ቅዱሳት መጻህፍት
ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች ፸፮


ክፍል ፸፮

በየካቲት ፲፮፣ ፲፰፻፴፪ (እ.አ.አ.) በሀይረም ኦሀዮ ውስጥ ለነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ እና ለስድኒ ሪግደን የተሰጠ ራዕይ። ከዚህ ራዕይ ጽሑፉ አስቀድሞ፣ የጆሴፍ ስሚዝ ታሪክ እንደሚገልጸው፥ “ከአምኸርስት ጉባኤ እንደተመለስኩ፣ ቅዱሳን መጻህፍትን መተርጎምን ቀጠልኩ። ከተቀበልኳቸው ከተለያዩ ራዕዮች፣ የሰውን ልጅ ደህንነት የሚመለከቱ ብዙ አስፈላጊ ነጥቦች ከመፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደተወሰዱ፣ ወይም ከመከማቸቱ በፊት እንደጠፉ ግልፅ ነበር። እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ በስጋ ባከናወነው በኩል ደመወዙን የሚሰጥ ከሆነ፣ ለቅዱሳን የዘለአለም ቤት እንዲሆን የተወሰነበት ሰማይ ከአንድ በላይ የሆኑ መንግስታትን እንደሚያጠቃልል ቀሪው እውነት በራሱ የሚያስረዳ ነው። በዚህም መሰረት፣… የቅዱስ ዮሐንስን ወንጌል ስንተረጉም፣ እኔ እና ሽማግሌ ሪግደን የሚቀጥለውን ራዕይ ተመለከትን።” ራዕዩ በተሰጠበት ግዜ፣ ነቢዩ ዮሐንስ ፭፥፳፱ን እየተረጎመ ነበር።

፩–፬፣ ጌታ እግዚአብሔር ነው፤ ፭–፲፣ የመንግስት ሚስጥራት ለታማኞቹ ሁሉ ይገለጣሉ፤ ፲፩–፲፯፣ ሁሉም በጻድቃንም ሆነ በኃጢአተኛ ትንሳኤ ከሞት ይነሳሉ፤ ፲፰–፳፬፣ የብዙ አለማት ኗሪዎች በኢየሱስ ክርስቶስ የኃጢአት ክፍያ አማካይነት የእግዚአብሔር ወንዶች እና ሴቶች ልጆች ናቸው፤ ፳፭–፳፱፣ የእግዚአብሔር መልአክ ተጣለ እናም ዲያብሎስም ሆነ፤ ፴–፵፱፣ የጥፋት ልጆችም በዘለአለም እርግማን ይሰቃያሉ፤ ሌሎች ሁሉም የተወሰነ የደህንነትን ደረጃ ያገኛሉ፤ ፶–፸፣ በሰለስቲያል መንግስት ውስጥ ዘለአለማዊ ክብር ያላቸው ፍጡራን ክብር እና ደመወዝ ተገልጿል፤ ፸፩–፹፣ የተረስትሪያልን መንግስት የሚወርሱትም ተገልጸዋል፤ ፹፩–፻፲፫፣ በቲለስቲያል፣ ተረስትሪያል፣ እና በሰለስቲያል ክብሮች ውስጥ ያሉት ሁኔታቸው ተገልጿዋል፤ ፻፲፬–፻፲፱፣ ታማኝ የሆኑት የእግዚአብሔርን መንግስት ሚስጥራት በመንፈስ ቅዱስ ሀይል አማካይነት ማየት እና መረዳት ይችላሉ።

አድምጡ፣ እናንት ሰማያት ሆይ፣ ምድር ሆይ ጆሮሽን ስጪ፣ እናም ነዋሪዎችዋም ተደሰቱ፣ ጌታ እግዚአብሔር ነውና፣ እናም ከእርሱም በቀር ማንም አዳኝ የለምና።

