አጠቃላይ ጉባኤ
የመጽናት ሀይል
የጥቅምት 2020 (እ.አ.አ) አጠቃላይ ጉባኤ


የመጽናት ሀይል

እምነት እና ውስጣዊ ነፍሳችንን የሞላው የእግዚያብሄር ቃል ብቻ ናቸው ሊያጸኑን—እንዲሁም ሃይሉን እንድናገኝ ለመፍቀድ በቂ የሚሆኑት።

የውድ ነቢያችንን የፕሬዚዳንት ራስል ኤም. ኔልሰንን ትምህርቶች ስከልስ በብዙ ንግግሮቹ ደጋግሞ የተጠቀመውን አንድ ቃል አገኘሁኝ። ይህም ቃል ሃይልነው።

እንደሃዋርያ ድጋፍ ከተቀበለ በኋላ በተካሄደው የመጀመሪያው አጠቃላይ ጉባኤ ላይ ፕሬዚዳንት ኔልሰን ስለሃይል ተናግሮ ነበር።1 ለአመታት ስለሃይል ማስተማሩንም ቀጥሏል። ፕሬዚዳንት ኔልሰንን እንደነቢያችን ከደገፍነው ጊዜ ጀምሮ ስለሃይል መርሆ—በተለይ ስለእግዚያብሄር ሃይል—እና እንዴት ልናገኘው እንደምንችል አስተምሯል። ሌሎችን ስናገለግል የእግዚያብሄርን ሃይል እንዴት ማግኘት እና መጠቀም እንደምንችል ፣2 ንስሃ ኢየሱስ ክርስቶስን እና የሃጢያት ክፍያውን ሃይል ወደህይወታችን እንዴት እንደሚጋብዝ፣3 እና የክህነት ስልጣን—የእግዚያብሄር ሃይል እና ስልጣን—ከእርሱ ጋር ቃል ኪዳን የሚገቡትን እና የሚጠብቁትን ሁሉ እንደሚባርክ አስተምሯል።4 ፕሬዚዳንት ኔልሰን በቤተመቅደስ ቡራኬ ለተቀበሉት ሁሉ ቃልኪዳናቸውን ሲጠብቁ የእግዚያብሄር ሃይል እንደሚፈስ መስክሯል።5

በተለይ ፕሬዚዳንት ኔልሰን በሚያዝያ 2020 (እ.አ.አ) አጠቃላይ ጉባኤ ላይ ባቀረበልን ፈተና በእጅጉ ስሜቴ ተነክቶ ነበር። “ስለተባረካችሁበት —ወይም ስለምትባረኩበት ኃይል እና እውቀት የበለጠ ለመማር አንብቡ እንዲሁም ጸልዩ“ ሲል መመሪያ ሰጠን።6

ለዚህ ፈተና ምላሽም ስለተባረኩበት—ወይም ስለምባረክበት ኃይል እና እውቀት አጥንቻለሁ፣ ጸልያለሁ እንዲሁም አንዳንድ ጠቃሚ ነገሮችን ተምሪያለሁ።

የእግዚያብሄርን ሃይል ለማግኘት እና ለመጠቀም ምን ማድረግ እንዳለብን ማወቅ ቀላል አይደለም ነገር ግን በአእምሯችን በመመርመር እና መንፈስ ቅዱስ እንዲገልጥልን በመጸለይ ሊደረግ የሚችል ሆኖ አግኝቼዋለሁ።7 ሽማግሌ ሪቻርድ ጂ.ስካት ስለእግዚያብሄር ሃይል ምንነት ግልጽ ትርጉም ሰጥቷል፦“በራሳችን ልናደርግ ከምንችለው በላይ የማድረግ ሃይል” ነው።8

