ቅዱሳት መጻህፍት
የሞርሞን ቃላት ፩


የሞርሞን ቃላት

ምዕራፍ ፩

ሞርሞን የኔፊን ትልቁን ሰሌዳ አሳጠረ—ትንሹን ሰሌዳ ከሌላኛው ሰሌዳ ጋር አስቀመጠ—ንጉስ ቢንያም በምድሪቱ ውስጥ ሰላምን መሰረተ። በ፫፻፹፭ ዓ.ም. ገደማ።

እናም አሁን እኔ ሞርሞን ለልጄ ሞሮኒ የፃፍኩትን ታሪክ ለመስጠት እየተዘጋጀሁ እያለሁ፣ እነሆ፣ የህዝቤን የኔፋውያንን በሙሉ የመጥፋትን ምስክር ሆኛአለሁ።

እናም እነዚህን መዛግብት ለልጄ የሰጠሁት ክርስቶስ ከመጣ ከብዙ መቶ ዓመታት በኋላ ነው፤ እርሱም የህዝቡን ፈፅሞ መጥፋት ይመሰክራል ብዬ አስባለሁ። ነገር ግን አንድ ቀን እነርሱን እንዲጠቅማቸው ዘንድ፣ እነርሱን በተመለከተ እናም ክርስቶስን በተመለከተ ጥቂት ይፅፍ ዘንድ እግዚአብሔር ከእርሱ እንዲድን ይፍቀድ።

እናም አሁን፣ የፃፍኩትን በተመለከተ በመጠን እናገራለሁ፤ አማሌቂ ስለተናገራቸው ከኔፊ ሰሌዳዎች ጀምሮ እስከ ንጉስ ቢንያም ድረስ፣ ያሉትን አሳጥሬ ከፃፍኩ በኋላ፣ የተሰጠኝን መዝገብ መረመርሁ፣ እናም ከያዕቆብ እስከ ንጉስ ቢንያም ንግስና ድረስ ትንሹን የነቢያት ታሪክ የያዙትን እነዚህን ሰሌዳዎችና ደግሞ ብዙዎቹን የኔፊን ቃላት አገኘሁ።

እናም በእነዚህ ሰሌዳዎች ላይ ያሉት ነገሮች እኔን ያስደስቱኛል፣ ምክንያቱም የክርስቶስን መምጣት ስለሚተነብዩ፤ እናም አባቶቼ ብዙዎቹ እንደተፈፀሙ ያውቃሉ፤ አዎን፣ እናም ደግሞ እስከአሁን ድረስ ብዙ ነገሮች እኛን በተመለከተ የተተነበዩት እንደተፈፀሙና ከዚያ በኋላ የሚሆኑትም ብዙዎችም በእርግጥ መፈፀም እንዳለባቸው አውቃለሁ—

ስለሆነም፣ በእነርሱ ላይ ምዝገባዬን ለመጨረስ እነዚህን ነገሮች መረጥሁ፣ ቀሪውን ታሪክ ከኔፊ ሰሌዳዎች ላይ እወስዳለሁ፣ እናም ህዝቤን በተመለከቱ ነገሮች መቶኛውን መፃፍ አልችልም።

ነገር ግን እነሆ፣ ትንቢቶችንና ራዕዮችን የያዙትን እነዚህን ሰሌዳዎች እወስዳለሁ፣ እናም ከቀሪው ፅሁፌ ጋር አስቀምጣቸዋለሁ፣ ለእኔ ምርጥ ናቸውና፤ እናም ለወንድሞቼ ምርጥ እንደሚሆኑ አውቃለሁ።

እናም ይህን ለብልህ ዓላማ አደርገዋለሁ፤ በእኔ ውስጥ ያለው የጌታ መንፈስ በዝግታ ድምፅ ተናግሮኛልና። እናም አሁን፣ ሁሉንም ነገሮች አላውቅም፤ ነገር ግን ጌታ የሚመጡትን ነገሮች ሁሉ ያውቃል፤ ስለሆነም፣ እንደፈቃዱ ለማድረግ በእኔ ይሰራል።

እናም ወደ እግዚአብሔር የምፀልየው ወንድሞቼን በተመለከተ ነው፣ ይኸውም እነርሱ አንዴ እንደገና እግዚአብሔርን ወደማወቅ፣ አዎን፣ በክርስቶስ ቤዛነት ይመጡ ዘንድ፤ አንዴ እንደገና የተወደዱ ህዝቦች ይሆኑ ዘንድ ነው።