ጥበቡ ታላቅ ነው፣ መንገዶቹም ድንቅ ናቸው፣ እናም የአሰራሩንም መጠን ማንም ሊያገኘው አይቻለውም።

አላማዎቹ አይወድቁም፣ እጁንም ይከለክል ዘንድ የሚቻለው ማንም የለም።

ከዘለአለም እስከ ዘለአለም አንድ ነው፣ እና አመታቱም ከቶ አያልቁም

ጌታ እንዲህ ይላል—እኔ ጌታ ለሚፈሩኝ መሀሪ እና ይቅር ባይ ነኝ፣ እና በፅድቅ እና በእውነት እስከ መጨረሻው የሚያገለግሉኝንም በማክበር እደሰታለሁ።

ዋጋቸውም ታላቅ እና ክብራቸውም ዘለአለማዊ ይሆናል።

እና ለእነርሱም ሁሉንም ሚስጥራት፣ አዎን፣ ከጥንት ጀምሮ የተሰወሩትን የመንግስቴን ሚስጥራት ሁሉ እገልጽላቸዋለሁ፣ እና በሚመጡት ዘመናትም መንግስቴን የተመለከቱትን ነገሮች ሁሉ በጎ ፈቃዴን ያውቁ ዘንድ አደርጋቸዋለሁ።

አዎን፣ የዘለአለምን ድንቆችንም ያውቃሉ፣ የሚመጡትን፣ እንዲሁም የብዙ ትውልዶች ነገሮችንም አሳያቸዋለሁ።

እናም ጥበባቸውም ታላቅ ይሆናል፣ እናም መረዳታቸውም እስከ ሰማያት የዘለቀ ይሆናል፤ እናም የጥበበኞችም ጥበብ ትጠፋለችና፣ እናም የአስተዋዮችም ማስተዋል ትሰወራለች።

በመንፈሴም አብራላቸዋለሁና፣ እናም የፈቃዴን ሚስጥራት—አዎን እንዲሁም ዓይን ያላየውን ጆሮም ያልሰማውን፣ በሰውም ልብ ያልታሰቡትንም ነገሮች፣ በሀይሌ አሳውቃቸዋለሁ።

፲፩ እኛ፣ ጆሴፍ ስሚዝ ዳግማዊ እና ስድኒ ሪግደን፣ በጌታችን አንድ ሺ ስምንት መቶ ሰላሳ ሁለት አመት በየካቲት አስራ ስድስት ቀን በመንፈስ ሆነን—

፲፪ በመንፈስ ሀይልም፣ የእግዚአብሔርን ነገሮች ለማየት እና ለመረዳት፣ አይኖቻችን ተከፈቱ እናም እውቀቶቻችንም ብሩህ ሆኑ—

፲፫ እንዲሁም አለም ከመፈጠሯ በፊት ከመጀመሪያ ጀምሮ የነበሩት ነገሮችም፣ በአብ እቅፍ ውስጥ በነበረው በአንድያ ልጁ በኩል፣ ከመጀመሪያው ጀምሮ፣ በአብ ተቀድሰው የነበሩትም፤

፲፬ ስለ እርሱም ምስክርን እንሰጣለን፤ እናም የምንመሰክረውም፣ ልጅ ስለሆነው፣ ያየነው እናም በሰማያዊ ራዕይ ስላነጋገርነው ስለኢየሱስ ክርስቶስ ሙሉ ወንጌል ነው።

፲፭ ጌታ የሰጠንን የትርጉም ስራ እየሰራን እያለ፣ እንደሚከተለው ወደ ተሰጠን ወደ ዮሐንስ መፅሐፍ በአምስተኛው ምዕራፍ ቁጥር ሀያ ዘጠኝ ላይ ደረስን—

፲፮ ስለ ሙታን ትንሳኤ፣ እነዚያ የሰው ልጅ ድምፅ ስለ ሚሰሙት በመናገር፥

፲፯ መልካምም ያደረጉ ጻድቃን ትንሣኤ፣ ክፉትንም ያደረጉ በኃጥአን ትንሣኤ ይነሳሉ።

፲፰ አሁን ይህም እንድንደነቅ አደረገን፣ ምክንያቱም በመንፈስ ለእኛ ተሰጥቶን ነበርና።

፲፱ እናም በእነዚህ ነገሮች ላይ እያሰላሰልን ሳለን፣ ጌታ የመረዳት አይኖቻችንን ነካ እናም ተከፈቱ፣ እናም የጌታ ክብርም በዙሪያችን በራ።

