ቅዱሳት መጻህፍት
ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች ፻፴፫


ክፍል ፻፴፫

በህዳር ፫፣ ፲፰፻፴፩ (እ.አ.አ.) በሀይረም ኦሀዮ ውስጥ በነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ በኩል የተሰጠ ራዕይ። ይህን ራዕይ በማስተዋወቅ የጆሴፍ ስሚዝ ታሪክ እንደሚገልጸው፥ “በዚህ ጊዜ ሽማግሌዎች ወንጌሉን ለምድር ነዋሪዎች ስለመስበክ፣ እና መሰብሰብን በሚመለከት ብዙ ነገሮችን ለማወቅ ፈልገው ነበር፤ እና በእውነት ብርሀን ለመራመድ፣ እና ከበላይም ለመመራት፣ በህዳር ፫፣ ፲፰፻፴፩ (እ.አ.አ.)፣ ጌታን ጠየቅሁ እና ይህን አስፈላጊ ራዕይ ተቀበልኩ።” ይህም ክፍል በትምህርት እና ቃል ኪዳን መፅሐፍ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደ ተጨማሪ ሆኖ ነበር እና በኋላም የክፍል ቁጥር ተመደበለት።

፩–፮፣ ቅዱሳን ለዳግም ምፅዓት እንዲዘጋጁ ታዝዘዋል፤ ፯–፲፮፣ ሁሉም ሰዎች ከባቢሎን እንዲሸሹ፣ ወደ ፅዮን እንዲመጡ፣ እና ለጌታም ታላቅ ቀን እንዲዘጋጁ ታዝዘዋል፤ ፲፯–፴፭፣ እርሱ በፅዮን ተራራ ላይ ይቆማል፣ ክፍለ አህጉራትም አንድ ምድር ይሆናሉ፣ እና የጠፉት የእስራኤል ነገዶች ይመለሳሉ፤ ፴፮–፵፣ ወንጌሉ በአለም እንዲሰበክ በጆሴፍ ስሚዝ በኩል ዳግሞ ተመልሷል፤ ፵፩–፶፩፣ ጌታ በክፉዎች ላይ ለበቀል ይወርዳል፤ ፶፪–፶፮፣ የቤዛነቱም አመት ይሆናል፤ ፶፯–፸፬፣ ወንጌል ቅዱሳንን ለማዳን እና ክፉዎችንም ያጠፉ ዘንድ ተልኳል።

የቤተክርስቲያኔ ህዝብ ሆይ፣ አድምጡ፣ ይላል ጌታ አምላ ካችሁ፣ እና እናንተን በሚመለከት የጌታን ቃል ስሙ—

ወደ ቤተመቅደሱ በድንገት የሚመጣው ጌታ፤ አዎን፣ እግዚአብሔርን በእርሱ ህዝብ ላይ፣ እና በመካከላችሁ ላሉ ኃጢአተኞች ላይ ሁሉ ለፍርድ እርግማን ይዞ በምድር ላይ የሚወርደው ጌታን አድምጡ።

እግዚአብሔር የተቀደሰውን ክንዱን በአሕዛብ ሁሉ ፊት ይገልጣልና፣ እና በምድር ዳርቻ የሚኖሩትም ሁሉ የአምላካቸውን መድኃኒት ያያሉ።

ስለዚህ ህዝቤ ሆይ፣ ተዘጋጁ፣ ተዘጋጁ፤ ራሳችሁን ቀድሱ፤ የቤተክርስቲያኔ ህዝብ ሆይ፣ እንድትቆዩ ያልታዘዛችሁት ሁሉ አብራችሁ በፅዮን ምድር ውስጥ ተሰብሰቡ።

ከባቢሎንም ውጡ። የጌታን ዕቃ የምትሸከሙ ንፁሀን ሁኑ።

የክብር ስብሰባችሁን ጥሩ፣ እና አንዳችሁ ከሌላችሁ በየጊዜው ተነጋገሩ። እና እያንዳንዱም ሰው የጌታን ስም ይጥራ።

አዎን፣ ደግሞም እውነት እላችኋለሁ፣ የጌታ ድምፅ ለእናንተ የሚሆንበት ጊዜ መጥቷል፥ ከባቢሎን ውጡ፤ ከአራቱ ነፋሳት፣ ከሰማያትም ዳርቻ እስከ ዳርቻው ከሀገሮች መካከል ተሰብስባችሁ ውጡ።

