ቅዱሳት መጻህፍት
ኦምኒ ፩


መፅሐፈ ኦምኒ

ምዕራፍ ፩

ኦምኒ፣ አማሮን፣ ቼሚሽ፣ አቢናዶም፣ እና፣ አማሌቂ እያንዳንዳቸው በተራ መዝገቡን አስቀመጡ—ሞዛያ በሴዴቅያስ ዘመን ከኢየሩሳሌም የመጡትን፣ የዛራሔምላን ህዝብ አገኘ—ሞዛያ በእነርሱ ላይ እንዲነግስ ተደረገ—በዛራሔምላ የሙሌቅ ዝርያዎች የያሬዳውያን መጨረሻ የሆኑትን፣ ቆሪያንተመርን አገኙ—ንጉስ ቢንያም ሞዛያን ተካ—ሰዎች ለክርስቶስ እንደሚቀርብ መስዋዕት ነፍሳቸውን መስዋዕት ማድረግ ይኖርባቸዋል። ከ፫፻፳፫–፩፻፴ ም.ዓ. ገደማ።

እነሆ እንዲህ ሆነ እኔ ኦምኒ፣ በአባቴ ጄረም በመታዘዜ፣ የትውልዳችንን ሐረግ ለማቆየት በእነዚህ ሰሌዳዎች ላይ ጥቂት መፃፍ አለብኝ—

ስለሆነም፣ በዘመኔ ህዝቤን ኔፋውያንን በጠላቶቻቸው ላማናውያን እጅ እንዳይወድቁ ለመጠበቅ በሰይፍ ብዙ መዋጋቴን እንድታውቁልኝ እፈልጋለሁ። ነገር ግን እነሆ፣ እኔ ራሴ ኃጢአተኛ ሰው ነኝ፣ እናም ማድረግ እንደሚገባኝ የጌታን ህግና ትዕዛዛት አልጠበቅሁም።

እናም እንዲህ ሆነ ሁለት መቶ ሰባ ስድስት አመታት አለፉ፣ ብዙ የሰላም ወቅት ነበረንም፤ እናም ብዙ የከፋ ጦርነትና የደም መፋሰስ ወቅት ነበረን። አዎን፣ በአጠቃላይ ሁለት መቶ ሰማንያ ሁለት ዓመታት አለፉ፣ እናም እነዚህን ሰሌዳዎች እንደ አባቶቼ ትዕዛዝ አስቀመጥሁት፤ እነርሱንም ለልጄ አማሮን ሰጠሁ። እናም አበቃሁ።

እናም አሁን እኔ አማሮን፣ ጥቂት የሆኑትን በአባቴ መፅሐፍ ውስጥ የፃፍኩትን ፅፌአለሁ።

እነሆ፣ እንዲህ ሆነ ሶስት መቶ ሀያ ዓመታት አለፉ፣ እናም እጅግ ክፉ የሆኑት ኔፋውያን ጠፉ

ምክንያቱም ጌታ እነርሱን ከኢየሩሳሌም ምድር ካስወጣቸውና በጠላቶቻቸው እጅ እንዳይወድቁ ባለመፍቀዱ ጠብቆ ካቆያቸው በኋላ፣ አዎን፣ ለአባቶቻችን እናንተ ትዕዛዛቴን እስካልጠበቃችሁ ድረስ በምድሪቱ ላይ አትበለፅጉም ብሎ የተናገረው ቃል እንዳይረጋገጥ አይፈቅድምና።

ስለሆነም፣ ጌታ በታላቅ ፍርድ ጎብኝቷቸዋል፤ ይሁን እንጂ፣ ፃድቃኖችን እንዳይጠፉ አስቀርቷል፣ ነገር ግን እነርሱን ከጠላቶቻቸው እጅ አድኗቸዋል።

እናም እንዲህ ሆነ ሰሌዳዎቹን ለወንድሜ ቼሚሽ ሰጠሁት።

እናም እኔ ቼሚሽ ወንድሜ በፃፈበት መፅሐፍ ላይ የምፅፋቸውን ጥቂት ነገሮችን ፃፍኩ፤ እነሆም በመጨረሻ በራሱ እጅ የፃፋቸውን ተመልክቻለሁ፤ ይህንንም የጻፈው እርሱ ለእኔ በሰጠኝ ቀን ነበር። እናም እንደ አባቶቻችን ትዕዛዛት መሰረት መዝገቡን ጠብቀን ያቆየናቸው በዚህ መልኩ ነበር። እናም አበቃለሁ።

እነሆ፣ እኔ አቢናዶም፣ የቼሚሽ ልጅ ነኝ። እነሆ እንዲህ ሆነ በህዝቤ በኔፋውያንና በላማናውያን መካከል ብዙ ጦርነቶችንና ፀቦችን ተመልክቻለሁ፤ እናም እኔ ወንድሞቼን ለመከላከል በራሴ ሰይፍ የብዙ ላማናውያንን ነፍስ አጥፍቻለሁ።

