ቅዱሳት መጻህፍት
ሞዛያ ፳፱


ምዕራፍ ፳፱

ሞዛያ በንጉስ ቦታ ዳኛዎች እንዲመረጡ ሀሳብ አቀረበ—ፃድቃን ያልሆኑ ንጉሶች ህዝባቸውን ወደኃጢያት ይመራሉ—ትንሹ አልማ ዋና ዳኛ እንዲሆን በህዝቡ ድምፅ ተመረጠ—እርሱም ደግሞ በቤተክርስቲያኗ ላይ ሊቀ ካህን ነው—አልማ ትልቁና ሞዛያ ሞቱ። ከ፺፪–፺፩ ም.ዓ. ገደማ።

አሁን ሞዛያ ይህንን ሲያደርግ ንጉሳቸው ማን መሆን እንዳለበት ፈቃዳቸውን በተመለከተ ለማወቅ በህዝቡ ሁሉ መካከል በምድሪቱ ዙሪያ ላከ።

እናም እንዲህ ሆነ የህዝቡ ድምፅ እንዲህ ሲል መጣ፥ የአንተ ልጅ አሮን ንጉሳችን እና ገዢአችን እንዲሆን እንፈልጋለን።

አሁን አሮን ወደ ኔፊ ምድር ተጉዟል፣ ስለዚህ ንጉሱ መንግስቱን ለእርሱ ሊሰጠው አልተቻለውም፤ አሮንም በራሱ ላይ መንግስትን አይቀበለም፣ ወይም ማንም የሞዛያ ልጆች የሆኑ መንግስቱን በራሱ ላይ ለማድረግ አልፈቀደም።

ስለዚህ ንጉስ ሞዛያ በህዝቡ መካከል በድጋሚ ላከ፤ አዎን፣ እንዲሁም የፅሁፍ መልዕክትን በህዝቡ መካከል ላከ። እናም እነዚህም የተፃፉትም ቃላት እንዲህ የሚሉ ነበሩ፥

እነሆ፣ አቤቱ እናንተ ህዝቦቼ ሆይ፣ ወይም ወንድሞቼ፣ እኔ እንደዚህ በጣም አከብራችኋለሁና፣ እኔ እንድታስቡበት የሚፈለግባችሁን ጉዳይ እንድታስቡበት እፈልጋለሁ—ንጉስ እንዲኖራችሁ ፈልጋችኋልና።

አሁን መንግስቱ በትክክል የሚገባው እንዳልተቀበለው፣ እናም መንግስቱንም በራሱ ላይ እንደማይወስድ እነግራችኋለሁ።

እናም አሁን በእርሱ ምትክ ሌላ የሚሾም መኖር ካለበት፣ እነሆ በእናንተ መካከል ጠብ እንዳይነሳ እፈራለሁ። እናም ምናልባት የእኔ ልጅ መንግስቱ የሚገባው ተቆጥቶና የህዝቡን ግማሽ ከእርሱ ጋር ይወስድ ይሆናል፣ ይህም ከእናንተ ጋር ጦርነትና ፀብን ይፈጥራል፣ ያውም ለብዙ ደም መፋሰስ ምክንያት ይሆንና፣ እናም የጌታን ቀጥተኛ መንገድ የሚያጣምም ሊሆን ይችላል፣ አዎን እናም የብዙ ሰዎችን ነፍስ ያጠፋል።

አሁን እንዲህ እላችኋለሁ ብልሆች እንሁን፣ እናም እነዚህን ነገሮች እንመርምር፣ ልጄን የማጥፋት ምንም መብት የለንም፣ ወይም በእርሱ ቦታ ሌላ የሚተካውንም የማጥፋት መብት የለንም።

እናም ልጄ በድጋሚ ወደ ኩራቱና ወደ ከንቱ ነገሮች የሚመለስ ከሆነ የተናገራቸውን ነገሮች መልሶ ከወሰደ፣ እናም ለመንግስቱ መብቱን ይገባኛል የሚል ከሆነ፣ ይህም እርሱን እናም ደግሞ ህዝቡን ኃጢያት እንዲፈፅሙ ያደርጋልና።

እናም አሁን ብልህ እንሁንና፣ እነዚህን ነገሮች እንመልከት፣ ለዚህም ህዝብ ሰላምን የሚያረጋግጥለትን ነገር እንስራ።

፲፩ ስለዚህ በተቀሩት ቀናቴ ንጉሳችሁ እሆናለሁ፤ ይሁን እንጂ፣ በህጋችን መሰረት ለዚህ ህዝብ እንዲፈርዱ ዳኞችን እንሹም፤ እናም ለዚህ ህዝብ እንደ አዲስ ስልት እናዘጋጅለት፣ ዳኞች እንዲሆኑ ብልህ ሰዎችን እንሾማለንና፣ እነርሱም በእግዚአብሔር ትዕዛዛት መሰረት ይዳኙአቸዋልና።