መጀመሪያ ወደ አህዛብ እና ከዚያም ወደ አይሁድ፣ ሁሉንም ሀገሮች እንዲጠሯቸው የቤተክርስቲያኔን ሽማግሌዎች ወደ ራቅ ሀገሮች፣ ወደ ባህር ደሴቶች ላኳቸው፤ ወደ ባዕድ ሀገሮችም ላኳቸው።

እናም እነሆ እና አስተውሉ፣ ይህም ጩኸታቸው እና ለሁሉም ህዝብ የጌታ ድምፅ ነው፥ የህዝቤ ድንበር ይሰፋ ዘንድ፣ እና ካስማዎቿም ይጠናከሩ ዘንድ፣ እና ፅዮንም በአካባቢው ባሉ ሀገራት ትጎለብት ዘንድ ወደ ፅዮን ምድር ሂዱ።

አዎን፣ ከሁሉም ህዝብ መካከል ጩኸቱ ይውጣ፥ ንቁ፣ እና ተነሱ እና ሙሽራውንም ለመገናኘት ሂዱ፤ እነሆ እና አስተውሉ፣ ሙሽራው ይመጣል፣ ትቀበሉትም ዘንድ ውጡ። ለጌታ ታላቅ ቀንም ራሳችሁን አዘጋጁ።

፲፩ ቀኒቱንና ሰዓቲቱን አታውቁምና እንግዲህ ንቁ

፲፪ ከአህዛብ መካከል ያሉትም ወደ ፅዮን ይሽሹ።

፲፫ እና የይሁዳ የሆኑትም ወደጌታ ቤት ተራራዎች ወደ ኢየሩሳሌም ይሽሹ።

፲፬ ከሀገሮች መካከል፣ እንዲሁም ከባቢሎን፣ መንፈሳዊ ባቢሎን ከሆነው ከክፋት መካከል ውጡ።

፲፭ ነገር ግን በእውነት ጌታ እንዲህ ይላል፣ ሽሸታችሁ በችኮላ አይሁን፣ ነገር ግን ሁሉም ነገሮች በፊታችሁ ይዘጋጁ፤ እና የሚሄደውም፣ ድንገተኛ ጥፋትም እንዳይደርስበት ወደኋላ አይመልከት

፲፮ የምድር ነዋሪዎች ሁሉ፣ አድምጡ እና ስሙ። የቤተክርስቲያኔ ሽማግሌዎች የሆናችሁ በአንድነት አብራችሁ አድምጡ፣ እና የጌታንም ድምፅ ስሙ፤ ሁሉንም ሰዎች ይጣራልና፣ እና በየትኛውም ስፍራ ለሚገኙ ሰዎች ሁሉ ንስሀ ይገቡ ዘንድያዝዛቸዋል።

፲፯ እነሆም፣ ጌታ አምላክ በሰማያት መካከል እንዲህ በማለት በመጮህ መልአክ ልኳል፥ የጌታን መንገድ አዘጋጁ፣ እና ጥርጊያውንም ቀና አድርጉ፣ የመምጣቱም ጊዜ ቀርቦአልና—

፲፰ በጉ በፅዮን ተራራ ሲቆም፣ እና ከእርሱም ጋር የአባቱ ስም በግምባራቸው የተጻፈላቸው መቶ አርባ አራት ሺህ ነበሩ።

፲፱ ስለዚህ፣ ለሙሽራው ምጻት ተዘጋጁ፤ ሂዱ፣ ከእርሱም ጋር ለመገናኘት ሂዱ።

እነሆም፣ በደብረ ዘይት ተራራና በታላቋ ባህር ላይ፣ እንዲሁም በታላቁ ጥልቅ፣ እና በባህር ደሴት ላይ፣ እና በፅዮን ምድር ላይ ይቆማል

፳፩ እና በፅዮንም ሆኖ ድምፁን ከፍ አድርጎ ይጮኻል፣ እና ከኢየሩሳሌምም ይናገራል፣ እና ድምጹም በሁሉም ህዝብ መካከል ይሰማል፤

፳፪ ይህም ተራሮችን በሚሰብር፣ እና ሸለቆዎችን እንደሚለያይ በሚያደርግ እንደ ብዙ ውሀዎች ድምፅና እንደ ታላቅ ነጐድጓድ ድምፅ ይሰማል።

