ቅዱሳት መጻህፍት
ሞዛያ ፲፭


ምዕራፍ ፲፭

ክርስቶስ አባትም ልጅም እንዴት እንደሆነ—እርሱ ያማልዳል እናም የህዝቡን አመፅ ይሸከማል—እነርሱ እና ሁሉም ቅዱሳን ነቢያት ዘሮቹ ናቸው—ትንሳኤን ያመጣል—ህፃናት ዘለዓለማዊ ህይወት ይኖራቸዋል። በ፻፵፰ ም.ዓ. ገደማ።

እናም አሁን፣ አቢናዲ እንዲህ አላቸው፥ እግዚአብሔር ራሱ በሰው ልጆች መካከል እንደሚወርድና፣ ህዝቡንም እንደሚያድን እንድትረዱ እፈልጋለሁ።

እናም በስጋ በመኖሩም የተነሳ የእግዚአብሔር ልጅ ተብሎ ይጠራል፣ እናም ሥጋውን ለአብ ፈቃድ በማስገዛቱ አብም፣ ወልድም ነው—

በእግዚአብሔር ኃይል የተፀነሰ ስለሆነም አብ ነው፤ ስጋን ለብሷልና ወልድ ነው፣ ስለዚህ አብም ወልድም ነው—

እናም አንድ አምላክ፣ አዎን፣ እውነተኛ የሰማይና የምድር ዘለዓለማዊ አባት ናቸው።

እናም ስጋው ለመንፈስ ወይንም ወልድም ለአብ በመገዛቱ፣ አንድ አምላክ በመሆን፣ መከራን በመሰቃየቱና፣ ለፈተናም ራሱን ባለመስጠቱ፤ ነገር ግን እንዲሳለቁበትና፣ እንዲገረፍ፣ እንዲሁም በህዝቡ እንዲጣልና እንዲወገዝ ራሱን አሳልፎ ሰጠ።

እናም ከዚህ ሁሉ በኋላ፣ በሰው ልጆች መካከል ብዙ ኃያል ድንቅ ሥራዎችን ከሰራ በኋላ ይመራል፣ አዎን፣ ኢሳይያስ እንዳለው ሁሉ፣ በጉም በሸላቾቹ ፊት ዝም እንዳለው፣ እንዲሁም አፉን አልከፈተም።

አዎን፣ እንደዚያ ቢሆንም እርሱ ይነዳል፣ ይሰቀላል እናም ይገደላል፣ የወልድም ፈቃድ በአብ ፈቃድ ተሸፍኖ፣ ስጋውም ቢሆን ሞትን እንዲቀምስ ይደረጋል።

እና በሞት ላይ ድልን በማግኘት፣ ለሰው ልጆች እንዲማልድ ለወልድ ኃይልን በመስጠት፣ እንደዚህም እግዚአብሔር የሞትን እስር ይበጥሳል፤

ወደሰማይ በማረጉ፣ ለሰው ልጆች አንጀቱ በምህረት በመሞላቱ፣ በእነርሱና በፍርድ መካከል በመቆም ለሰዎች ልጆች በርህራሄ ይሞላል፣ የሞትን እስር በመበጣጠስ፣ በራሱም ላይ ክፋታቸውንና መተላለፋቸውን በማድረግ፣ እነርሱን በማዳን፣ እናም የፍትህን ፍላጎት አሟልቷል

እናም አሁን እላችኋለሁ፣ ትውልዱን የሚያውጅ ማን ነው? እነሆ፣ እላችኋለሁ፣ ነፍሱ ለኃጢያት መስዋዕት ሲሆን ዘሩን ያያል። እናም አሁን ምን ትላላችሁ? እናም ዘሩስ ማን ይሆናል?

፲፩ እነሆ እላችኋለሁ፣ ማንም የነቢያቱን ቃላት የሰማ፣ አዎን የክርስቶስን መምጣት በተመለከተ የተነበዩትን ቅዱሳን ነቢያት ሁሉ—እላችኋለሁ፣ ቃላቸውን የሰሙ ሁሉ፣ እናም ጌታ ህዝቡን ማዳኑን ያመኑና፣ ለኃጢአታቸው ስርየት ያንን ቀን የሚጠብቁ፣ እላችኋለሁ፣ እነዚህ የእርሱ ዘር ናቸው፣ ወይም የእግዚአብሔርን መንግስት ወራሾች ናቸው።

፲፪ ኃጢአታቸውን የተሸከመላቸው እነዚህ ናቸው፤ ከመተላለፋቸው እንዲያድናቸው እርሱ የሞተላቸው እነርሱ ናቸው። እናም አሁን የእርሱ ዘሮች አይደሉምን?

፲፫ አዎን፣ እናም ለትንቢት አፉን የከፈተ እያንዳንዱ፣ በመተላለፍ ያልወደቀ፣ ማለትም ዓለም ከመፈጠሩ ጀምሮ የነበሩ ቅዱሳን ነቢያት ሁሉ አይደሉምን? እነርሱ ዘሮቹ ናቸው እላችኋለሁ።

፲፬ እናም ሰላምን የተናገሩት፣ መልካሙን የምስራች ዜና ያመጡት፣ ደህንነትን የተናገሩት፣ እናም ለፅዮንም አምላክሽ ነግሷል! ያሉት እነኚህ ናቸው።

፲፭ እናም አቤቱ እግራቸው በተራራው ላይ ምን ያህል ያማረ ነው!