እናም የወልድን ክብርበአብ ቀኝ በኩል ተመለከትን እናም እርሱን በሙላት ተቀበልን፤

፳፩ እናም ቅዱሳን መላእክት፣ እና በዙፋኑ ፊት ተቀድሰው የነበሩትን፣ እግዚአብሔርን ሲያመልኩት እና እርሱንም ለዘለአለም የሚያመልከውን በጉን አየን።

፳፪ እናም አሁን፣ ስለ እርሱ ከተሰጡት ብዙ ምስክሮች በኋላ፣ ይህም በመጨረሻ ስለ እርሱ የምንሰጠው ምስክርነት፥ እርሱ ህያው መሆኑን ነው!

፳፫ በእግዚአብሔር ቀኝ አይተነዋልና፤ እናም እርሱ የአብ አንድያ ልጅ እንደሆነም ሲመሰክርም ድምፅ ሰምተናል—

፳፬ አለማትም በእርሱ፣ እናም በእርሱም አማካይነት፣ እናም ከእርሱም ዘንድ ናቸው እናም ተፈጥረዋል፣ እናም ነዋሪዎችዋም የእግዚአብሔር ወንዶችና ሴቶች ልጆች ናቸው።

፳፭ እናም ይህንም አየን፣ እንመሰክራለንም፣ በእግዚአብሔር ፊት ስልጣን የነበረው፣ አብ ይወደው የነበረው እና በአብም እቅፍ የነበረው በአንድያ ልጁ ያመጸው፣ የእግዚአብሔር መልአክ ከእግዚአብሔር እና ከወልድ ፊት ተጥሎ ነበር፣

፳፮ እና የጥፋት ልጅ ተብሎም ተጠራ፣ ሰማያትም ስለእርሱ አነቡ—እርሱም ሉሲፈር፣ የንጋት ልጅ ነበር።

፳፯ እናም የንጋት ልጅ የሆነው እርሱም የወደቀ ነው፣ ወድቋልም፣ ይህንንም ተመለከትን፣ እናም አስተዋልን!

፳፰ እናም በመንፈስ እያለን፣ ጌታ ራዕይን እንድንፅፍ አዘዘን፤ ሰይጣንን፣ እንዲሁም በእግዚአብሔር ላይ ያመጸውን፣ እና የእግዚአብሔርንና የእርሱን ክርስቶስ መንግስት ለመውሰድ የሻውን የቀደመውን እባብ ዲያብሎስ አይተነዋልና—

፳፱ እነሆ፣ ከእግዚአብሔር ቅዱሳን ጋርም ተዋጋ፣ እናም በዙሪያቸውም ከበባቸው።

እናም በራዕይም የተዋጋቸውን እና ያሸነፋቸውን ስቃይ ተመለከትን፣ እንደህም ሲል የጌታ ድምፅ ወደ እኛ መጣ፥

፴፩ ጌታም ሀይሌን ስለሚያውቁት ሁሉ፣ እናም በዚህም ተካፋይ ስለሆኑት፣ እናም በዲያብሎስም ሀይል አማካይነት ራሳቸውን እንዲሸነፉ እውነትንም እንዲክዱና ሀይሌም እንዲረክስ የፈቀዱትን በተመለከተ እንዲህ ይላል—

፴፪ ባይወለዱ ይሻላቸው ብዬ ያልኳቸው፣ የጥፋት ልጆች እነርሱ ናቸው፤

፴፫ ከዲያብሎስ እና ከመላእክቱ ጋር ለዘለአለም በእግዚአብሔር ቁጣ ለመሰቃየት የተረገሙ የቁጣ እቃዎች ናቸውና፤

፴፬ እነርሱን በተመለከተ በዚህም አለም ይሁን በሚመጣው አለም ይቅርታ የላቸውም ብያለሁ—

፴፭ ከተቀበሉት በኋላ መንፈስ ቅዱስን፣ እና የአብን አንድያ ልጅ ስለካዱት፣ እናም እርሱንም በራሳቸው ስለሰቀሉት እና ስላዋረዱት ይቅርታ የላቸውም።