፳፫ ታላቁን ጥልቅ ያዝዘዋል፣ እና ይህም ወደ ሰሜን አገሮችም ይገፋል፣ እና ደሴቶችም አንድ ምድር ይሆናሉ፤

፳፬ እና የኢየሩሳሌም ምድር እና የፅዮን ምድር ወደስፍራቸው ይመለሳሉ፣ እና ምድርም ከመከፋፈልዋ ቀን አስቀድሞ እንደነበረችበትም አይነት ትሆናለች።

፳፭ እና ጌታ፣ እንዲሁም አዳኝ፣ በህዝቡ መካከል ይቆማል፣ እና ስጋ ለባሽ ሁሉ መካከል ይነግሳል

፳፮ እና በሰሜን ሀገሮች ያሉትም ጌታን ያስታውሳሉ፤ እና ነቢያቶቻቸውም ድምጹን ይሰማሉ፣ እና ራሳቸውን ከዚህም በኋላ የሚታገሱ አይሆኑም፤ እና ድንጋይን ይመታሉ፣ እና በፊታቸውም በረዶዎች ይፈሳሉ።

፳፯ እና አውራ መንገድም በታላቁ ጥልቅ መካከል ይዘረጋል።

፳፰ ጠላቶቻቸውም ለእነርሱ እንደ አደን ይሆናሉ፣

፳፱ እና ፍሬ በማያፈራ በረሀ ውስጥም የህይወት ውሀ ምንጭ ይፈልቃል፤ እና በጸሀይ የደረቀውም መሬት ዳግም የተጠማ ምድር አይሆንም።

እና የከበረ ሀብታቸውንም ወደ አገልጋዬ ኤፍሬም ልጆች ያመጣሉ።

፴፩ እና የዘለአለም ኮረብቶች ድንበሮችም በፊታቸው ይንቀጠቀጣሉ።

፴፪ እና በዚያ፣ እንዲሁም በፅዮን ውስጥ፣ ይወድቃሉ እና በጌታ አገልጋዮች እጆችም፣ እንዲሁም በኤፍሬም ልጆች፣ የክብር አክሊል ይጎነጸፋሉ።

፴፫ እና እነርሱም በዘለአለም የደስታ መዝሙር ይሞላሉ።

፴፬ እነሆ፣ ይህም በእስራኤል ጎሳዎች ላይ የዘለአለማዊው እግዚአብሔር በረከት፣ እና በኤፍሬም እና በባልንጀሮቹ ራስ ላይ ዋጋ ያለው በረከት ነው።

፴፭ እና የይሁዳ ጎሳ ለሆኑትም፣ ከስቃያቸው በኋላ በቅድስና በጌታ ፊት፣ በቀን እና በማታ፣ ለዘለአለም፣ በፊቱ እንዲኖሩ ይቀደሳሉ።

፴፮ አሁንም፣ በእውነት ጌታ እንዲህ ይላል፣ የምድር ነዋሪዎች ሆይ፣ እነዚህ ነገሮች በእናንተ መካከል የታወቁ ይሆኑ ዘንድ የዘለአለም ወንጌል ያለው፣ ለአንዳንዶች የታየ እና ለሰውም ይህን የሰጠ፣ እና በምድር ላይ ለሚኖሩት ለብዙዎች የሚታየው መልአክ ከሰማይ መካከል እንዲበር ልኬአለሁ።

፴፯ እና ይህም ወንጌል ለእያንዳንዱ ሕዝብ፣ ለነገድ፣ ቋንቋ፣ እና ወገንም ሁሉ ይሰበካል

፴፰ እና የእግዚአብሔርም አገልጋዮች በታላቅ ድምፅ፥ የፍርዱ ሰዓት ደርሶአልና እግዚአብሔርን ፍሩ ክብርንም ስጡት በማለት ይሄዳሉ፤