፲፪ አሁን ሰው ከሰው ይልቅ በእግዚአብሔር ቢፈረድበት ይሻለዋል፣ የእግዚአብሔር ፍርድ ሁልጊዜም ጻድቅ ነውና፣ ነገር ግን የሰው ፍርድ ሁልጊዜ ጻድቅ አይደለም።

፲፫ ስለዚህ፣ የእግዚአብሔርን ህግጋት የሚመሰርቱ፣ እናም በትዕዛዛቱ መሰረት በዚህ ህዝብ ላይ የሚፈርዱ ትክክለኛ ሰዎች የእናንተ ንጉስ እንዲሆኑ ቢቻል፣ አዎን፣ አባቴ ቢንያም ለዚህ ህዝብ እንዳደረገው የሚሰራ ሰው ንጉስ ሊኖራችሁ ቢችል—እላችኋለሁ፣ ሁልጊዜም ሁኔታው ይህ መሆን ከቻለ እናንተን የሚገዛ ንጉስ ሁልጊዜም ቢኖራችሁ አስፈላጊ ነው።

፲፬ እናም እኔም እንኳን ብሆን በሁሉም ኃይልና ባለኝ ችሎታ፣ የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት ላስተምራችሁ እናም በምድሪቱ ላይ ሰላምን ለማስፈን፣ ምንም ዓይነት ጦርነትም ሆነ ፀብ፣ ስርቆት፣ ወይም ዝርፊያ፣ ወይም ግድያ፣ ወይም ማንኛውም ዓይነት ኃጢያት እንዳይኖር ሰርቼአለሁ፣

፲፭ እናም ኃጢያትን የፈፀመውን በፈፀመው ወንጀል መሰረት በአባቶቻችን በተሰጠን ህግ መሰረት ቀጥቼዋለሁ

፲፮ አሁን እላችኋለሁ፣ ሁሉም ሰው ጻድቅ ባለመሆኑ እናንተን የሚገዙ ንጉሶችም ሆኑ ንጉስ አስፈላጊ አይደለም።

፲፯ እነሆም፤ አንድ ኃጢአተኛ ንጉስ ምን ያህል ኃጢያት እንዲፈፅም ያደርጋል፤ አዎን፣ እናም እንዴት ታላቅ የሆነ ጥፋት!

፲፰ አዎን፣ የንጉስ ኖህን፣ ኃጢአቱንና እርኩሰቱን፣ እናም ደግሞ የህዝቡን ኃጢያትና እርኩሰት አስተውሉ። እነሆ ምን ያህል ታላቅ እርኩሰት በእነርሱ ላይ ሆነ፤ እናም ደግሞ በኃጢአታቸው የተነሳ ወደ ባርነት ተወሰዱ።

፲፱ እናም በጥበበኛው ፈጣሪአቸው ጣልቃ ገብነት፣ እና ይህም በጥልቁ ንስሃቸው ምክንያት፣ ባይሆን ኖሮ እስካሁን ድረስ በማይታመን ሁኔታ በባርነት ሊቀሩ ይገባቸው ነበር።

ነገር ግን እነሆ በእርሱ ፊት እራሳቸውን ትሁት በማድረጋቸው እነርሱን አዳናቸው፤ እናም በኃይል ወደእርሱ በመጮሀቸው ከባርነት አዳናቸው፣ እናም ጌታ በእርሱ ላይ እምነታቸውን በጣሉት የምህረት ክንዱን በመዘርጋት በሁሉም ሁኔታዎች ከሰዎች ልጆች መካከል በኃይሉ እንደዚህ ይሠራል።

፳፩ እናም እነሆ፣ አሁን እላችኋለሁ በብዙ ፀብና ደም መፋሰስ ካልሆነ በቀር ክፉውን ንጉስ ልታስወግዱት አይቻላችሁም።

፳፪ እነሆ በክፋት ያሉ ወዳጆች ስለአሉት፣ እናም ጠባቂዎቹን በእርሱ ዙሪያ ያስቀምጣቸዋል፤ እናም ከእርሱ በፊት በፅድቅ የነገሱትን ሰዎች ህግ ያጠፋል፣ የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት በእግሩ ይረጋግጠዋልም።

፳፫ እናም ህጎችን ያወጣል፣ በህዝቡ መካከልም ይልካል፣ አዎን እንደ እርሱ ክፋት የሆኑ ህጎችን፤ እናም ህጉን ያልተቀበለ እንዲጠፋ ይደረጋል፤ በእነርሱም ላይ የሚያምፅ ለጦርነት ወታደሮቹን በእነርሱ ላይ ይልካል፤ እናም የሚችል ከሆነ ያጠፋቸዋል፤ ፃድቅ ያልሆነ ንጉስም የፃድቃንን መንገድ በሙሉ እንደዚህ ያጣምማል።