፴፮ እነዚህም፣ ከዲያብሎስ እና ከመላእክቱ ጋር ወደ እሳቱና ወደ ዲኑ ባሕር የሚሄዱት ናቸው—

፴፯ እናም ሁለተኛው ሞትም ሀይልን የሚያገኝባቸውም እነርሱ ናቸው፤

፴፰ አዎን፣ በእውነትም፣ ከቁጣው ስቃይ በኋላ፣ በጌታ ዘመንም የማይድኑት እነርሱ ብቻ ናቸው።

፴፱ ሌሎቹም ሁሉ፣ በታረደው፣ አለማትም ከመሰራታቸው አስቀድሞ በአብ እቅፍ በነበረው በበጉ ታላቅ ድል እና ክብር የተነሳ፣ በሙታን ትንሳኤ ይመጣሉ

እና ይህም የሰማያት ድምፅ ለእኛ የመሰከረልን ምስራች ወንጌል ነው—

፵፩ እርሱም፣ እንዲሁም ኢየሱስ፣ ለአለም ሊሰቀልና የአለም ኃጢአቶችን ሊሸከም፣ እናም አለምንም ሊቀድስና፣ ከርኩሳትም ሊያጸዳ ወደ አለም እንደመጣ፣ የሰማያት ድምፅ የመሰከረልን ምስራች ይህ ነው፤

፵፪ በእርሱም አማካይነት አብ በእርሱ ሀይል ያደረጋቸውን እና በእርሱ የተሰሩት ሁሉ ይድኑ ዘንድ፤

፵፫ እርሱም አብን የሚያከብር፣ እናም አብም ከገለጠው በኋላ ወልድን ከሚክዱት የጥፋት ልጆች በስተቀር የእጆቹን ስራዎች ሁሉ የሚያድን ነው።

፵፬ ስለዚህ፣ ከእነርሱም በስተቀር ሁሉን ያድናል—እነርሱም መጨረሻ ወደሌለው፣ የዘለአለም ቅጣት ወደሆነው፣ ከዲያብሎስ እና ከመላእክቱ ጋር ገዢ ለመሆን ስቃያቸው የሆነው ትላቸው ወደ ማይሞትበት እሳቱም ወደ ማይጠፋበት ወደ ዘለአለም ቅጣት ይሄዳሉ—

፵፭ እናም መጨረሻውን፣ ወይም ስፍራውን፣ ወይም ስቃያቸውን ማንም ሰው አያውቅም፤

፵፮ ይህም አልተገለጠም፣ ወይም የዚህ ተካፋዮች ከሆኑት በስተቀር፣ ይህም የተገለጠም አይደለም፣ ወይም ለሰውም አይገለጠም፤

፵፯ ይሁን እንጂ፣ እኔ ጌታ ይህን በራዕይ ለብዙዎች አሳይቻለሁ፣ ነገር ግን ወዲያውም ደግሜ ዘግቼዋለሁ።

፵፰ ስለዚህ፣ የዚህን መጨረሻ፣ ስፋት፣ ከፍታ፣ ጥልቀት፣ እና ስቃይ አልተረዱትም፣ ወይም በዚህ ፍርድ ከተመደቡት በስተቀር ማንም ሰው አይረዳውም።

፵፱ እናም ድምፅም እንዲህ ሲል ሰማን፥ ይህን ራዕይ ጻፍ፣ የኃጢአተኞችም ስቃይ መጨረሻ ይህ ነውና።

ደግሞም እንመሰክራለን—አይተን ሰምተናልና፣ እናም ይህም መልካምን በማድረግ በጻድቃት ትንሣኤ የሚነሱትን በሚመለከት የክርስቶስ ወንጌል ምስክርነት ይህ ነው—