፴፱ እና ሰማይንና ምድርንም ባሕርንም የውኃንም ምንጮች ለሠራው ስገዱለት

በቀን እና በማታ የጌታን ስም በመጥራት፥ ሰማያትን ቀድደህ ብትወርድስ፣ ተራሮችም በፊትህ ቢናወጡስ በማለትም።

፵፩ እናም በራሳቸው ላይ መልስ ይሰጣል፤ የጌታ መገኘት እሳት እንደሚያቀልጥ እሳት፣ እና ውኃንም እንደሚያፈላ እሳት ይሆናል።

፵፪ ጌታ ሆይ፣ ስምህ ለጠላቶችህ ይገለጥ ዘንድ፣ እና አሕዛብም በፊትህ ይንቀጠቀጡ ዘንድ ትወርዳለህ—

፵፫ ያልጠበቁትን የሚያስፈራውን ነገር ባደረግህም ጊዜ፤

፵፬ አዎን፣ ወረድህ፣ እና ተራሮችም በፊትህ ተንቀጠቀጡ፣ የሚደሰተውንና ጽድቅን የሚያደርገውን በመንገዶችህም የሚያስቡህን ትገናኛቸዋለህ

፵፭ እግዚአብሔር ሆይ፣ ሰዎች ከጥንት ጀምሮ ለሚጠብቁህ ከምትሠራላቸው ከአንተ በቀር ሌላ አምላክን አልሰሙም፣ በጆሮአቸውም አልተቀበሉም፣ ዓይንም አላየችም።

፵፮ እና እንዲህም ይባላል፥ ከእግዚአብሔር ዘንድ ከሰማይ የወረደው፣ ልብሱም የቀላ፣ ከባሶራ የሚመጣ አለባበሱም ያማረ፣ በጕልበቱስ ጽናት የሚራመድ ይህ ማን ነው?

፵፯ እርሱም ይላል፥ በጽድቅ የምናገር ለማዳንም የምበረታ እኔ ነኝ።

፵፰ እና ጌታም በልብሱ ቀይ፣ እና ልብሱም ወይን በመጥመቂያ እንደሚረግጥ ሰው ልብስ ይሆናል።

፵፱ እና ከፊቱም ክብር ታላቅነት የተነሳ ጸሀይ በእፍረት ፊቱን ይሸፍናል፣ እና ጨረቃም ብርሀኗን ትከለክላለች፣ እና ከዋክብትም ከስፍራቸው ይወረወራሉ።

እና ድምጹም ይሰማል፥ ወይን መጭመቂያን ብቻዬን ረግጫለሁ፥ እና በሁሉም ህዝብ ላይ ፍርድ አምጥቻለሁ፤ እና ማንም ሰው ከእኔ ጋር አልነበረም፤

፶፩ በቍጣዬ ረገጥኋቸው በመዓቴም ቀጠቀጥኋቸው፣ ደማቸውም በልብሴ ላይ ተረጭቶአል፣ ልብሴንም ሁሉ አሣድፌአለሁ፤ ይህም በልቤ የነበረው የምበቀልበት ቀን ነውና።

፶፪ አሁንም የምቤዥበትም ዓመት ደርሶአል፤ እና የጌታቸውን አፍቃሪ ደግነትን እና በመልካምነቱም መሰረት፣ እናም በአፍቃሪ ደግነቱ መሰረት፣ በእነርሱ ላይ ስላፈሰሰው ሁሉ ለዘለአለም ይናገራሉ።

፶፫ በጭንቃቸው ሁሉ እርሱ ተጨነቀ። የፊቱን መልአክ አዳናቸው፤ በፍቅሩና በርኅራኄውም ተቤዣቸው፣ በቀደመውም ዘመን ሁሉ አንሥቶ ተሸከማቸው፤

፶፬ አዎን፣ እና ሔኖክ ደግሞም፣ እና ከእርሱም ጋር የነበሩት፤ ከእርሱ በፊት የነበሩት ነቢያት፤ እና ኖህም ደግሞ፣ እና ከእርሱም በፊት የነበሩት፤ እና ሙሴም፣ እና ከእርሱ በፊት የነበሩት፤

፶፭ ከሙሴ እስከ ኤልያስ፣ እና ከኤልያስ በትንሳኤው ከክርስቶስ ጋር እስከ ነበረው ዮሐንስ፣ እና ቅዱስ ሐዋርያት፣ ከአብርሐም፣ ይስሀቅ፣ እና ያዕቆብ ጋር በበጉ ፊት ይሆናሉ።

፶፮ የቅዱሳን መቃብሮችም ይከፈታሉ፤ እና በፅዮን ተራራ ላይ፣ እና በቅዱስቲቱ ከተማ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ላይ ሲቆምም፣ እነርሱም ይመጣሉ እና በበጉም ቀኝ ይቆማሉ፤ እና በቀን እና በማታ ለዘለአለም የበጉን መዝሙሮች ይዘምራሉ።

