አጠቃላይ ጉባኤ
በመላእክት አምናለሁ
የጥቅምት 2020 (እ.አ.አ) አጠቃላይ ጉባኤ


በመላእክት አምናለሁ

ስለሚያጋጥሟችሁ ፈተናዎች ጌታ ያውቃል። ያውቃችኋል፤ ይወዳችኋል፤ እናም እርሱ ሊረዳችሁ መላእክትን እንደሚልክ ቃል እገባላችኋለሁ።

ወንድሞች እና እህቶች፣ በመላእክት አምናለሁ፣ እና ከእነርሱ ጋር ያለኝን ተሞክሮ ላካፍላችሁ እወዳለሁ። ያን በማድረግ፣ በህይወታችን ውስጥ የመላእክትን አስፈላጊነት እንድንገነዘብ ተስፋ እና ጸሎቴ ነው።

ባለፈው አጠቃላይ ጉባኤ ሽማግሌ ጀፍሪ አር. ህላንድ የተናገሯቸው ቃላት እነኚህ ናቸው፥ “በእግዚአብሔር እጅ መሳሪያ ስለሆኑት ስናወራ፣ ሁሉም መላእክቶች ከመጋረጃ በሌላ በኩል ያሉት ብቻ እንዳልሆኑ እንድናስታውስ ተደርጓል። ጠቂቶቹ እዚህም፣ አሁን፣ እናም በየቀኑ ያሉ አብረን የምንራመደው እና አብረን የምናወራው ናቸው። ጥቂቶቹ በራሳችን ሰፈር ይኖራሉ። … በእርግጥ፣ ሰማይ ከመቼውም በላይ የቀረበ መስሎ የእግዚአብሔር ፍቅር በጣም መልካም እና በጣም ንጹህ በሆኑ ሰዎች ደግነት እና ታታሪነት ሲገለጽ ወደ አእምሮ የሚመጣው ብቸኛ ቃል መላእካዊ ነው” (“የመላዕክት አገልግሎት፣” ሊያሆና፣ ህዳር 2008 (እ.አ.አ)፣ 30)።

በዚህኛው መጋረጃ በኩል ስላሉት መላእክት ነው እኔ መናገር የምፈልገው። አብረውን በህይወታችን በየቀኑ የሚጓዙት መላእክት ሃያል እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ፍቅር ማስታወሻዎች ናቸው።

መጀመሪያ የምጠቅሳቸው መላእክቶች ወጣት ሳለሁ ወንጌልን ያስተማሩኝን ሁለት እህት ወንጌል ሰባኪዎች ናቸው፣ እህት ቪልማ ሞሊና እና እህት ኢቮኔት ሪቪቲ። ታናሽ እህቴ እና እኔ እነዚህን ሁለት መላእክት ወዳገኘንበት የቤተክርስቲያን እንቅስቃሴ ተጋብዘን ነበር። ያ ቀላል እንቅስቃሴ ምን ያህል ህይወቴን እንደሚቀይረው በፍጹም አልገመትኩም ነበር።

በዚያ ጊዜ ወላጆቼ እና ወንደሞቼና እህቶቼ ስለ ቤተክርስቲያኗ የበለጥ ለመማር ፍላጎት አልነበራቸውም። ወንጌል ሰባኪዎች እቤታችን እንዲገኙ እንኳ አይፈልጉም ነበር፣ ለዚያም የሚስዮን ትምህርቶችን በቤተክርስቲያን ውስጥ ወሰድኩኝ። ያ በቤተክርስቲያን አዳራሽ የነበረው ትንሽ ክፍል የእኔ “ቅዱስ ጥሻ” ሆነ።

ምስል
ወጣቱ ሽማግሌ ጎዶይ ከእህታቸው ጋር

እነዚህ መላእክት ወንጌልን ካስተዋወቁኝ ከአንድ ወር በኋላ፣ ተጠመቅኩኝ። 16 አመቴ ነበር። እንዳለመታደል ሆኖ፣ የዚያ ቅዱስ ክስተት ፎቶ የለኝም፣ ነገር ግን እኔ እና እህቴ በዚያ ዝግጅት በተካፈልንበት ወቅት የተነሳነው ፎቶ አለኝ። በዚህ ፎቶ ላይ ማን ማን እንደሆነ ማብራራት ያስፈልገኝ ይሆናል። እረጅሙ በስተቀኝ ያለሁት እኔ ነኝ።

