መንፈሳዊ ትምህርት ቤት እና ኢኒስቲትዩት
ለተለያዩ የትምህርት ሁኔታዎች እና ተማሪዎች ሃሳቦች


“ለተለያዩ የትምህርት ሁኔታዎች እና ተማሪዎች ሃሳቦች፣” በአዳኙ መንገድ ማስተማር፦ በቤት እና በቤተክርስቲያን ውስጥ ለሚያስተምሩ ሁሉ [2022 (እ.አ.አ)]

“ለተለያዩ የትምህርት ሁኔታዎች እና ተማሪዎች ሃሳቦች፣” በአዳኙ መንገድ ማስተማር

ምስል
ሰዎች ቤተሰብን ሲያስተምሩ

ለተለያዩ የትምህርት ሁኔታዎች እና ተማሪዎች ሃሳቦች

በአዳኙ መንገድ የማስተማር መርሆዎች በቤት፣ በቤተክርስቲያን እና በሌላ ቦታ ለማንኛውም የማስተማር እድል ተግባራዊ መሆን ይችላሉ። ይሁን እንጂ፣ እያንዳንዱ እድል የራሱን የተለዩ ሁኔታዎች ይዞ ይመጣል። ይህ ክፍል ለተለያዩ ተማሪዎች እና የትምህርት ሁኔታዎች የተለዩ ተጨማሪ ሃሳቦችን ይሰጣል።

ቤት እና ቤተሰብ

ወንጌልን ለማስተማር እና ለመማር ቤት የተሻለ ቦታ ነው።

ፕሬዝደንት ረስልኤም. ኔልሰን ቤት “የወንጌል መማሪያ መካከል” መሆን እንዳለበት አስተምረዋል (“ምሳሌያዊ የኋለኛው ቀን ቅዱሳን መሆን፣” ሊያሆና፣ ህዳር 2018 (እ.አ.አ)፣ 113)። በቤተክርስቲያን ወይም በሴሚነሪ ውስጥ የሚሰጠው ትምህርት ዋጋ አለው እንዲሁም አስፈላጊ ነው፣ ነገር ግን አላማው በቤት ውስጥ የሚካሄደውን ትምህርት ለመርዳት ነው። ለእኛ እና ለቤተሰባችን ወንጌል የመማሪያ ዋናው ስፍራ እና ከሁሉም የተሻለው ስፍራ ቤት ነው።

ነገር ግን ያ መልካም የወንጌል ትምህርት እንዲያው ዝም ብሎ በቤት ውስጥ ይከሰታል ማለት አይደለም፣ ያላሰለሰ ጥረትን ይጠይቃል። ፕሬዝደንት ኔልሰን “ቤታችሁን መቀየር” ወይም “ማደስ” ሊያስፈልጋችሁ እንደሚችል ሃሳብ አቅርበዋል፣ ማለትም የግዴታ ግድግዳውን በማፍረስ ወይም አዲስ ወለል በማስገባት ሳይሆን ነገር ግን ምናልባት ለመንፈሱ ያደረጋችሁትን አስተዋጽዖ ጨምሮ በቤታችሁ ውስጥ ያለውን መንፈስ በአጠቃላይ፣ በመመዘን እንጂ (“Becoming Exemplary Latter-day Saints፣” 113)። ለምሳሌ በቤታችሁ ውስጥ ያለውን መዝሙር፣ ቪዲዮዎችን እና ሌላ ሚዲያ፤ በግድግዳዎች ላይ ያሉትን ፎቶዎች እና የቤተሰባችሁ አባላት የሚያወሩበትን እና እርስ በእርስ የሚንከባከቡበትን መንገድ አስቡ። እነዚህ ነገሮች የመንፈስ ቅዱስን ተፅዕኖ ይጋብዛሉ? እንደ ግለሰብ እና እንደ ቤተሰብ ወንጌልን ለመማር ሰዓትን ታመቻቻላችሁ? የቤተሰብ አባሎች በቤታችሁ ውስጥ ሲሆኑ እንደተወደዱ፣ ደህንነት እንደሚሰማቸው እና ወደ እግዚአብሔር እንደቀረቡ ይሰማቸዋልን?