፶፯ እና ለዚህም ምክንያት ሰዎች የሚገለጡትን ክብሮች ተካፋይ ይሆኑ ዘንድ፣ ጌታ የወንጌሉን ሙላት፣ ዘለአለማዊ ቃልኪዳኑን፣ በግልጽ እና በቀላል ምክንያቱን ላከ—

፶፰ በምድር ላይ ለሚመጡት ነገሮች ደካማዎችን ለማዘጋጀት፣ እና ጥበበኞችን በሚያሳፍሩበት ቀን ለጌታ መልእክት፣ እና አነስተኛው ብርቱ ሕዝብ ይሆናል፣ እና ሁለቱ አሥሩን ሺህ ያሸሻሉ።

፶፱ እና በመንፈሱ ኃይል ጌታ በአለም ደካማ ነገሮች አህዛብን ይወቃል

እና ለዚህም ምክንያት እነዚህ ትእዛዛት ተሰጥተው ነበር፤ በተሰጧቸውም ቀን ከአለም ይሰውሯቸው ዘንድ ታዝዛው ነበር፣ ነገር ግን አሁን ወደ ሁሉም ስጋ ለባሾች ይሂዱ

፷፩ እና ይህም ሁሉንም ስጋ ለባሽ በሚገዛው በጌታ አዕምሮ እና ፈቃድ መሰረት ነው።

፷፪ እና ንስሀ ለሚገባው እና በጌታ ፊት ራሱን ለሚቀድስም የዘለአለም ህይወትን ይሰጣል።

፷፫ እና የጌታን ድምፅ ለማያደምጡም፣ ከህዝብ መካከል ይቆረጡ ዘንድ፣ በነቢዩ ሙሴ የተጻፈውም ይፈጸማል።

፷፬ እና በነቢዩ ሚልክያስ እንደተጻፈውም፥ እነሆ፣ እንደ ምድጃ እሳት የሚነድድ ቀን ይመጣል፤ ትዕቢተኞችና ኃጢአትን የሚሠሩ ሁሉ ገለባ ይሆናሉ፤ የሚመጣውም ቀን ያቃጥላቸዋልና፥ ሥርንና ቅርንጫፍንም አይተውላቸውም፣ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።

፷፭ ስለዚህ፣ ይህም ለእነርሱ የጌታ መልስ ይሆናል፥

፷፮ በዚያም ቀን ወደ ራሴ ስመጣ፣ በመካከላችሁ ማንም አልተቀበለኝም፣ እና ተሰድዳችሁም ነበር።

፷፯ በጠራሁስ ጊዜ የሚመልስ ማንም አልነበረም፤ ነገር ግን መታደግ እንዳልችል እጄ አጭር አልሆነችም፣ ወይስ ለማዳን ኃይል የለኝም።

፷፰ እነሆ፣ በገሠጽሁ ጊዜ ባሕርን አደርቃለሁ። ወንዞችንም ምድረበዳ አደርጋቸዋለሁ፤ ዓሦቻቸውም ይገማሉ በጥማትም ይሞታሉ።

፷፱ ሰማያትን ጥቍረት አለብሳቸዋለሁ፥ መጋረጃቸውንም ማቅ አደርጋለሁ።

እና ይህ ከእጄ ይሆንባችኋል—በኀዘን ትተኛላችሁ።

፸፩ እነሆ እና አስተውሉ፣ የሚያድናችሁ ማንም የለም፤ ከሰማያት ስጠራችሁ ድምጼን አልታዘዛችሁበትምና፤ በአገልጋዮቼ አላመናችሁም፣ እና ወደ እናንተም ሲላኩ አልተቀበሏቸውም።

፸፪ ስለዚህ፣ ምስክሩን ያትማሉ እና ህግንም ያስራሉ፣ እና ወደ ድቅድቅ ጭለማም ትጣላላችሁ።

፸፫ እነዚህም በድቅድቅ ጨለማ ይሄዳሉ፣ በዚያ ልቅሶ፣ ሀዘንና፣ ጥርስ ማፏጨት ይሆናል።

፸፬ እነሆ ጌታ አምላካችሁ ይህን ተናግሯል። አሜን።