የእግዚያብሄርን ሃይል ለመጋበዝ ልባችንን እና ነፍሳችንን በእግዚያብሄር ቃል እና በኢየሱስ ክርስቶስ የእምነት መሰረት መሙላት በእነዚህ አስቸጋሪ ጊዝያት ወሳኝ ነው። የእግዚያብሄርን ቃል እንዲሁም በጥልቀት በልባችን በኢየሱስ ክርስቶስ እምነት ሳናገኝ ምስክርነቶቻችን እና እምነታችን ውጤታማ ላይሆኑ ይችላሉ እናም እግዚያብሄር ሊሰጠን የሚፈልገውን ሃይል እንዳናገኝ ልንሆን እንችላለን። የላይ ላይ እምነት በቂ አይደለም። እምነት እና ውስጣዊ ነፍሳችንን የሞላው የእግዚያብሄር ቃል ብቻ ናቸው ሊያጸኑን—እንዲሁም ሃይሉን እንድናገኝ ለመፍቀድ በቂ የሚሆኑት።

እህት ጆንሰን እና እኔ ልጆቻችንን እያሳደግን በነበረበት ጊዜ የሙዚቃ መሳሪያ መጫወትን እንዲማሩ አበረታታናቸው። ነገር ግን ልጆቻችን የሙዚቃ ትምህርት እንዲወስዱ የምንፈቅድላቸው በእነሱ በኩል ሊያደርጉ የሚገባቸውን ካደረጉ እና በየቀኑ የሙዚቃ መሳሪያዎቻቸውን ከተለማመዱ ብቻ ነበር። አንድ ቅዳሜ እለት ሴት ልጃችን ጄሊን ጓደኞቿ ጋር ሄዳ ለመጫወት ጓጉታ ነበር ነገር ግን የፒያኖ ልምምዷን ገና አላደረገችም ነበር። ለሰላሳ ደቂቃ ልምምድ የማድረግ ውሳኔ አድርጋ እንደነበር በማወቅ የሰአት ማሳወቂያውን ለማስተካከል ፈለገች ምክንያቱም ከሚፈለገው ከአንድ ደቂቃም በላይ ለመለማመድ አልፈለገችም ነበር።

ወደፒያኖው ለመሄድ በማይክሮዌቭ ማብሰያው እያለፈች እያለች ቆም አለችና ቁልፎችን ተጫነች። ነገር ግን የሰአት ማሳወቂያውን በማስተካከል ፋንታ የማይክሮዌቭ ማብሰያው ለሰላሳ ደቂቃ እንዲያበስል አስተካከለችው ከዚያም የማስጀመሪያ ቁልፉን ተጫነችው። ከሃያ ደቂቃ ልምምድ በኋላ ምን ያህል ሰአት እንደቀረ ለማረጋገጥ ወደማዕድ ቤቱ ተመልሳ ሄደች እና ማይክሮዌቩ በእሳት ተያይዞ አገኘችው።

ከዚያም ቤቱ በእሳት ተያያዘ እያለች እየጮኸች የጓሮ ስራ እየሰራሁ ወደነበርኩበት ወደጓሮ እየሮጠች መጣች። ወደቤት እየሮጥኩኝ ሄድኩኝ ከዚያም በእርግጥም የማይክሮዌቭ ማብሰያው እየነደደ አገኘሁት።

ቤታችንን ከመቃጠል ለማዳን ጥረት ለማድረግ ወደማይክሮዌቭ ማብሰያው ጀርባ ተንጠራራሁና ሶኬቱን ነቀልኩት እንዲሁም ገመዱን እየተቀጣጠለ የነበረውን የማይክሮዌቭ ማብሰያ ከመደርደሪያው ላይ ለማንሳት ተጠቀምኩበት። ጀግና ለመሆን እና ቀኑን እንዲሁም ቤታችንን ለማትረፍ ተስፋ በማድረግ እየነደደ የነበረውን የማይክሮዌቭ ማብሰያ ከሰውነቴ ለማራቅ ዙሪያውን በገመዱ አዞርኩት፣ ወደጓሮ ሄድኩና ለአንድ ተጨማሪ ጊዜ አወዛውዤ የማይክሮዌቭ ማብሰያውን ወደሳሩ አሽቀነጠርኩት። እዚያም የባንቧ ውሃ በመክፈት የእሳት ነበልባሉን ለማጥፋት ቻልን።