በቤታችሁ ውስጥ ያለውን መንፈሳዊ ሁኔታ ለመቆጣጠር እንደምትችሉ ላይሰማችሁ ይችላል። ጉዳዩ ያ ከሆነ፣ የምትችሉትን ያህል ተፅዕኖ የምትፈጠሩ ሁኑ ከዚያም የጌታን እርዳታ ጠይቁ። የእናንተን የጽድቅ ጥረቶች ያከብራል። ወንጌልን ለማስተማር እና ለመማር ስትሞክሩ ምንም እንኳን የምትፈልጉትን ውጤቶች ወዲያውኑ ባታዩም፣ ውጤታማ እየሆናችሁ ነው

በቤት ውስጥ መማር በግንኙነቶች ላይ ነው የተመሰረተው

“የምታስተምሯቸውን ሰዎች ውደዱ” ለሁሉም ወንጌልን የማስተማር ሁኔታዎች ተግባራዊ የሚሆን ነው፣ ነገር ግን በቤት ውስጥ፣ ፍቅር በተፈጥሮ መልኩ መምጣት እና በጥልቅ መሰማት አለበት። ቤታችሁ እንደሚጠበቀው ባይሆንም እንኳን የወንጌል መማር ማዕከል መሆን አለበት ምክንያቱም ዘላቂ ግንኙነታችን እዚያ ውስጥ ነው የሚገነባው። ከቤት ውጪ ያሉ አስተማሪዎች የበለጠ ልምድ ወይም ስልጠና ሊኖራቸው ይችላል፣ ነገር ግን በቤት ውስጥ ያሉትን ፍቅራዊ የዘላለማዊ ግንኙነቶች አቅም መፍጠር አይችሉም። ስለዚህ እነዚያን ግንኙነቶች ተንከባከቧቸው። የቤተሰብ አባላቶቻችሁን ለማዳመጥ እና ከእነሱ ጋር መተማመንን ለመፍጠር እና የእርስበርስ መረዳትን ለመገንባት አስፈላጊ ሰዓት መድቡ እንዲሁም ጥረትን አድርጉ። ይህ ወንጌልን በቤታችሁ በማስተማር እና በመማር ጥረታችሁ ላይ ጠንካራ መሰረትን ለመፍጠር ይረዳል።

በቤት ውስጥ መማር ሊታቀድ የሚችል ሲሆን ነገር ግን ድንገተኛ መሆንም ይችላል

አብዛኞቹ የቤተክርስቲያን ክፍሎች የሚከናወኑት በሳምንት አንዴ ሲሆን፣መጀመሪያቸው እና መጨረሻቸው የታቀደ ነው፤ ነገር ግን በቤት ውስጥ ሁልጊዜ እንደዚህ አይሆንም። የታቀደ የቤተሰብ ምሽት ትምህርት ወይም የቤተሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ሊኖራችሁ ይችላል፣ ነገር ግን በቤተሰብ ውስጥ የማስተማር እድሎች ብዙውን ጊዜ ቀጥተኛ ባልሆነ መልኩ በቀን ተቀን ክስተቶች ውስጥ ይከሰታሉ፣ ማለትም ምግብን በመብላት ላይ፣ በቤት ውስጥ ስራን በመስራት ላይ፣ ጨዋታን በመጫውት ላይ፣ ወደ ስራ ወይም ትምህርት ቤት በመጓዝ ላይ፣ መጽሐፍን በማንበብ ላይ ወይም ፊልምን በጋራ በማየት ላይ። የዝናብ አውሎ ነፋስ አዳኙ ከመንፈሳዊ ማዕበሎች እንዴት እንደሚከልለን ለመናገር እድል ሊሆን ይችላል። ከባድ ውሳኔን ሊያደርግ ያለ አንድ ታዳጊ ስለግላዊ ራዕይ ለመማር ዝግጁ ሊሆን ይችላል። አንድ የፈራ ልጅ ስለ አፅናኙ በምትሰጡት ምስክርነት ሊጠቀም ይችላል። የሚረብሹ ወይም እርስ በእርሳቸው የሚጣሉ ልጆች ስለንስሃ እና ይቅርታ መማር ይችላሉ።

እንደዚህ ዓይነት ክስተቶች ስለማይታቀዱ፣ ለባህላዊ ትምህርቶች እንደምትዘጋጁት ሁሉ ለእነሱም መዘጋጀት አትችሉም። ይሁን እንጂ፣ እራሳችሁን ለመንፈስ ቅርብ በማድረግ እና “ሁሌም ዝግጁ ለመሆን” በመጣር መዘጋጀት ትችላላችሁ (1 ኛ ጴጥሮስ 3፥15)። የትኛውም ወቅት የማስተማር ወይም የመማር ወቅት መሆን ይችላል።