፶፩ እነርሱም የኢየሱስን ምስክር የተቀበሉ፣ እናም በስሙም ያመኑ እና ቀብሩን በሚመስል ድርጊት፣ በስሙ በውሀ ውስጥ በመቀበር የተጠመቁ ናቸው፣ እና ይህንም ያደረጉት እርሱ በሰጣቸው ትእዛዝ መሰረት ነው—

፶፪ ይህም ትእዛዛትን በማክበርም ከኃጢአታቸው ሁሉ እንዲታጠቡ እና እንዲጸዱ፣ እናም ወደዚህ ሀይል በተሾመው እና በተሳሰረው እጆችንም በመጫን መንፈስ ቅዱስን ይቀበሉ ዘንድ በሰጠው ትእዛዝ መሰረት ነው፤

፶፫ እናም በእምነት ያሸነፉም፣ እናም መልካም ለሚያደርጉት እና ለእውነተኞች ሁሉ አብ በሚያፈሰው በቅዱሱ የተስፋ መንፈስ ታትመዋል

፶፬ እነርሱም የበኩር ልጅ ቤተክርስቲያን ናቸው።

፶፭ እነርሱም አብ ሁሉንም ነገሮች በእጆቻቸው የሰጣቸው ናቸው—

፶፮ እነርሱም የእርሱን ሙላት እና ክብር የተቀበሉ ካህናት እና ነገስታት ናቸው፤

፶፯ እናም ከአንድያ ልጅ ስርዓት እና የሔኖክ ስርዓት ከነበረው እንደ መልከ ጼዴቅ ስርዓት የልዑልም ካህናት ናቸው።

፶፰ ስለዚህ፣ እንደተጻፈውም፣ እነርሱ አማልክቶች፣ እነሆ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸው፣

፶፱ ስለዚህ፣ ሁሉም ነገሮች የእነርሱ ናቸው፣ በህይወትም ይሁን በሞት፣ ወይም አሁን ያሉ ነገሮች ወይም ወደፊት የሚመጡት ነገሮች፣ ሁሉም የእነርሱ ናቸውም እነርሱ የክርስቶስ ናቸው፣ እናም ክርስቶስም የእግዚአብሔር ነው።

እናም እነርሱም ሁሉንም ነገሮች ያሸንፋሉ

፷፩ ስለዚህ፣ ማንም በሰው አይመካ፣ ነገር ግን ጠላቶቹን ሁሉ ከእግሩ በታች በሚያደርገው በእግዚአብሔር ይመካ

፷፪ እነዚህም በእግዚአብሔር እና በእርሱ ክርስቶስ ፊት ለዘለአለም ይኖራሉ

፷፫ በምድር በህዝቡ ላይ ሊነግስ በሰማይ ደመና በሚመጣበት ጊዜ ይዞአቸው የሚመጣውም እነዚህ ናቸው።

፷፬ እነዚህም በመጀመሪያው ትንሳኤ ስፍራም የሚኖራቸውም እነዚህ ናቸው።

፷፭ እነዚህም በጻድቃን ትንሳኤ የሚመጡት ናቸው።

፷፮ ወደ ፅዮን ተራራ፣ እናም ከሁሉም በላይ ቅዱስ ወደሆነው ሰማያዊ ስፍራ፣ ወደ ህያው እግዚአብሔር ከተማ የሚመጡትም እነዚህ ናቸው።

፷፯ እነዚህም ወደ አእላፋት መላእክት፣ ወደ ሔኖክ እና ወደ በኩራት ቤተክርስቲያንና ወደ ታላቁ ጉባኤ የመጡት ናቸው።

፷፰ እነዚህም እግዚአብሔር እና ክርስቶስ ሁሉንም በሚፈርዱበት በሰማይ ስሞቻቸው የተጻፉላቸውም ናቸው።

፷፱ እነዚህ የአዲስ ኪዳን አማላጅ በሆነው፣ ይህን ፍጹም የኃጢአት ክፍያን በመፈጸም የራሱን ደም በማፍሰስ ባከናወነው በኢየሱስ ፍጹም የሆኑት ጻድቃን ሰዎች ናቸው።

