ቅዱሳት መጻህፍት
ሞዛያ ፲፫


ምዕራፍ ፲፫

አቢናዲ በመለኮታዊ ኃይል ተጠበቀ—አሥርቱን ትዕዛዛት አስተማረ—ደህንነት በሙሴ ህግ ብቻ አይመጣም—እግዚአብሔር ራሱ የኃጢያት ክፍያ ያደርጋል፣ እናም ህዝቡን ያድናል። በ፻፵፰ ም.ዓ. ገደማ።

እናም አሁን ንጉሱ ይህንን ቃላት በሰማ ጊዜ፣ ለካህናቱ እንዲህ አላቸው፥ ይሄንን ሰው ውሰዱና ግደሉት፤ እብድ ስለሆነ ከእርሱስ ምን እናደርጋለን።

እናም ተነሱና እጃቸውን ሊጭኑበት ሞከሩ፣ ነገር ግን ተቋቋማቸውና እንዲህ አላቸው፥

አትንኩኝ፣ እጃችሁን በእኔ ላይ ብትጭኑብኝ እግዚአብሔር ይመታችኋል፤ ምክንያቱም ጌታ እንድሰጥ የላከኝን መልዕክት አልሰጠሁምና፤ ወይም እንድነግራችሁ የጠየቃችሁኝንም አልነገርኳችሁም፤ ስለዚህ እግዚአብሔር በዚህ ጊዜ እንድጠፋም አይፈቅድም።

ነገር ግን እግዚአብሔር ያዘዘኝን ትዕዛዝ መፈፀም አለብኝ፤ እናም እውነቱን ስለነገርኳችሁ ተቆጥታችሁኛል። እናም እንደገና፣ የእግዚአብሔርን ቃል በመናገሬ እብድ ነው ብላችሁ ፈረዳችሁብኝ።

አሁን እንዲህ ሆነ አቢናዲ እነዚህን ቃላት ከተናገረ በኋላ የንጉስ ኖህ ህዝብ የጌታ መንፈስ በእርሱ ላይ በመሆኑ እጃቸውን ሊጭኑበት አልደፈሩም፤ እናም ልክ ሙሴ ፊቱ በሲና ተራራ ከጌታ ጋር ሲነጋገር እንደበራው ፊቱ እጅግ አበራ

እናም በእግዚአብሔር ኃይልና በስልጣን ተናገረ፤ እናም እንዲህ በማለት ንግግሩን ቀጠለ፥

እኔን የመግደል ኃይል እንደሌላችሁ ተመልክታችኋል፣ ስለዚህ፣ መልዕክቴን እጨርሳለሁ። አዎን፣ እናም ኃጢአታችሁን በተመለከተ እውነቱን ስለነገርኳችሁ ልባችሁን እንደሚሰነጥካችሁ አስተውላለሁ።

አዎን፣ እናም ቃሌ በመገረምና በአድናቆትና በቁጣ ይሞላችኋል።

ነገር ግን መልዕክቴን እጨርሳለሁ፤ የምድን እስከሆነ፣ እናም የትም መሄዴ ችግር አያመጣም።

ነገር ግን ይህን ያህል እነግራችኋለሁ፣ በእኔ ላይ የምታደርጉትም ከዚህ በኋላ ስለሚመጡት ነገሮች ዓይነትና ጥላ ይሆናሉ።

፲፩ እናም አሁን ቀሪውን የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት አነብላችኋለሁ፣ ምክንያቱም እንደምገምተው በልባችሁ ውስጥ አልተፃፉምና፤ በአብዛኛው የህይወታችሁ ጊዜም ክፋትን እንዳጠናችሁና እንደተማራችሁ እገምታለሁ።

፲፪ እናም አሁን፣ በላይ በሰማይ ካለው፣ ከምድር በታች፣ ወይም ከምድር በታች በውኃ ካለው ነገር የማናቸውንም ምሳሌ፣ የተቀረፀውን ምስል ለአንተ አታድርግ ያልኩአችሁን ታስታውሳላችሁ።

፲፫ እናም በድጋሚ፣ ራሳችሁን ለእነርሱ አትስገዱላቸው፣ ወይም አታገልግሉአቸውም፤ በሚጠሉኝ በልጆች፣ በሦስተኛና አራተኛ ትውልዶች፣ ላይ የአባቶችን ጥፋት የምጎበኝ እኔ ጌታ አምላክህ ቀናተኛ አምላክ ነኝና።

፲፬ እናም ለሚወዱኝና ትዕዛዛቴንም ለሚጠብቁ እስከ ሺህ ትውልድ ድረስ ምህረትን የማሳይ ነኝ።

፲፭ የእግዚአብሔር አምላክህን ስም በከንቱ አትጥራ፣ እግዚአብሔር ስሙን በከንቱ የሚጠራውን ከበደል አያነፃውምና።

፲፮ የሰንበትን ቀን ትቀድሰው ዘንድ አስብ።

፲፯ በስድስቱ ቀን ስራ፣ ተግባርህን ሁሉ አድርግ፤

፲፰ ሰባተኛው ቀን ግን ለእግዚአብሔር አምላክህ ሰንበት ነው፤ አንተ፣ ወንድ ልጅህም ሴት ልጅህም፣ ሎሌህም፣ ገረድህም፣ ከብትህም፣ በደጆችህ ውስጥ ያለ እንግዳ በእነርሱ ምንም ስራ አይሠራም፤