በቤት መማር ትንሽ፣ ቀላል፣ ቀጣይነት ያላቸውን ጥረቶች ያካትታል።

ወላጆች በቤት ውስጥ ወንጌልን የማስተማር ሙከራቸው ውጤታማ ያልሆነ ሲመስላቸው አንዳንድ ጊዜ ተስፋ ይቆርጣሉ። በተናጠል ስናያቸው አንድ የቤተሰብ ምሽት፣ አንድ የቅዱስ ጽሁፍ ጥናት ክፍለ ጊዜ ወይም አንድ የወንጌል ንግግር ብዙ ነገር እያከናወነ እንደሆነ ላይመስል ይችላል። ነገር ግን ትንሽ፣ ቀላል ጥረቶች በጊዜ ሂደት ያለማቋረጥ ሲደጋገሙ አልፎ አልፎ ከሚደረግ አስገራሚ ዝግጅት ወይም ወሳኝ ትምህርት ይበልጥ ኃይለኛ እና የሚያጠነክር መሆን ይችላል። “ሁሉም ነገሮች በጊዚያቸው ይከናወኑ ዘንድ ግድ ነው” ብሏል ጌታ። “ስለዚህ፣ መልካም ሥራን ትሰሩ ዘንድ አትታክቱ፣ የታላቅ ስራን መሰረት እየገነባችሁ ነውና። እናም ከትንንሾቹ ነገሮች ታላቅ የሆነው ይወጣል” (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 64፥32–33፤ እንዲሁም አልማ 37፥6–7 ይመልከቱ)። ስለዚህ ተስፋ አትቁረጡ፣ እናም ሁሌም ታላቅ የሆነን ነገር ለማከናወን አትጨነቁ። ብቻ ጥረታችሁ ቀጣይነትን ይኑረው።

በቤት ውስጥ፣ መማር እና መኖር አይነጣጠሉም

በቤት ውስጥ የወንጌል አግባብነት ወዲያውኑ ይታያል ። እዚያ ወንጌሉን አብራችሁ የምትማሯቸው ሰዎች በየቀኑ አብራችሁ ወንጌሉን የምትኖሩት ሰዎች ናቸው። በእርግጥ፣ ብዙውን ጊዜ ወንጌልን መኖር ወንጌልን የምንማርበት መንገድ ነው። ወንጌልን በቤት ውስጥ ስትማሩ እና ስታስተምሩ፣ የምትማሩትን ነገር ከምታደርጉት ነገር ጋር ለማገናኘት መንገዶችን ፈልጉ። ቤታችሁ ስለወንጌሉ የምታወሩበት ብቻ ሳይሆን እርሱን ለመኖር ጥረት የምታደርጉበት እንዲሆን ፍቀዱ።

ምስል
አንዲት ሴት ልጆችን እያስተማረች

በቤተሰብ ውስጥ የማስተማር እድሎች በተደጋጋሚ የሚፈጠሩት ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ፣ በቀን ተቀን ክስተቶች ውስጥ ነው።

ልጆችን ማስተማር

ልጆች የተለያዩ ነገሮችን ይፈልጋሉ

ሁሉም ልጆች የተለዩ ናቸው እናም ሲያድጉ ፍላጎታቸው ይቀይራል። የማስተማር ዘይቤያችሁን መቀያየር የተለያዩ ፍላጎታቸውን እንድታሟሉ ይረዳችኋል። ለምሳሌ፣ የሚከተሉትን ለመጠቀም አስቡ፦

  • ታሪኮች። ታሪኮች ወንጌል በቀን ተቀን ሕይወት ውስጥ እንዴት ተግባራዊ እንደሚሆን ልጆች እንዲያዩ ይረዳሉ። ታሪኮችን ከቅዱሳት መጻህፍት፣ ከገዛ ሕይወታችሁ፣ ከቤተሰብ ታሪካችሁ ወይም ከቤተክርስቲያን መጽሔቶች ውስጥ ተጠቀሙ፣ በተለይ ስለአዳኙ የሚናገሩ ታሪኮችን። ፎቶዎችን በመያዝ፣ ሃረጎችን በመድገም ወይም ታሪኩን በመተወን ልጆችን በታሪኩ ውስጥ ለማሳተፍ መንገዶችን አቅዱ።

  • የዕይታ የማስተማሪያ መርጃዎች። ፎቶዎች፣ ቪዲዮዎች እና ቁሶች ልጆች የወንጌል መርሆዎችን ለመረዳት እና ለማስታወስ ይረዳሉ። ብዙ ፎቶዎች እና ቪድዮዎች በ Media Library ውስጥ በ ChurchofJesusChrist.org ላይ ይገኛሉ።

  • መዝሙር መዝሙሮች እና ሌሎች ቅዱስ ዘፈኖች ልጆች የእግዚአብሔር ፍቅር እንዲሰማቸው፣ መንፈስ እንዲሰማቸው እና የወንጌል እውነታዎችን እዲማሩ ሊረዷቸው ይችላሉ። ዜማዎች፣ ሪትሞች እና ቀላል ግጥሞች ልጆች የወንጌልን እውነቶች ለአመታት እንዲያስታውሱ መርዳት ይችላል። ከልጆች ጋር ስትዘምሩ፣ በመዝሙሩ ውስጥ የሚማሩትን መርሆዎች እንዲያገኙ እና እንዲረዱ አግዟቸው።

