ቅዱሳት መጻህፍት
ሙሴ ፬


ምዕራፍ ፬

[ሰኔ–ጥቅምት ፲፰፻፴ (እ.አ.አ.)]

እንዴት ሰይጣን ዲያብሎስ እንደሆነ—ሰይጣን ሔዋንን ፈተነ—አዳምና ሔዋን ወደቁ፣ እናም ሞት ወደ ምድር መጣ።

እና እኔ እግዚአብሔር አምላክም ለሙሴ እንዲህ አልኩት፤ በአንድያ ልጄ ስም ያዘዝከው ያ ሰይጣንም ከመጀመሪያው ጊዜ የነበረ ነው፣ እና በፊቴም እንዲህ በማለት መጣ፣ እነሆ፣ አለሁ፣ እኔን ላከኝ፣ ልጅህም እሆናለሁኝ፣ እና አንድም ነፍስ እንዳይጠፋ፣ የሰውን ዘር አድናለሁ፣ እና በእርግጥም ይህን አደርጋለሁ፤ ስለዚህ ክብርህን ስጠኝ።

ነገር ግን እነሆ፣ ውዱና ከመጀመሪያ ጊዜ ጀምሮ የተመረጠው ተወዳጁ ልጄም እንዲህ አለኝ—አባት ሆይ፣ ፈቃድህ ይፈጸም፣ እናም ክብርም ለዘለአለም ያንተ ይሁን።

ስለዚህ ሰይጣን ስለዐመፀብኝና እኔ እግዚአብሔር አምላክ የሰጠሁትን የሰው ነጻ ምርጫ ለማጥፋት ስለፈለገ፣ እና ደግሞም የራሴን ሀይል ለእርሱ እንድሰጠው ሰለፈለገ ዘንድ፣ በአንድያ ልጄ ሃይል እንዲጣል አደረግሁኝ፤

እና እርሱም ሰይጣን፣ አዎን፣ እንዲሁም ድምጼን የማያደምጡትን ሁሉ የሚያታልለው እና ሰዎችን እንዳያዩ አድርጎ በፈቃዱም እንደ እስርኞች የሚመራቸው፣ እንዲሁም የሀሰት አባት ዲያብሎስ ሆነ።

እና እኔ እግዚአብሔር አምላክ ከፈጠርኳቸው ከምድር አውሬዎች ሁሉ ይልቅ እባብም ተንኮለኛ ነበር።

እና (ብዙዎችን ወደ ራሱ ስለወሰደ) ሰይጣን በእባቡ ልብ ውስጥ ይህን አደረገ፣ እና እርሱም ሔዋንን ለማሳሰት ፈለገ። የእግዚአብሔርንም ሀሳብ አያውቅምና፣ ስለዚህ ምድርን ለማጥፋት ፈለገ።

እና ሴቲቱንም እንዲህ አላት፥ አዎን፣ እግዚአብሔር—ከገነት ዛፍ ሁሉ እንዳትበሉ ብሏል? (እና በእባቡ አፍ ነበር የተናገረው።)

እና ሴቲቱም እባቡን እንዲህ አለችው፥ በገነት ካለው ከዛፍ ፍሬ እንበላለን፤

ነገር ግን በገነት መካከል ከምትመለከቷቸው ከዛፉ ፍሬ፣ እግዚአብሔር እንዳትሞቱ ከእርሱ አትብሉ አትንኩትም ብሏል።

እና እባብም ለሴቲቱ አላት፥ በእርግጥም አትሞቱም፤

፲፩ ከእርሱም በበላችሁ ቀን ዓይኖቻችሁ እንዲከፈቱ እንደ እግዚአብሔርም መልካምንና ክፉን የምታውቁ እንድትሆኑ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው እንጂ።

፲፪ እና ሴቲቱም ዛፉን ለመብላት ያማረ እንደ ሆነ፣ ለዓይንም እንደሚያስጎመጅ፣ ለጥበብም መልካም እንደ ሆነ አየች፤ ከፍሬውም ወሰደችና በላች፤ ለባልዋም ደግሞ ሰጠችው እርሱም ከእርስዋ ጋር በላ።

፲፫ እና የሁለቱም ዐይኖች ተከፈቱ፣ እና ራቁታቸውን መሆናቸውንም አወቁ። እናም የበለስ ቅጠሎች ሰፍተው ለእነርሱ ለራሳቸው ግልድም አደረጉ።

፲፬ እነርሱም ቀኑ በመሸ ጊዜ የእግዚአብሔር አምላክን ድምፅ ከገነት ውስጥ ሲመላለስ ሰሙ፤ አዳምና ሚስቱም ከእግዚአብሔር ከአምላክ ፊት በገነት ዛፎች መካከል ተሸሸጉ።

፲፭ እና እኔ እግዚአብሔር አምላክም አዳምን ጠርቼ፣ የት ነህ? አልኩት።

፲፮ እርሱም አለ፥ ድምጽህን በገነት ሰማሁ፤ ራቁቴን ስለሆንሁ ፈራሁ፤ ተሸሸግሁም።

፲፯ እና እኔ እግዚአብሔር አምላክም ለአዳም እንዲህ አልኩት፥ ራቁትህን እንደሆንህ ማን ነገረህ? ከእርሱ እንዳትበላ፣ ከበላህም መሞት አለብህ ብዬ ካዘዝሁህ ዛፍ በላህ?

