ቅዱሳት መጻህፍት
ሞዛያ ፲፬


ምዕራፍ ፲፬

ኢሳይያስ ስለመሲሁ ተናገረ—የመሲሁ መዋረድና መሰቃየት ተገልፆአል—ነፍሱን ለኃጢያት መስዋዕት ሰጠ፣ እናም ለተላለፉት አማላጅ ሆነ—ኢሳይያስ ፶፫ን አነጻፅሩ። በ፻፵፰ ም.ዓ. ገደማ።

አዎን፣ ኢሳይያስም እንኳን ይህን አላለምን፤ የእኛን ዜና ማን አምኗል፣ እናም የጌታስ ክንድ ለማን ተገልጧል?

በፊቱ እንደቡቃያ ከደረቅም መሬት እንደስር አድጓል፣ መልክና ውበት የለውም፣ ባየነውም ጊዜ እንወደው ዘንድ ደም ግባት የለውም።

በሰውም የተጠላና የተናቀ ነው፤ ህማምና ሀዘንን የሚያውቅ ሰው ነው፣ እናም ፊታችንንም ከእርሱ ሰወርን፤ የተጠላ ነበር፤ እኛም አላከበርነውም።

በእውነት ስቃያችንን ተቀበለ፤ እናም ሀዘናችንን ተሸከመ፤ እኛ ግን እንደተቸገረ፣ በእግዚአብሔር እንደተቀሰፈና እንደተመታ ቆጠርነው።

ነገር ግን ስለመተላለፋችን እርሱ ቆሰለ፤ ስለበደላችንም ደቀቀ፤ የሰላማችን ተግሳፅ በእርሱ ላይ ነበር፤ እናም በቁስሉ ተፈወስን

እኛ ሁላችንም እንደ በጎች ተቅበዝብዘን ጠፋን፤ ከእኛ እያንዳንዱ ወደገዛ መንገዱ አዘነበለ፤ እናም ጌታ የሁላችንንም በደል በእርሱ ላይ አኖረ።

ተጨነቀ፤ እናም ተሰቃየ፣ አፉንም አልከፈተም ነበር፤ እንደበግ ለመታረድ ቀረበ፤ እናም በሸላቾቿ ፊት ዝም እንደምትል በግ አፉን አልከፈተም።

ከወህኒና ከፍርድ ተወሰደ፤ እናም ስለ ትውልዱስ የሚያስተውልስ ማን ነው? እርሱ ከህያዋን ምድር ተወግዶአልና፤ ስለህዝቤም መተላለፍ ተመቷልና።

እናም መቃብሩን ከክፉዎች ጋር አደረገ፤ እናም ሞቱን ከባለጠጋዎች ጋር፤ ምንም ክፉ ነገር አላደረገምና፤ በአንደበቱም ተንኮል አልተገኘበትም።

ይሁን እንጂ ጌታ እርሱን ማቁሰል አስደሰተው፤ በሃዘን ውስጥ ጨመረው፤ ነፍሱን ስለኃጢያት መስዋዕት ካደረገ በኋላ ዘሩን ያያል፣ እድሜውን ያረዝማል፣ እናም የጌታ ፈቃድ በእጁ ውጤታማ ይሆናል።

፲፩ የነፍሱን ስቃይ ይመለከታል፣ እናም ደስ ይለዋል፤ ፃድቁ ባሪያዬም በእውቀቱ ብዙዎችን ያጸድቃል፤ ኃጢአታቸውንም ይሸከማልና

፲፪ ስለዚህ ከኃያላን ጋር ትልቁን አካፍለዋለሁ፤ እናም ከጠንካሮች ጋር ምርኮን ይከፋፈላል፤ ነፍሱን ለሞት አሳልፎ ሰጥቷልና፤ ህጉን ከተላለፉት ጋር ተቆጥሯልም፣ እናም የብዙዎችን ኃጢያት ተሸከመ፤ ስለአመፀኞችም ማለደ