አብዛኛዎቹ ልጆች ብዙ የስሜት ህዋሳትን ሲጠቀሙ የበለጠ ይማራሉ። በሚማሩበት ጊዜ የማየት፣ የመስማት እና የመንካት የስሜት ህዋሳተቶቻቸውን እንዲጠቀሙ ልጆችን ለመርዳት መንገዶችን አግኙ። በተወሰኑ ሁኔታዎች ውስጥ፣ የማሽተት እና የመቅመስ የስሜት ህዋሳቸውን ለማካተት መንገዶችን ልትፈልጉም ትችላላችሁ!

ልጆች መፍጠር ይችላሉ

ልጆች ከወንጌል መርሆ ጋር የሚዛመድን ነገር እንዲስሉ፣ እንዲገነቡ፣ ቀለም እንዲቀቡ ወይም የሆነ ነገርን እንዲፅፉ ስትጋብዙ፣ መርሆውን የበለጠ እንዲገነዘቡት ተረዷቸዋላችሁ እና ስለተማሩት ነገር ተጨባጭ ማስታወሻን ትሰጧቸዋላችሁ። የተማሩትን ለሌሎች ለማካፈል የፈጠሩትን ነገር መጠቀምም ይችላሉ። እያንዳንዱ የጓደኛ መጽሔት እትም ለልጆች የፈጠራ እንቅስቃሴዎችን ያካትታል።

ልጆች ለማወቅ ጉጉ ናቸው

ልጆች ጥያቄዎችን ሲጠይቁ፣ እንደ እረብሻ ሳይሆን እንደ እድሎች እዩዋቸው። የልጆች ጥያቄዎች ለመማር ዝግጁ መሆናቸው ጠቋሚ ናቸው እናም ጥያቄዎቻችው ስለ ምን እንደሚያስቡ እና ምን እንደሚሰማቸው ጠቃሚ ሃሳቦችን ይሰጧችኋል። የመንፈሳዊ ጥያቄዎቻቸው መልሶች በቅዱሳት መጻህፍት እና በህያው ነብያት ቃላት ውስጥ ሊገኙ እንደሚችሉ እንዲያዩ እርዷቸው።

ረባሽ በሚሆኑበትም ሰዓት እንኳን ልጆች ፍቅር ይፈልጋሉ።

አንዳንድ ጊዜ አንድ ልጅ የሌሎችን ትምህርት በሚረብሽ መልኩ ነገሮችን ያደርጋል። አብዛኛዎቹ የረብሻዎች ባህሪ ካልተሟላ ፍላጎት ይመነጫል። ይህ ሲከሰት፣ ልጁ ለሚያጋጥሙት ችግሮች ትዕግስተኛ፣ አፍቃሪ እና ተረጂ ሁኑ። እሱ ወይም እሷ በትምህርቱ ውስጥ አወንታዊ በሆኑ መንገዶች ለምሳሌ፣ ፎቶን በመያዝ፣ የሆነ ነገርን በመሳል ወይም ቅዱስ ጽሁፍን በማንበብ ለመሳተፍ ብዙ እድሎችን ይፈልጉ ይሆናል።

አንድ ልጅ ረብሻውን ቢቀጥል፣ ከእሱ ወይም ከእሷ ጋር ለብቻ መነጋገር ሊጠቅም ይችላል። በፍቅር እና በትዕግስት መንፈስ እሱ ወይም እሷ እንዲያደርጉ የምትጠብቋቸውን ነገሮች እና እነዚያን ነገሮች ሊያደርጓቸው እንደሚችሉ ያላችሁን እምነት ግለፁ። ልጁ ወይም ልጅቷ የተሻለ ምርጫዎችን ሲያደርጉ አሞግሷቸው።

ልጆች ብዙ የሚያካፍሉት ነገር አላቸው

ልጆች አዲስ ነገሮችን ሲማሩ፣ በተፈጥሮ ለሌሎች ለማካፈል ይፈልጋሉ። ልጆች የወንጌል መርሆዎችን አንዳቸው ላንዳቸው፣ ለቤተሰብ አባሎች እና ለጓደኛቸው እንዲያስተምሩ እድሎችን በመስጠት ይህን ፍላጎት አበረታቱ። እንዲሁም ከምታስተምሯቸው መርሆዎች ጋር የሚዛመዱ ሃሳቦቻቸውን፣ ስሜቶቻቸውን እና ልምዶቻቸውን ለእናንት እንዲያካፍሉ ጠይቋቸው። ቀላል፣ ንፁህ እና ኃይለኛ ሃሳቦች እንዳሏቸው ትገነዘባላችሁ።