፲፰ አዳምም አለ፥ የሰጠኸኝ እና ከእኔ ጋር እንድትሆን ያዘዝከኝ ሴት፣ እርስዋ የዛፉን ፍሬ ሰጠችኝና በላሁ።

፲፱ እና እኔ እግዚአብሔር አምላክም ሴቲቱን፥ ይህ ያደረግሽው ነገር ምንድን ነው? አልኳት። እና ሴቲቱም አለች፥ እባቡ አሳተኝና በላሁ።

እና እኔ እግዚአብሔር አምላክም እባቡን እንዲህ አልሁት፤ ይህን ስላደረግህ ከእንስሳት ከምድር አራዊትም ሁሉ ተለይተህ አንተ የተረገምህ ትሆናለህ፤ በሆድህም ትሄዳለህ፣ አፈርንም በሕይወትህ ዘመን ሁሉ ትበላለህ።

፳፩ በአንተና በሴቲቱ መካከል፣ በዘርህና በዘርዋም መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ፤ እና እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፣ አንተም ሽኰናውን ትቀጠቅጣለህ።

፳፪ ለሴቲቱም እኔ እግዚአብሔር አምላክም እንዲህ አልኳት፥ በፀነስሽ ጊዜ ጭንቅሽን እጅግ አበዛለሁ። በጭንቅ ትወልጃለሽ፤ እና ፈቃድሽም ወደ ባልሽ ይሆናል፣ እርሱም ገዥሽ ይሆናል።

፳፫ ለአዳምም እኔ እግዚአብሔር አምላክ አልኩት፣ የሚስትህን ቃል ሰምተሀል፣ ከእርሱ አትብላ ብዬ ያዘዝኩህን ዛፍ በልተሀልና፣ ምድር ከአንተ የተነሣ የተረገመች ትሁን፤ በሕይወት ዘመንህም ሁሉ በድካም ከእርስዋ ትበላለህ።

፳፬ እሾህንና አሜከላን ታበቅልብሃለች፤ የምድርንም ቡቃያ ትበላለህ።

፳፭ ከምድር ወደ ወጣህበት መሬት እስክትመለስ ድረስ በፊትህ ወዝ እንጀራን ትበላለህ—በእርግጥም ትሞታለህና—ከዚህም ስለመጣህ፥ ዐፈር ነህና ወደ ዐፈር ትመለሳለህና።

፳፮ አዳምም ለሚስቱ ሔዋን ብሎ ስም አወጣ፣ የሕያዋን ሁሉ እናት ናትና፤ እንደዚህም ነው እኔ እግዚአብሔር አምላክ ከብዙዎቹ ሴቶች ሁሉ የመጀመሪያዋን የጠራኋት።

፳፯ እኔ እግዚአብሔር አምላክም ለአዳምና ለሚስቱ የቁርበትን ልብስ አደረግሁላቸው፣ እና አለበስኳቸው

፳፰ እና እኔ እግዚአብሔር አምላክም ለአንድያ ልጄ እንዲህ አልኩት፥ እነሆ ሰውም መልካምንና ክፉን ለማወቅ ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ፤ አሁንም እጁን እንዳይዘረጋ፣ ደግሞም ከሕይወት ዛፍ ወስዶ እንዳይበላ፣ ለዘላለምም ሕያው ሆኖ እንዳይኖር፤

፳፱ ስለዚህ የተገኘባትን መሬት ያርስ ዘንድእኔ እግዚአብሔር አምላክ ሰውን ከዔድን ገነት አስወጣዋለሁ፤

እኔ እግዚአብሔር አምላክ ህያው እስከሆንኩኝ ድረስ፣ ቃላቶቼ ውጤት የሌላቸው መሆን አይገባቸውም፣ ከአፌ እንደወጡ መከናወን አለባቸውና።

፴፩ ለዚህ ሰውን አስወጣሁት እና ወደ ሕይወት ዛፍ የሚወስደውንም መንገድ ለመጠበቅ ኪሩቤልንና የምትገለባበጥ የነበልባል ሰይፍን በዔድን ገነት ምሥራቅ አስቀመጥኩኝ።

፴፪ (እነዚህ ለአገልጋዬ ሙሴ የተናገርኳቸው ቃላት ነበሩ፣ እና እውነተኛ እንዲሁም እንደፈቃዴ ናቸው፤ እና ለእናንተም ነግሬአቸዋለሁ። ከሚያምኑት በስተቀር፣ እስከማዝህ ድረስ ከሚያምኑት ሌላ ለማንም ሰው አታሳይ። አሜን)