እነዚህ ሰውነታቸው ሰለስቲያል የሆኑ ናቸው፣ ክብራቸውም እንደ ጸሀይ፣ እንዲሁም ከሁሉም በላይ በሆነ የእግዚአብሔር ክብር፣ ክብሩም የጠፈር ጸሀይ አይነተኛ ሆኖ እንደተጻፈ የሆነው ነው።

፸፩ እና ደግሞም፣ የተረስትሪያልን አለም አየን፣ እና እነሆ እናም አስተውሉ፣ እነዚህም የተረስትሪያል የሆኑ፣ ጨረቃ ከጠፈር ጸሀይ እንደሚለይ፣ ክብራቸው የአብን ሙላት ከተቀበለው የበኩር ቤተክርስቲያን የተለዩ ናቸው።

፸፪ እነሆ፣ እነዚህም ካለህግ የሞቱት ናቸው፤

፸፫ እና እነርሱ ደግሞም እንደ ሰዎች በሥጋ ይፈረድባቸው ዘንድ ወልድ የጎበኛቸው፣ እናም ወንጌሉንም የሰበከላቸው በወኀኒ ውስጥ የነበሩ የሰዎች ነፍሳት ናቸው፤

፸፬ በስጋ የኢየሱስን ምስክር ያልተቀበሉ፣ ነገር ግን በኋላ የተቀበሉት ናቸው።

፸፭ እነዚህ በምድር የተከበሩ፣ በሰዎች ተንኮል ምክንያት የታወሩ ሰዎች ናቸው።

፸፮ እነርሱ ክብሩን ቢቀበሉም፣ ሙላቱን ግን የማይቀበሉ ናቸው።

፸፯ እነዚህ የወልድን መገኘት ቢቀበሉም፣ የአብን ሙላት የማይቀበሉ ናቸው።

፸፰ ስለዚህ፣ የተረስትሪያል ሰውነቶች እንጂ የሰለስቲያል ሰውነቶች አይደሉምና፣ እናም ጨረቃ ከጸሀይ ልዩ እንደሆነም ክብሩም እንዲሁ ልዩ ነው።

፸፱ እነዚህም በኢየሱስ ምስክርነት ደፋር ያልሆኑት ናቸው፤ ስለዚህ፣ የአምላካችንን መንግስት አክሊል አይቀበሉም።

እናም አሁን ይህም በመንፈስ እያለን ጌታ እንድንፅፈው ያዘዘን ስለ ተረስትሪያል ያየነው ራዕይ መጨረሻ ነው።

፹፩ እና ደግሞም፣ እንዲሁም በጠፈር ውስጥ የኮኮብ ክብር ከጨረቃ ክብር ልዩ እንደሆነ፣ አነስተኛ የሆነውን የቲለስቲያልን ክብር ተመለከትን።

፹፪ እነዚህም የክርስቶስን ወንጌል ወይም የኢየሱስን ምስክርነት ያልተቀበሉት ናቸው።

፹፫ እነዚህም መንፈስ ቅዱስን ያልካዱት ናቸው።

፹፬ እነዚህም ወደ ሲኦል የተጣሉት ናቸው።

፹፭ እነዚህ እስከመጨረሻው ትንሳኤ ድረስ፣ ጌታ እንዲሁም ክርስቶስ፣ በጉ፣ ስራውን እስከሚጨርስ ድረስ ከዲያብሎስ ነጻ የማይሆኑት ናቸው።

፹፮ እነዚህም ዘለአለማዊ በሆነው አለም ውስጥ የእርሱን ሙላት የማይቀበሉ፣ ነገር ግን በተረስትሪያል አገልግሎት አማካይነት የመንፈስ ቅዱስን ሙላት የሚቀበሉት ናቸው፤