እናም አሁን እኔ ሞርሞን፣ ከኔፊ ከወሰድኳቸው ሰሌዳዎች ምዝገባዬን ለመጨረስ እቀጥላለሁ፤ እናም ይህን የማደርገው እግዚአብሔር በሰጠኝ እውቀትና መረዳት መሠረት ነው።

ስለሆነም፣ እንዲህ ሆነ አማሌቂ እነዚህን ሰሌዳዎች ለንጉስ ቢንያም በእጁ ከሰጠው በኋላ፣ ወሰዳቸውና ከትውልድ እስከ ትውልድ እስከ ንጉስ ቢንያም ዘመን ድረስ ለንጉሶች የተላለፉትን ታሪክ ከያዙት ከሌሎች ሰሌዳዎች ጋር አስቀመጣቸው።

፲፩ እናም ከትውልድ ወደ ትውልድ በእጄ እስከሚገቡ ድረስ ከንጉስ ቢንያም ተላልፈዋል። እናም እኔ ሞርሞን ከዚህ ጊዜ ጀምሮ እስከሚመጣው እንዲጠበቁ ወደ እግዚአብሔር እፀልያለሁ። እንደሚጠበቁም አውቃለሁ፤ ምክንያቱም በተጻፈው በእግዚአብሔር ቃል መሰረት ከውስጣቸው ህዝቦቼና ወንድሞቻቸው በታላቁና በመጨረሻው ቀን የሚፈረዱባቸው ብዙ ታላቅ ነገሮች በእነርሱ ተፅፈዋልና።

፲፪ እናም አሁን፣ ይህን ንጉስ ቢንያምን በተመለከተ—በህዝቡ መካከል ጥቂት ፀብ ነበረበት።

፲፫ እናም ደግሞ እንዲህ ሆነ የላማናውያን ወታደሮች ከህዝቡ ጋር ሊዋጉ ከኔፊ ምድር ወረዱ። ነገር ግን እነሆ፣ ንጉስ ቢንያም ወታደሮቹን በአንድ ላይ ሰበሰበ እናም ተቋቋማቸው፤ በገዛ ክንዱ ብርታት በላባን ሰይፍ ተዋጋቸው።

፲፬ እናም በጌታ ኃይል ብዙ ሺህ ላማናውያንን እስከሚገድሉ ድረስ ከጠላቶቻቸው ጋር ተጣሉ። እናም እንዲህ ሆነ ከውርስ ምድራቸው ሙሉ በሙሉ እስከሚያስወጧቸው ድረስ ከላማናውያን ጋር ተዋጉ።

፲፭ እናም እንዲህ ሆነ ሀሰተኛ ክርስቶሶች ከነበሩና፣ አፋቸው ከተዘጋና፣ እንደ ወንጀላቸው ከተቀጡ በኋላ፤

፲፮ እናም በህዝቡ መካከል ሀሰተኞቹ ነቢያት፣ ሀሰተኛ ሰባኪዎችና መምህራን ከነበሩ፣ እናም እነዚህ ሁሉ እንደ ወንጀላቸው ከተቀጡ በኋላ፤ እናም ከብዙ ፀብና ብዙዎች ተገንጥለው ወደ ላማናውያን የሄዱ ከነበሩ በኋላም፤ እነሆ፣ እንዲህ ሆነ ንጉስ ቢንያም፣ ከህዝቡ መካከል ከነበሩት ቅዱስ ነቢያት እርዳታ ጋር—

፲፯ እነሆም ንጉስ ቢንያም ቅዱስ ሰው ነበረ፣ እናም በህዝቡም ላይ በፅድቅ ነገሰ፤ ብዙ ቅዱሳን ሰዎች በምድሪቱ ላይ ነበሩም፣ እናም የእግዚአብሔርንም ቃል በኃይልና በስልጣን ተናገሩ፤ በህዝብ አንገተ ደንዳናነት የተነሳም ብዙ ወሳኝ ቃላትን ተጠቀሙ—

፲፰ ስለሆነም፣ በቅዱሳን ነቢያት ድጋፍ፣ ንጉስ ቢንያም፣ እናም ነቢያት፣ በሰውነቱ ሙሉ ኃይልና በአከላተ ነፍሱ ሁሉ በመስራት፣ በምድሪቱ ላይ አንዴ በድጋሚ ሰላምን መሠረተ።