ቅዱሳት መጻህፍት
ትምህርት እና ቃል ኪዳኖች ፻፳፯


ክፍል ፻፳፯

ከነቢዩ ጆሴፍ ስሚዝ ለናቩ ኢለኖይ የኋለኛው ቀን ቅዱሳን ስለሙታን መጠመቅ መመሪያን የያዘ፣ በመስከረም ፩፣ ፲፰፻፵፪ (እ.አ.አ.) በናቩ የተጻፈ ደብዳቤ።

፩–፬፣ ጆሴፍ ስሚዝ በስደት እና በመከራ መካከል ይደሰታል፤ ፭–፲፪፣ ስለሙታን ጥምቀቶችን በሚመለከት መዛግብት መጠበቅ አለባቸው።

ጌታ ለእኔ በገለጠልኝ መጠን ጠላቶቼ በሚዙሪ እና በዚህ ስቴት ውስጥ ዳግም እየፈለጉኝ ናቸው፤ እና ያለምክንያትም እየፈለጉኝ እስከሆነ ድረስ፣ እና በእኔ ላይ በሚያመጡት ክስ በጎናቸው ጥቂት የሆነ የፍትህ ወይም የትክክለኛነት ጥላ ወይም ቀለም የላቸውም፤ እና ጥያቄዎቻቸው በጨለመ ሀሰት ላይ የተመሰረቱ እስከሆኑ ድረስ፣ ለራሴ ደህንነት እና ለዚህ ህዝብም ደህንነት ለአጭር ዘመን ይህን ስፍራ ትቼ መሄዴ አስፈላጊ እና ጥበባዊ እንደሆነም አስቤአለሁ። ጉዳዮቻችን በአንድነት ስላሉት ሁሉ ይህን እላለሁ፣ ጉዳዮችን ሁሉ በፍጥነት እና በትክክለኛው አኳኋን በሚያከናውኑ እና ንብረቶችን በመሸጥ ወይም ጉዳዩ አስፈላጊ በሚሆንበት ወይም ጉዳዩ እንደሚፈቅደው በጊዜውም እዳዎቼን ሁሉ እንዲሰረዙ ለሚያደርጉ ወኪሎች እና ጸሀፊዎች ጉዳዮቼን ትቼአቸዋለሁ። ማእበሉ እንዳለፈ ባወቅሁ ጊዜ፣ ከዚያም ወደ እናንተ ዳግሞ እመለሳለሁ።

እንዳልፍባቸው ስለተጠራሁባቸው አደገኛ ነገሮችም፣ ለእኔ እንደ ጥቂት ነገር ነው የሚመስሉኝ፣ የሰው ቅናት እና ቁጣ በህይወቴ ቀናት ሁሉ የየጊዜው እድሌ ነበርና፤ እና እናንተም ልትጠሩት በምትመርጡት ከምድር መመስረት በፊት ለመልካም ወይም ለመጥፎ አላማ የተሾምኩኝ ካልሆነ በስተቀር፣ ይህ በምን እንደሚከሰት ሚስጥር ይመስላል። ለራሳችሁም ፍረዱ። መልካምም ይሁን መጥፎ፣ እግዚአብሔር እነዚህን ነገሮች ሁሉ ያውቃል። ይህም ቢሆን ግን፣ ለመዋኘት የምፈልግበት ጥልቅ ውሀ ነው። ለእኔ ሁለተኛ ህይወት ሆኖልኛል፤ እና እንደ ጳውሎስ በመከራዎች እደሰታለሁ፤ እስከዚህም ቀን ድረስ የአባቶቼ አምላክ ከሁሉም አድኖኛልና፣ እና ከዚህም በኋላ ያድነኛልና፤ እነሆ እናም አስተውሉ፣ ጠላቶቼን ሁሉ አሸንፋለሁ፣ ጌታ አምላክ ተናግሮታልና።