፹፯ እናም ተረስትሪያልም በሰለስቲያል አገልግሎት አማካይነት ይቀበላሉ።

፹፰ እና ደግሞ የቲለስቲያልም እንዲያገለግሉአቸው በተመረጡት መላእክት ወይም ለእነርሱ አገልጋይ መናፍስት እንዲሆኑ በተመረጡ ይህን ይቀበላሉ፤ እነርሱም የደህንነት ወራሾች ይሆናሉና።

፹፱ እናም በሰማያዊ ራዕይ አዕምሮን ሁሉ የሚያልፈውን የቲለስቲያል ክብርን እንደዚህም ተመለከትን፤

እና እግዚአብሔር ከገለጠለት በስተቀር ማንም አያውቀውም።

፺፩ እናም ከቲለስቲያል ክብር በሁሉም ነገሮች፣ እንዲሁም በክብር፣ በሀይል፣ እናም በስልጣን፣ እናም በአለቅነት የላቀውን የተረስትሪያል ክብርን እንዲህ ተመለከትን።

፺፪ እናም ከሁሉም ነገሮች በላይ የሆነውን፣ እግዚአብሔር፣ እንዲሁም አብ፣ በዙፋኑ ላይ ለዘለአለም የሚነግስበትን የሰለስቲያል ክብርን እንዲህ ተመለከትን፤

፺፫ በዙፋኑ ፊትም ሁሉም ነገሮች በትህትና በማወደስ ይሰግዳሉ፣ እናም ለእርሱም ለዘለአለም ክብርን ይሰጣሉ።

፺፬ በእርሱ ፊት የሚኖሩትም የበኩር ቤተክርስቲያን ናቸው፤ እናም የእርሱን ሙላት እና ጸጋ በመቀበልም እንደሚታዩም ያያሉ፣ እናም እንደሚታወቁም ያውቃሉ፤

፺፭ እና በሀይልም፣ እና በስልጣን፣ እና በአለቅነትም እኩል ያደርጋቸዋል።

፺፮ እና የጸሀይ ክብር አንድ እንደሆነ የሰለስቲያል ክብርም አንድ ነው።

፺፯ እናም የጨረቃ ክብር አንድ እንደሆነም፣ የተረስትሪያል ክብር አንድ ነው።

፺፰ እናም የከዋክብት ክብር አንድ እንደሆን፣ እንዲሁ የቲለስቲያል ክብር አንድ ነው፤ አንዱ ኮከብ ከሌላው ኮከብ በክብር እንደሚለይም፣ በቲለስቲያል ክብር ውስጥ በክብር አንዱ ከሌላው የተለየ ነው፤

፺፱ እነዚህም የጳውሎስ፣ እናም የአጵሎስ፣ እናም የኬፋ ናቸው።

እነዚህም የአንድ እና የሌላም—አንዳንዶች የክርስቶስ እና አንዳንዶች ዮሐንስ፣ እናም አንዳንዶቹም የሙሴ፣ እናም አንዳንድ የኤልያስ፣ እናም አንዳንዱ የኢሳይያስ፣ አንዳንዱ የኢሳይያስ፣ እናም አንዳንዱ የሔኖኮች ነን የሚሉ ናቸው፤

፻፩ ነገር ግን ወንጌሉን፣ ወይም የኢየሱስን ወይም የነቢያትን ምስክርነት፣ ወይም የዘለአለም ቃል ኪዳንን ያልተቀበሉ ናቸው።

፻፪ በመጨረሻም፣ እነዚህም ከቅዱሳኑ ጋር፣ ወደ በኩር ቤተክርስቲያን በደመና እንዲነጠቁ የማይሰበሰቡት ናቸው።

፻፫ እነዚህም ሀሰተኞች፣ እና አስማተኞች፣ እና ሴሰኞች፣ እና አመንዝሮች፣ እና ሀሰትንም የሚወዱ እና የሚያደርጉትም ናቸው።

፻፬ እነዚህ በምድር ላይ የእግዚአብሔርን ቁጣ የሚቀበሉት ናቸው።

፻፭ እነዚህ፣ ዘለአለማዊ እሳት የቂም በቀልን የሚቀጡትም ናቸው።

፻፮ እነዚህ ወደ ሲኦል የሚጣሉት እናም፣ ክርስቶስ ጠላቶቹን ሁሉ ከእግሩ በታች እስከሚያደርግበት፣ እና ስራውን ፍጹም እስከሚያደርግበት እስከ ዘመኑ ፍጻሜ፣ ሁሉን በሚገዛው እግዚአብሔር ብርቱ ቁጣም የሚሰቃዩት ናቸው፤