፲፩ እናም እነሆ፣ የዚህ ህዝብ ታሪክ የተቀረፀው ነገሥታቱ በነበሩአቸው ሰሌዳዎች ላይ እንደ ትውልዳቸው መሰረት ነው፤ እና እኔ ከተፃፉት በስተቀር ትንቢትም ሆነ ራዕይ አላውቅም፤ ስለሆነም፣ የተፃፉት በቂ ናቸው። እናም አበቃለሁ።

፲፪ እነሆ፣ እኔ አማሌቂ፣ የአቢናዶም ልጅ ነኝ። እነሆ፣ የዛራሔምላ ምድር ንጉስ ስለሆነው ሞዛያ ጥቂት እናገራለሁ፤ እነሆም ከኔፊ ምድር እንዲወጣ፣ እናም የጌታን ድምፅ የሰሙ ደግሞ ብዙዎችም ከእነርሱ ጋር ወደ ምድረበዳው መሸሽ እንዳለባቸው በጌታ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶት ስለነበረ—

፲፫ እናም እንዲህ ሆነ ጌታ እንዳዘዘው አደረገ። እናም ብዙዎች የጌታን ድምፅ የሰሙ ወደ ምድረበዳው ሸሹ፤ በብዙ ስብከትና ትንቢቶችም ይመሩ ነበር። እናም ያለማቋረጥ በእግዚአብሔር ቃል ተገሰፁ፤ በምድረበዳ ውስጥ ዛራሔምላ ወደሚባለው ምድር እስከሚመጡ ድረስ በክንዱ ኃይልም ተመሩ።

፲፬ እናም የዛራሔምላ ህዝብ ተብለው የሚጠሩትን ህዝቦች አገኙ። በዛራሔምላ ህዝብ መካከል አሁን ታላቅ ደስታ ነበር፤ እናም ደግሞ ዛራሔምላ እጅግ ተደሰተ፣ ምክንያቱም ጌታ የአይሁዶችን ታሪክ ከያዘው የነሀስ ሰሌዳዎች ጋር የሞዛያን ህዝብ ልኳልና።

፲፭ እነሆ፣ እንዲህ ሆነ ሞዛያ፣ የይሁዳ ንጉስ ሴደቅያስ፣ ወደ ባቢሎን በምርኮ በተወሰደበት ጊዜ የዛራሔምላ ህዝብ ከኢየሩሳሌም እንደወጡ ተረዳ።

፲፮ እናም በምድረበዳ ውስጥ ተጓዙ፤ እናም በጌታ እጅ ሞዛያ ወዳገኘው ምድር ታላቁን ውሃ ተሻገሩ፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በዚያ ኖሩም።

፲፯ እናም ሞዛያ ባገኛቸው ጊዜ፣ በቁጥር እጅግ ብዙ ነበሩ። ይሁን እንጂ፣ ብዙ ጦርነትና የከፋ ፀብ ነበራቸው፣ እናም ከጊዜ ወደ ጊዜ በሰይፍ ወደቁ፤ ቋንቋቸውም ተበላሽቶ ነበር፣ ምንም የታሪካቸውንም መዝገብ አላመጡም ነበር፤ እንዲሁም ፈጣሪያቸው መኖሩን ካዱ፣ እናም ሞዛያ ወይም የሞዛያ ህዝብ ሊረዷቸው አልቻሉም።

፲፰ ነገር ግን እንዲህ ሆነ ሞዛያ እነርሱ የእርሱን ቋንቋ እንዲማሩ አደረገ። እናም እንዲህ ሆነ በሞዛያ ቋንቋ ከተማሩ በኋላ፣ ዛራሔምላ የአባቶቹን ትውልድ ሐረግ ባስታወሰው መጠን ሰጠ፤ እናም ተጻፉ፣ ነገር ግን በእነዚህ ሰሌዳዎች ውስጥ አይደለም።

፲፱ እናም እንዲህ ሆነ የዛራሔምላና የሞዛያ ህዝብ በአንድነት ተዋሃዱ፤ እናም ሞዛያ ንጉሳቸው ይሆን ዘንድ ተሾመ።

እናም እንዲህ ሆነ በሞዛያ ዘመን፣ በላዩ ላይ የተቀረጸበት ትልቅ ድንጋይ መጣለት፤ እናም ጽሑፉን በእግዚአብሔር ኃይልና ስጦታ ተረጎመው