ቅዱሳን ሁሉ ይደሰቱ፣ እና ከመጠንም በላይም ይደሰቱ፤ የእስራኤል አምላክ አምላካቸው ነውና፣ እና በሚጨቁኗቸው ራሶች ላይ ሁሉ የጽድቅን ብድራት መዝኖ ይሰጣቸዋል።

ደግሞም፣ በእውነት ጌታ እንዲህ ይላል፥ የቤተመቅደሴ ስራ፣ እና የመደብኩላችሁ ስራ ሁሉ ይቀጥሉ እና አያቁሙ፤ እና ትጋታችሁ እና የፅናት ስራዎቻችሁ፣ እና ትእግስታችሁ፣ እና ስራዎቻችሁ ይጠንክሩ፣ እና ዋጋችሁን አታጡም ይላል የሰራዊት ጌታ። እና ከጨቆኗችሁም፣ ከእናንተ በፊት የነበሩትን ነቢያትን እና ጻድቅ ሰዎችን ጨቁነው ነበር። ለዚህም ሁሉ በሰማይ ደመወዝ አለና።

ደግሞም፣ ስለሙታናችሁ ጥምቀት በሚመለከት መልእክትን እሰጣችኋለሁ።

በእውነት ስለሙታናችሁ በሚመለከት ጌታ እንዲህ ይላል፥ ማንኛችሁም ለሙታናችሁ ስትጠመቁዘጋቢ ይኑር፣ እና እርሱም ለጥምቀቶቻችሁ የአይን ምስክር ይሁን፤ ስለእውነት ይመሰክር ዘንድ በጆሮዎቹም ይስማ፣ ይላል ጌታ፤

መዛግብቶቻችሁን በሚመለከትም በሰማይ ውስጥ ይመዘገባሉ፤ በምድር የሚታሰረው ሁሉ በሰማይ የታሰረ ይሆናል፣ በምድርም የሚፈታው ሁሉ በሰማያት የተፈታ ይሆናል፤

ክህነትን በሚመለከት፣ በምድር ላይ ብዙ ነገሮችን ዳግም ልመልስ ነውና፣ ይላል የሰራዊት ጌታ።

ደግሞም፣ በቅዱስ ቤተመቅደሴ የመዝገብ ማከማቻ ውስጥ እንዲቀመጡ፣ ከትውልድ ወደ ትውልድም በማስታወሻነት ይቀመጡ ዘንድ መዛግብት በስርዓት ይጠበቁ፣ ይላል የሰራዊት ጌታ።

ለቅዱሳን ሁሉ እላለሁ፣ በሚቀጥለው ሰንበት ስለሙታን የመጠመቅን ርዕስ በመስበኪያው ቆሜ እነርሱን ለማነጋገር በጣም ታላቅ የሆነ ፈቃድ አለኝ። ነገር ግን ይህ ከእኔ ሀይል ውጪ ሆኖ ሲገኝ፣ ስለዚህ ርዕስ እና ስለሌሎች ብዙ ነገሮችም፣ የጌታን ቃል ከጊዜ ወደጊዜ እፅፋለሁ፣ እና በፖስታም እልክላችኋለሁ።

፲፩ ጊዜ ስለሌለኝ፣ አሁን ለጊዜው ደብዳቤዬን በዚሁ እፈፅማለሁ፤ ጠላት ዝግጁ ነውና፣ እና አዳኛችን እንዳለውም፣ የዚህ አለም ገዢ ይመጣል፣ ነገር ግን በእኔ ላይ አንዳች የለውም።

፲፪ እነሆ፣ ለእግዚአብሔር የምጸልየው እናንተ ትድኑ ዘንድ ነው። እና እንደ ጌታ አገልጋይ፣ እንደ የኋለኛው ቀን ቅዱሳን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን ነቢይ እና ባለራዕይ ራሴን አቀርባለሁ።

ጆሴፍ ስሚዝ።