፻፯ አሸንፌአለሁ እናም መጥመቂያው፣ እንዲሁም ሁሉን የሚገዛ የእግዚአብሔርን የብርቱ ቍጣውን ወይን መጥመቂያን፣ ብቻዬን ረግጫለሁ፣ በማለት መንግስትን ወደ አብ በፍጹም ንፅህና እንከሚያስረክብበት ድረስ የሚሰቃዩት እነርሱ ናቸው።

፻፰ ከዚያም እርሱም በስልጣኑ ዙፋኑ ለዘለአለም ይነግስ ዘንድ የክብር አክሊል ይጫንለታል።

፻፱ ነገር ግን እነሆ፣ እናም አስተዋሉ፣ የቲለስቲያል አለምን ክብር እና ኗሪዎችን፣ በሰማይ ጠፈር እንዳሉት ከዋክብት አይነት፣ ወይም እንደ ባህር ዳር አሸዋዎች ለመቆጠር እንደማይቻሉም አየን።

፻፲ እናም የጌታ ድምፅ እንዲህ ሲል ሰማን፥ በዙፋኑ ላይ ለሚቀመጠው ከዘለአለም እስከ ዘለአለም እነዚህ ሁሉ በጉልበት ይንበረከካሉ፣ እናም እያንዳንዱ ምላስም ይናዘዝለታል

፻፲፩ እንደ ስራቸውም መጠን ይፈረድባቸዋል፣ እናም ለእያንዳንዱ ሰውም እንደስራው በተዘጋጀለት መኖሪያ ግዛቱን ይቀበላል፤

፻፲፪ እና እነርሱም የልዑል አገልጋዮች ይሆናሉ፣ ነገር ግን እግዚአብሔር እና ክርስቶስ በሚኖሩበት፣ ከዘለአለም እስከዘለአለም መምጣት አይችሉም።

፻፲፫ ይህም በመንፈስ ሳለን ያየነውና እንድንፅፈውም የታዘዝነው ራዕይ መጨረሻ ነው።

፻፲፬ ነገር ግን የጌታ ስራዎች፣ እናም በክብርና፣ በሀይል፣ እናም በአለቅነት ለማስተዋል ከሚቻለው በላይ እንደሆኑ ያሳየን የመንግስቱ ሚስጥራት ታላቅና አስደናቂ ናቸው፤

፻፲፭ እነዚህንም በመንፈስ እያለንም እንዳንፅፋቸው አዝዞናል፣ እናም ሰው ይናገራቸው ዘንድ በህግ ያልተገቡ ናቸው።

፻፲፮ ሰው ያሳውቃቸው ዘንድ ችሎታ አይኖረውም፣ እግዚአብሔር ለሚወዱት እና በፊቱም ራሳቸውን ለሚያጸዱት በሚሰጠው በመንፈስ ቅዱስ ሀይል ብቻ ሰው ሊያያቸው እና ሊረዳቸው ይቻለዋልና፤

፻፲፯ ለእነዚህም ራሳቸው የሚያዩበትን እና የሚያውቁበትን ልዩ መብት ይሰጣቸዋል፤

፻፲፰ በስጋ እያሉም፣ በመንፈስ ሀይል እና በመገለጥ በኩል በክብር አለም ውስጥ የእርሱን መገኘት ያዩ ዘንድም ይሰጣቸዋል።

፻፲፱ እናም ለእግዚአብሔር እና ለበጉ ክብር እና ውዳሴ፣ እናም አለቅነትም ከዘለአለም እስከዘለአለም ይሁን። አሜን።