ምንድን ነበር ችግሩ? የማይክሮዌቭ ማብሰያ ሃይሉን የሚወስድ አንድ ነገር ይፈልጋል እናም ሃይሉን የሚወስድ አንድ ነገር በውስጡ ከሌለ ማብሰያው እራሱ ሃይሉን ይወስደዋል፣ ይግላል እንዲሁም በእሳት በመያያዝ በእሳት ነበልባል እና አመድ ክምር ውስጥ እራሱን ሊያወድም ይችላል።9 በውስጡ ምንም ነገር ስላልነበረ የማይክሮዌቭ ማብሰያችን እንዳለ በእሳት ተያያዘ እና ተቃጠለ።

እንደዚሁም በልባቸው ውስጥ ጥልቅ የሆነ እምነት እና የእግዚያብሄር ቃል ያላቸው ጠላት ሊያጠፋን የሚልካቸውን የእሳት ነበልባል ፍላጻዎች ለመምጠጥ እና ለማሸነፍ ይችላሉ።10 ያለበለዚያ እምነታችን፣ ተስፋችን እና አጠንክረን የያዝነው ሃሳባችን ላይጸና ይችላል እንዲሁም እንደ ባዶው የማይክሮዌቭ ማብሰያ የአደጋ ተጎጂ ልንሆን እንችላለን።

የእግዚአብሔር ቃል በነፍሴ ውስጥ በጥልቀት መኖር በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እና በኃጢያት ክፍያ ላይ ካለኝ እምነት ጋር ተደምሮ፣ ጠላትን እና በእኔ ላይ ሊወረውርብኝ የሚችለውን ማንኛውንም ነገር ለማሸነፍ የእግዚአብሔርን ኃይል ለማግኘት እና ለመጠቀም እንደሚያስችለኝ ተምሪያለሁ። ፈተናዎች ሲያጋጥሙን ጳውሎስ ባስተማረው የጌታ ተስፋ ላይ መደገፍ እንችላለን፦“እግዚአብሔር የኃይልና የፍቅር መንፈስ እንጂ የፍርሃት መንፈስ አልሰጠንም።”11

አዳኙ እንደልጅ “[እንደ]አደገ፥ ጥበብም ሞልቶበት በመንፈስ [እንደ]ጠነከረ፤ የእግዚያብሄርም ጸጋ በእርሱ ላይ [እንደ]ነበረ” እናውቃለን።12 እያደገ ሲሄድ “ኢየሱስ በጥበብና በቁመት በሞገስም በእግዚአብሔርና በሰው ፊት [እንደ]አደገ” እናውቃለን።13 እናም አገልግሎቱን ሲጀምር ያዳመጡት “ቃሉ በስልጣን ነበርና በትምህርቱ [እንደ]ተገረሙ” እናውቃለን14

በዝግጅት አዳኙ በኃይል አድጓል እንዲሁም የሰይጣንን ፈተናዎች ሁሉ መቋቋም ችሏል።14 የአዳኙን ምሳሌ ስንከተል እንዲሁም የእግዚያብሄርን ቃል በማጥናት ስንዘጋጅ እና እምነታችንን ጥልቅ ስናደርግ እኛም ፈተናዎችን ለመቋቋም የእግዚያብሄርን ሃይል ማግኘት እና መጠቀም እንችላለን።

የተለመደውን የቤተመቅደስ ተሳትፎ የማይቻል ባደረገው በዚህ መሰባሰብ ውስን በሆነበት ወቅት የቤተመቅደስን ቃል ኪዳኖች ስንገባ እና ስንጠብቅ ወደ እኛ ስለሚመጣው የእግዚአብሔር ኃይል ማጥናቴን ለመቀጠል እና የበለጠ ለመማር በርግጥ ትኩረት ሰጥቻለሁ። በከርትላንድ ቤተመቅደስ የመወሰን ጸሎት ላይ ቃል እንደተገባው፣ በእግዚአብሔር ኃይል ታጥቀን ከቤተመቅደሱ እንወጣለን።16 የቤተመቅደስ ቃል ኪዳኖችን ለሚገቡ እና ለሚጠብቁ እግዚአብሔር ከሚሰጠው ኃይል ጋር የተያያዘ የመጠቀሚያ ማብቂያ ቀን ወይም በወረርሽኝ ጊዜ ያንን ኃይል ከማግኘት የሚገድብ ነገር የለም። የእርሱ ኃይል በሕይወታችን ውስጥ የሚቀንሰው ቃል ኪዳኖቻችንን መጠበቅ ሳንችል ስንቀር እና ያለማቋረጥ ኃይሉን ለመቀበል ብቁ ለመሆን በሚያስችለን መንገድ መኖር ካልቻልን ብቻ ነው።