፲፮ እናም እንደገና፣ ሰላምን በተራራው ላይ የሚያውጁ እግራቸው እንዴት ያማረ ነው?

፲፯ እናም እንደገና፣ አዎን፣ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ እስከዘለዓለም በተራራው ላይ ሰላምን የሚያውጁት እግራቸው እንዴት ያማረ ነው!

፲፰ እናም እነሆ፣ እንዲህ እላችኋለሁ፣ ይህ ብቻም አይደለም። የሰላም መስራቹ የምስራች ወሬን ያመጣው፣ ህዝቡን ያዳነው አዎን፣ ያውም ጌታ ቢሆን እንኳን፤ አዎን፣ ለህዝቡ ደህንነትን የሰጠው፣ እግሮቹ በተራራው ላይ ምን ያህል ያማሩ ናቸው።

፲፱ ከዓለም መፈጠር ጀምሮ የተዘጋጀው ለህዝቡ ያደረገው ቤዛነት ባይሆን ኖሮ፣ ይህ ባይሆን ኖሮ የሰው ዘር በሙሉ መጥፋት ነበረባቸው እላችኋለሁ።

ነገር ግን እነሆ፣ የሞት እስር ይበጠሳል፣ እናም ወልድም ይነግሳል፣ በሞት ላይ ስልጣን ይኖረዋልም፣ ስለዚህ፣ የሞትን ትንሣኤ ያመጣል።

፳፩ እናም ትንሳኤ፣ እንዲያውም የመጀመሪያው ትንሣኤ፣ አዎን፣ ትንሣኤውም እንኳን ለነበሩትና፣ አሁን ላሉት፣ እናም ወደፊት ለሚኖሩት እስከ ክርስቶስ ትንሳኤም ድረስ እንኳን ይመጣል፤ እንዲህም ተብሎ ነው ይጠራልና።

፳፪ እናም አሁን፣ ሁሉም ነቢያትና፣ በቃላቸው ያመኑት ሁሉ፣ ወይም የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት የሚጠብቁ ሁሉ፣ በመጀመሪያው ትንሳኤ ይነሳሉ፣ ስለዚህ፣ የመጀመሪያው ትንሣኤ ናቸው።

፳፫ ካዳናቸው ከእግዚአብሔር ጋር ለመኖር ይነሳሉ፤ እንደዚህም የሞትን እስር በበጠሰው፣ በክርስቶስ በኩል ዘለዓለማዊ ህይወት ያገኛሉ።

፳፬ እናም እነዚህ በመጀመሪያው ትንሣኤ ቦታ ያላቸው ናቸው፤ እነዚህም ባለማወቃቸው፣ ደህንነት ሳይታወጅላቸው፣ ክርስቶስ ከመምጣቱ በፊት የሞቱት ናቸው። እናም ጌታ የእነዚህ መታደስን ያመጣል፤ በመጀመሪያው ትንሣኤ ቦታ፣ ወይም በጌታ በመዳን ዘለዓለማዊ ህይወት ይኖራቸዋልም።

፳፭ እናም ትናንሽ ልጆች ዘለዓለማዊ ህይወት ይኖራቸዋል።

፳፮ ነገር ግን እነሆ፣ እናም በእግዚአብሔር ፊት ፍሩና ተንቀጥቀጡ፣ መንቀጥቀጥ ይገባችኋልና፣ ጌታም በእርሱ ላይ ያመፀውንና በኃጢያት የሞተውን አያድንምና፤ አዎን፣ እንዲሁም ዓለም ከተፈጠረች ጀምሮ በኃጢአታቸው የሞቱትም፣ ወደው በእግዚአብሔር ላይ ያመፁትም፣ የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት የሚያውቁ እናም የማይጠብቁትም ሁሉ፣ በመጀመሪያው ትንሳኤ ቦታ ያልኖራቸው እነዚህ ናቸው።

፳፯ ስለዚህ እናንተስ መንቀጥቀጥ አይገባችሁምን? ደህንነት እንደነዚህ ላሉት ለማናቸውም አይመጣም፣ ጌታ እንደዚህ ያሉትን ማናቸውንም አያድንምና፤ አዎን፣ ጌታ እንዲህ አይነቱን ሊያድን አይቻለውምና፣ እራሱን ሊክድ አይችልምና፣ ፍትህ በሰው ላይ ቅጣት ለመስጠት መብት ሲኖራት መካድ አይችልምና።

፳፰ እናም አሁን እንዲህ እላችኋለሁ፣ የጌታ ደህንነት ለሁሉም ሀገር፣ ነገድ፣ ቋንቋና ህዝብ የሚታወጅበት ጊዜ ይመጣል።

፳፱ አዎን፣ ጌታ፣ ጠባቂዎችህ ድምፃቸውን ከፍ ያደርጋሉ፣ በአንድነትም ይዘምራሉ፤ ጌታ ፅዮንን በድጋሚ ሲያመጣ ዐይን ለዐይን ይተያያሉና።

በደስታ በድንገት ውጡ፤ የፈራረሳችሁ የኢየሩሳሌም ቦታዎች በአንድነት ዘምሩ፤ ጌታ ህዝቡን አፅናንቷል፣ ኢየሩሳሌምን አድኗልና።

፴፩ ጌታ ቅዱስ ክንዱን በሁሉ ሀገሮች ዐይን ላይ ገልጧል፤ እናም የአለም ዳርቻዎች ሁሉ የአምላካችንን ማዳን ያያሉ።