መገመት እንደምትችሉት፣ የአኗኗር ዘይቤው ለተቀየረበት እና ቤተሰቦቹ ተመሳሳይ መንገድ ሳይከተሉ ለነበረበት ወጣት በቤተክርስቲያን ውስጥ ንቁ ተሳታፊ መሆን ከባድ ነበር።

ወደ አዲሱ ህይወቴ፣ አዲሱ ባህል፣ እና አዲስ ጓደኞች ለመስተካከል ስሞክር፣ ከቦታዬ ውጪ እንደሆንኩ ተሰምቶኝ ነበር። ብዙ ጊዜ ብቸኝነት እና ብርታት ማጣት ይሰማኝ ነበር። ቤተክርስቲያኗ እውነት እንደሆነ አውቅ ነበር፣ ነገር ግን የዚያ አካል እንደሆንኩኝ እንዲሰማኝ ለማድረግ ከብዶኝ ነበር። በአዲሱ ሃይማኖቴ አካል ለመሆን ስሞክር ምቹ እና እርግጠኛ አለመሆን እንዳለ ሆኖ፣ አዲስ ጓደኞች ለማግኘት ይጠቅመኛል ብዬ ባሰብኩት፣ የሶስት ቀን የወጣቶች ጉባኤ ላይ ለመካፈል ብርታትን አገኘሁ። በዚያ ነው ሞኒካ ብራንዶ ከምትባለው ሌላኛዋ አዳኝ መላእክ ጋር የተዋወቅኩት።

ምስል
እህት ጎዶይ

ከሌላ የብራዚል ክፍል ስለመጣች፣ ለአካባቢው አዲስ ነበረች። በቶሎ ቀልቤን ሳበች፣ እድለኛ ሆኜ፣ እኔን እንደ ጓደኛዋ ተቀበለች። ከውጫዊው ይበልጥ ከውስጣዊ እንደተመለከተችኝ እገምታለሁ።

ጓደኛዬ በመሆኗ ምክንያት፣ ከእርሷ ጓደኞች ጋር ተዋወቅቅኩኝ፣ እነርሱም ጓደኞቼ ሆነው በቀጣይ ብዙ የወጣቶች ዝግጅት ተደሰትን። ወደዚህ አዲስ ህይወት ለመቀላቀል እነዚያ ዝግጅቶች በጣም ወሳኝ ነበሩ።

ምስል
የሽማግሌ ጎዶይ ጓደኛ

እነዚህ መልካም ጓደኞች ብዙ ለውጥ አመጡ፣ ነገር ግን ወንጌል በቤት ውስጥ ከሚድግፉ ቤተሰቦች ጋር አለመኖሩ የእኔን ቀጣይ መለወጥ አደጋ ላይ ጥሎት ነበር። በቤተክርስትያን ውስጥ ያለኝ የወንጌል ግንኙነቶች ለአዳጊው መለወጤ ይበልጥ አስፈላጊ ሆኑ። ከዛም፣ ሁለት ተጨማሪ መላእክት ለመርዳት በጌታ ተላኩ።

አንደኛዋ ለዳ ቬቶሪ የማለዳ ሴሚናሪ መምህሬ ነበረች። በተቀባይ ፍቅሯ እና መንፈስ በሚያነቃቁ ክፍሎቿ፣ በጊዜዬ በጣም አስፈላጊ የነበሩትን የየቀኑን “የእግዚአብሔርን መልካም ቃል” (ሞዛያ 6፥4) መጠን ሰጠችኝ። ይህም እንድቀጥል የመንፈሳዊ ጥንካሬን እንዳገኝ ረዳኝ።

ሌላው ወደ እኔ የተላከው መላእክ የወጣት ወንዶች ፕሬዝዳንት፣ ማርኮ አንቶኒዮ ፉስኮ ነበር። እርሱ የእኔ ታላቅ የቤት ለቤት ትምህርት አጣማሪ እንዲሆን ተመድቦም ነበር። አናሳ ተሞክሮ እና የተለየ እይታ ቢኖረኝም እንኳ፣ እርሱ በክህነት ስብሰባዎች እና የቤት ለቤት ትምህርቶች ላይ እንዳስተምር ሃላፊነቶችን ሰጠኝ። እርሱ እንድተገብር እና እንድማር እናም የወንጌል ተመልካች ብቻ እንዳልሆን እድል ሰጠኝ። ራሴን ከማምነው በላይ፣ እርሱ አመነኝ።

