃል የተገባለት ዳግም መመለስም በሚቀጥል ራዕይ በኩል ወደፊት እንደሚሄድ በደስታ እናውጃለን። ምድርም እንደገና አንድ አይነት አትሆንም፣ እግዚአብሔር “ያለውን ሁሉ በክርስቶስ [ይጠቀልላልና]” (ኤፌሶን 1፥10)።

እኛ እንደምናውቀው፣ ሰማያት ክፍት እንደሆኑ ያውቁ ዘንድ፣ እኛ የእርሱ ሐዋሪያት ሁሉንም በአምልኮ እና በምስጋና እንጋብዛለን። እግዚአብሔር ፍላጎቱን ለውድ ወንድ እና ሴት ልጆቹ እያሳወቀ እንደሆነ እናረጋግጣለን። የዳግም መመለስ መልዕክትን በጸሎት የሚያጠኑ እና በእምነት የሚተገብሩ ሰዎች ስለዚያ መለኮታዊነት እና ተስፋ ለተገባለት ለጌታችን እና ለአዳኛችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ምፅዓት አለምን ለማዘጋጀት ስላለው እቅድ የራሳቸውን ምስክርነት በማግኘት እንደሚባረኩ እንመሰክራለን።