ልጆች መንፈስ ሊሰማቸው ይችላል፣ ነገር ግን የእርሱን ተፅዕኖ ለመገንዘብ እርዳታ ሊፈልጉ ይችላሉ።

የመንፈስ ቅዱስ ስጦታን ያልተቀበሉ ልጆችም እንኳን የእርሱ ተፅዕኖ ይሰማቸዋል፣ በተለይ ስለኢየሱስ ክርስቶስ እና ስለወንጌሉ በሚማሩበት ወቅት። የጽድቅ ምርጫዎችን ሲያደርጉ፣ የአዳኙ ማረጋገጫ በመንፈስ አማካኝነት ሊሰማቸው ይችላል። መንፈስ ከእኛ ጋር የሚነጋገርባቸውን የተለያዩ መንገዶች ለልጆች አስተምሩ። እርሱ ሲናገራቸው የእርሱን ድምፅ እንዲገነዘቡ እርዷቸው። ይህ በሕይወታቸው ውስጥ ግላዊ ራዕይን የመሻት እና የመተግበር ልምድን እንዲያዳብሩ ይረዳቸዋል።

ወጣቶችን ማስተማር

ወጣቶች ታላቅ አቅም አላቸው

ወጣቶች በጌታ አገልግሎት ውስጥ አስገራሚ ነገሮችን የማድረግ አቅም አላቸው። በቅዱሳት መጻህፍት ውስጥ የተመዘገቡት ብዙ ልምዶች እግዚአብሔር በወጣት ሰዎች መንፈሳዊ ችሎታዎች እንደሚተማመን ይገልፃሉ። ወጣቶች እንደምታምኗቸው ከተሰማቸው፣ በመለኮታዊ ብቃታቸው መተማመናቸው ያድጋል እንዲሁም ማከናወን በሚችሉት ነገር ያስገርሟችኋል። የሰማይ አባት መሆን እንደሚችሉ የሚያውቀውን እንዲያዩ በፍቅር እርዷቸው። እነሱን መውደድ እና ማበረታታት በመቀጠል፣ በትዕግስት ከእነሱ ጋር በመራመድ እና በእነሱ መቼም ተስፋ ባለመቁረጥ የአዳኙን ምሳሌ ተከተሉ።

ወጣቶች ስለራሳቸው እየተማሩ ነው

የምታስተምሯቸው ወጣቶች የምስክርነታቸውን መሰረቶች እየገነቡ ነው። እምነታቸውን እና ፅናታቸውን በማግኘት ሂደት ላይ ናቸው። የሕይወት ጉዟቸውን የሚነካ ውሳኔዎችን እያደረጉ ነው። በእነዚህ አደገኛ ጊዜዎች ውስጥ በመንፈሳዊነት ተጠብቆ ለመኖር እና ጌታ ለእነሱ ያለውን ተልዕኮ ያሳኩ ዘንድ የምታስተምሯቸው ወጣቶች በፈተናዎቻቸው ወቅት ጥንካሬን፣ ለጥያቄዎቻቸው መልሶችን እና “እንደ እግዚአብሔር ምስክር ለመቆም” ብርታትን እንዴት እንደሚያገኙ ማወቅ ይፈልጋሉ (ሞዛያ 18፥9)።

ወጣቶች በቀላሉ ስለነገሮች እየተነገራቸው ከመማር ይልቅ በምክንያት እና በልምድ የመማር ፍላጎታቸው ከፍ ያለ ነው። ይህ ማለት ወጣቶችን ማስተማር ጥሩ የማዳመጥ ችሎታን ይጠይቃል ማለት ነው። ወጣቶች ሰዎች የተረዷቸው ሲመስላቸው፣ ምክርን እና ምሪትን ለመቀበል የበለጠ የፍቃደኝነት ስሜት ይሰማቸዋል። በጥያቄዎች እና በፈተናዎች ሲጨናነቁ ጌታ እንደሚያውቃቸው እና እንደሚረዳቸው አረጋግጡላቸው። የቀን ተቀን የጸሎት እና የቅዱስ ጽሁፍ ጥናትን እና ሌሎችን የማገልገል ልምድን በማዳበር በእርሱ ላይ ያላቸውን እምነት መግለፅ ይችላሉ። ወጣቶች በቤተክርስቲያን ክፍሎች ውስጥ እንዲካፈሉ እና በግላቸው እንዲያጠኑ ማበረታታት የመለኮታዊ ውርሳቸውን ምስክርነት የሚገነባ ግላዊ ልምዶች እንዲኖራቸው ሊረዳቸው ይችላል።