ለእነዚህ እና ሌሎችም በዚህ ቀዳሚ አመታት ላገኘኋቸው መላእክት ሁሉ ምስጋና ይግባቸውና፣ የእውነታውን መንፈሳዊ ምስክር በማግኘቴ በቃል ኪዳኑ መንገድ ለመቆየት በቂ ጥንካሬን አገኘሁ።

እናም በነገራችሁ ላይ፣ ያቺ ወጣት መላእክ፣ ሞኒካ? ሁለታችንም በወንጌል ሰባኪነት ካገለገልን በኋላ፣ ባለቤቴ ሆነች።

መልካም ጓደኞች፣ የቤተክርስቲያን ሃላፊነቶች፣ እና በመልካም የእግዚአብሔር ቃል መታነጽ የዚያ ሂደት አካል የሆኑት በአጋጣሚ አይመስለኝም። ፕሬዘደንት ጎርደን ቢ. ሒንክሊ በጥበብ እንዳስተማሩት፥ “ይህችን ቤተክርስቲያን ለመቀላቀል የሚደርግ የለውጥ ክስተት ቀላል አይደለም። የበፊት እስሮችን መቁረጥ ማለት ነው። ጓደኞችን መተው ማለት ነው። የተወደዱ እምነቶችን ወደ ጎን ማደርግ ማለት ይሆናል። ልምዶችን መቀየር እና ፍላጎት መገደብን ሊጠይቅ ይችላል። በአብዛኛው ሁኔታዎች ብቸኝነት እና የማይታወቅ ፍራቻ ጭምር ማለት ይሆናል። በዚህ ከባድ የተለዋጭ ህይወት ወቅት መንከባከብ እና ማጠንክር ሊኖር ግድ ነው” [“መልእክተኞች መኖር አለባቸው፣” ኤንዛይን፣ ጥቅምት 1987 (እ.አ.አ)]።

በኋላም እንዲህ ብለው ጨመሩ፣ “እያንዳንዱም ሶስት ነገሮች ያስፈልጓቸዋል፥ ጓደኛ፣ ሀላፊነት፣ እና ‘በእግዚአብሔር በመልካም ቃላት’ እንክብካቤ” (“ተለዋጮች እና ወጣት ወንዶች፣” ኤንዛይን፣ ግንቦት 1997 (እ.አ.አ)፣ 47).

ይህን ተሞክሮ ከእናንተ ጋር የማካፍለው ለምንድን ነው?

መጀመሪያ፣ በአሁን ጊዜ በተመሳሳይ ሂደት ውስጥ እያለፉ ላሉት መልእክት ለማስተላለፍ ነው። ምናልባት አዲስ አባል፣ ወይም ለብዙ ጊዜ በሌላ ቦታዎች ቆይታችሁ ወደ ቤተክርስቲያን የተመለሳችሁ፣ ወይም ለመቀላቀል እየታገላችሁ ያላችሁ ልትሆኑ ትችላላችሁ። እባካችሁ፣ እባካችሁ፣ የዚህ ትልቅ ቤተሰብ አካል ለመሆን ባላችሁ ጥረት ተስፋ አትቁረጡ። ይህች የኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ ቤተክርስቲያን ናት።

ወደ ደስታችሁ እና ደህንነታችሁ ሲመጣ፣ በመሞከር መቀጠል ሁሌም አዋጭ ነው። የህይወት አኗኗርን እና ባህልን ለማስተካከል መጣር አዋጭ ነው። ስለሚያጋጥሟችሁ ፈተናዎች ጌታ ያውቃል። ያውቃችኋል፤ ይወዳችኋል፤ እናም እርሱ ሊረዳችሁ መላእክትን እንደሚልክ ቃል እገባላችኋለሁ።

አዳኝ በእራሱ ቃላት እንዳለው፣ “በፊታችሁ እሄዳለሁ። በቀኛችሁ እና በግራችሁ እሆናለሁ፣ እናም መንፈሴም በልቦቻችሁ ውስጥ ይገኛል፣ እናም መላእክቶቼም እንዲያዝሏችሁ ይከብቧችኋል” (ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች 84፥88)።