፳፬ እናም አሁን እነሆ እላችኋለሁ እንደዚህ አይነት እርኩሰት በእናንተ ላይ መምጣቱ አስፈላጊ አይደለም።

፳፭ ስለዚህ ትክክለኛ የሆነው እናም በጌታ እጅ የተሰጠው በአባቶቻችን በተሰጣችሁ ህጎች መሰረት ይፈረድባችሁ ዘንድ በዚህ ህዝብ ድጋፍ ዳኛን ምረጡ።

፳፮ አሁን ህዝቡ ትክክለኛ ከሆነው ከማንኛውም ነገር ተቃራኒ የሆነ ድምፅ መፈለግ የተለመደ አይደለም፤ ነገር ግን ትክክል ያልሆነውን መፈለግ በትንሹ የህብረተሰብ ክፍል የተለመደ ነው፤ ስለዚህ ይህንን ጠብቁ እናም የራሳችሁ ህግ አድርጉት—በህዝቡም ድምፅ ጉዳያችሁን እንድትፈፅሙ።

፳፯ እናም የህዝቡ ድምፅ መጥፎውን የሚመርጥበት ጊዜ ከመጣ፣ የእግዚአብሔር ፍርድ በእናንተ ላይ የሚመጣበት ጊዜ ይሆናል፤ አዎን ከዚህ በፊት ይህንን ምድር እንደጎበኘው እናንተን በታላቅ ጥፋት የሚጎበኝበት ጊዜ ይሆናል።

፳፰ እናም አሁን መሳፍንቶች ካሏችሁና በተሰጣችሁ ህግ መሰረት የሚፈርዱባችሁ ካልሆነ በጠቅላይ ዳኛ እንዲፈረድባቸው ማድረግ ትችላላችሁ።

፳፱ ጠቅላይ ዳኞቻችሁ ጽድቅ ፍርድ ካልፈረዱላችሁ፣ አነስተኞች የበታች ዳኛዎቻችሁ በአንድነት እንዲሰበሰቡ ታደርጋላችሁ፣ እና እነርሱም በጠቅላይ ዳኞቻችሁ ላይ በህዝቡ ድምፅ መሰረት ይፈርዳሉ።

እናም በጌታ ፍራቻ እነዚህን ነገሮች እንድታደርጉ አዛችኋለሁ፤ እናም ንጉስ እንዳይኖራችሁ እነዚህን ነገሮች እንድታደርጉ አዛችኋለሁ፤ ይህ ህዝብ ኃጢያትና ክፋትን ከፈፀመ በራሳቸው ላይ መልስን ያገኛሉ።

፴፩ እነሆም እላችኋለሁ፣ የብዙዎች ኃጢያት የሆነው በንጉሶቻቸው ክፋት ምክንያት ነው፤ ስለዚህ ክፋታቸው በንጉሶቻቸው ራስ ላይ ይመለሳሉ።

፴፪ እናም አሁን በዚህ ምድር አድልዎ ከእንግዲህ በዚህ ምድር፣ በተለይ በህዝቤ መካከል እንዲኖር አልፈልግም፤ ነገር ግን ይህ ምድር የነፃነት ምድር እንዲሆን እፈልጋለሁ፣ እናም ጌታ ምድሪቱን እንድንኖርበትና እንድንወርስ አስፈላጊ ነው እስካለ ድረስ፣ አዎን፣ ማንኛውም ሰው የእኛ ዘር በምድር ፊት እስከቀረበም ድረስ ማንኛውም ሰው በእኩል ልዩ መብቱንና እድሎቹን ይደሰትባቸው።

፴፫ እናም ንጉስ ሞዛያ፣ የፃድቃኑን ንጉስ ፍርድና ችግር ሁሉ በማያያዝ፣ አዎን፣ ለህዝባቸው ያላቸው የመንፈስ ስቃይ ሁሉ፣ እናም ደግሞ በንጉሱ ላይ የህዝቡን ማጉረምረምን በመግለፅ ከዚህ የበለጡ ብዙ ነገሮችን ፅፎላቸዋል፤ እናም ይህንን ሁሉ ገልፆላቸዋል።

፴፬ እናም እነዚህ ነገሮች መሆን እንደሌለባቸው ነግሯቸዋል፣ ነገር ግን ሸክሙ በህዝቡ ላይ ሁሉ ላይ መምጣት አለበት፣ እያንዳንዱም ሰው የእራሱን ክፍል ይሸከም ዘንድ።