ብዙ ወጣቶች ቴክኖሎጂን መጠቀም ያስደስታቸዋል

የምታስተምሯቸው ወጣቶች የራሳቸው የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች ካሏቸው፣ እነዚህ እቃዎች መማርን የሚያዳብሩ እቃዎች እንደሆኑ አስታውሱ። የኤሌክትሮኒክስ ቅዱሳት መጽሃፍቶቻቸውን እና በወንጌል ላይብረሪ ውስጥ የሚገኙ ሌሎች ግብዓቶችን እንዴት እንደሚጠቀሙ አስተምሯቸው። ለሚቀጥለው ትምህርቶች እንዲዘጋጁ ለመርዳት መልዕክቶችን እና አገናኞችን ለወጣቶች መላክ ትችላላችሁ።

ምስል
የሰንበት ትምህርት ክፍል

ወጣቶች የሰማይ አባት መሆን እንደሚችሉ የሚያውቀውን መረዳት ይኖርባቸዋል።

ጎልማሶችን ማስተማር

ጎልማሶች ለትምህርታቸው ሃላፊነትን መውሰድ ይችላሉ

ጎልማሳ ተማሪዎች በወንጌል መማር ሁኔታዎች ውስጥ በራሳቸው የመተግበር ችሎታ አላቸው (2 ኛ ኔፊ 2፥26 ይመልከቱ)። ቀደም ብለው የሆነ ነገር በማጥናት ለወንጌል ውይይቶች እንዲዘጋጁ ጋብዟቸው እንዲሁም እየተማሩ ያሉትን ነገር በመንፈስ እንዲያካፍሉ አበረታቷቸው። የትኞቹን የወንጌል መርሆዎችን በጋራ በመማር ጊዜ ማሳለፍ እንደሚፈልጉ ልትጠይቋቸውም ትችላላችሁ።

ጎልማሶች ሲማሩ ልምዶቻቸውን ይጠቀማሉ

ኢዮብ እንዲህ ብሏል፣ “በሽምግልና ጊዜ ጥበብ፣ በዘመንስ ርዝመት ማስተዋል ይገኛል” (ኢዮብ 12፥12)። በአጠቃላይ፣ ጥበብ እና መንፈሳዊ መረዳት ከዓመታት ልምድ በኋላ ይመጣሉ። ጎልማሶችን ስታስተምሩ፣ በሰማይ አባት እና በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያላቸውን እምነት የገነቡላቸውን ልምዶች እንዲያካፍሉ ጋብዟቸው። ይህ የሚያጠኗቸው የወንጌል መርሆዎች እውነት እንደሆኑ እንዴት እንዳወቁ ለመመስከር እድሎችን ይሰጣቸዋል። “ሁሉም … ሁሉም ይታነፁ ዘንድ” በመርዳት ልምዶችን ማካፈል ከምታስተምሯቸው ሰዎች ጋር ያላችሁን ግንኙነቶች ይገነባል (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 88፥122)።

ጎልማሶች የሚተገበሩ ነገሮችን ይፈልጋሉ

የምታስተምሯቸው ጎልማሶች በስራዎቻቸው፣ በማህበረሰባቸው፣ በቤተክርስቲያን ጥሪዎቻቸው እና በቤተሰባቸው ውስጥ ብዙ ሚናዎች እና ሃላፊነቶች ሊኖራቸው ይችላል። ወንጌልን ሲያጠኑ፣ ብዙውን ጊዜ የሚማሩት ነገር በእነዚያ ሚናዎች ውስጥ እንዴት እንደሚረዳቸው ያስባሉ። የእግዚአብሔር ቃል ለተለየ ሁኔታዎቻቸው እንዴት አግባብነት እንዳለው እንዲያዩ ጋብዟቸው። የወንጌል መርሆዎች በሕይወታቸው ውስጥ እንዴት ትርጉም እንደሚሰጡ እና ተግባራዊ እንደሚሆኑ እነርሱን በመጠየቅ ይህንን ማድረግ ትችላላችሁ።

ጎልማሶች ውስብስብ በሆነ መልኩ ማሰብ ይችላሉ

በልምዳቸው እና እውቀታቸው ምክንያት፣ ጎልማሶች ለወንጌል ጥያቄዎች ሁልጊዜ ቀላል መልሶች እንደሌሉ ያውቃሉ። አንድ የቅዱስ ጽሁፍ ምንባብ ብዙ ትርጉሞች ሊኖረው እንደሚችል ማድነቅ ይችላሉ እንዲሁም አንድን የወንጌል መርህ ለተለያዩ የሕይወት ሁኔታዎች ተግባራዊ ማድረግ ይችላሉ። የወንጌል መርሆዎች እርስ በእርስ እና በሕይወታቸው ውስጥ እየሆነ ካለ ነገር ጋር እንዴት እንደሚዛመዱ እንዲያሰላስሉ ጋብዟቸው። ያላቸውን የተለዩ አመለካከቶች እርስ በእርስ መማማር እንዲችሉ ተሳትፎን እና ውይይትን አበረታቱ።