እነዚህን ተሞክሮዎች የምካፈልበት ሁለተኛው አላማ፣ ለሁሉም የቤተክርስቲያን አባልት መልእክት ለማስተላለፍ ነው—ለሁላችንም። ለአዲስ አባላት፣ ለሚመለሱ ጓደኞች፣ እና የተለየ አኗኗር ላላቸው በአንዴ ለመቀላቀል ቀላል እንዳልሆነ ማስታወስ አለብን። የሚያጋጥማቸውን ፈተናዎች ጌታ ያውቃል፣ እና ለመርዳት ፈቃደኛ የሆኑ መላእክትን እየፈለገ ነው። ጌታ ሁሌም በሌሎች ህይወት ውስጥ መላእክት ለመሆን ፈቃደኛ የሚሆኑትን በመፈለግ ላይ ነው።

ወንድሞች እና እህቶች፣ በጌታ እጆች መሳሪያዎች ለመሆን ትፈልጋላችሁን? ከእነዚህ መላእከት ውስጥ አንዱ ለመሆን ትፈልጋላችሁን? ከዚህኛው መጋረጃ በኩል፣ ለሚያስብለት ሰው ከእግዚአብሔር የተላከ፣ ልኡክ ለመሆንስ? ታስፈልጉታላችሁ። እነርሱም ይፈልጓችኋል።

በእርግጥ፣ ሁሌም በሚስኦናውያኖቻችን ልንደግ እንችላለን። እነርሱ ሁሌም እዚያ አሉ፣ ለዚህ መላእክታዊ ስራ ቀዳሚ ተመዝጋቢዎች በመሆንም። ነገር ገን በቂ አይደሉም።

በዙሪያቹ አትኩራችሁ ብትመለከቱ፣ የመላእክት እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ብዙ ታገኛላችሁ። እነዚህ ሰዎች ነጭ ሸሚዝ፣ ሙሉ ቀሚስ፣ ወይም የእሁድ አለባበስ አይነት ለብሰው ላይሆን ይችላል። ከቤተክርስቲያኗ አዳራሽ ጀርባ ብቻቸውን ተቀምጠው፣ አንዳንዴ የማይታዩ እየመሰላቸው ይሆናል። ምናልባት የጸጉር አሰራራቸው ትንሽ ወጣ ያለ ወይም አነጋገራቸው የተለየ ሊሆን ይችላል፣ ነገር ግን እዛ አሉ፣ እናም እየሞከሩ ናቸው።

ጥቂቶቹ ምናልባት እንዲህ እያሉ እያሰቡ ይሆናል፣ “ተመልሼ መምጣቴን ልቀጥል? ። በመሞከር ልቀጥል ይሆን?” ሌሎች አንድ ቀን እንደተቀበሉን እና እንደሚወዱን ይሰማን ይሆናል ብለው እያሰቡ ይሆናል። መላዕክት ያስፈልጋሉ፣ ወዲያውንም፤ የሚመቻቸውን ቦታ ለመተው ፈቃደኛ የሆኑ መላዕክትም ያስፈልጋሉ፤ “በጣም መልካም እና በጣም ንጹህ [የሆኑ ሰዎች] ከመሆናቸው የተነሳ [እነርሱን ለመግለጽ] ወደ አእምሮ የሚመጣው ቃል መላእክታዊ ብቻ ነው” (ጄፍሪ አር. ሆላንድ፣ “የመላእክት አገልግሎት፣” 30)።

ወንድሞች እና እህቶች፣ በመላእክት አምናለሁ። በዚህ በኋላኛው ቀን የተዘጋጀን ትልቅ የመላእክት ሰራዊት፣ እንደ ተወዳጁ ፈጣሪያችን እጆች ቅጥያ ሆነን ሌሎችን እንድናገለግል ዘንድ፣ ዛሬ ሁላችንም እዚህ አለን። ለማገልገል ፍላጎት ካለን፣ አገልጋይ መላእክት ለመሆን እድሎችን ጌታ እንደሚሰጠን ቃል እገባለሁ። ማን መላእክታዊ እርዳታ እንደሚያስፈልገው እርሱ ያውቃል፣ እናም እርሱ በመንገዳችን ያስቀምጣቸዋል። ጌታ መላእክታዊ እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን በየቀኑ በመንገዳችን ያስቀምጣቸዋል።

በህይወቴ ሁሉ በመንገዴ ጌታ ስላስቀመጣቸው መላእክት እጅግ አመስጋኝ ነኝ። አስፈላጊዎች ነበሩ። እንድንለወጥ ስለሚረዳን እና እንድንሻሻል እድሉን ለሚሰጠን ወንጌሉም አመስጋኝ ነኝ።

ይሄ የፍቅር ወንጌል ነው፣ የአገልግሎት ወንጌል። ስለዚህ የምመሰክረው በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ነው፣ አሜን።