፳፩ እናም ኮርያንቱመር ስለሚባል አንድ ሰው ታሪክና ስለህዝቡ ማለቅ ታሪክ ይናገሩ ነበር። እናም ቆሪያንተመር በዛራሔምላ ህዝብ ተገኝቶ ነበር፤ እርሱም ለዘጠኝ ወራት ያህል ከእነርሱ ጋር ኖረ።

፳፪ አባቶቹን በተመለከተ ደግሞ ትንሽ ቃላት ተናገረ። እናም የመጀመሪያ ወላጆቹ የመጡት ጌታ የህዝቡን ቋንቋ በቀላቀለበት ጊዜ ከግንብ ነው፤ እናም ትክክለኛው የጌታ ቁጣ በፍርዱ መሰረት ወረደባቸው፤ እናም አጥንታቸው በሰሜናዊው ምድር ተበትነዋል።

፳፫ እነሆ፣ እኔ አማሌቂ በሞዛያ ዘመን ተወለድሁ፤ እናም ሞቱን እስከማይ ዘንድ ኖርሁ፤ እናም ልጁ ቢንያም በምትኩ ነገሰ።

፳፬ እናም እነሆ፣ በንጉስ ቢንያም ዘመን የከፋ ጦርነትና የደም መፋሰስ በኔፋውያንና በላማናውያን መካከል ተመልክቻለሁ። ነገር ግን እነሆ፣ ኔፋውያን በእነርሱ ላይ ብዙ ብልጫ አገኙ፤ አዎን፣ እንዲህም ሆኖ ንጉስ ቢንያም ከዛራሔምላ ምድር አስወጣቸው።

፳፭ እናም እንዲህ ሆነ ማርጀት ጀመርሁ፤ እናም ዘርም ስላልነበረኝና ንጉስ ቢንያም በጌታ ፊት ትክክለኛ ሰው መሆኑን ስለማውቅ፣ ስለሆነም፣ ሰዎች ሁሉ ወደ እስራኤሉ ቅዱስ እግዚአብሔር እንዲመጡና፣ በትንቢትም፣ በራዕይም፣ በመላዕክት አገልግሎትም፣ በልሳን በመናገር ስጦታም፣ በልሳን መናገርን በማስተርጎም ስጦታም፣ እንዲሁም መልካም በሆኑ ነገሮች ሁሉ እንዲያምኑ በጥብቅ በመምከር እነዚህን ሰሌዳዎች ለእርሱ እሰጣለሁ፤ ምክንያቱም ከጌታ ከሚመጣው በስተቀር መልካም የሆነ ምንም ነገር የለምና፤ እናም መጥፎ የሆነው ከዲያብሎስ ይመጣል።

፳፮ እናም አሁን፣ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ፣ የእስራኤል ቅዱስ ወደ ሆነው ክርስቶስ እንድትመጡና፣ የማዳኑን ኃይል እንድትካፈሉና፣ የቤዛነቱን ኃይል እንድታገኙ እፈልጋለሁ። አዎን፣ ወደ እርሱ ኑ፣ እናም መላ ነፍሳችሁን ለእርሱ እንደ መስዋዕትነት አቅርቡ፣ በፀሎታችሁና ፆማችሁ ቀጥሉም፣ እስከመጨረሻው ፅኑም፤ እናም ጌታ ህያው እንደሆነ ትድናላችሁ።

፳፯ እናም አሁን ወደ ኔፊ ምድር ለመመለስ ወደ ምድረበዳው የሄዱትን የተወሰኑ ሰዎች በሚመለከት በመጠን እናገራለሁ፤ ምክንያቱም የርስት ምድራቸውን ለመውረስ የተመኙ ብዙ ሰዎች ነበሩና።

፳፰ ስለሆነም፣ እነርሱ ወደ ምድረበዳው ሄዱ። እናም መሪያቸው ጠንካራና ኃይለኛ ሰው ነበር፣ እንዲሁም አንገተ ደንዳና ሰው ነበር፤ ስለሆነም፣ በእነርሱ መካከል ፀብ እንዲኖር አደረገ፤ እናም በምድረበዳ ውስጥ ከሀምሳዎቹ በቀር ሁሉም ተገደሉ፣ እናም እንደገና ወደ ዛራሔምላ ምድር ተመለሱ።

፳፱ እናም እንዲህ ሆነ ሌሎች ቁጥራቸው ከፍ ያለውን ደግሞ ወሰዱ፣ እናም ወደ ምድረበዳ እንደገና ጉዞአቸውን ቀጠሉ።

እናም እኔ አማሌቂ፣ ከእነርሱ ጋር የሄደ ወንድም ነበረኝ፤ እናም እነርሱን በተመለከተ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አላውቅም። ወደ መቃብሬም መውረዴ ነው፤ እነዚህ ሰሌዳዎችም ሙሉ ናቸው። እናም ንግግሬን አበቃለሁ።