ምስል
አንዲት ሴት እያስተማረች

ጎልማሶች በእግዚአብሔር እና በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያላቸውን እምነት የገነቡትን ብዙ ልምዶች ማካፈል ይችላሉ።

አካል ጉዳት ያለባቸውን ሰዎች ማስተማር

እያንዳንዱ ሰው እንዲያድግ እና እንዲሻሻል አግዙ

ጆሴፍ ስሚዝ ፣ “እግዚአብሔር ወደ ዓለም የላካቸው ሁሉም አእምሮዎች እና ነፍሶች ለማደግ ብቁ ናቸው” ሲል አስተምሯል (የቤተክርስቲያኗ ፕሬዝዳንቶች ትምህርቶች፤ ጆሴፍ ስሚዝ [2007 እ.አ.አ]፣ 210)። ሁሉም የእግዚአብሔር ልጆች በእውቀት የማደግ እና የመሻሻል ብቃት እንዳላቸው አስቡ። እያንዳንዱን ሰው እንዴት እንደምትረዱ ለማወቅ ጌታን ጠይቁ።

ስለተለዩ ፍላጎቶች ተማሩ

ከተማሪዎች ወይም ከቤተሰባቸው ወይም ከተንከባካቢዎቻቸው ጋር ተነጋገሩ። እያንዳንዱ ግለሰብ እንዴት በተሻለ ሁኔታ መማር እንደሚችል እና ምን ዓይነት ስልቶች የበለጠ እንደሚረዱ እወቁ። ልምድ እና ሃሳብ ካላቸው ከሌሎች መሪዎች እና አስተማሪዎች ጋር መማከርም ትችላላችሁ። ለጠቃሚ የትምህርት ስልቶች፣ disabilities.ChurchofJesusChrist.org ይመልከቱ።

አወንታዊ ሁኔታን ፍጠሩ

ሁሉም ደህንነት እና መወደድ እንዲሰማው የሚያደርግን አወንታዊ ሁኔታ ፍጠሩ። ሁሉም አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ተመሳሳይ ናቸው ብላችሁ አታስቡ፣ እናም እያንዳንዱን ሰው በፍቅር እና በክብር ያዙ። ሌሎች ደግ እና ሰው ተቀባይ እንዲሆኑ አበረታቱ።

ሁሉም መሳተፍ እንደሚችሉ አረጋግጡ

የአካል ውስንነቶች እና የመማር ችግሮች ያሉባቸውን ሰዎች ጨምሮ ሁሉም ተማሪዎች መማር እንደሚችሉ ለማረጋገጥ በእንቅስቃሴዎች ላይ ትንሽ ለውጦችን ማድረግ ይቻላል። ለምሳሌ፣ አንድ እንቅስቃሴ ፎቶ ማሳየትን ቢያመለክት፣ የማየት እክል ያላቸውን ሰዎች ለማካተት በምትኩ የሚዛመድ መዝሙርን መዘመር ትችላላችሁ።

ወጥነት ያላቸው በመደበኛነት የሚከናወኑ ድርጊቶችን እና መዋቅሮችን መስርቱ

በመደበኛነት የሚከናወኑ ድርጊቶችን ለመመስረት አንዱ መንገድ የጊዜ ሰሌዳ የያዘን ፖስተር መፍጠር ነው። የጊዜ ሰሌዳችሁ ጸሎቶችን፣ የማስተማሪያ ሰዓትን እና የእንቅስቃሴ ሰዓትን ሊያካትት ይችላል። የጊዜ ሰሌዳን መከተል ለተወሰኑ ተማሪዎች እርግጠኛ ያለመሆንን እና የጭንቀትን ስሜቶች ለመቀነስ ሊረዳ ይችላል።

አስቸጋሪ ባህሪዎች ለምን እንደሚከሰቱ ተረዱ

ስለአካል ጉዳተኝነት ወይም አንድን ሰው ተገቢ ባልሆነ መልኩ እንዲተገብር ተፅዕኖ ሰለሚያደርጉበት ሁኔታዎች ተማሩ። አስቸጋሪ ባህሪያት ሲከሰቱ እየሆነ ስላለው ነገር ነገር በጥንቃቄ ትኩረት ስጡ። ተማሪዎችን በተሻለ ሁኔታ ለመደገፍ ሁኔታውን እንዴት እንደምታስተካክሉ በጸሎት አስቡ።

አካል ጉዳተኛ ሰዎችን ስለማስተማር ለበለጠ መረጃ ለማግኘት፣ disabilities.ChurchofJesusChrist.org ይመልከቱ።