ውድ ባለቤቴ እና እኔ በላኦስ እና በምያንመር ታይላንድ ውስጥ እንደ ሚስዮን መሪዎች ስናገለግል፣ በቤተመቅደስ ውስጥ ቅዱስ ቃል ኪዳኖችን ለሚፈጽሙና ለሚጠብቁ የሚመጣን የእግዚአብሔር ኃይል በቀጥታ ተመልክተናል። የቤተመቅደስ ተሳታፊዎች ድጋፍ ፈንድ በእነዚህ ሶስት ሀገሮች ውስጥ የሚገኙ ብዙ ቅዱሳን በግል መስዋእትነት እና ዝግጅት የቻሉትን ሁሉ ካደረጉ በኋላ በቤተመቅደስ እንዲሳተፉ አስችሏል። ወደሆንግ ኮንግ የሚያደርጉትን በረራ ለመያዝ በባንኮክ ወደ ሌላ አውሮፕላን ማረፊያ እንዲዛወሩ ልረዳቸው በነበረበት ወቅት ከላኦስ ከመጡ 20 ታማኝ ቅዱሳን ቡድን ጋር በታይላንድ ባንኮክ በሚገኘው አውሮፕላን ማረፊያ መገናኘቴን አስታውሳለሁ። እነዚህ አባላት በመጨረሻ ወደ ጌታ ቤት ሊጓዙ በመሆናቸው በደስታ ተሞልተው ነበር፡፡

ምስል
በላኦስ ያሉ አባሎች

እነዚህ መልካም ቅዱሳን ሲመለሱ ባገኘናቸው ጊዜ የቤተመቅደስ ቡራኬያቸውን በመቀበል እንዲሁም ከእግዚአብሄር ጋር ቃል ኪዳኖችን በመግባት ያደገው የወንጌል ብስለት እና ተጓዳኝ ሀይል በግልጽ ይታይ ነበር። እነዚህ ቅዱሳን በግልጽ ከቤተመቅደስ “[በእርሱ] ሃይል ታጥቀው” ወጥተው ነበር።17 እራሳቸው ከሚችሉት በላይ ለማድረግ የሚያስችላቸው ይህ ኃይል በሀገራቸው ውስጥ ያሉትን የቤተክርስቲያን አባልነት ችግሮች ለመቋቋም እና የጌታን መንግስት በላኦስ ሲገነቡ “በእውነት በጣም ታላቅ እና የክብር ዜና”18 እየተናገሩ እንዲሄዱ ብርታት ሰጣቸው።

በቤተመቅደስ ለመሳተፍ ባልቻልንበት ወቅት እያንዳንዳችን በሕይወታችን ውስጥ ግልጽና የማይለወጥ አቅጣጫ ለማስቀመጥ በቤተመቅደስ ውስጥ በገባናቸው ቃል ኪዳኖች ላይ ተደግፈናል? እነዚህ ቃል ኪዳኖች ከተጠበቁ፣ የወደፊቱን የተመለከተ ራዕይ እና የሚጠበቁ ነገሮችን እንዲሁም በታማኝነታችን ጌታ ቃል የገባቸውን ሁሉ ለመቀበል ብቁ ለመሆን ግልጽ ቁርጠኝነት ይሰጡናል።

እግዚያብሄር ሊሰጣችሁ የሚፈልገውን ሃይል እንድትሹ እጋብዛችኋለሁ። ይህንን ሃይል ስንሻ ሰማያዊ አባታችን ለሁላችን ባለው ፍቅር እውቀት ታላቅ ግንዛቤ እንደምንባረክ እመሰክራለሁ።

የሰማይ አባት እኔን እና እናንተን ስለሚወደን ውድ ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ አዳኛችን እና ቤዛችን እንዲሆን እንደላከ እመሰክራለሁ። ሃይል ሁሉ ስላለው ስለኢየሱስ ክርስቶስ እመሰክራለሁ፤19 ይህንንም የማደርገው በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ነው፣ አሜን።