፲፱ በስድስቱ ቀን ጌታ ምድርንና ሰማይን፣ እናም ባህርንና፣ በውስጡ ያሉትን ሁሉ ሰርቷልና፤ ስለሆነም ጌታ የሰንበትን ቀን ባረካትና ቀደሳት።

ጌታ እግዚአብሔር በምድር ላይ የተሰጡህ ቀናትም ይረዝሙልህ ዘንድ እናትና አባትህን አክብር

፳፩ አትግደል

፳፪ አታመንዝርአትስረቅ

፳፫ በባልንጀራህ ላይ በሃሰት አትመስክር

፳፬ የባልንጀራህን ቤት አትመኝ፣ የባልንጀራህን ሚስት፣ ሎሌውንም፣ ገረዱንም፣ በሬውንም፣ አህያውንም፣ የባልንጀራህ የሆነውን ማንኛውንም ነገር አትመኝ

፳፭ እናም እንዲህ ሆነ አቢናዲ ይህንን አባባሉን ከጨረሰ በኋላ እንዲህ ሲል ተናገራቸው፥ እነዚህ ሰዎች የጌታን ትዕዛዛት ይጠብቁ ዘንድ እነዚህን ነገሮች ሁሉ እንዲያደርጉ በእርግጥ አስተምራችኋቸዋልን?

፳፮ አይደለም እላችኋለሁ፤ ብታደርጉት ኖሮ፣ ጌታ ይህንን ህዝብ በተመለከተ መጥቼ መጥፎ እንድተነብይ አያደርገኝም ነበር።

፳፯ እናም አሁን ደህንነት በሙሴ ህግ ይመጣል ብላችኋል። የሙሴን ህግ መጠበቅ አሁንም ጠቃሚ ነው እላችኋለሁ፤ ነገር ግን የሙሴን ህግ መጠበቁ ከእንግዲህ ጠቃሚ የማይሆንበት ጊዜ ይመጣል እላችኋለሁ።

፳፰ እናም ከዚህ በተጨማሪ፣ እንዲህ እላችኋለሁ ደህንነት በህግ ብቻ አይመጣም፤ እናም ኃጢያት ክፍያን ለዚህ ህዝብ ኃጢያትና ጥፋት እግዚአብሔር እራሱ ባያደርገው ኖሮ በሙሴም ህግ ቢሆን መወገድ በማይችሉበት ሁኔታ መጥፋት ነበረባቸው።

፳፱ እናም አሁን ለእስራኤል ልጆች ህጉ መሰጠቱ አስፈላጊ ነበር፤ አዎን ጥብቁ ህግም እንኳን ቢሆን፣ ምክንያቱም እነርሱ አንገተ ደንዳና፣ ኃጢያትን ለማድረግ ፈጣንና ጌታ አምላካቸውን ለማስታወስ የዘገዩ ነበሩ፤

ስለዚህ ለእነርሱ የተሰጣቸው ህግ ነበር፣ አዎን የስራና የስርዓት ህግ፣ ከቀን ቀን አጥብቀው የሚጠብቁት ህግ፤ እነርሱን በመጠበቅ እግዚአብሔርን እና ለእርሱ ያላቸውን ተግባር እንዲያስታውሱ

፴፩ ነገር ግን እነሆ እንዲህ እላችኋለሁ፣ እነዚህ ነገሮች ሁሉ ወደፊት ሊመጡ ላሉት ምሣሌዎች ነበሩ።

፴፪ እናም አሁን፣ ህጉን ተረድተውት ነበርን? አልተረዱም እላችኋለሁ፤ ሁሉም ህጉን አልተረዱትም፤ እናም ይህም የሆነው ልባቸውን በማጠጠራቸው ነው፤ በእግዚአብሔር ቤዛነት ካልሆነ በቀር ማንም ሰው መዳን አለመቻሉን አልተረዱምና።

፴፫ እነሆ፣ ሙሴ ስለመሲሁ መምጣት፣ እንዲሁም እግዚአብሔር ህዝቡን እንደሚቤዥ አልተነበየምን? አዎን፣ እናም ዓለም ከመፈጠሯ ጀምሮ ይተነብዩ የነበሩ ሁሉም ነቢያት ከሞላ ጎደል ይህን በተመለከተ አልተነበዩምን?

፴፬ እግዚአብሔር እራሱ በሰው ልጆች መካከል እንደሚመጣ፣ የሰዎችን አምሳል እንደሚወስድ፣ እናም በታላቅ ኃይሉ በምድር ገፅ ፊት እንደሚሄድ አልተናገሩምን?

፴፭ አዎን፣ እናም ደግሞ የሙታንን ትንሳኤ እንደሚያስገኝ፣ እናም እራሱ እንደሚጨቆንና እንደሚሰቃይም አልተናገሩምን?