፴፭ እናም ደግሞ ፃድቅ ባልሆነ ንጉስ በመገዛታቸው፣ ጥቅም በሌለው የደከሙበትን እንዲያውቁ አደረገ።

፴፮ አዎን፣ ሁሉም ክፋቶቹንና እርኩሶቹን፣ እናም ጦርነትቶችን፣ ፀቦችንም፣ ደም መፋሰስንም፣ ስርቆትንም፣ ዝርፊያንም፣ ዝሙትንም መፈፀም፣ እናም ሊቆጠሩ የማይችሉ ሁሉም አይነት ክፋት—እነዚህ ነገሮች መሆን እንደሌለባቸው ከእግዚአብሔርም ትዕዛዛት ጋር ተፃራሪ መሆናቸውን ተናገረ።

፴፯ እናም አሁን እንዲህ ሆነ፣ ንጉስ ሞዛያ እነዚህን ነገሮች በህዝቡ መካከል ከላከ በኋላ የእርሱ ቃላት እውነት እንደሆኑ ታመኑ።

፴፰ ስለዚህ ለንጉስ ያላቸውን ፍላጎት ተዉ፣ እናም በምድሪቱ ሁሉም ሰው እኩል እድል እንዲኖረው እጅግ ጓጉ፤ አዎን፣ እናም እያንዳንዱ ሰው የራሱን ኃጢያት ለመመለስ ፈቃደኝነቱን ገለፀ።

፴፱ ስለዚህ እንዲህ ሆነ በምድሪቱ ላይ ሁሉ በተሰጠው ህግ መሰረት እነርሱን የሚፈርድ ዳኛ ማን መሆን እንዳለበት በሚመለከት ድምጻቸውን ለመስጠት በቡድን እራሳቸውን በአንድነት ሰበሰቡ፣ እናም በተሰጣቸው ነፃነት የተነሳ እጅግ ተደስተው ነበር።

እናም በሞዛያ ያላቸው ፍቅር ጠነከረ፤ አዎን፣ ከማንም ሰው የበለጠ አከበሩት፤ ጥቅም፣ አዎን ነፍስን የሚያስረክሰውን አስቀያሚ ገንዘብ፣ የሚፈልግ ጨካኝ እንደሆነ አድርገው አልተመለከቱትም፤ ከእነርሱም ሀብታቸውን ለመውሰድ አልፈለገም፣ ወይም በደም መፋሰስም አልተደሰተምና፤ ነገር ግን በምድሪቱ ሰላምን መስርቷል፣ እናም ለህዝቡ ከሁሉም ባርነት እንዲለቀቁ አድርጓል፤ ስለዚህም፣ አዎን፣ እጅግ ከልክ በላይ አከበሩት።

፵፩ እናም እንዲህ ሆነ በእነርሱ ላይ የሚገዙ ዳኛዎችን፣ ወይንም በህጉ መሰረት የሚዳኛቸውን ሾሙ፤ እናም ይህንን በምድሪቱ ዙሪያ ሁሉ አደረጉ።

፵፪ እናም እንዲህ ሆነ አልማ የመጀመሪያ ዋና ዳኛ በመሆን ተመረጠ፣ አባቱም ሀላፊነቱን ለእርሱ በመስጠቱ፣ እናም የቤተክርስቲያኑን ጉዳዮች ሁሉ በሚመለከት ሀላፊነቱን ስለሰጠው ደግሞ ሊቀ ካህንም ነበር።

፵፫ እናም አሁን እንዲህ ሆነ አልማ በጌታ መንገድ ተራመደና፣ ትዕዛዛቱን ጠበቀ፣ እናም ጻድቅ ፍርድን ፈረደ፤ እናም በምድሪቱ ሁሉ የማያቋርጥ ሰላም ነበረ።

፵፬ እናም ኔፋውያን ከሚባሉ ህዝቦች መካከል ሁሉ በዛራሔምላ ምድር የዳኛዎች አገዛዝ እንደዚህ ተጀመረ፣ እናም አልማ የመጀመሪያውና ዋናው ዳኛ ነበር።

፵፭ እናም አሁን እንዲህ ሆነ ሰማንያ ሁለት ዓመት ሆኖት አባቱ ሞተ፤ እርሱም የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት በመፈፀም ይኖር ነበር።

፵፮ እናም እንዲህ ሆነ በንግስናው ሠላሳ ሶስተኛ ዓመት፣ ስልሳ ሦስት ዓመት ሆኖት ሞዛያም ደግሞ ሞተ፤ ይህም በአጠቃላይ ሌሂ ኢየሩሳሌምን ለቆ ከወጣ አምስት መቶ ዘጠኝ ዓመት ነበር።

፵፯ እናም በኔፊ ህዝብ ላይ የነገስት አገዛዝ በዚሁ አበቃ፣ እናም የቤተክርስቲያናቸው መስራች የነበረው የአልማ ቀናትም እንደዚህ ተፈፀሙ።