ምስል
የወጣት ሴቶች ክፍል

አስተማሪዎች፣ እያንዳንዱ ተቀባይነት እንዳለው እና የመወደድ ስሜት እንዲሰማው የሚያደርግ አወንታዊ የመማር ሁኔታን መፍጠር ይችላሉ።

በቴክኖሎጂ በታገዘ በርቀት የገጽ ለገጽ ዘዴ ማስተማር

ከቴክኖሎጂ ጋር ተዋወቁ

ከክፍላችሁ ወይም ከስብሰባችሁ በፊት፣ ከምትጠቀሙት ቴክኖሎጂ ጋር ለመተዋወቅ የተወሰነ ጊዜ አሳልፉ። ቪድዮዎችን ወይም ፎቶዎችን እንደማካፈል ያሉ የተወሰኑ ገጽታዎችን ተለማመዱ። ከቤተሰብ አባላት ወይም ከጓደኞች ጋር “የልምምድ” ስብሰባ ማካሄድን አስቡ።

አብዛኛዎቹ አጥቢያዎች እና ካስማዎች የቴክኖሎጂ ባለሞያዎች አሏቸው። በቴክኖሎጂ የታገዘ የርቀት የገጽ ለገጽ ስብሰባ ልምድ ያላቸውን ሌሎች ሰዎች ልታውቁ ትችላላችሁ። የእነርሱን ምክር ወይም መመሪያ ጠይቁ።

ሊረብሹ የሚችሉ ነገሮችን አስወግዱ

ከተቻለ ስብሰባችሁን ለማካሄድ ጸጥ ያለ ቦታ ፈልጉ። በስተጀርባ ያሉ ድምፆች ሊረብሹ ይችላሉ። ተማሪዎችም ተመሳሳይ ነገር እንዲያደርጉ ወይም የማይናገሩ ከሆኑ የማይክሮፎናቸውን ድምጸ-እንዲያጠፉ አበረታቱ።

ካሜራን ተጠቀሙ።

ከተቻለ ተማሪዎች ፊታችሁን መመልከት እንዲችሉ ካሜራችሁን አብሩ። ተማሪዎችም እንዲሁ ካሜራዎቻቸውን እንዲያበሩ ጋብዙ (ግን አታስገድዱ)። ይህ የአንድነት እና የመተባበር መንፈስን ለመፍጠር ሊረዳ ይችላል።

በቴክኖሎጂ የታገዘ የርቀት የገጽ ለገጽ የመልዕክት መለዋወጫ ገጽታን ተጠቀሙ

ብዙ በቴክኖሎጂ የታገዘ የርቀት የገጽ ለገጽ ስብሰባ ፕሮግራሞች ተሳታፊዎች በውይይት መስኮት ውስጥ ጥያቄዎችን ወይም አስተያየቶችን እንዲተይቡ ያስችላሉ። እንዲሁም አንዳንዶቹ፣ በቴክኖሎጂ የታገዘ የርቀት የገጽ ለገጽ ፕሮግራሞች ተሳታፊዎች እጃቸውን ወደ ላይ የማንሳት ምልክት እንዲያሳዩ ይፈቅዳሉ። ተማሪዎች ስለእነዚህ ገጽታዎች እንዲያውቁ አድርጉ። ትኩረታችሁ ውይይቱን በመምራት ላይ ለማድረግ ትችሉ ዘንድ የሚነሱ እጆችን ወይም የሚጻፉ መልዕክቶችን የሚመለከት የሆነ ሰው ለመመደብ ትፈልጉ ይሆናል።

ተማሪዎችን ለማሳተፍ መንገዶችን ፈልጉ

በቴክኖሎጂ የታገዘ የርቀት የገጽ ለገጽ ትምህርት ሁኔታዎች አንዳንድ ጊዜ ሰዎች እንዲታዩ እና እንዲሰሙ ማድረግን ከባድ ያደርጉታል። መሳተፍ የሚፈልጉትን ሰዎች ለማሳተፍ የታሰበበት ጥረት አድርጉ። አንዳንድ ጊዜ ይህ ማለት (ለምሳሌ፣ ትልቅ የሰንበት ክፍልን በመክፈል) ትንንሽ ቡድኖችን መፍጠር ማለት ነው። አንዳንድ ጊዜ ተማሪዎች በተወሰነ መንገድ እንዲሳተፉ አስቀድሞ መጠየቅ ማለት ነው። የቴክኖሎጂ ውስንነቶች ለመማር ፍቃደኛ እና ጉጉ የሆኑ ሰዎችን እንድትረሱ ወይም ችላ እንድትሉ እንዲያደርጓችሁ አትፍቀዱ።